Saturday, 20 May 2023 21:23

ሩቅያ

Written by  -ድረስ ጋሹ-
Rate this item
(2 votes)

 ከጤነኛው የሕይወት ዑደት ያፈነገጠች ነፍስ ይዛ ተቀምጣለች።ከክብ ውጭ እንዳለች ነጥብ ..ገለል ..ፈንጠር ብላ ትታያለች።እንባ ጨርሳ ደም እያነባች ነው።የተቀመጠችበት ድንጋይ ብቻ የተፈቀደላት እስኪመስል ለቀሪው ዓለም ጀርባ ሰጥታለች። ሴትነቷ በልብሷ ተሸፍኖ ሊቀር ሲዳዳው ይታያል_የሩቅያ።
[ጠና ያለ ሰው፣ ሩቅያ፣ ጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ፣ ከተራራው አናት...]
ቀርቦ «ልጄ»ሲላት አካሏ ክፍል ..ስንጥቅ...ትርትር። ይኼን ድንጋጤ ደንግጣው አታውቅም። እንግዳ ፊት ያለው አዛውንት፣ከዚች ቀን ቀድማ የማታውቀው ሰው አቅርቦ ስለጠራት ተገርማለች።
የድንጋይ መቀመጫ እና የእናት ሞት እየቆየ ይቆረቁራል...
ቆርቁሯት ተነሳች። ድንጋዩም የእናቷም ሞት። ሩቅያ እናቷን ያጣችው የ 6 ዓመት ልጅ እያለች ነው። የእናትን እንክብካቤ ለማወቅ አልታደለችም። የአባቷንስ!?
«ለመሆኑ እዚህ ገደል ጫፍ ምን አመጣሽ?» (ጠና ያለው ሰው ጠያቃት)
መልስ አጠራት። ለአፏ የቀረበው «ምናገባህ!» ነው ፤ግን እንደምንም «ዝም ብዬ » ብላ ሸነገለችው። ኹኔታዋ ያዘነች ሳይሆን ኀዘን ራሱን የሆነች አስመስሏታል። በእምቡጥ ጉንጮቿ ላይ የፈሰሱት ጠይም እንባዎች፣ መላ ቅጡን ያጣው የፀጉር አስተሳሰሯ፣ እሳት የበላው ቀሚሷ ስሜት ያውካሉ። የሽማግሌው ደቃቅ ዓይኖች ከሩቅያ ዓይን ኀዘን ቀድተው ይመለሱ ያዙ። እንደ ልጅ ስቅስቅ ብለው አለቀሱም።
እንባዋን በተካፈላት ሰው...
ታለቅስበት ትክሻ ባልነፈጋት አባት ...ደስታ ተሰማት።
ታሪኳን በስሱ ልትነግረው ተመቻች ...
[ ኹለቱም ተቀምጠው፣ቁልቁል የቆላውን ማህበረሰብ እያዩ፣በተራራው ንፋስ እየተወለወሉ...]
ሩቅያ እባላለሁ። በዛች ትንሽዬ መንደር ውስጥ ተወልጄ አደግኩ። እናቴን በ6 ዓመቴ ነው ያጣኋት። ያሳደገኝ አባቴ ነው። አባት አልኩ ልበል?..አይ በቃ እሱ ነው። እናቴ ጠላ ሻጭ ነበረች። አባት የምለው ሰውም የጠላ ደንበኛዋ። ታሪኩን ደርሼ አላየሁትም፤ የነገሩኝን ነው የምነግርዎት..
«ችግር የለውም ቀጥይልኝ ልጄ»
በአንድ የተረገመ ምሽት አባቴ ተብዬው ይሰክራል። ሰክሮ ከቤት አልወጣም ይላታል። እናቴም በሰው ላይ ክፋት አታውቅምና ጮኻ ልታስይዘው አልፈቀደችም። ለምናው አልወጣ ሲል ግን ወጥታ ፖሊስ ለመጥራት ተነሳች። የሰከረ የመሰለው አባቴ ተነስቶ አቅፎ ያስገባታል። በሩን በውስጥ ሸንጉሮ የሥጋ አምሮቱን ይወጣባታል። በዛች ዕለት እኔ ተረገዝኩ። የተረገመች ቀን ናት አይደል?
«ተይው ልጄ ..ታሪኩን ቀጥይልኝ»
በዘጠኝ ወሯ እኔን ወለደች። ጎረቤቱ ኹሉ እየተሰባሰበ መልኬን አይቶ አባቴን አወቀ። እገሌን ትመስላለች፣ እገሌን ትመስላለች ይሏት ጀመር። መንፈሷ የተጨነቀው እናቴ፤ እንዲያገባት ጠይቃ ይጋባሉ። ከሃሜት ለመሸሽ ጠላቷን ባል አደረገችው። ይኼ ኹሉ ሲሆን  እኔ ማደግ ላይ ነኝ። 6 ዓመቴ ገደማ አባቴ ቀንድ አበቀለ። ወላጅ እናቴን አልይሽ ማለት አበዛ። እሷ ጫንቃዋን አደንድና ኑሮ ብትጀምርም፣ እሱ አልተዋጠለትም። ይኼ እርጉም ሰው ነው ግን?
«ተይው ልጄ ...ታሪኩን ጨርሽልኝ»
የፍጻሜው መጀመሪያ ሆነ። ለረቡዕ አጥቢያ እንደተኛን እኔን ከእናቴ ጉያ ቀስ ብሎ አሹልኮ ውጭ አስቀመጠኝ። እናቴ ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ እንዳለች ቤቱን በእሳት አጋይቶ ገደላት። እኔን ይዞ እሪ ይል ጀመር ፤አስመሳይ ነውና። ከዚያ ጀምሮ እየገረፈም ምን እያለም አሳደገኝ። ከተደፈረችና ከተገደለች እናቴ የተገኘሁ ባካኝ ፍጡር መሆኔን ካወቁ ይበቃል።
አዛውንቱን ትታ ኼደች።
[እሁድ ቀን፣ ከጓደኛዋ ሐና ጋር፣አጃና ክምር...
ሐና እና ገንዘብ ፤ባለሥልጣንና ሙስና ናቸው። ይፈላለጋሉ አይተታጡም። ይሁዳ የገንዘብ ኃላፊ ሆኖ እንኳ ጌታውን አሳልፎ ለመሸጥ ያነሳሳው የገንዘብ ስስቱ ነው። ሴቷ ይሁዳ_ሐና። የሩቅያን እንባ ለወግ ብታብስም በልቧ ትሸርበው ሴራ አላት። መንገዷ ላይ እሾህ ከማንጠፍ አትቆጠብም። የኃዘን ጡብ ልትደረድርባት የማታዝን ፍጡር...
«ሩቅያ»
«ወዬ ሐኒቾ»
«ስላገኘሁሽ ደስ ብሎኛል። ዛሬ ጭንቀትሽን፣ ኃዘንሽን ትረሻለሽ። በምን አትይም?_እንጠጣለና። ለሚኪ እደውልለታለሁ _ይመጣል። አብረን ፏ ፈሽ እንላለን»
«እ..ማ..ማለት..ሚኪ ለምን ይመጣል?»
«ገንዘቡን እሱ ይሸፍናል ፤ይኼ ላም እናልበዋለን። ብዙ አትጨነቂ በዚህ። ተነሽ ልብስ ቀያይረን ወደተዘጋጀው ቦታ እንኺድ»
ኼዱ።
በሩቅያ ፊት ላይ የብርኀን አጥቆች በሩ። በከንፈሯ ዘብ ሲጠበቅ የኖረው ጥርሷ ሳቅ ረጨ። ኀዘኔን የምታስረሳ፣ ደስታዬን የምትመልስ ጓደኛ ሰጥተኸኛል የሚል የምሥጋና ዶፍ ታወርድ ጀመር። ወደ ተዘጋጀው ክፍል ሲገቡ የሚሸት ልዩ መዓዛ ተቀበላቸው_ቤቱ የሐና ነው።
ሐና ትጠቅሰዋለች...
ሚኪ ሳይታይ ለሩቅያ አይበጃትን ይቀዳል...
ሩቅያ በየዋህ ልቧ ትጠጣለች።
ሌሊቱ ተጋመሰ። የሩቅያ ምላስ ተያያዘ። ስካር መላ አካላቷን ተቆጣጠራት። ልብሴን በመሐላችሁ ካላወለቅኩ እያለች አስቸገረች። ሐና፣ያሰበችው እንዲሳካ እየጸለየች ነው። ሚኪን በምልክት ነግራው በውጭ ዘግታባቸው ወጣች።
ሁለት ተቃራኒ ጾታ አንድ ቤት።
እሳትና ጭድ...ነዳጅና ክብሪት...
ሚኪ ርኅራኄን ከልቡ ፋቀ። የምታነባው እንባ አልገደደውም። ጭፍን ስሜቱን ተወጣባት። ለዘመናት የጠበቀችውን ድንግልናም አስገድዶ አጎደፈ። ሲነጋ ሩቅያ ከእብድ በማይተናነስ ሁኔታ በጩኸት እየተናጠች ወደ ቤቷ...
ታሪክ ራሱን ደገመ፣ የእናቷን ዕጣ የወረሰች ልጅ።
ስለ ጓደኛዋ ሐና፣«አለኹ አለኹ ብለሽ እንደ ክረምት ጀንበር »ትዝ አላት። አመቻችታ ለስቃይ፣አስተካክላ ለህመም ጋበዘቻት፤ያውም በጥቂት ብር። መጥፎ የኋላ ታሪኳ እንደ ጣት ቁስል እንዲጠዘጥዛት፣ ጸጸቷ የልቧን ግድግዳ በልቶ እንዲያፈርሳት፣ ነገዎቿን በትናንት ጆንያ ጠቅልላ እንድትከታቸው ሆነች።
ጠዋት ትነሳለች።
ድባቴ ከእሷ ጋር አድሮ ይነቃል። በሰው መሐል ብቻዋን ናት። አለኝ ትለው ዘመድ፣ ትሾልክበት በቂ መንገድ አልነበራትም። ኀዘን ቁርሷ ...ኅዘን ምሣዋ። «ላለው ይጨመርለታል»..ምሥጋና ላለው በረከት፤ኀዘንም ላለው ኅዘን። ወደ ትናንት በእናቷ ተመልሳ ነበር ፤በራሷ ወደ ነገ እንዳታይ ሆነች። አቀርቅራ ያነባችው እንባ ብሌአሰብን የለመነውን ሰው ጥም ይቆርጥ ነበር።
የዮሴፍ ወንድሞች ...
ከሃዲው ይሁዳ...
የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎችን ፈራች። የጠሉት እንዲወርስ..የፈሩት እንዲደርስ ሆነ። በእናቷ የሚከነክናትን ድርጊት ለበሰችው። ሰውም ይጠየፋት ያዘ። ሳትፈልግ በተፈጸመው ነውርን አሸከሟት። የሚገፋት እጅ ፣የሚገፈትራት ፊት አጋጠማት። ያለፈ ጠባሳዋ ሳያንሳት «ሸርሙጣ» የሚል ጸያፍ ቃል ደረቡላት። አንዷ በግ ሩቅያ ሆነች ...እረኛዋ ያልፈለጋት በግ። በየሽንቁርቁሪያው የምትውል የምታድር ፣ዘመድ አግልሎ የተዋት፣ ማንም ችግሯን ሊረዳት የማይፈልጋት...
ሆዷ ገፋ አለ።
አባቷ ከቤት አስወጣት።
ሸራ ወጥራ ማደር ጀመረች።
ጽንሱን ልታስወርደው አሰበች፤ደግሞም አምላኳን ፈራች:: ልውለደው? ልቅር?_ተጨነቀች። ብወልደውስ?_ጠባሳዬን በአካል ማየት ነው ‘ሚሆንብኝ..ባልወደውም አምላክ አለ። ከተደፈረችበት ዕለት በላይ ፈተናት። ስትደፈር_የደም አበላ በላት፣አካሏ ያለመጠን ተበደለ፣ፊቷ በደፋሪዋ ተመታ። ስታረግዝ ውስጣዊ ህመሟ ባሰ።
አካላዊ ህመም...ሊድን ሊታከም ይችላል።
መንፈሳዊ ህመም...በምን ይፈወሳል? አያድስሱት አካል አልቦ፣አያማክሩት አይታይ...
ወሰነች።
አልወለድም ይላትን ልትወልደው። አቤ ጉበኛን ልትቃወም፤ሞት ተፈርቶ ከመኖር አይቀር ልትለው አሰበች ፤አደረገችውም።
መሬቱ አልመጠናትም።
ፍራሹ ቀዳዳ ነው።
የአራስ ሁኔታዋ ያስነባል።
ኀዘን ቁርስ_ኀዘን ምሣ_ኀዘን እራት።
«አይዞሽ»የሚል የተስፋ ቃል ራቃት። ወገቧ እስኪጸና ሥራ ያገዛት የለም። ለአራስ ሴት ለምናምን ወር ጠባቂ  አይለያት የሚሉት ሰዎች ጥበቃ ነሷት። በዚህ ኹሉ መሐል የሁልጊዜ ረዳቷ  አንድ እናት አከል ሰው ቀረበቻት። እንደ አና ፍራንክ «ሰው ኹሉ ክፉ አይደለም» አለች። እየቋጠረች ረሃቧን ታስታግስላት፣ጨቅላውን ታጫውትላት ያዘች። ከወለደችበት የሸራ ቤት አውጥታ የቤተሰቧ አባል አደረገቻት። አልጋ ላይ ተኝቶ መታረስን ጀመረች..ጸናች ፡:
«ያለፈን ላይመልስ ፥በከንቱ ይለፋል
መቼም ሰው ደፋር ነው፥አምላኩን ይጋፋል»...ገባት።
ከ20 ዓመት በኋላ...
 «የሥነ-ልቡና አሠልጣኝ»ሆና ተገለጠች። የኖረችውን ልታጋራ፣በእሷ መንገድ የመጡትን ልብ ልትሰጥ። አንዷ ተማሪዋ ተነሳች...
«የእኔም ጸጸት የበዛው ታሪክ አለኝ። አባቴ የሚወደው ጓደኛ ነበረው። የጓደኛው ሚስት በወለደች ሰዓት የሚያርሳት አጣ። ለአባቴ ቀርቦ ነገረው። አባቴ ይወደዋልና እኔ እንዳርሳት ፈቀደ። የአባቴን ቃል ላከብር ከጓደኛው ቤት ገባሁ። ወር ያህል የሽንት ጨርቅ እያጠብኩ ሳርስ ቆየሁ። በወሩ መጨረሻ፣ በተረገመች ሰዓት ሽንት ቤት ውስጥ ደፈረኝ። በሰው ልጅ ተስፋ ቆርጬ ነበር _አንቺን እስካገኝ። ወንዶችም ኹሉ አራዊት ይመስሉኝ ነበር..»
ጸጥታ በክፍሉ ሆነ።
የሁሉንም ብሶት ማድመጥ ተሳናት። በኹለት በኩል ስለት ሁን የሚለው በአእምሮዋ ያቃጭላል ፤በእናቷም በራሷም ተደፋሪ መሆኗን ለመኮነን። እንደምንም ተቋቋመችው። ለተማሪዎቿ ይገባቸውን መግባ፣አይበጃቸውን ደብቃ ዘለቁ...
ልጇ አደገ ዘር ከልጓም ሊጠቅስ...
የአያቱንና የእናቱን ታሪክ አገር ነግሮ አሳደገው...
እናቱ የደበቀችው ምሥጢር ጤና ነሳው ...
ሞክሮ ማየትን ፣ ደፈረ መባልን ፈቀደ። ደግማ ደጋግማ የእናትነቷን መከረችው። ከመሥመር እየወጣ እንደሆነ አውቃለች። ቀን ሲሰጠው በሰፈራቸው የምትገኘዋን መለሎ ሴት መሐል ሜዳ ላይ አንቆ ያዛት። የተንቀለቀለ ሙቀቱ በውኃ እሚቀዘቅዝ አይመስልም። ጉርንቢ ለጉርንቢ ተናንቀው ለ30 ደቂቃ ታገሉ። እናቱ ለሥነ-ልቡና ሰልጣኝ ተማሪዎቿ ሽልማት ይዛ እየኼደች ባለችበት ይኼን ጉድ ሰምታ እየከነፈች ወደ ልጇ።
በደረሰች ጊዜ አፈረች።
ሊደፍራት ሲታገል እንደቆየ አውቃ እንባዋ መጣ።
«እማዬ ይቅር በይኝ» (አፍሯል)
«ራስህን ይቅር በለው። ከአባትህ ይኼን ወረስክ በቃ?»
አቀረቀረ፣እንባ ቢጤም ዓይኑ ዳር። ለተማሪዎቿ  የያዘችውን ሽልማት ታግላ ራሷን ነጻ ላወጣችው ሴት ሸለመቻት። ልጇን ትታ ፤ ልትደፈር የነበረችውን አቅፋ ወደ ቤት ወሰደቻት። ይቺ ልጅ የሐና ታናሽ እህት ናት።
«እማዬ ጨክነሽ ተውሽኝ? የወለድሽኝ’ኮ እኔን ነው።» (በሚያሳዝን ድምጽ)
«ብወልድህስ? »
 ‘ራቁት፤ራቃቸው።

Read 898 times