Saturday, 20 May 2023 21:06

“ዝንጀሮ እንኳን ባቅሙ ያውቃታል ወዳጁን”

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(2 votes)

ስቅየት ተጠራቅሞ፣ እን‘ዳስም ሲያፍነኝ፣
እንደ ማርያም መንገድ፣ መሿለኪያ የሆንከኝ፤
ገነት እንድገባ፣ ትኬት የለገስከኝ፤…
§
አባቴ እዚህች ምድር ላይ ሳለ የሠራውም ሆነ የዘራው ሐጢያት አንድ ብቻ ነበር - እኔ። ባለ ቀይ ዳማ ፊቱ አባቴ፣ እስከ እስትንፋሱ ሕቅታ ድረስ ከእኔ ውጭ ሌላ ሕጸጽ አልነበረበትም::   
§
ሰዎች ስለ ውቅያኖስ ስክነት፣ ስለ ወይን ጠጅ አዝናኝነት፣ ስለ ኮልታፋ አንደበት አስደሳችነት፣ ስለ ግጥም ረቂቂነት፣ ስለ ፈላስፋ ሊቅነት፣ ስለ ጣኦስ ውበት፣ ስለ ገጣሚ ቅኔያዊነት፣ ስለ ነቢዩ ሞሐመድ ሠለላህ ወ ሠለላህ ቁጥብነት፣ ስለ ጃዝ ሙዚቃ ልከኛነት፣ ስለ ሰዓሊ ምዕናባዊነት፣ ስለ ፈጣሪ ከኀሊነት፣ ስለ ኢድ አል ፈጥር አበክሮአዊነት፣ ስለ ቢራቢሮ አበባ ወዳድነት፣ ስለ ድርሳናት አስተማሪነት፣ ስለ ፋሲካ ዋጅነት፣ ስለ ለምለም መስክ አካሚነት፣ ስለ ጥቁር አዝሙድ ፍቱንነት፣ ስለ አራራይ ስልት እምቅነት፣ ስለ ማንጎ ጣፋጭነት፣ ስለ ዋሽንት አንሰፍሳፊነት፣ ስለ ዘምዘም መድኀኒትነት፣ ስለ ሕጻናት ትንፋሽ ተናፋቂነት፣ ስለ ደንደሳም ዳሌ አማላይነት፣ ስለ ቡና አንቂነት፣ ስለ ሚዳቋ ሥጋ ጣፋጭነት፣ ስለ በገና ድምጽ አስገምጋሚነት፣ ስለ ጫካ ማር ፈዋሽነት… ሲወያዩ የቁብ እንኳን አይደነቅም። አይነቅፍም፤ አይደግፍም…
…ሽንቁር ሰንኮፉን በዝምታ ያዳፍናል። ዘለግ ባለ ዝምታ መሀል ከኮት ኪሱ ሲጃራ አከታትሎ እያወጣ ይምጋል። ከአክዋኋኑ ቤተ-መቅደስ ዘልቆ የሚያጤስ ይመስለኛል፤
ከሰውነት ይልቅ ግዑዝነት ይጠቀልለዋል፤ በስሜት አስገዳጅነት ተለዋዋጭ ጠባይ አያሳይም፤
ሲደበት አያንጎላጅም። ሲናደድ እጆቹን አያናጥብም። በእንቢተኝነት አያንገረብብም። ማጤስ ውል ሲለው አያፋሽክም። ቀፈቱ ሲጎድል ‹እንጀራ› አይልም። ሲራመድ እግሮቹን በመንሳፈፍ ስልት ያንከላውሳል። ሲሳካለት አይፈነጭም። ዓላማው ሲከሽፍ ጠጉሩን አይነጭም። ሲቆጣ አይጎፈላም። በማን አኽሎኝነት አይንጎራደድም። በድል አድራጊነት አይወራጭም። ሲበሳጭ አይንጠረበብም። ሲደሰት ፊቱ የቁብ አይፈካም። ሕይወቱ በእምርታ ውስጥ ትውደቅ በዕክል እንጃለት። በጆሯም የሸክላ ብርጭቆ ሻሂ ይምጋል፤ ቅርናቱ ናላ የሚያዞር ትንባሆ ያጤሳል። ውጭ አያምረውም። ለመሆኑ ሥራ ነበረው እንዴ? ቅቤ እንደ ተቀባች ሴት ከቤት አይወጣም። ሲብሰለሰል አይስተዋልም። ጉዳቱን፣ ስብራቱን፣ ደስታውንና ኀዘኑን ከሁኔታው እንዳልረዳ ፈጽሞ ሁኔታ አልነበረውም፤
አባቴ እንደ ስዕል ረቂቂ ነበር፤ እንደ ቅኔ ድብቅ፤ ጭው ያለ ባሕር ነው፤ ተፈጥሮ አሽሟጣበታለች፤
§
የአባቴን ሁኔታ አይቼ-አይቼ ተፈጥሮን እቃኛለሁ…
…እርሱ ልጓም ነውና፣ ደንታ ቢያጣም ዝምታ ቢያበዛም ሃምሳ እግር ጥርሱን በወይራ ሊያፀዳ ይሆናል። አጋዘን ከእግሩ የገባውን እሾክ በወረንጦ ካወጣ በኋላ ጫፉን በጥርሶቹ ይሰባብር እንደሆነ ብዬ እገምታለሁ። ዝንቦች ሊያነጥሱ ይችላሉ። ትንኞች ሲያናፉ፣ ጅቦች የእንቁጣጣሽ ዕለት አበባ ስለው የመንደርተኛውን በር እየቆረቆሩ ፍራንክ ይለቅሙ ይሆናል፤ ቆቅ እንደ ባልቴት ቡናዋን ቀቅላ ወሬ ስትፈትል ትውል ይሆናል። ዔሊዎች ጭው ያለ ሜዳ ላይ ዓመታዊ የአትሌቲክስ ውድድር የሚያካሂዱ ይመስለኛል። ቡላ ጅንጀሮ ከቀይ ዳማ ጅንጀሮ ተቧድነው ፍልሚያ ሊገጥሙ ይችላሉ። የዱር አራዊት አምባገነኑ አንበሳ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ያውጁ ይሆናል። ሌላው ደግሞ ሃያ ሁለት ጉንዳኖች በሁለት ጎራ ሜዳ ገብተው ቅሪላ ሊነርቱ ይችላሉ። ቢራቢሮ እዝን ሸክፎ ለቀስተኛ ዘመዱን ያጽናና ይሆናል። ርግብ የማርያም ጥዋ የምትጠጣ ይመስለኛል። ድኩላ ኒካ ሊያደርግ ይችላል። ዝሆን እዩዋት ስትናፍቀኝ የሚልበት የሙዚቃ ኮንሰርት ይኖረው ይሆናል። አሳማ ችሎት እንደቆመስ ማን ያውቃል? ወጠጤ የሜዳ አህያ ጫት ቅሞ ፖለቲካውን ሊደስኩር ይችላል።
 ቆርኪ ሥራ ደርሳ ስትመለስ እግረ-መንገድዋን የታመመ ዘመድዋን የምታጽናና ይመስለኛል። ጦጣ ከመጠን በላይ ጠጥታ መኺና ታሽከረክር ይሆናል - አደጋ አድርሳ የጦጣ መንጋ እንድትፈጅ። ከቀብር መልስ አይጦች ድመት ቤት ድንኳን ጥለው ካርታ በመጫወትና ጠጅ በመጠጣት ድብርታቸውን ይወጡ ይሆናል። ሽማግሌው እባብ ነውጠኛውን እባብ ጠርቶ የሚመክር ይመስለኛል። ዳኪዬ ተማሪ ቤት ዘልቃ ‹ሀ፣ ሁ› ታንበለብል ይሆናል። ወንዱ ነብር ከአደን ተዘናግቶ የሴቷን ነብር ዳሌ እያየ የሚነኾልል ይመስለኛል፤   
ቢሆንም አልጠይቅም፤ ዝም፣ ጽልም…     
§
ተማሪ ቤት በእረፍት ሰዓት ሜዳ ለሜዳ ስንሯሯጥ በፈስ የሚያጥነኝ ጓደኛዬ ጣሂር…
‹‹አባትህ ከቤት የማይወጡት ስለሚያጠቡ ነው እንዴ?›› አለኝ
ስክር አልኩ፤ ስክርክር….
ጣሂር ‹ለሒሳብ ስሌት› እያለ ጥሬ ባቄላ ያመጣል፤ ከዚያ በዝግታ እያሻመደ ሰዓት ይገድላል። ፈሱ እንዲያ የሚያውከው በሚቅመው ጥሬ ባቄላ ምክንያት ይሆናል። የክር ሹራቡ በግራ እጁ ክርን በኩል ተቦትርፎ ላት መስሏል፤
አንገቱ ላይ የደረሰ ሆዱን ወደ እኔ ገፋ አድርጎ አፍጦብኛል…
‹‹እንዴት?››
ንውዝ ሆኜአለሁ
‹‹አባትና እናቴ ሲያወሩ ሰማሁ፤ ግን አላመንኩም››
‹‹ምኑን?››
‹‹አባትህ ማጥባታቸውን››
ግራ ስለገባኝ ራሴን ግራና ቀኝ አማታሁ
ንውዝ ውስጥ እንዳለሁ፣ የእረፍት ሰዓት ሲገባደድ እክፍል ገባን። የሣይንስ አስተማሪያችን እትዬ ጫልቱ ገብታ ስለ ጾታ ማስተማር ጀመረች። አያይዛ ስለ አጥቢ እና ኢ-አጥቢ አወሳች። ሰውም ይሁን አውሬ አጥቢ ከሆነ ጡት እንዳለውና ኢ-አጥቢ ደግሞ ጡት እንደሌለው አወሳችን። የሰው ልጆች ጡት ደረታቸው ላይ እንደሚገኝ ማብራሪያ ሰጠች…
…ነገሩ ስለተሳከረብኝ እጄን አውጥቼ…     
‹‹እትዬ፣ አባት ያጠባል እንዴ?›› ጠየኩ
ተማሪው አውካካ። እትዬ በኩርኩም አጎነቺኝ፤ እራሴን ስቼ ክልትው ካልኩበት ሰይጣን እንደምንም ተሯሩጦ አወጣኝ እንጂ።
ትምህርቱ አልቆ በጥድፊያ ቤት ደረስኩ። እናቴ ደፍ ላይ ቆማ በጉጉት እየጠበቀቺኝ ነበር። እንደ ወትሮዋ ጉንጬን ስማ ቅራቅንቦዬን ተቀበለቺኝ። ትኩረት እንደነሳኋት ገብቷታል። ቁንዳላዬን እያሻሸች እውስጥ ከተተቺኝ።
አባቴ ወደ በር ሰጎ ቁጭ ብሏል፤ በቁሜ ለሰኮንዶች ትክ ብዬ ፈተሽኩት። ደረት ደረቱን ገረመምኩ። ግን ምን ያደርጋል የጡት ቅርጽ አጣሁበት። ታዲያ ጡት ደረት ላይ ካልሆነ በየት በኩል ሊሆን ይችላል? እትዬ ተሳስታ ይሆናል…
…መስከን ስለታከተኝ ደጋግሜ ሰለልኩት፤ አሁንም አጣሁበት። ጡት ለዓይን ተጋላጭ አልነበረምን? ለመሆኑ የሚጠባ ነገር ፋይዳው ለምግብነት ከሆነ ስለምን አልተደበቀም? ምግብ ሲጋለጥ ጥሩ አይመጣም። ያባቴ ጡት ከእይታ ውጪ ነው፤ በሸቅኩ በጣም። የእሱ ተፈጥሮ የተቃረነ ሊሆን ስለሚችል ጡቱ ደረቱ ላይ ሳይሆን እንብርቱ አካባቢ፣ ወይም ሌላ አካሉ ላይ በስልት ተለጥፎ ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል።
ምግብ ተሰጥቶኝ ችላ ብዬ ጥቂት አሰብኩ፤ እናቴ የሚጠጣ ውኃ አሰናድታ ቀርባኝ…
‹‹ምነው አትበላም እንዴ?›› አነቃቺኝ
ቀና አልኩ፤ ምን ልበላት? በሃሜት ደረጃ፣ ሴቴ ውህድ ወንድ አባቴ የሰውነት አካሉ…. ጣሂር ጮሎ እንደሆነ አውቄአለሁ፤
‹‹እማ፣ አባቴ ያጠባል እንዴ?››
ትን ብሏት ልትሞት
ካ…ካ…ካ…ካ…ካ…ካ….ካ…ካ…
‹‹ማነው እንደሱ ያለህ?›› ሳቋ በከፊል ሲበርድላት
‹‹ጣሂር፣‹ከቤትየማይወጣው            ስለሚያጠባ ነው አሉኝ› አለ››
‹‹አይይለም››
‹‹እና?››
‹‹ላንተ አዝኖ››
‹‹ላ… ን… ተ…?››
አባቴ ተወንጭፎ መጥቶ እግሬ ሥር ተደፋ። እግሮቼን አጥብቆ አቀፋቸው። የእግሮቼን ሽታ ተቋቁሞ በለኾሳስ ያነበንባል። ጫማዬን እንደ መሳም ካለ በኋላ…
‹‹ልጄ ማረኝ፣ ማረኝ!›› ተማጠነ
ብርክ መታኝ
‹‹ይነሱ እንጂ፣ ይነሱ›› እናቴ ተቆጣች  
‹‹ይኼውልህ፣ በተደጋጋሚ እናትህ ‹ይቅርብን› እያለች እኔው ችክ ብዬ ወለድንህ። በኋላ አንተን ለማስገረዝ ጥበቃ ከምሠራበት ድርጅት ከቀጣይ ደሞዝ የሚቆረጥ ሃምሣ ብር ተበደርኩ። ወሩ ሲደርስ ዕዳችንን ከፈልን… ወዲያው ኑሯችን ተናጋ፤ ጎረበጠን አልጋ።
እናልህ ተው ስባል ባለመተዌ ከዚያች ቀን አንስቶ ተጎዳን። አንተንም እናትህንም ለችግር ዳረኳችሁ። በዚህ ተበሳጭቼ ኬላ ጥሼ ኬኒያ መሰደድ ቃትቶኝ መንገድ ጀምሬ መመለሴን ብነግርህ እንዳትደነቅ››   
አልተዋጠልኝም
‹‹እና ታጠባለህ ማለት ነው?››
‹‹አዪ››
‹‹ታዲያ ለምን ከቤት አትወጣም?››
‹‹ከቤት የማልወጣው ቁጭቱንና ሃፍረቱን ስለማልወጣው ነው››
ጥያቄም ምላሽም ደበተኝ። እንደተንኮታኮትኩ ገበታው ተነሳ። ነገሩ ባይገለጥልኝም ውስጤ ተሸነቋቁሯል…
…መስክ ሸሽቶ እልፍኝ የመሸገው አባቴ፣ ትክክል ያድርግ አያድርግ ለይቶ ማወቅ ታከተኝ፤ ይህንን መዳኝት ከባድ የሕሊና ሥራ አይሆንም? የቱ ነው ትክክል? ሥራው፣ ወይስ ጸጸቱ? ደግሞ ጸጸት፣ ቁጭት፣ ተብሰልስሎት፣ ራስን መቅጣት፣ ከሃፍረት መሸሸግ… ስንት ዓይነት መልክ አላቸው? መጠናቸውስ ስንት ነበርን?  
Read 7439 times