Saturday, 20 May 2023 21:22

“ካስቻለህ ቅር---”

Written by  -ወጋየሁ ማዴቦ-
Rate this item
(3 votes)

  ከሶስት ወር በፊት ....” በጣም ደፋር ነሽ ወይም በድፍረትና ግድየለሽነት መካከል ያለ መስመር የሚገልፀዉ ባህሪ  አይነት ያለሽ ቆንጅዬ ልጅ ነሽ፡፡ እፈራሻለሁ! በእዉቀትሽ ልክ...በከፍታሽ ልክ...በቁንጅናሽ ልክ እወድሻለሁ፡፡ ነገር ግን እዉነቱን ንገረኝ ካልሽኝ ...ባህሪሽን ልወደዉ አልቻልኩም! መጥፎ ልምምድ ነዉ ብዬ መንቀስ ባልችልም፣ እኔ በቀላሉ ልቀበለዉና ልተገብረው የማልችለዉ ስለሆነ ተማምኜብሽ የፍቅር ጀልባሽ ላይ ለመሳፈር ድፍረቱን አጣሁ... እባክሽኝ ዳሩ ላይ ተይኝ!” የሚል መልዕክት ልኬላት ነበር፡፡  
ዛሬ ከሶስት ወር በኋላ ...ዛሬ ሊነጋጋ አዛን ሲል... “በነገራችን ላይ እኔ ግብረ-ገብነት የጎደላት ሴት አይደለሁም! የነዋሪነት መታወቂያ ላወጣ ሄጄ ጉቦ አልሰጥም! ሲሰጥ ባይም ዝም አልልም! ትክክል ያልሆነን ነገር በቦታዉ መቃወምና መጠየፍ እንዴት ስህተት  ሊሆን ይችላል? የኔ ባህሪ አስችጋሪ ሆኖ አይደለም፤ ግን ሆኖም ከተገኘ እስቲ ሞግተኝ፡፡ ደግሞ ደግ ነሕ... በጣም ሩህሩህ...እናም ስላንተ አልተሳሳትኩም ...ከሁሉም ከሁሉም ላገኝህ እፈልጋለሁ...መጀመርያ የተገናኘንበት  ቦታ ላይ በጠዋት እቆማለሁ፡፡ ካስቻለህ ቅር.....” የሚል መልዕክት ላከችልኝ፡፡
እንግዲህ እንዴት ይፀለያል? እንዴትስ ለሩጫ ይወጣል? ከቶ እንዴትስ ይቀራል???
እስዋ ....
የሆነ ወደ ሱቅ ስንሄድ ምንም ያልነበረ ወዲያው ስንመለስ አካፍቶ እንደሚያርሰን ካፍያ...በርዶን ደራርበን ወጥተን ድንገት ሰማዩ ላይ የምትናኝ ፀሃይ ሙቀትዋን ለቃብን እንደሚጨንቀን ወበቅ...ናት! ድንገት እንዲያዉ ድንገት ከአበቦች አናት ላይ የማር መስርያ የምትቀስም ..ድንገት ብርር ብላ ነድፋን እንደምታሳብጠን  ... ንብ ነገር ናት!
እስዋ...
የሆነች ዉብ ልጅ... ሩታ የምትባል መንገዴን ድንገት ያቋረጠች... በዉበትዋ ልክ የወደድኳት...በገባኝ ልክ ያወቅኳት..ነገር ግን...ሳዉቃት...ስቀርባት...ስነካት...ህልሜ ላይ ስደርስ...በነፍሴ ስረዳት... ለነገሮች ያላት መረዳት እኔ ከለመድኩት ያፈነገጠች የመሰለችኝ ሴት ናት፡፡
እስዋ...
ሜዳሊያ ልንቀበል ከቆምንበት ረዥም ሰልፍ ወጥታ ከፊት ካሉት ጉምቱ ወረፋ ጠባቂዎች መሃል ገብታ...”እባካችሁኝ ተባበሩኝ!,ወረፋዬ እሩቅ ነዉ ትቼ እንዳልሄድ ደግሞ ሜዳልያዉ ያስፈልገኛል” ብላ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለኔም ጭምር ይዛ መጣች፡፡ እኔ በፍጹም ይህን አላደርግም! ግራ ትገባኛለች! ግን ደፋር ናት፡፡
እስዋ...
ቸርች ይዣት ሄጄ ስብከት መሃል ጥያቄ አለኝ ብላ እጇን ያወጣች ጀግና ናት... ፓስተራችን በስብከቱ መሃል ስድስት ልጅ እንዳለዉና እኛም ብዙ ልጆች ብንወልድ ችግር እንደሌለዉ እንደቀልድ እየነገረን ነበር...እንደዛ ቀን ደንግጬ አላውቅም፡፡ ግራ ትገባኛለች! ግን ደፋር ናት፡፡
መንገድ ተዘጋግቶ እየተንፏቀቅን በማሽከርከርበት ጊዜ  ከኋላችን የነበረ አሽከርካሪ ጥሩንባ ሲነፋ...እየተንቀሳቀሰ ከነበረ መኪና ወርዳ አነቀችው፡፡ ተለምና ተመለሰች! ግራ ትገባኛለች ...ግን ደፋር ናት!
እኔ
ጤፍ መሬት ላይ የማልጥል ጠንቃቃ ነኝ...ትክክል ያልሆነን ነገር ነፍሴ ትጠየፋለች! ግን እኔ እራሴን ብቻ ነዉ የማግደዉ...የማርቀዉ...
እኔ ጠብ ያለበት የለሁም! ጮክ ብዬ አላወራም! ጫጫታ ያለበት አልለመድም!
እናም ፈራሁ... የሆነ ሊመጣ ያለ ከባድ ነገር እንዳለ ተሰማኝ...እናም ይቅርብን ...ቅሪብኝ አልኳት፡፡ ይኸዉ ነበር፡፡ ትንፍሽ አላለችም...የሰፈር ጥጃ የጠፋ እንኳን አልመሰላትም...እናም ልክ ነበርኩኝ ብዬ...እየናፈቀችኝ...እየራበችኝ... እንዳቃዠችኝ..ችዬዉ ወራትን ገፋሁ፡፡
    *             *             *                     
... ያኔ ያወቅኳት ቀን... ወደ ደብረብርሃን አቅጣጫ ወደ ፊልድ እየወጣሁ ነበር ፤ በእንግሊዝ ኤምባሲ በኩል 02 በሚባለዉ አስፋልት ... ከንጋቱ 12.30 አካባቢ ይሆናል.. ወደ ዋናዉ የኮተቤ መንገድ ስቃረብ በተቃራኒ አቅጣጫ ቆማ ሊፍት ትለምናለች ... ግር እንዳለኝ ቆምኩ፤ የመንገዱን አካፋይ ተሻግራ ሰተት ብላ መጣች፤ “እኔኮ የምሄደዉ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ነዉ” አልኳት፡፡  “…ጨንቆኝ ነዉ እባክህ ላዳ ቀጥሬ ነበር ቀረብኝ፤ የስራ ቅጥር ፈተና ነበረብኝ፤ ትንሽ ከፍ ብዬ ዋናው መንገድ ላይ ታክሲ ካገኘሁ ብዬ ነዉ ... ግራ ገባኝ! “ መለማመጧ ይታያል ግን የለመደችዉን ሰዉ የምታናግር ነበር የምትመስለዉ ... አጋጣሚ በቅፅበቱ ስስ ካፍያ መጣል ጀምሮ ነበር ... ገባችና ወደመጣሁበት ዞርኩኝ... ያዉ በሷ ልክ ዉብ ለሆኑ ሴቶች፣ በኔ ደረጃ ያሉ ወንዶች ልንፈፅመው የሚገባን ማህበራዊ ግዴታ እንደሆነ የተረዳችዉ ነው ብዬ ወስጃለሁ፡፡ ብዙም አልደነቃትም፡፡
“ምን መሥርያ ቤት ነዉ ቃለመጠይቅሽ?”
“ኢሴኤ... እስጢፋኖስ ከፍ ብሎ”
“ምን ላይ ነዉ የምትሰሪዉ... ሙያሽ?”
“የህብረተሰብ ጤና ነው የሚባለው? ፐብሊክ ሄልዝ...”
“ሃኪም ለመሆን ግን ልጅ ነሽኮ...”
“ፐብሊክ ሄልዝ ነው ያጠናሁት... ያው ልሞክር ብዬ ነው...”
“ካለዛሬ ያላየሽዉ ሰው ከዚህ ዝናብ አስጥሎሽ ከሚሄድበት ተመልሶ ኢሴኤ በሩ ላይ ካወረደሽ ደመ-ነፍስሽ ፈተናዉን እንደምታልፊ ሊነግርሽ ይገባል! ቃለመጠይቁ መጨረሻ ላይ ...ወጣት ነኝ... ታታሪና ታዛዥ ነኝ... ስለስራዉ በቂ እዉቀት አለኝ... እድሉን ከሰጣችሁኝ በምርጫችሁ እንዳልተሳሳታችሁ አስመስክራለሁ  በያቸዉ፡፡ ይህ እድል ያንቺ ነዉ...እኔ እንዳለፍሽ አምኛለሁ... መልካም የስራ ዘመን!!” መኪናዉን አቆምኩት፡፡
“... እኔ የምለዉ የለኝም አመሰግናለሁ! ብድር ከፋይ ያርገኝ... ሩታ እባለለሁ” ብላ ... ለሰላምታ... ለስንብት...ለምስጋና... እና ለጥያቄ እጆቿን ዘረጋች...
“...ስለረዳሁሽ ደስ ብሎኛል ሩታ...”
“... ስምህን አልነገርከኝም...? ስልክ እንኳን  አንለዋወጥም እንዴ?” እጆቿ እየተሰሙኝ ነበር...
“ወደ ታች በሚወርድ ወንዝ ወደ ላይ የምትፈሺ ቆንጆና ደፋር ልጅ ነሽ... መልካም እድል! ቻዉ ሩታዬ!!” ተንጠራርታ ጉንጬን ስማ ቅር እያላት ወረደች፡፡
   *            *               *                  
ከዛች ቅጽበት በኋላ በመንገዴ ሁሉ... በየቀኑ... ሠርክ አስባት ጀመር ... የአይኖቿ ዉበት የድምጿ መስረቅረቅ፣ የእጆቿ ልስላሴ፣ የተቀባችዉ ነገር መአዛዉ... በተለይ በተለይ ጉንጬን የሳመችኝ ጊዜ የተሰማኝ ስሜት... አንዳንዱ ቀን ለእንደዚህ አይነት የማያባራ ሃሳብ ይጥልሃል፡፡ ለምን ነበር ስልክ ስትለኝ ዝም ያልኩት? አንድ ጊዜ የሸኘዃት ሴት መዉረጃዋ ጋ ስትደርስ “ስልክ አትጠይቅም እንዴ? “ያለችኝን አልረሳዉም ...የሸኛት ሰው ስልክ ቁጥርዋን መዉሰዱ ምንዳዉ ነው ማለቷ መሰለኝ፡፡ ሁልጊዜ ለሌላ ፍላጎት ሰዎችን የምንረዳ ከሆነማ በጎነት ሊሆን አይችልም... ግን የዚችን ልጅ ነገር በዋዛ እንደማላልፈዉ አዉቄያለሁኝ፡፡ ለጋ ናት ሎጋ ናት፤ በጣም ታምራለች፤ ደፋር ነች ታምራለች...ማንም ያያት ሰው በቀላሉ ሊወዳት ይችላል፤ ቢሆንም የኔ ባሰና ሰርክ አስባት ጀመር ...ትናፍቀኝ ጀመር፡፡ እንግዲህ ያሳፈርኳት ሰፈር ሄጄ ...ሩታ እምትባል ቆንጅዬ ልጅ...በዚህ በኩል መግቢያዋ...ቤቷን ታውቃላችሁ? ልበል...? ኢሲኤ ገብቼ በቅርብ ጊዜ የተቀጠረች...ወይም ልትቀጠር የምትችል ዉብ የጤና ባለሙያ...ሩታ የምትባል...አለች ልበል? ጉድኮ ነው፡፡ ሰዉን ማመን...በቀላሉ መግባባት መቻል...ራስን ዛሬ ላወቁት ሰዉ ቅርብና ግልፅ ሆኖ ማሳየት...ፈገግታን፣ አድናቆትን፣ምስጋናን ፣ ስሜትን ጣፋጭ አድርጎ በሌላ ሰዉ ነፍስ ዉስጥ መዝራት መታደል ነዉ፡፡ ከዚያ በሰዉ አእምሮ ዉስጥ መንገስ!!!
          *       *           *           
ከሳምንታት በዃላ የቢሮአችን እንግዳ ማረፊያ ዉስጥ ተከሰተች፡፡ ፀሃፊያችን ...በዉስጥ መስመር..”ዉብ የሆነች ልጅ ትፈልግሃለች ብቅ በል” ብላኝ ስትቀልድ ድንጋጤዬን አስታዉሳለሁ...ቀልቤ ነግሮኝ ነበር ፡፡ እንደገባሁ ተጠመጠምኩባት ...ይህን ባላደርግ እስከዛች ቀን ድረስ ስለሷ የተሰማኝ ስሜት ሁሉ የዉሸት ነበር የሚሆነዉ፡፡ ሰላምታ ባይኖር እንዴት ነበር ናፍቆታችንን ልንገልፅ የምንችለዉ? መጨባበጥ መተቃቀፍ መሳሳም ነፍሳችን ዉስጥ ያለዉን ስሜት ለወዳጃችን ይነግሩልናል፤ የሱንም ይነግሩናል... አቤት አስተቃቀፍዋ!  አጸፋዋ...ሙቀትዋ...መአዛዋ..ሰላምታዋ፤ ውስጤን በሃሴት ሞላዉ፡፡
መኪናህ ላይ ያለዉን የመሥርያ ቤታችሁን አርማ ስላየሁት፣ አድራሻህ አልቸገረኝም ባይ ናት ... ወደ ላይ እየሄድኩ ወደ ታች ዉሰደኝ ለምትል ልጅ ይህ ምን ይቸግራታል? ዛሬ ደግሞ ፈጣሪ ዉበት ደፍቶባታል... ምን ተአምር ናት!?   “... ሩታ አንቺን የማዉቅሽ ከላምበረት እስከ እስጢፋኖስ ባለችዉ ርቀት ብቻ መሆኑን ለማመን እስኪቸግረኝ ድረስ ራሴን ጠይቂያለሁ... ያለሟቋረጥ ሳስብሽ ነበር...ካወረድኩሽ ቅጽበት ጀምሮ የሆነ የጎደለኝ ነገር እንዳለኝ ሲሰማኝ ነበር... ደግሜ የማይሽ አልመሰለኝም  ነበር..ዉብ የሆነች እንግዳ ትፈልግሃለች  ስባል... አንቺ እንደሆንሽ አዉቂያለሁ... ገና እንዳዩሽ የሚያስቀባጥር ዉበት ያላት ሴት የማዉቀዉ  አንቺን ብቻ ነዉ፡፡ ይኸዉ እየቀባጠርኩ ነው እኔም... “ ባታቋርጠኝ ቀን ሙሉ አወራ ነበር፡፡
“...ስምህን እንግዳ ተቀባይዋ ነግራኛለች ግን ካንደበትህ ልስማዉ?” ....ታዜማለችኮ...
  “... ማንን እፈልጋለሁ አልሻት?”
“... እንዴት እንዳገኘሁህ ገና ነግርያት ሳልጨርስ... ጌትሽ ነዉ? አለችኝ፡፡ ምን ብለሃት ነበር?”
“ ... ስቃዥ ሰምታኝ ነዉ...ስላንቺ ያላወራሁለት የለም፡፡...ጌትነት እባላለሁ... ግን ስሜ ምን ይረባሻል? ይህን ሁሉ ከሆንኩ ወዲያ...ስልክ ቁጥርስ ትጠይቂኛለሽ?”
“...እኔም አብስትራክት የነበርከዉን ሰዉዬ፣ እንደፈጣን ሎተሪ ፍቄ በርህ መጥቻለሁ... አይበቃህም?” ሌላ ዜማ...
“.. ስራ ጀመርሽ?”
  “...ፈተናዉን አለፍሽ ማለትህ ነዉ?”
   “... እሱን ያኔ ነግሬሻለሁኮ”
 ...እንደገና ሌላ ሞቃት መተቃቀፍ... “ኢት ዎዝ ዩ! አምስት ደቂቃ ባረፍድ አይሆንም ነበር...እስጢፋኖስ  አንተን ጣለልኝ...ታንኪዩ!!”  ጉንጬ ላይ ከባለፈዉ ጠበቅ አርጋ ሳመችኝ፡፡
 ይኸዉ ...እንግዲህ እንዲህ  ነበር  እኔና ሩታ ....መንገድ የጀመርነው...
  *      *     *     
ከዛ ደግሞ ..ከወራቶች በኋላ .እንደ ታክሲዉ ጽሁፍ ...”የፈራ ይመለስ” በሚለው መሰረት ተመልሼ ነበር ወይም የተመለስኩ መስሎኝ ነበር፡፡ ይኸዉ ዛሬ ደግሞ ...”ካስቻለህ ቅር” ... ብላኝ እየጠበቀችኝ ነዉ... ያቺ ንብ፡፡ ... መቅረት  የምችል አይመስለኝም... ግን በየቦታዉ...በየእለት የኑሮ ኡደታችን ...በማህበራዊ መስተጋብራችን...የምናየዉን  ግብረገብነት የጎደለው ተግባር እያረቅን...እየተጣላን...እየተቸን... መኖር ይቻል ይሆን!!


Read 990 times