Saturday, 20 May 2023 20:07

“ሕልቀት” የቤተሰብ ማዕከል ተመስርቶ ስራ ጀመረ ጤናማና ደስተኛ ቤተሰብን ማፍለቅ ዋነኛ ዓላማው ነው ተብሏል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በእውቁና አንጋፋው ጋዜጠኛና የሚዲያ አማካሪ ሐበኒዮም ሲሳይ የተቋቋመው “ሕልቀት” የቤተሰብ ማእከል በይፋ ተመስርቶ ስራ ጀመረ፡፡ ማእከሉ ባለፈው ሰኞ ጊዮን ሆቴል ውስጥ በሚገኘው “ግሮቭ ጋርደን ዎክ” አዳራሽ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ምሁራን በቤተሰብና በትዳር ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማትና ግለሰቦች፣ ታዋቂ ሰዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በይፋ ሥራ መጀመሩም ተበስሯል፡፡
በማብሰሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረገው የሕልቀት የቤተሰብ ማእከል መስራች ጋዜጠኛ ሀበኒዮም ሲሳይ ማእከሉን እውን ሆኖ የማየት የረጅም ጊዜ ህልም እንደነበረው ገልፆ፣ ይህን ማዕከል ለመክፈት ያነሳሳውም የራሱ ቤተሰብ ያለፈበት ምስቅልቅል ህይወት እንደሆነ አብራርቷል፡፡ የማዕከሉን ሥያሜም በተመለከተ ማብራሪያ የሰጠው ጋዜጠኛ ሐበኒዮም፣ “ሕልቀት” የሚለው ቃል የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም “ቀለበት” ማለት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ቀለበት አንድነት ፍቅር መተሳሰብን የሚወክል እንደመሆኑ ማእከሉ ለሚሰራው የጋብቻና የቤተሰብ ጉዳይ ትክክለኛ ስያሜ ነው ብሎ ማመኑን አብራርቷል፡፡
በእለቱ መጋቢ ሃዲስ እሸቱ አለማየሁ የጋብቻና የቤተሰብ አማካሪ ፓስተር ቸርነት በላይ (ፓስተር ቸሬ) በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርስቲ የቋንቋና የስነ ተግባቦት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ሩቂያ ሀሰንና ሌሎችም ባለሙያዎች የማእከሉን መመስረት አድንቀው ንግግር ያደረጉ ሲሆን በተለይ ዶ/ር ሩቂያ ሀሰን “በንቃት ማሳደግ” በሚል ርእስ ባደረጉት ንግግር፣ በአካል መገኘት፣ ትኩረት መስጠት፣ ልጆች ስናሳድግ ለዚህ ዓለም ልጆችን እንዳበረከትን አድርገን የምናስበውን ኢጎ ማስወገድና ኢንቴግሪቲ ወሳኝ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ ዶ/ር ሩቂያ በተለይ በልጅ አስተዳደግ ላይ ምንም እንኳን የአባት ሚና ባይናቅም የእናቶች ሚና የተለየና ትልቅ መሆኑን አውስተው የአለማችንን ትልቁን ሳይንቲስትና የፈጠራ ሰው የቶማስ ኤድሰንን እናት በምሳሌነት አንስተዋል፡፡
“ቶማስ ኤድሰን በልጅነት ዘመኑ እጅግ ሰነፍና በዚህም ስንፍናው የመምህራኑን ትዕግስት የጨረሰ ነበር፡፡ እናም የት/ቤቱ ሃላፊዎች ይህ ልጅ ሰነፍ ስለሆነና ስላስቸገረ ሁለተኛ ወደ ትምህርት ቤት ድርሽ እንዳይል የሚል ደብዳቤ ፅፈው ለእናቱ መላካቸውን ያስታወሱት” ዶ/ር ሩቅያ ደብዳቤ እንደተፃፈበት ያወቀው ቶማስ ኤድሰን ት/ቤቱ ስለፃፈው ደብዳቤ ምንነት እናቱን ይጠይቃል፡፡ እናቱም “ልጅሽ እጅግ ጎበዝና የአዕምሮ ምጥቀቱ ከፍተኛ ስለሆነ ከሌሎቹ እኩዮቹ ጋር አዕምሮው ስለማይመጣጠን እቤቱ ሆኖ ያጥና” ብለው እንደፃፉ ለልጇ በመንገር ዛሬ በብርሃን የሚያደምቀንን አምፖል የፈጠረው ጂኒየስ አእምሮው እንዳይጎዳ ያደረገቸውን ተጋድሎ አውስተዋል፡፡ ፓስተር ቸርነት በላይ (ፓስተር ቸሬ) “አራቱ የልጅ ማሳደጊያ ሀይሎች” በሚል ርዕስ ባስተላለፉት መልእክት አንደኛው የኛ ጉልበት ገንዘብና ጊዜ ነው ያሉ ሲሆን በአካል በመገኘትና በመንከባከብ የሚያስፈልጋቸውን በገንዘብ በማሟላትና በመንከባከብ ሲሆን ሁለተኛው ጉዳይ “የወላጅነት መብት” ነው ብለዋል፡፡
የወላጅነት መብትን ተጠቅመን ልጆቻችንን መቅጣትና መገሰፅ ችላ ልንለው የማይገባ ጉዳይ ስለመሆኑም አሳስበዋ፡፡
በእንግድነት ሰው ቤት ሄደው የቀረበላቸውን ሚሪንዳ ቀምቶ የጠጣባቸውን የቤቱን ህፃንና የቤተሰቡን ምላሽ በምሳሌነት ጠቅሰው እንግዳ ፊት የቀረበን መጠጥ አፈፍ ሲያደርግ ያልገሰፅነው ህፃን አድጎ ከአንገት ላይ ሀብል ከእጅ ላይ ስልክ፣ ከትከሻ ላይ ቦርሳ መንትፎ ሲሮጥ ሊገርመን አይገባም፣ ሰው ከነህይወቱ ቢያቃጥል ጉድ ልንል አይገባም፣ አገር እየፈረሰች ያለችው ቤት ውስጥ ነው በማለት ቤተሰብ ልጅ አስተዳደግ ላይ የወላጅነት መብቱን ተጠቅሞ ልጁን መስመር ማስያዝ አለበት ሲሉ መክረዋል፡፡
ፓስተር ቸሬ አክለውም ሌላውና 3ኛው የልጅ ማሳደጊያ ሀይል “የዳበረ የህይወት ልምዳችን” ነው ያሉ ሲሆን፣ እኛ ያለፍንበትን የህይወት ልምድ፣ የተሳሳትንበትን ሁኔታ፣ የተሸወድንበት ወቅት፣ ከስህተታችን ለመታረም ያለፍነውን ፈተናና ሌላው የህይወት ልምዳችን ለልጆቻችን መስመር መቃናት ያለውን ጉልህ ሚና አብራርተው ቤተሰብ ለልጆቹ ይህን ልምድ ማጋራት አለበት ሲሉ መክረዋል፡፡
እንደ ፓስተር ቸሬ ገለፃ አራተኛውና ዋናው የልጅ ማሳደጊያ ሀይል “ፍቅር” የሚለው ትልቅ ጉዳይ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ልጆቻችንን “ቢሳካልህም ባይሳካልህም ጎበዝም ሆንክ ሰነፍ እኔ አለሁልህ እወድሃለሁ” በማለት ፍቅር ሰጥቶ ማሳደግ ትልቅና በዋጋ የማይተመን ስለመሆኑ ተናግረው በእሳቸው እድሜና አካባቢ የሚኒስትሪ ውጤት ያልመጣላቸው ልጆች ራሳቸውን በተለያየ መንገድ ያጠፉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይህም ካልተሳካልኝ የሚወደኝና የሚቀበለኝ የለም በሚል ተስፋ ማጣት የሚወሰድ እርምጃ በመሆኑ ልጆቻችንን በምንም ሁኔታ ውስጥ እንውደድ እናፍቅር ሲሉ መክረው የሕልቀት የቤተሰብ ማዕከል መመስረት በቤተሰብና በትዳር ጉዳይ ግንዛቤ በመፍጠርና ማህበረሰብን በማስተማር በኩል ሊኖረው የሚችለውን ሚና አውስተው አድንቀዋል፡፡
ሕልቀት የቤተሰብ ማዕከልም ከ20 በላይ አላማዎችን ይዞ የተመሰረተ ሲሆን ማበረሰቡን ለማንቃትና ለማስገንዘብ በየወሩ እንደ ዲስኩር ምሽት ያለ የትዳርና የቤተሰብ ጉዳይን የሚመለከት ወርሃዊ መሰናዶ ማዘጋጀት፣ ቅድመና ድህረ የጋብቻ ስልጠና መስጠት፣ የጥሪ ማዕከል ማቋቋምና ማህበረሰቡ በጥሪ ማዕከሉ እየደወለ የምክር አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ፣ አቅም የሌላቸውን ጥንዶች እንዲጋቡ ማገዝ፣ የትዳርና የቤተሰብ ጉዮች ላይ ጥልቅ ጥናትና ምርምር በማድረግ በፖሊሲ አውጪዎ ዘንድ ይህ ጉሰይ ቦታና ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግና ሌሎችም አላማዎችን ይዟል፡፡ ማዕከሉ በእለቱ ከኢትዮጵያ ልጆች ቴልቪዥን ከምቹ ቤት መልቲ ሚዲና ከኢትዮ ሄላ የእውቀት ማበልፀጊያ አክሲዮን ማህበር ጋር በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ መርሃ ግብሩ በእራት ግብዣ ተጠናቅቋል፡፡

Read 1004 times