Print this page
Monday, 22 May 2023 00:00

የኢትዮጵያ ሩጫ በስፖርት መሠረተልማቶች መጠናከር ያስፈልገዋል

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(1 Vote)

52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በምትገኘው ትንሿ ስታድየም ላይ እየተካሄደ ነው። በአትሌቲክስ የስፖርት መሰረተልማቶች መሥፋፋታቸው አስፈላጊ መሆኑን በዘንድሮው ሻምፒዮና መገንዘብ ተችሏል። በሻምፒዮናው ላይ 11 ክልሎች፤ የከተማ አስተዳደሮች ፤ 30 ክለቦችና ከማሰልጠኛ ተቋማት የተውጣጡ 1,270 (743 ወንዶች ፤ 527 ሴቶች) አትሌቶች እየተሳተፉ ናቸው። የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው  በክልሎች፤ በክለቦችና በማሰልጠኛ ተቋማት ለሚገኙ አትሌቶች የውድድር እድል ለመፍጠር፤ ተተኪ አትሌቶችን ለማውጣትና በዓለም ሻምፒዮና ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን የሚሆኑ ብቁ አትሌቶችን ለመለየት ያግዛል። ከ2.7 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት ሻምፒዮናውን 80 ዳኞችና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባለሙያዎች በብቃት እየመሩት ናቸው። ሻምፒዮናውን በማስመልከት ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የኮምኒኬሽን ዲያሬክተር አቶ ስለሺ ብስራት ጋር  ልዮ ቃለምልልስ ያደረግን ሲሆን ሻምፒዮናው ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ  ታላቅ መድረክ እንደመሆኑ በላቀ ደረጃ መካሄዱና በመሰረተልማቶች መጠናከር እንደሚገባው መረዳት ችለናል።
የኮምኒኬሽን ዲያሬክተሩ ስለሺ ብስራት ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው ሻምፒዮናው አትሌቶችን መመልከቻ፤ ሰዓታቸው የሚፈተሽበትና ወደ የዓለም ሻምፒዮና መሸጋገርያ የሚሆን ነው፡፡ የኮምኒኬሽን ዲያሬክተሩ እንደገለፀው ባለፉት አራት ሻምፒዮናዎች ያልተሳተፉት የትግራይ ክልል አትሌቶች ለመካፈል መብቃታቸው የተሳታፊውን ቁጥር ጨምሮታል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ብሄራዊ ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት በዋና አጋርነት የሚሰራው ከጀርመኑ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ አዲዳስ ጋር ነው፡፡ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ደግሞ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናውን፤ የአበበ ቢቂላ ማራቶንና ሌሎች ውድድሮችን ስፖንሰር በማድረግም ከፌደሬሽኑ ጋር ይሠራል፡፡ የኮምኒኬሽን ዲያሬክተሩ እንደገለፀው ፌደሬሽኑ ከስፖንሰሮቹ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለው፡፡ ሻምፒዮናው ባለፈው ዓመት በሐዋሳ ሲካሄድ በጀቱ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የነበረ ሲሆን፤ ዘንድሮ በአዲስ አበባ ላይ ሲካሄድ ከ2.7 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ይወጣባታል። በጀቱ የአትሌቶችን የምግብ፤ ማረፊያና የውሎ አበልን ለመሸፈን፤ ለተለያዩ ባለሙያዎች ክፍያ እና ሌሎችንም ወጭዎች ለመሸፈን ይውላል፡፡
የስፖርት መሠረተ
ልማቶችን በማስፋፋት ረገድ
ብሄራዊ አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ከግማሽ ምዕት አመት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም የሚጠበቀውን ደረጃ ሊደርስ ግን አልቻለም፡፡ በየዓመቱ ክለቦች፤ ክልሎችና የማሰልጠኛ ተቋማት በሻምፒዮናው ትኩረት ሰጥተው የሚሳተፉ ቢሆንም የስፖርት መሰረተልማቱ አለመመሟላት፤ የተመልካች ቁጥር ማነስ እና የሚዲያ ሽፋኑ አለመጠናከር ይስተዋላል፡፡
ሻምፒዮናው በየዓመቱ ሲካሄድ ከፍተኛ ተመልካች የሚያገኝ፤ ገቢ የሚያመነጭና በሚዲያ ሰፊ ሽፋን የሚሰጠው እንዲሆን ብዙ መስራት ይጠበቃል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የኮምኒኬሽን ዲያሬክተር ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው ሻምፒዮናው በከፍተኛ የተመልካች ድባብ የማይከናወነው የግንዛቤ እጥረት በመኖሩ ነው፡፡ በአገር ውስጥ ለአትሌቲክስ ስፖርት በህዝብም በመንግስትም በኩል አነስተኛ ትኩረት ነው የሚሰጠው፡፡ ስፖርት አፍቃሪው የአትሌቲክስ ውድድሮችን በስፍራው ተገኝቶ የመከታተል ትእግስት የለውም፡፡
ለእግር ኳስ በተለይም ለባህርማዶ የእግር ኳስ ውድድሮች የሚያጠፋው ጊዜ አትሌቲክስን እንዲዘነጋ አድርጎታል ነው የኮምኒኬሽን ዲያሬክተሩ ሃሳብ፡፡ በሌላ በኩል በመንግስት በኩል ለስፖርቱ በቂ ትኩረት አለመኖሩን ዲያሬክተሩ ይናገራል፡፡ አትሌቲክሱ ኬንያ ውስጥ የሚሰጠው ትኩረትና እዚህ ያለው ሁኔታ ለማነፃፀር የሚከብድ ነው፡፡ በኬንያ የአትሌቲክስ መሰረተ ልማቶች እጅግ በጣም ተስፋፍተዋል። ማሰልጠኛዎች፤ አካዳሚዎች፤ ስታድዬሞችና የመኖርያ ካምፖች በየሰፈሩ፤ በየከተማው ተገንብተዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የአትሌቲክስ ማናጀሮች ኬንያ ውስጥ በስፋት እየሰሩ ሲሆን ኢትዮጲያ ውስጥ ግን እጅግ ውስን ነው፡፡ እንድኮምንኬሽን ዲያሬክተሩ አስተያየት ኬንያ ውስጥ የአትሌቲክስ ማናጀሮች በነፃነት መስራታቸው ከመንግስት ፖሊሲ ጋር  የሚያያዝ ነው፡፡ መሬት መግዛት ከፈለገ በቀላሉ ይሳካላቸዋል፤ የመኖርያ ካምፕ፤ የስልጠና መሰረተልማት በማሟላት አትሌቶችን መልምለው ይሰራሉ፡፡ በየራሳቸው ቦታ እየኖሩ በመስራት አትሌቶችን ርስበርስ ያወዳደራሉ። ከዚያም አለም አቀፍ ውድድሮችን በማሳተፍ ስፖርቱን በኢኮኖሚ እንዲጠናከር አድርገዋል፡፡ ኢትዮጲያ ውስጥ ማናጀሮች መኖርና መስራት ከፈለጉ መሬት በሊዝ መግዛት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለስራቸው ስለማያመቻቸው አይፈልጉትም፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በማዘወተርያ ስፍራዎችና በስፖርት መሰረተልማቶች አለማሟላት ክፉኛ ተጎድቷል፡፡ የኢትዮጲያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የኮምኒኬሽን ዲያሬክተር ብሄራዊ ሻምፒዮናውን የሚካሄድበት ሜዳ በልመና መገኘቱን፤ ውድድሩን በተሟላ ትራክ ላይ ሳይሆን በልምምድ መሮጫ ላይ ለማካሄድ መገደዳቸውን ያስገነዝባል፡፡ በአገር ውስጥ በደንብ የተሟላ የስፖርት መሰረተልማት ሳይኖር አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ስኬታማ መሆናቸው እንደተዓምር ሊታይ እንደሚችልም ይገልፃል፡፡ የባህል ስፖርት ሚኒስትር የዘንድሮ ሻምፒዮናው ሲከፈት ይህን ችግር መገንዘቡን በሚኒስትሩ በኩል አስታውቋል፡፡ ሚንስተር ቀጀላ መርጋሳ ባሰሙት ንግግር አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ውድድሮችን እየመራ እንዲቀጥል መንግስት ደግሞ የስፖርት መሰረተልማቶችን በመገንባት፤ የስፖርት ማዘወተሪያና መወዳደርያ ስፈራዎች በብዛት በመስራት ሃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡

በረጅም ርቀት ያለው አቅምና
 የሐዋሳው ውድድር
የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው ባልተሟላ መሰረተ ልማት የሚካሄድ ቢሆንም በተለያዩ የውድድር መደቦች አስደናቂ ፉክክሮች እየተካሄዱ ናቸው፡፡ በተለይ በረጅም ርቀት ውድድሮች ከመክፈቻው ጀምሮ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው አትሌቶች በብዛት መሳተፋቸው ልዩ ድምቀት ማምጣቱን የጠቀሰው የኮምኒኬሽን ዲያሬክተሩ በ10ሺ ሜትር በሁለቱም ፆታዎች በተካሄዱት ውድድሮች ላይ በወንዶች 15 በሴቶች 14 ፕሮፌሽናል አትሌቶች መወዳደራቸውን አንስቷል፡፡ ባለፉት ሻምፒዮናዎች ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው አትሌቶች እንደሚሳተፉ ይገለፅና በተለያዩ ምክንያቶች ተሳትፎ አያደርጉም ነበር ያለው ስለሺ፤ ዘንድሮ ግን ሁሉም ክልሎችና ክለቦች ልዩ ትኩረት በመስጠታቸው ፕሮፌሽናል አትሌቶች ቃላቸውን አክብረው እየተሳተፉ ናቸው ብላል፡፡ ሰሞኑን በሻምፒዮናው በ10ሺ ሜትር ላይ በወንዶች እስከ 70 በሴቶች እስከ 40 አትሌቶች መወዳደራቸው አስደናቂ ሆኗል፡፡
 በመዝጊያው በሁለቱም ፆታዎች በሚደረጉት  የ5ሺ ሜትር ውድድሮችም ላይ ተመሳሳይ ድምቀት እንደሚፈጠርም ይጠበቃል፡፡
በአትሌቲክስ ሻምፒዮናው በተለይ በ10ሺ ሜትር ውድድር ላይ ከ1 እስከ ስምንተኛ ደረጃ ያገኙት አትሌቶች በቀጣይ የዓለም ሻምፒዮናን ለመሳተፍ በሚያስችለው እድል ለመግባት ልዩ ውድድር ሐዋሳ ላይ መዘጋጀቱንም የኮምኒኬሽን ዲያሬክተሩ ስለሺ ብስራት ገልጿል፡፡ የሐዋሳው ውድድር የተዘጋጀው በረጅም ርቀት ኢትዮጲያን በዓለም ሻምፒዮና ላይ የሚወክሉትን አትሌቶች ለመለየት ነው፡፡ በኢትዮጲያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከ1 እስከ 8ኛ ደረጃ ያገኙት፤ በሻምፒዮናው ያልተሳተፉና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥሩ ውጤት ያላቸው አትሌቶች በአንድ ላይ በሐዋሳው የዓለም ሻምፒዮና አትሌቶች መምረጫ ውድድር ላይ ይሳተፋሉ፡፡
የኮምኒኬሽን ዲያሬክተሩ ስለሺ ብስራት ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው የሃወሳው ውድድር ከዚህ በፊት በከፍተኛ ወጭ ሄንግሎ ላይ ሲካሄድ የነበረውን ተመሳሳይ ውድድር የተካ ነው፡፡ በሐዋሳ የሚገኘው ስታድዬም ለሁለት ተከታታይ ዓመት በአለም አትሌቲክስ የብቃት ማረጋገጫ የተሰጠው፤ በሜዳው የተሟላና ደረጃውን የጠበቀ ትራክ የተነጠፈለትና አየሩም ለሩጫ ውድድር ተስማሚ ሆኖ መገኘቱንም አብራርቷል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ባስቀመጠው ቀነ ገደብ መሰረት ለማራቶን እና የርምጃ ውድድሮች ሚኒማ የማሟያ እና ቡድንን የማሳወቂያ ጊዜው የቀረው ከሁለት ሳምንት ያነሰ ጊዜ ነው፡፡ በረጅም ርቀት፤ በመካከለኛ ርቀት፤ በአጭር ርቀት እና በሜዳ ላይ ስፖርቶች ለሚኒማው እስከ ሐምሌ አጋማሽ ጁላይ 30 ድረስ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ መሳተፍ ይቻላል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ እንዳመለከተው በዓለም ሻምፒዮናው የሚሳተፉ አትሌቶችን ሚኒማውን የማሟያ ቀነ ገደብ ተከትሎ በተለያዩ መስፈርቶች አወዳድሮ መምምረጥ የየፌደሬሽኑ አሰራር ነው፡፡ ባለፈው በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የወርቅ ሜዳልያ ያስመዘገቡና በ2022 የዳይመንድ ሊግን ያሸነፉ አትሌቶች በቀጥታ የመሳተፍ እድል ይኖራቸዋል፡፡
 ኬንያ አትሌቲክስ የዓለም ሻምፒዮና ቡድኑን የሚመርጠው ጁላይ 14 እና 15 ናይሮቢ ላይ በሚያካሂደው ብሄራዊ ሻምፒዮና ነው፡፡ ሻምፒዮናው የ2023 የአትሌቲክስ ደረጃ በሚል ስያሜ በዘመናዊው የአትሌቲክስ ስታድዬም ኪሳራኒ ላይ የሚደረግ ሲሆን በየውድድር መደቡ ከ1 እስከ 8ኛ ደረጃ የሚያገኙ አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮናው የምርጫ መስፈርት ውስጥ የመግባት እድል ያገኛሉ፡፡


Read 931 times Last modified on Saturday, 20 May 2023 20:49