Saturday, 20 May 2023 21:20

የእንዳለጌታ ድርሳነ ሳንሱር

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(0 votes)

 ከትላንት እስከ ዛሬ ባልተመቻቸ የአገራችን የስነጽሁፍ መስክ ላይ እየተጉ እምናነበውን ካላሳጡን እውቅ ደራሲያን ከቀዳሚዎቹ ቁንጮ ሆኖ የሚጠቀስ ነው - እንዳለጌታ ከበደ፡፡ በጋራ ከሰራቸው ውጭ በግሉ ያሳተማቸው አስራ ሶስት መጻሕፍቶቹ በተደጋጋሚ ታትመው በስፋት ተነበውለታል፡፡ ምናልባት ወደፊት ኢትዮጵያ ስለሚኖራት ስነጽሁፍ እንደነ-እንዳለጌታ ያሉ ከያንያን ከአሁኑ እያኖሩት ያሉት ቅርስ መነሻና መንደርደሪያ ስለመሆናቸው መልክዐ ምድሩን ግራና ቀኝ ቃኝተን መገመት አይሳነንም፡፡
የሳንሱር ነገረ-ጉዳይ በዋንኛነት አጽንኦት ተሰጥቶት የተቀነቀነበት (ድርሳነ ሳንሱር) የእንዳለጌታ በቅርቡ ለገጸ-ንባብ ያበረከተልን “እስረኞቹ” አዲሱ መጽሐፉም በኢ-ልቦለዱ ዘውግ ተካትቶ እሚመደብ ስራ ነው፡፡…እንዳለጌታ ዛሬም እንደወትሮ ሁሉ በነጠሩና በተመረጡ ስስ ውብ ቃላት (ሳንሱርን ከፊት አስቀድሞ) ስሜትን እያብረከረከ፣ ልብን እየማረከ…ትናትን ተርኳል፣ ዛሬን ዘግቧል፣ ነገንም ተንብይዋል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲያ፤ ከ“ደርሶ መልስ” ወዲህ…ባሳተማቸው (ያልተቀበልናቸው፣ ማዕቀብ፣ በዓሉ ግርማ ህይወቱና ስራዎቹ) ጥራዞቹ እጄ በገቡ ቁጥር፣ እጄን አፌ ላይ የሚያስጭን መገረም ውስጥ ይከቱኛል፡፡ በቃላት እያባበለ በሚሄድ ዜማ በቋንቋ የሚያጫውት አዝናኝ ብዕረኛ እየሆነ መጥቷል፡፡ እንዳለጌታ ተደናቂ ልቦለድ ደራሲ እንደሆነው ሁሉ ማለፍያ ኢ-ልቦለድ የሚታዘልበት አንቀልባ መሆኑን እነሆ በተደጋጋሚ እያስመሰከረ የመጣ ይመስለኛል፡፡
እንደሚታወቀው የሳንሱር ኢላማና ሰለባ ያልሆነ የጥበብ ስራ የለም ማለት ይቻላል፡፡  ሳንሱር አንድ ስራ ለህዝብ ከመቅረቡ በፊት አንድም ለወጣት ተማሪዎቻችን፣ አንድም ለህዝባችን አይበጅም፣ ባያነቧቸው ይመረጣል በሚል ሰበብ እንዳይታተሙ ያግዳል፣ እንዳይሰራጩም ያፍናል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ መጻሕፍት ገለልተኛ በሆኑ ተቋማት ተገምግመው በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማት የወሰዱ ቢሆኑም፣ ሳንሱር ግን በአፍራሽ ሚናው ጥርስ ሲነክስባቸው በታሪክ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡
 እንዳለጌታ በሳንሱር ሳቢያ ስለተቃጠሉና ስለጠፉ መጻሕፍት ታሪክ ሲነግረን፣ ዜና መዋዕልና ጥናታዊ ሰነዶችን እየገለጠ ሲያስረዳን…ታሪኮቹ አንዳች ነገር እንዳመለጠን አስበው የሚያሳስቡ፣ ተቆጭተውም የሚያስቆጩ ናቸው፡፡ የሳንሱር ነባራዊ ሁኔታ በብዙ ተመራማሪዎችና የታሪክ ባለሙያዎች፣ የአለማችን እውቅ ፈላስፎች ሲወሳ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለአብነት ከቀደምት የግሪክ ፈላስፎች መካከል ፕሌቶና አርስቶትል ስለ ሳንሱር የነበራቸው አመለካከትና ሙግት ይጠቀሳል፡፡ እይታቸው ግራና ቀኝ፣ አመድና ዱቄት የሆነ ነው፡፡ ፕሌቶ  The Republic  በሚለው መጽሐፉ ለሳንሱር ኅልው መሆን ያለውን አክብሮት ሲያሳይ፣ አርስቶትል በተቃራኒው፤ “ሳንሱር አፋኝና  የአምባገነኖች መጠቀሚያ፣ የጨቋኞች ጨቋኝነት ማረጋገጫ ነው” ባይ ነበር፡፡
እንዳለጌታም ሳንሱር በኢትዮጵያ እንዴት ያለ መልክ እንደነበረው፤ እነማን በሳንሱር ሳማ እንደተለበለቡ፣ እነማ ለሳንሱር መኖር አስፈላጊነት ጥብቅና እንደቆሙ፣ እነማን ሳንሱርን ለመኮነን በየአደባባዩ እንደተሰየሙ፣ ሽንጣቸውን ይዘው እንደተሟገቱ፣ በደርጉና በዘውዱ ምን አይነት መልክ እንደነበረው ወደ ኋላ እየተንደረደረ እያመሳከረና እያሰባጠረ ይተነትናል፣ ይፈትሻል፡፡ ደራሲው ቀደም ሲል “ማዕቀብ” በተሰኘ ስራው የሳንሱርን ሀቲት በምልአት ባይሆንም በተወሰነ መልኩ ሄዶበታል፡፡ በርግጥ ሳንሱር በሁሉም ነገስታትና ዘመነ መንግስታት  የተለያዩ መልኮች ነበሩት፡፡ ስርዓት በተቀየረና ዘመን በተቆጠረ ቁጥር መልኩን ለውጦ ዳግም ይወለዳል እንጂ፡፡ እነሆ ደራሲው በ”ማዕቀብ” ውስጥ ያነሳውን የሳንሱርን ነገረ-ጉዳይ ኩርማን ጭብጡን አስፍቶና አንሰራፍቶ በተሟላና በምልአት ዳግመኛ ታሪካዊ ዳራውን ፈትሾ በሙሉ መጽሐፉ አስደጉሶ ይዞልን የመጣበትን ምክንያት በመግቢያው እንደሚከተለው ያስረዳል፤ “ድርሳነ ሳንሱርን በተመለከተ የጻፍኩት ድርሰት አንድም በአንዳንድ አጥኚዎች የብዙኃን መገናኛ ሙያተኞችና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ከግምቴ በላይ ትኩረት ሲሰጠው ማየቴ፣ አንድም በሳንሱር ጉዳይ ከከያንያን ጋዜጠኞች የሰማኋቸውና ያነበብኳቸው ገጠመኛዊ ተረኮች ከጊዜ ወደ ጊዜ በዝተው ማግኘቴ፣ አንድም በእድሜም በልምድም መጎልመሴ ድርሳነ ሳንሱርን መልሼና መላልሼ እንድቆዝምበት ተገፋፋሁ፡፡” (ገጽ-9) እንዳለጌታ የሳንሱርን ትርክት የሚዳስሰው በልቦለዳዊ ተራኪ ሳይሆን በኢ-ልቦለዳዊ ተራኪ ነው፡፡ ኢ-ልቦለዳዊ ተራኪ ጽሁፍ ስሙ እንደሚያመለክተው ድርጊትን፣ ሁኔታንና ህይወትን በጊዜ ቅደም ተከተል የሚዘረዝርና የሚያቀርብ ነው፡፡ ይህ አጻጻፍ የፀሐፊውን ግላዊ ስሜትና በጉዳዩ ላይ ያለውን ትርጓሜ ወይም ገጠመኛዊ ትንታኔ በምስል ፈጣሪ ቃላትና አረፍተ ነገር አማካኝነት ተከሽኖ የሚቀርብበትም ነው፡፡ በአብዛኛው አደራደሩ የተለመደ የጊዜን ቅደም ተከተል ይዞ የሚፈስ አካሄድ አለው፡፡ የእስረኞቹን የጊዜ ቅደም ተከተል ስናይ ከአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መባቻና ማግስት የነበረውን ውጣ ውረድ እያስቃኘ አሁን እስካለንበት የብልጽግና ፓርቲ ዘመን ድረስ አምጥቶ በዝርዝር ያትታል፡፡ በዚያው ልክ አፍሪካ ውስጥ መጻሕፍት ለጥቃት ሰለባ የሆኑባቸው አጋጣሚዎችም ጥቂት አይደሉም፡፡ እንዳለጌታ፣ ኢፌዱባ ያጠናውን ጥናት ዋቢ አድርጎ እንዳሰፈረው፤ ናይጄሪያ ውስጥ ሳንሱር ጥርሱን ነቅሎ ሙያውን ማስተዋወቅ ከጀመረበት ከ1505 እስከ 2015 ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ 56 ዓይነት መጻሕፍት ለሕዝብ ከቀረቡ በኋላ ተሰብስበው ተቃጥለዋል፡፡ ሦስት መጻሕፍት ደግሞ ለቅድመ ምርመራ ከቀረቡ በኋላ እንዳይታተሙ ተግደዋል፡፡ የቹኑዋ አቸቤ እና ናዋል ሳዳዊን…እንዲሁ ስራዎቻቸው በሳንሱር እየተጠለፉ ከመውደቅ አልተረፉም፡፡ የአፄ ኃይለሥላሴ ስርአት ወድቆ የደርግ መንግስት ሲመጣ በሳንሱር ሳቢያ እፎይ ለማለት ካልታደሉ ደራሲያን መሀል እዩኤል ዮሀንስ፣ አቤ ጉበኛ፣ ተስፈዬ ገሠሠ፣ ፀጋዬ ገብረመድህን እና ተስፋዬ አበበ…ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ሁሉም በሚባል መልኩ የሳንሱር ክርን የበረታባቸውና ዕድሜ ልካቸውን ተደላድለው እንዳይተኙ ስርዓቱ የፈረደባቸው ነበሩ፡፡ በተደጋጋሚ  ተገፍተዋል፣ ታስረዋል፡፡ ከዚህ ስርአት ጋር ተያይዞ በሳንሱር እክል የገጠማቸው ዓይናችንን በብዕር ከመጠንቆላቸው፣ ያመጽና የክፋት ዘር ከማፍራታቸው በፊት ብለው ለአስቸኳይ ስደትም የተዳረጉ በርካታ ናቸው፡፡ ከዶግማቸውና ቀኖናቸው ያፈነገጠ አቋም ያላቸው ከያንያንን፣ በተለይ ደራሲያንን- ሲያስፈራሩ፣ ሲያስሩና ሲያስገርፉ፣ ስራዎቻቸው ህዝብ ዘንድ እንዳይደርሱ ሲያወግዙ፣ ስደት እጣ ፈንታቸው እንዲሆን መንግስታቱ ሲገፋፉ ቆይተዋል፡፡ እንዳለጌታ በዚህ መጽሐፉ ውስጥ ጋዜጠኞችን በሚመለከት ደግሞ ማዕረጉ በዛብህ፣ አጥናፍ ሰገድ ይልማ፣ ያዕቆብ ወልደማርያም፣ ከበደ አኒሳ እና ፀጋዬ  ታደሰን አነጋግሮ የሰበሰባቸውን መረጃዎች፣ ካደረገው ጭውውት ያገኛቸውን የቃል ገጠመኛዊ ተረኮች (እንዲሁም ደራሲው የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ ሳለ በኢትዮጵያ የህትመት ጋዜጠኞች ላይ ከሰራው ጥናትም ቀንጭቦ በማስገባት) የተጠቀመባቸው አሉበት፡፡ በግለሰባዊ ትረካዎች አስረጅነት የተነገሩበትን ዐውድና የአቀራረብ መንገድ ሳይስት አጠናቅሮ አቅርቧል፡፡
 እንዳለጌታ ከሳንሱር ውጣ ውረድ ባሻገር በታሪክ ውስጥ በጻፉት መጽሐፍ ግጭት ውስጥ የገቡና ውዝግብ የገጠማቸውን ደራሲያን ያልተሰሙ አዳዲስ ትርክቶችን ሸክፏል፡፡ ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ በ“ተረት ተረት” የሆኑትንና የሆነባቸውን፣ተክለጻዲቅ መኩሪያም እንዲሁ ያደረጉትን የተደረገባቸውን አትቷል፡፡ የሀዲስ አለማየሁ ይቆየንና የተክለጻዲቅን እንመልከት፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የነገስታትን ታሪክ ተከታትሎ፣ ተከታታይነት ባለው መንገድ በመጻፍ  ተክለጻዲቅ መኩሪያ  የከበረ ስም አለው፡፡ ተክለጻዲቅ ከነጻነት ወዲህና ቀደም ብሎ በተከፈቱ ትምህርት ቤቶች የኢትዮጵያ ታሪክ በአማርኛ ቋንቋ መሰጠት አለመቻሉ ከሚያንገበግባቸው ወጣንያን መካከል አንዱ ነበር፡፡ ከነጻነት ወዲህ “ከዓፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ” ብሎ የሰየመው መጽሐፉ መጠናቀቁን ተከትሎ፣ አበረታችም ጎንታይም አተረፈበት፤ ይለናል እንዳለጌታ በምርምሩ፡፡ ከመታተሙ በፊት ንጉሰ ነገስቱ እጅ ገብቶ አንብበውት ኖሮ ምላሻቸው ሳይታወቅ ሰነበተ፡፡ በዚህ ጊዜ ተክለጻዲቅ ግራ ገባው፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ በተክለጻዲቅ ውትወታ የድርሰቱ ዕጣ ፈንታ  ይነገረው ዘንድ ለንጉሱ አመለከተ፡፡ እናም አንድ ቀን ቤተ መንግስት  ተጠራ፡፡ ጃንሆይ ፊት ቀረበ፡፡ እንዲህም አሉት፡- “ንጉሰ ነገስቱ የእኔ  የእጅ ጽሑፍ ከፊታቸው ተዘርግቶ አንዳንድ ቦታ ላይ በቀይ ምልክት ተደርጎበት ይታይ ነበር፡፡ በቀይ ምልክት ያደረጉትን አንዳንድ ጥያቄ ጠይቀውኝ  ካብራራሁ በኋላ “ስለ ልጅ ኢያሱ ብዙ ሳትጽፈው የቀረኸው ነገር አለ አሉኝ፤ እኔ  ከመመለሴ በፊት አቶ መኮንን ደስታ፣ እኔ እንዲያውም የተጻፈው በዛ ብሎ ታይቶኛል፡፡ ብለው ሲመልሱ፤ ጃንሆይ አንተ እኮ እንዲያውም ዝም ብለህ ነው፤ ምንም የምታውቀው ነገር የለም› ብለው በቁጣ ቃል ተናገሩዋቸው፡፡ ያን ጊዜ እኔ ጃንሆይን ምንም ስለአለመድሁዋቸው ሲቆጡም አይቼ ስለማላውቅ ቲንሽ ጭንቅ አለኝ፡፡” (ገጽ 126)… እንዳለጌታ ወደ ሙዚቃው አለም ጎራ ብሎ ደግሞ የሳንሱርን ከማቃኛ ይልቅ የማፈኛ ስልቶቹን በርብሯል፡፡ በሁለቱ የነዋይ ልጆች የታህሳሱ ግርግር ለድምጻውያን ጥሩ አጋጣሚ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ በዘፈኑት ዘፈን ምክንያት ለጥያቄ ከመቅረብ የዳነ የለም፡፡ ከእውቅ ከያኒያን  መካከል የግጥምና ዜማ ደራሲው ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስም ለጥላሁን ገሰሰ በሰጠው የዘፈን ግጥም የተነሳ (ለግርግሩ ድጋፍ ሰጥተሀል በሚል) መፈተኑን እንዳለጌታ እንዲህ ያወጋናል፡፡
“ይህን የዘፈን ግጥም የጻፍከው ለማነው?”
“ለባለቤቴ ነው”
“ለባለቤቴ? ባለቤትህ ምን ስለሆነች?”
“ስለተጣላኋት፣ ስለሰለቸኝ፣ ስለመረረኝ..”
“አውቀንብሀል፡፡ ባለቤቴ ምናምን ይላል እንዴ? ፖለቲካ ቢቀርብህ ይሻላል”             
አልገባኝም
“እስኪ አንዴ ግጥሙን በለው፤ መረረኝ  ምናምን የሚለውን?”
ገጣሚው የጻፈውን ግጥም አነበበ፡፡
“እስከ መቼ ባንቺ ባህርይ እነዳለሁ
አልቻልኩም አርሚ ብያለሁ
ሰለቸኝ መረረኝ እኔን
ተጨነኩ እንደምን ልሁን?”
መርማሪው አደመጠ፡፡ “ከቅጣቱ የምትተርፈው ይሄ ግጥም እንዳለ ሆኖ ከታች ሌላ የዘፈን  ተቀባዮች ይግቡበትና ቅድም ሰለቸኝ መረረኝ እኔን ባዩን ያጽናኑት፤ ምን ያማርርሀል? ሰው የሚኖረው እንደዚህ ነው፣ ማማረር ይቅርብህ ይበሉት” አሉት ተኮሳትረው፡፡ አፈወርቅ ራሱን ለማዳን ምን ማድረግ እንዳለበት አሰበ፤ ከዚያም በል ያሉትን ጻፈ፤ እነሱም አነበቡት፡፡
“ይቅርብህ በጣም አትከፋ
ቻል አድርገው ተው አትቁረጥ ተስፋ
እንዲህ ነው ሰው የሚኖረው እንዲህ ነው
በርታ እንጂ ማማረርህ ለምን ነው?”
በተባለው መሠረት ተሰራ፡፡ መርማሪው ግጥሙን የተረዳው ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለውና ገጣሚው ስርዓቱ ሰለቸኝ፣ በቃኝ፣ መረረኝ ማለቱ ነው ብሎ ተረድቶታል፡፡” (ገጽ-142)       ያኔ በራድዮ እንዳይተላለፉ፣ በመድረክ እንዳይዘፈኑና በቴፕ እንዳይቀረጹ እገዳ የተጣለባቸው ዘርፎችና የኅትመት ውጤቶች ብዙ ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ በትክክል የነበረውን መንግስት የሚተቹ፣ ጉድለቱን የሚነቅሱና የአስተዳደሩን ጉድፍ የሚያመላክቱ ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ከያኒው በአዕምሮው ያልተፀነሱ ሐሳቦች በግድ አምጦ እንዲወልዳቸው የሚያደርጉና የሚያስገድዱም ነበሩ፡፡ በመሠረቱ ኢ-ልቦለዳዊ ተራኪዎች በመረጃና በማስረጃ ላይ ተመስርተው ይቅረቡ እንጂ በታሪክ ውስጥ የተጠኑም ድርጊቶችና ክንዋኔዎችን እንደየ ተራቸውና ፈርጃቸው እየገቡ የሚሰነዱበትም የአፃፃፍ ስልት ነው፡፡ በጋዜጣ የሚወጡ ዜናዎች፣ ስለ መኪና አደጋ፣ ስለ አገር ጉብኝት፣ ስለ በዓል አከባበር ወዘተ...፤ማንኛውም የግለሰብም ሆነ የህዝቦች ታሪክና የመሳሰሉት ሁሉ የዚሁ አጻጻፍ ዘርፍ ትኩረቶች ናቸው፡፡
 እንዳለጌታ በ”እስረኞቹ” የቀነበበልን የሳንሱር ትርክትም በዚህ ዘውግ ተቀንብቦ የሚተነተንና ለዚህ ይት-ባህል አይነተኛ ምሳሌ መሆን የሚችል ነው፡፡
(ልጁ ከተነሳበት እስከ ደረሰበት በስራዎቹ ያልሞከረው የአጻጻፍ ቴክኒክ የቱ ይሆን?) በአጠቃላይ በአለማችን ላይ በሳንሱር ሰበብ እንግልት የደረሰባቸውን ብቻ ሳይሆን ተቃውሟቸውን በማስደመጥ (ዮሪፒደስ፣ ጆን ሚልተንና ሳልማን ሩሽዲ) አንብቦ ያወቃቸውን፣ ጠይቆ የተረዳቸውን ከያንያን  በሚችለው አቅም ጉልኃንና ልሂቃንን ነቅሶና ተንትኖ ለማሳየት ሞክሯል፡፡ ሳንሱር ከመጣበት ጉልበቱን እስካፈረጠመበት የዘመን ሂደት ውስጥ ጎልተው የታዩ አቢይ ተግዳሮቶችን በየምዕራፉ አመላክቷል፡፡ ከዚህ ባለፈ ደራሲው የአማርኛ ሥነጽሁፍ የነባር ደራሲያን የተዘነጋና ያንቀላፋ ታሪክ ካሸለበበት አንቀልባ ወርዶ እንዲራመድ በዘመናችን የራሱን ይበል የሚያሰኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛልና፣ በርታልን እያልን፣ ከፍ ካለ አክብሮት ጋር እጅ እንነሳለን፡፡


Read 176 times