Print this page
Saturday, 20 May 2023 20:23

“እያንዳንዱ ሰው በቀን ለአምስት ደቂቃ...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“እያንዳንዱ ሰው በቀን ለአምስት ደቂቃ ያህል ደደብ ይሆናል፡፡ ብልህነት የሚባለው ያንን ገደብ አለማለፍ ነው” የምትል ነገር አለች፡፡ አሪፍ አይደለች! ገና መጻፍ ከመጀመሬ ነገር፣ ነገር ያሰኘኝ አስመሰለብኝሳ! በቃ “ኦፍ ዘ ሬከርድ” እንደሚሉት አይነት ውሰዱትማ!
“እንደው በባዶ ቤት መጥተሸ...”
“ኸረ ችግር የለውም፡፡ እኔ እኮ ላያችሁ ነው የመጣሁት፡፡”
“እንደው አንድ፣ ሁለት  ቲማቲም አለችኝ፡፡ እሷኑ ከተፍ፣ ከተፍ አድርጌ ልስጥሽ!”
አዎ፣ እንዲህ የምንባባልበት ዘመን እንኳን ‘ሜሞሪ’ ብቻ እየሆነ ነው፡፡ ኪሎ ቲማቲም ዘጠና ብር! “ስሚ ኪሎ ቲማቲም እኮ ዘጠና ብር ገባ!” ሲባል...አለ አይደል...”አንቺ አስደነገጥሽኝ እኮ! እኔ እንዲህ አይነት ቀልድ አልፈልግም፣” አይነት ምላሽ ሊያስከትል ይችል ነበር፡፡ ሠላሳ ብር ገባች የተባለ ጊዜ “እሪ!” ያስባለች ቲማቲም ነች፣ አሁን መቶ ልትደፍን ጫፍ ላይ የደረሰችው!
እናላችሁ... ‘ፈረንጅ’ ቢሆን እኮ እንዲህ የሚያስደነግጥ ነገር ሲገጥመው፣ “ውድ ቢሊቭ ኢት!” ይል ነበር፡፡ እኛ ግን ምንም ነገር ሊሆን የሚችልበት ዘመን ላይ ደርሰናል ብለን ስለደመደምን የተረፈችን “እህህ!” ብቻ ነች፡፡
ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...በአንድ መልኩ ወይ በሌላ ባለጊዜዎች፣ ወይም ባለጊዜ የምንመስል፣ ወይም እንደ ባለጊዜ የሚያደርገን ሰዎች አልበዛንባችሁም! እንክት ነዋ... በምንም ዘመን ባለጊዜ የሚባሉ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ አለ አይደል...ነገርዬው ሁሉ የተመቻቸላቸው፣ ሁሉም ምቹ ሁሉም ዝግጁ የሚሆንላቸው፣ ለሌላው የተከረቸሙ በሮች ለእነሱ ወለል የሚሉላቸው፡፡
ከአቅማቸው በላይ የሆነ ጉዳይ ሲገጥማቸውም “ምን የቆረጠው ነው እንዲህ የሚያደርግህ/የሚያደርግሽ!” የሚሉ ታላላቅ ወንድሞች ያሏቸው፡፡ (እንትና ሰሞኑን በጣም የተመቸህ የምትመስለው አንተም ‘ታላቅ ወንድም’ አገኘህ እንዴ! ቂ...ቂ...ቂ... የምር ግን፣ እንዲህ ብለን ብንጠይቃቸው እንደ ሀጢአት የማይመዘገብብን ወዳጆች የሉንም ትላላችሁ! ያው ጥያቄያችንን ‘ብራዘርሊ’ ባልሆነ መንፈስ ወስደው በኋላ እኛኑም ልክ ሊያገቡን መሞከራቸው ባይቀርም፡፡)
“እያንዳንዱ ሰው በቀን ለአምስት ደቂቃ ያህል ደደብ ይሆናል...”
ይህችን ቀልድ ቢጤ ስሙኝማ..ሴትየዋ ለብዙ ዓመታት አስተማሪ ሆነው ሲያገለግሉ ኖረው በመጨረሻ ጡረታ ይወጣሉ፡፡ በአስተማሪነታቸው ጊዜ ከሚታወቁባቸው ነገሮች መሀል ጥፋት የፈጸመ ተማሪን፣ “ሁለተኛ ጥፋት አልፈጽምም!” አይነት ነገሮች፣ ብዙ መቶ ጊዜ ደጋግመው እንዲጽፉ ማድረግ ነበር፡፡
ታዲያ ጡረታ ከወጡ በኋላ አንድ ቀን ከፍጥነት በላይ በማሽከርከር ተከሰው ዳኛ ፊት ይቀርባሉ፡፡ የቀረቡበት ችሎት ዳኛ ደግሞ አምስተኛ ክፍል ተማሪያቸው የነበሩ ናቸው፡፡ ዳኛው  ወዲያውኑ ነው የለዩዋቸው፡፡
“እማማ፣ አወቁኝ?”
“አላወቅሁዎትም፣ ክቡር ዳኛ፡፡”
“አምስተኛ ክፍል አስተምረውኝ ነበር፤”
“እህ፣ አሁን መልክሀ ትዝ አለኝ፡፡”
“እማማ፣ ለዓመታት እዚህ ወንበር ላይ ተቀምጬ፣ ይህችን ሰዓት በናፍቆት ስጠብቅ ነው የኖርኩት፡፡ አሁን እዛች ጠረጴዛ ጋ ቁጭ ይበሉና ‘ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ ማሽከርከር የለብኝም፣’ እያሉ አምስት መቶ ጊዜ ይጻፉ፣” ብለው ፈረዱባቸው ይባላል፡፡
“እያንዳንዱ ሰው በቀን ለአምስት ደቂቃ ያህል ደደብ ይሆናል...”
እናማ፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል... ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ... ባለጊዜ የሚባሉ ሰዎችን  የሚከብበው አጃቢ ብዛቱ፡
የባለጊዜ ‘ቦተሊከኛ’ አጃቢው መአት ነው፡፡
የባለጊዜ ‘ባለሀብት’ አጃቢው መአት ነው፡፡
የባለጊዜ ‘አርቲስት’ አጃቢው መአት ነው፡፡
የባለጊዜ ‘አክቲቪስት’ አጃቢው መአት ነው፡፡
የባለጊዜ ጋዜጠኛ…አጃቢው መአት ነው፡፡ (አሀ፣ ድሮ ነዋ ጋዜጠኛ አጃቢ ያልነበረው፡፡ በአንድ ወቅት እንዳጫወትኳችሁ፣ አንድ ጊዜ የሆነ ወዳጅ፣ ከሆነች ዜጋ ጋር ሊያስተዋውቀኝ ሲሞክር፣ “እሱ ደግሞ ጋዜጠኛ ነው፣” ይላታል፡፡ እሷዬዋ ምን ብትል ጥሩ ነው...
“አፈር በበላሁ!”
“ስማ ከመቼ ወዲህ ነው እነ እንትና ከዛ ማነው ከሚሉት ጋር ይህን ያህል ወዳጅ የሆኑት? በፊት እንደዛ ሲያጥላሉት፣ እንደዛ ሲንቁት የነበረ ሰው አይደለም እንዴ! አሁን ምን ተገኘና ነው ከስሩ አልጠፋ ያሉት?”
“እባክህ ወዳጅ ሆነው አይደለም፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ እነሱ እንኳን እንዲህ  ይጠቅመናል የሚሉት ሰው አግኝተው እንዲሁም እንዲሁ ናቸው፡፡”
“ስለማን እያወራሁ እንደሆነ ገብቶሀል?”
“አዎ፣ ስለእንትና አይደለም?”
“እኮ፣ እንዴት ነው እሱ ለእነሱ የሚጠቅማቸው? እስከዛሬ እሱ አይደል እንዴ ሲጠቀምባቸው የኖረው!”
“አንተ ሰውዬ አየር ላይ ተንሳፈህ ነው እንዴ ያለኸው! ነገር ተገለባብጦ እነሱ የባለጊዜዎች ቺርሊደር፣ እሱ ደግሞ እጩ ባለጊዜ ከሆነ ቆየ እኮ! አሁን እሱ ባለገንዘብና ባለወፋፍራም ዘመዶች፣ እነሱ ደግሞ ገንዘብ ፈላጊዎችና ገንዘብ ሊያስገኙላቸው የሚችሉ ወፋፍራም ዘመዶች ፈላጊዎች ሆነዋል፡፡”
“አትለኝም! በቃ እኛ ብቻ ነና አንድ ቦታ ላይ ተቸክለን የቀረነው!”
“ይልቅ እወቅበትና ወይ የባለፖለቲካ፣ ወይ የባለገንዘብ፡ ወይ ‘የባለሴሊብሪቲ’ ምናምን አጃቢ ብትሆን ይሻልሀል፡፡
አይዞህ፣ ሞራልና ህሊና የሚባሉ ነገሮች አውላላ ሜዳ ላይ ጥለውን ከጠፉ ስለሰነበቱ የሰላም እንቅልፍህን የሚወስድብሀ የለም፡፡”
“እያንዳንዱ ሰው በቀን ለአምስት ደቂቃ ያህል ደደብ ይሆናል...”
ምን መሰላችሁ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ ... ቦተሊከኞች በሏቸው፣ ባለገንዘቦች በሏቸው፣ ባለዝናዎች በሏቸው ራሳቸው ከሚያበላሿቸው ነገሮች ይልቅ አጃቢዎቻቸው በእነሱ ስም የሚፈጽሟቸው የታሰበባቸውና የታቀደባቸው እልፍ ስህተቶች ናቸው ነገሮችን ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚባለው አይነት ቁልቁል የሚያንደረድሯቸው፡፡
አሀ...የባለጊዜ አጃቢ እኮ ብዙ ጊዜ ከዋነኞቹ አማካሪዎች አንዱ ነዋ፣ ዋነኛ የ‘ዜና ምንጭ’ (“አሳባቂ” ልል ጀምሬ ራሴን በራሴ በ‘ብሎክ’ ጭጭ አደረግሁት! ቂ...ቂ...ቂ...) ነዋ፣ ከዋነኞቹ ነገር አባባሾችና፣ የ‘አማሪካን’ ኤምባሲ ደጃፍ ላይ ያለው አይነት አረንጓዴ መስክ ላይ አቧራ ለማስነሳት ከሚሞክሩት መሀል አንዱ ነዋ!  
እናላችሁ..የባለጊዜ አጃቢ መአት ነን፡፡ ሳያስነጥሰው መሀረብ የምናቀርብ፣ የሌለ አቧራ ከመኪናው የፊት መስታወት ላይ በሸሚዛችን እጀታ አበስ የምናደርግ፣ ለሚሰጠን ማንኛውም አይነት “የዛች የእንትናን መውጫ መግቢያ አጥናልኝ...” ሚሽን ሁሌም በተጠንቀቅ የምንገኝ፡፡
ሰውየው በተደጋጋሚ ከሥራ ፈቃድ በመጠየቅ ይታወቃል፡፡ አንድ ቀንም አለቃው ዘንድ ቀርቦ “የሦስት ቀን ፈቃድ እንዲሰጠኝ እፈልጋለሁ፣” ይላል፡፡
አለቅየውም፣ “ለምን ምክንያት?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
“አስቸኳይ ጉዳይ ገጥሞኝ ነው፡፡”
“አሁንም አስቸኳይ ጉዳይ! የአሁኑን ምክንያትህን ባውቅ ደስ ይለኛል፤” ይለዋል፡፡ “ከዚህ ቀደም ለወንድ አያትህ ቀብር አራት ጊዜ ፈቃድ ወስደህ፣ የአሁኑ ምክንያትህ ምንድነው?” ሰውየው ምን ቢል ጥሩ ነው...
“አያቴ እንደገና ለአምስተኛ ጊዜ ባል ልታገባ ነው፡፡” (እኔ የምለው ሴትየዋ ከዚህች አስቀያሚ ዓለም ወደዚያኛው ዓለም አስተላላፊ ኬላ ነገር ናቸው እንዴ! ቂ...ቂ...ቂ...)
“እያንዳንዱ ሰው በቀን ለአምስት ደቂቃ ያህል ደደብ ይሆናል...”
ምናልባትም የባለጊዜ አጃቢና ‘ቺርሊደር’ የሚያደርገን ይቺ የአምስት “ጦሽ” ማለት ሳትሆን አትቀርም!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1022 times