Saturday, 20 May 2023 15:18

“ቢወዱት ታንቆ የሞተ-ቢጠሉት ምን ሊሆን ነበር?”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 አቶ ኃይልና አቶ ትህትና የአንድ አገር ተወላጅ በመሆን አብረው ሲኖሩ ሲኖሩ፣ ከድህነት ወጥተውና በልፅገው ያለ ቅጥ ከበርቴነት ተሰማቸው፡፡ መቼም ሰው መክበርና መበልፀግ ሲጀምር ምኞቱ ሁሉ በዚያው ክብርና ሀብቱ ላይ ቶሎ ቶሎ ሲጨምርበትና ተፊተኛው የበለጠ ሃብት ለማፍራት መባዘን መሆኑን ማንም አይስተውም፡፡
“ገንዘብም አግኝተን ቶጅረናል፡፡ እዚህ ሌሎች የመሰረቱትና እየጠበበ ያለ ከተማ ሰለቸን፡፡ አዲስና ውብ ከተማ እንድንሰራ ንጉሱ በሀገሪቱ ውስጥ ጠፍ የሆነ ሰፊ ቦታ ፈልጎ ይስጠን” ሲሉ አመለከቱ፡፡
ንጉሱም፤ “እንደ እናንተ ያሉ ልማትንና ክብረትን ለሀገሬ ያሳዩ ጎበዛዝት እንዲበዙልኝ ስል የጠየቃችሁትን ያህል እንዲሰጣችሁ እፈቅዳለሁ፡፡ ለመሆኑም ምን ያህል ቦታ ነው የምትፈልጉት?” በማለት ለአቶ ኃይልና ለአቶ ትህትና ጥያቄ አቀረበ፡፡ እነሱም እንደ ዘመኑ ልማድ ለጥ ብለው እጅ ነሱ፡፡ መሬት ሳሙና “ተፀሃይ መውጫ እስተ ፀሃይ መግቢያ ያለውን የሚያህል መሬት ይሰጠን” በማለት አስር አስር ጊዜ እጅ ነሱ፡፡
ንጉሱም፤ “ምን ልትሰሩበት ነው የወጠናችሁት?” አለ፡፡ አቶ ኃይልና አቶ ትህትና እንደተማከረ ሰው በአንድነት “ቤተ መንግስትና ከተማ” አሉ፡፡  
ንጉሡ፤ “እንዲህ ያለ የተቀደሰ ሀሳባችሁንማ ቦታ በመስጠት ብቻ ሳይሆን የጎደለባችሁን ሁሉ እኔ እየሞላሁላችሁ እንድትሰሩ ለመደገፍ ከአምላክ የተቀበልኩት የህዝብ አደራ አለብኝ” አለና ለሀገር ግዛት ሚኒስትሩ የጠየቁት እንዲሰጣቸው ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ በትእዛዙም መሰረት መሬቱን ተረከቡ፡፡
ተረከቡና እንደየጠባያቸው ለመስራት እንዲቻላቸው መሬቱን ለሁለት መካፈል ጀመሩ፡፡ ክፍፍልም ጀምረው ጥቂት ሳይቆዩ፣ በሁለቱም በኩል “የኔን ቤተ መንግስት ወደ ላይ ልስራ! ወደ ላይ ልስራ!” በማለት ወደ አለመግባባት ተዳረሱና አዋቂ ይለየን! ብለው በፈቃዳቸው ወደ ሽማግሌ ቀረቡ፡፡
ሽማግሌዎቹም አቤቱታውን መስማት ሲጀምሩ ያገኙት ፍሬ ነገር፣ አቶ ኃይልና አቶ ትህትና በየፊናቸው ከፍ ያለውን ቦታ መርጠው “ወደ ላይ ልስራ! ወደ ላይ ልስራ!” ማለታቸውን ነበር፡፡
ከሽማግሌዎቹ የሚበዙት አቶ ኃይል “ወደ ታች ይስራ”፣ ያነሱት ደግሞ “ወደ ላይ ይስራ” ብለው ወሰኑ፡፡ ለአቶ ትህትና በተቃራኒው ተመሳሳይ ውሳኔ ተሰጠ፡፡
የሽማግሌዎቹ ፍርድ ያልተዋጠላቸው ሁለቱ ተከራካሪዎች፣ ይግባኝ ጠየቁና ወደ መጨረሻው ፍርድ ሰጪ ወደ ‘ብላታ ህሊና‘ ዘንድ ቀረቡ፡፡
ብላታ ህሊናም “አቶ ኃይልና አቶ ትህትና ተስማምተው በህብረት ሰርተው በአንድነት ቢኖሩበት መልካም ነበር፡፡ ስምምነት ከሌለ ግን እንኳንስ አንድነቱ ጉርብትናውም ያስቸግራል። ስለዚህ ትህትናን ማሸነፍ ይቻላልና ወደ ላይም ወደ ታችም ስራ ብንለው ባላወከንም ነበር፡፡ ኃይልን ግን ወደ ላይ እንዲሰራ ማድረግ ታላቅ አደጋ የሚያስከትል በመሆኑ ሃይል ወደ ታች ይስራ፣ ትህትና ወደ ላይ ይስራ በማለት በግጥምና ምሳሌ መደምደሚያ ፍርዳቸውን ሰጡ፡፡
አንዲት የሱፍ ፍሬ ተዘርታ ሳለች
እሷ ሳትነሳ አገዳ ሰራች፡፡
የሚያምር አበባ በአገዳው ላይ ታይቶ፣
እሾህ ያጥር ጀመር ቤቱን ከዚያ ሰርቶ፡፡
ያቺ ቅንጣት ፍሬ ከስር የወጣች፣
አገዳው የኔ ነው ስትል ከሰሰች፡፡
አበባ ግን ደፍሮ በሰጠው አርአያ፣
እሾህን ቆጠረ ለመከላከያ፡፡
አበባ መኖሩን ከፍሬ በፊት፣
እሾህ መሰከረ ነውና እውነት፡፡
ነገ ግን በርትታ ያቺ ቅንጣት ሱፍ፣
በመከራከሯ ከስር እስከ ጫፍ፣
ነገሩን ከስሩ ዳኞቹ ቢያዩት፣
የሚያከራክረው ያገዳው ንብረት፣
ከ ‘ዘር’ የተገኘ ሆኖ አገኙት፡፡
ስሩ ሳይታወቅ በጣም ተፈልፍሎ
ነገር አይያዝም ጫፍ ያምራል ተብሎ፡፡
***
እዚህ አገር የተጫነን አባዜ ሃይልና ትህትናን ለማቀራረብ ስልታችን እያደር አንድ አይነት መሆኑ ነው፡፡ ከዘር የተገኘው የባህሪ ዳፋ አልቀን ብሎ ከፍሬው ይልቅ እሾሁ ይታየናል፡፡ ምን እናፈራለን? ሳይሆን ምን ይወጋናል? ማለቱ ያመዝንብናል፡፡
መንግሥቱ ንጉሱን ከሰሱ እንጂ እሳቸው አልተማሩበትም፡፡ አዲሶቹም መንግሥቱን ወቀሱ እንጂ እነሱ አልተማሩበትም፡፡ ተቃዋሚዎቹም ይወቅሳሉ፤ ይከሳሉ እንጂ ከተከሳሾቹ መሻላቸውን በተግባር ማሳየት ተስኗቸዋል፡፡
መንግስትም ሆነ ተቃዋሚዎች ስለ ህዝብ የሚሰጡት አስተያየት “ባፍ ይጠፉ በለፈለፉ” እንዳይባሉ ከወዲሁ አርቀው ቢያስቡ ይበጃቸዋል፡፡ “በማን ላይ ቆመሽ ማንን ታሚያለሽ” መባል ይከተላል፡፡ “የእንትን ህዝብ ፈሪ ነው፤ የእንትን ህዝብ ጀግና ነው” በማለት የትም አይደረስም፡፡ ለህዝብ በጅምላ አመልና ፀባይ መስጠቱ ይቅር የማይባል የታሪክ በደል ነው፡፡
“መነኩሴ አሳማ በላ፣ ከበላው የሰማው ገማ” እንዲል መፅሐፉ፣ የጅምላ መትረየስ ርሸና ትዝታችን ሳይደበዝዝ፣ የጅምላ ቃላት ርሸና ስናክልበት አዲስ ስርአት ለመገንባት ያለንን ብቃትና ችሎታ ጥያቄ ዉስጥ ይከተዋል፡፡
ትህትና የጎደለው ጀግንነት ማንን ወደምን እንዳደረሰ ከራሳችን በላይ ምስክር የለም፡፡ “የእንትን ህዝብ ፈሪ ነው” ማለትን ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅትና መሪ መስማት፣ እንደ ዜጋ ለእኛ አስፈሪ ምስል ይከስትብናል፡፡ በ1968 እና 69 ጀግና የነበሩት ወጣቶች የት ደረሱ? ምን አፈሩ? ናቅፋ ቃሮራ የወደቁት ጀግኖች ምን አገኙ? 30 ዓመት ጦር ነክሰው የረገፉ የኤርትራ ወጣቶች ዛሬ ምን ተሸለሙ? … ምን?!ምን?!...‘ጀግንነት በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ተደብቃ ምንጊዜም አለች፡፡ ግን ጊዜ ቦታንና ሰው ትፈልጋለች- ትመርጣለች’ እንዲል ማክሲም ጎርኪ፤ ጀግንነት ያለ ጊዜውና ያለ ቦታው ሲሆን ትጨነግፋለች፡፡
መምህርና ባለቅኔ ዮፍታሄ ንጉሴ፣ ቢደንቃቸው …
“ሲያቅተኝ ዝም ብል ዝም ያልኩኝ መስሎታል
ሲታሰብ ነው እንጂ ዝም ማለት የታል?”
በማለት የተቀኙትን ያስታውሷል፡፡ ያለበለዚያ…
“ካቻምና በፈረስ አምና በበሬ አረስኩ፣
ዘንድሮ በአህያ የእህል አረማሞ፣
በፍየል ቀርቶኛል ከእንግዲህ ለከርሞ”… መባልን ያስከትላልና ልብ ያለው ልብ ይበል!
መብትና ነፃነት ለጥቂት ታዋቂ ሰዎችና ለህጋዊ ፓርቲዎችም ቢሆን በመጠኑ እንጂ ለህዝቡማ ገና አልተዳረሰችም፡፡ ቀበሌና ገበሬ ማህበር የዲሞክራሲ ወሬዋን ከርቀት እየሰሙ ናቸው እንጂ እነሱ ዘንድ አልደረሰችም፡፡ በየትኛውም ዘመን ከፈረሱ ጋሪው ቀድሞ አያውቅማ!! ተቃዋሚዎች “አስቀድመህ ስሩን ትከል፣ ጫፉ ኋላ ብቅ ይልልሃል” የሚለውን ብሂል ተከትለው በተስተዋለ እርምጃ ህዝቡን በህብረት ለማታገል መታጠቅ ለነገ የማይባል የቤት ስራቸው መሆኑን ማጤን ግድ ነው፡፡
“ለሚፈታተነው የንፋስ ማእበል?
ማማው ለአፍታ እንኳን ጎንበስ ዝቅ እንዳይል፣
ተጠናክረህ ግፋ እንዳትዘናበል…”
እንዲል ባለቅኔው ዳንቴ አሊጌራ፣ ከኛም ይኸው ይጠበቃል፡፡ የህዝቡን የልብ ትርታ እያዳመጡ በመራመድ ፋንታ ያለጊዜው ድል ማማጥ፣ ያለፈርጁ ሸማ መልበስ ይሆናል፡፡ ህዝብ ታሪክ ሰሪ ነው፡፡ ታሪክ ሰሪን አይሰድቡትም፤ እስኪ ከታሪክ ሰልፍ ቀላቅለኝ ይሉታል እንጂ! ከታሪክ ሰልፍ መቀላቀልም “ቢወዱት ታንቆ የሞተ- ቢጠሉት ምን ሊሆን ነበር?” ከመባል ያድናል፡፡


Read 1968 times