Saturday, 20 May 2023 21:24

የሩህ ዘመን ቅፅበቶች፡ ፍቅር እና መለየት

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(2 votes)

መግቢያ
 የአንድ ደራሲ ሥራ ብቻዉን የአንድ አገር የአንድ ዘመን ሥነ ጽሑፍ ዕድገት ደረጃ ዋቢ ሰነድ ነዉ፡፡ በእዚህ ጽሑፌ የማነሳዉ አዩብ ዑመር፣ የራሱን ቱባ የግጥም አጻጻፍ ስልት (stylistics) አዳብሮ በመምጣት የአገራችን ዘመነኛ ሥነ ጽሑፍ አንድ ደረጃ ከፍ እንዲል በማድረግ የበኩሉን ጉልህ ድርሻ የተወጣ ጎምቱ ባለቅኔ ነዉ፡፡ የአዩብ የሩህ ዘመን ቅፅበቶች (2015) በእዚህ ሃያ ዓመት በአማርኛ ቋንቋ ተፅፈዉ ለህትመት ከበቁ፣ በኪናዊ ፋይዳቸዉ (aesthetic value) ከላቁ ታላላቅ የሥነ ግጥም ሥራዎች (classic poetry works) ተርታ የሚቀመጥ ሸጋ ሥራ (magnum opus work) ነዉ፡፡        
ባለቅኔ በግጥም መሳሪያነት፣ አንድም ሥነ ልቦናዊ ሁናቴዉን (psychic state) እና ጣዕመኑን (experience) (ቃሉ የስንቅነህ እሸቱ (ኦ’ታም ፑልቶ) ነዉ) በርቀት ያትትበታል፡፡ እዚህ ላይ ቅኔ ባለቅኔዉ ሥነ ልቦናዊ ሁናቴዉን ማለትም ፍቅሩን፣ ደስታዉን፣ መከዳቱን፣ ፀፀቱን፣ ብሶቱን፣ ትዝታዉን … ወዘተ እና የሁለንታን ኪን ለማተት መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሁለትም፣ የተገነባበትን ነባር የወል ርዕዮት ወይም የኀልዮት መዋቅር አምድ (collective thought system) ይነቅስበታል፣ ይፈክርበታል፣ አፍርሶ ይገነባበታል፡፡ ይህ የቅኔ ዐቢይ ሚና ነዉ፡፡ ለመሆኑ ግን ግጥም ምንድን ነዉ?
     የግጥምን ምንነት አስመልክቶ አርኪ የሆነ ብያኔ ማቅረብ የቻለዉ የሥነ ጽሑፍ ምሁር አምሃ አስፋዉ ነዉ፡፡ አምሃ የአማርኛ ግጥም ባህሪዉ፣ መደቡና ዉበቱ በተሰኘዉ ጥናታዊ መጣጥፉ እንደ ጻፈዉ፣ ግጥምን ግጥም የሚያደርገዉ ቤት በሚመታ ስንኝ (ስንኝ ጎረቤቱ ካለ ስንኝ ጋር ቤት የሚመታ የሀረግ ስብስብ ነዉ) መዋቀሩ ነዉ (አምሃ አስፋዉ፣ 1994፡ ገጽ 6-7)፡፡ ቤት መምታት ግጥም ከሌላዉ ሥነ ጽሑፍ የሚለይበት ልዩ ባህሪዉ ነዉ፡፡ ይህ የአምሃ የግጥም ብያኔ፣ የግጥም ብያኔ አሻሚ ነዉ የሚለዉን የብዙ ገጣሚያን የተሳሳተ አተያይ የሚያስቀር ተቀባይነት ያለዉ ብያኔ ነዉ፡፡  
     የጎምቱ ባለቅኔ ኪናዊ ክህሎት ማሳያዉ ሥራዉን የከተበበት ቋንቋ ደረጃ (diction) ነዉ፡፡ በእዚህ አንግል በሩህ ዘመን ቅፅበቶች  መድበል ዉስጥ ተሰንደዉ የቀረቡት ሥራዎች የአዩብን በቋንቋ የመራቀቅ ልህቀት ያሳዩ ሥራዎች ናቸዉ፡፡ ነፍሴ ሆይ!፣ ጥበበ ነብይ፣ ተማፅኖተ ሙሾ፣ ምን አልሽኝ?!፣ መሲህ ላኩ፣ የወለሎ ወለሎታ ቃል ቋጠሮዉ ሳይፈታ ወደ ጌታ!!፣ ዘመንሽ ለጫንቃ አይችልሽም አንገት!፣ መሆን ሳለ ላለመሆን መዉተርተር በነበር መተርተር!!፣ በዕንተ ስሟ ምህረት  እና ዝናብ አዝዬ በጎዳና ያለ ዳና ገባሁ ወደ ማይተመን!! ለአብነት የሚጠቀሱ፣ ለባለቅኔዉ የቋንቋ ባለሟዕልነት ምስክር ሆነዉ የሚቆሙ ዉብ ቅኔያት ናቸዉ፡፡ ቅኔን ለኪነት ንግስና ያበቃዉ የቋንቋ ዉበት ልዕልናዉ ነዉ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ የሸጋ ቅኔ የኪን ዋልታዉ ቋንቋዉ ነዉ፡፡ ጎምቱ ባለቅኔ ይህን ሐቅ በወጉ ያዉቃል፡፡
     አዩብ በየሩሕ ዘመን ቅፅበቶች የህልዉናን ጉራማይሌ ገፅ በጥልቀት ዳሷል፡፡ ቅኔ የነገረ ህልዉና ጥልቅ ትንተና (complex analysis of existence) ነዉ፡፡ በእዚህ አግባብ፣ ፈረንሳዊዉ አብዘርዲስት ፈላስፋ እና ደራሲ አልበርት ካሙ እንደ ተናገረዉ፤ ወደ ፍልስፍና ማዕረግ ከፍ የሚለዉ ልብወለድ (novel) ብቻ አይደለም፤ ቅኔም እንጂ፡፡ እናም፣ ቅኔ በዐይን የሚታይ ምሥል ሆኖ የቀረበ ተጨባጭ ፍልስፍና እንጂ ፈፅሞ ሌላ አይደለም፡፡ A poetry is never anything but a philosophy expressed in images. ቅኔ ፍልስፍና መሆኑን በአዩብ ሥራ በገሀድ አይተናል፡፡          
፩. መለየት
     መለየት (apart) በየሩህ ዘመን ቅፅበቶች መድበል ዉስጥ ተደጋግሞ የተፈከረ ጭብጥ (recurrent theme) ነዉ፡፡ አንች የኑረቴ ወዝ አንች የዜማዬ ወንዝ አዩብ መለየትን ከፈከረባቸዉ ሸጋ ግጥሞቹ አንዱ ነዉ፡፡ ይህ ሥራ በዉበ ቋንቋ የተከተበ ነዉ፡፡
         ዘመን እያጓራ
    ቆፈናም ወቅት ሲዝረበረብ
     ቁልቁል ከዳገቱ
   ወርዶ እየተጋጨ ፏፏቴ ሲወርብ
    ደመና እንደኩታ
    መልክሽን ደርቦ ኑረቴን ሲታከክ
   ነፋስ በድምፀትሽ በዜማ ሲያንሾካሹክ
    ናፍቆት እያስተዛ የትናንትን ላይሽር
     ዶፍ እየጎፈላ ወቅቴን ሲሸረሽር፡፡
   በንጉደትሽ ወበቅ አካሌ እየራደ
    ልቤ እየነደደ
     ዛሬዬ እያመደ፡፡
      በፅልመት መካከል በተስፋ እየበራሁ
       ትላንትን በዋሽንት አርቄ እየጠራሁ
     አለሁ!!
       አለሁ!   
        አለሁ ካ’ፋፉ ዳር
         አለሁ ያንቺዉ ትዳር፡፡
       ለሩሔ የዳርኩሽ በትላንት ቀለበት
       ሳቅሽን እየለቀምኩ ካ’ዕዋፋት አንደበት፡፡
      ልቤን እያከምኩት በዛፎች ሽንገላ
 አዜማለሁ ዜማ…
    አለቅሳለሁ ለቅሶ በሸምበቆ ገላ፡፡
    “እህህ .. እህህ… ህህ
     እህህ… እህህ… ህህ”
        በቆፈን ብርታት ጅስሜ ቀርዝዟል
  ልቤ ልብሽን - ከገላሽ ነጥሎ ይዟል፡፡
ይዟል ተስፋ አንጠልጥሎ
  ካ’ለመኖርሽ መኖር ነጥሎ፡፡
   እያነከሰ ወደ ዘመን
 ያሻቅባል ያለተመን፡፡
 በትከሻዉ ላይ
   ሽበት ያዘለ ጊዜ ይዘንባል
   እሱ ግን ብርቱ!
   በዋሽንት እንባ ቀማኛ ወጀብ ያጅባል፡፡
   እህህ .. እህህ … ህህ
     እህህ.. እህህ…ህህ
      በከንፈሩ መዳፍ
     ዋሽንት እያስነባ ልብ እያስጨፈነ
      ስንኩል እያቀና ሞት እየከፈነ፡፡
      በስትንፋስ ሽቅብ በዜማ ዳገት
         ያሽኮረምማል የጊዜን አንገት፡፡
   ንዝረት ያድላል ያንቀጠቅጣል
 ያቅበጠብጣል፡፡
      የፅልመት እርጎ
     በፉሪት ጡዘት እየሰበቀ
    ጀንበር ከትላንት እየሰረቀ
 ነገን ያዜማል!
    ዛሬን ያዘማል!!
እህህ.. እህህ…ህህ
 እህህ..እህህ…ህህ
ከደመናዉ ግርጌ…
   ከተራራዉ አናት ከፏፏቴዉ ግድም
 በ’ስትንፋሴ ዜማ ማልዳዬን ስደግም፡፡
 ካ’ለመኖር ወዲህ
      በትዝታ ስድህ!!
   ከሄድሽበት ቦታ!
እመላለሳለሁ! መሸ ነጋም እዛዉ
 አለች! ማለቴ ነዉ ኑረቴን ያወዛዉ
የተስፋ ዜማ ነዉ የናፍቆቴ ለዛዉ፡፡
       እጠብቅሻለሁ!!  
     መለየት ልብን ከሚሰብሩ ፍዳዎች ወደር አልባዉ ነዉ፣ ልብ ከስብራቱ በዜማ ተፅናንቶ እንዳይጠግ ትዝታና ናፍቆት በሾተል ሰርክ ስለሚያቆስሉት፡፡ ልብ ጥላቻን በማለምለም እርሙን አዉጥቶ፣ በጎ ትናንቱን ከማህደሩ ፍቆ የእጁን ሲሳይ እንዳያጣጥም ደግሞ ተስፋ ደንቃራ ሆኖ ዛሬዉን ያመክንበታል፡፡ ይህ ተስፋ ግን የህልዉናዉ ብቸኛዉ ካስማ ነዉ፡፡ አፍቃሪ ልብ ስንቁ ተስፋ ነዉና፡፡ የኮብላዩ ግብር ክህደት ቢሆን እንኳ አፍቃሪ ልብ በወደደዉ ላይ የመደንደን አቅም አይኖረዉም (አዩብ ዑመር፣ 2015፡ ገጽ 16-19፤ ገጽ 110-114)፡፡        
፪. ፍቅር
     አዩብ ታላቅ የፍቅር ገጣሚ ነዉ፡፡ አንች የኑረቴ ወዝ አንች የዜማዬ ወንዝ  እና በጨረስነዉ የምንጀምር ባሰርነዉ የምንፈታ በቋጨነዉ የምንተረተር እና ዕልፍ ሞት - ዕልፍ ትንሳኤ ሸጋ የፍቅር ግጥሞቹ መካከል ለዋቢነት የሚጠቀሱት ናቸዉ፡፡
     አዩብ በፍቅር ቅኔዎቹ ባቀረበልን የፍቅር ፍልስፍናዉ (አንች የኑረቴ ወዝ አንች የዜማዬ ወንዝን፣ በጨረስነዉ የምንጀምር ባሰርነዉ የምንፈታ በቋጨነዉ የምንተረተርን  እና ዕልፍ ሞት - ዕልፍ ትንሳኤ ተመልከት) ፍቅር ፅናት እና ግለ-አምልኮን መሰዋት መሆኑን ይነግረናል፡፡ እንደ አዩብ አተያይ፤ የአፍቃሪ ልብ ፅናት የሚገለጠዉ በጥበቃ ነዉ፡፡ ራስን ክዶ ሌላን ማምለክ እና ፅናት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸዉ፡፡ የትዝታ ቁራኛ ሆኖ በእጅ ያለን ሀፍተ ሥጋ (የዛሬን ህላዌ) ወደ ጎን ገፍቶ የሚወዱትን መጠበቅ ፅናትን ይገልጣል፡፡  
     አዩብ ዕልፍ ሞት - ዕልፍ ትንሳኤ በተሰኘዉ ሥራዉ የፍቅርን ልዩ ጠባይ ያሳየናል፡፡ ለአዩብ፣ ፍቅር ሰዉ መለኮትን ሳይቀር እንዲገዳደር የሚያስገድድ ኃያል ስሜት ነዉ፡፡ ይህ ማለት፣ ፍቅር ሰዉ ትርፍና ኪሳራዉን እንዳያሰላ (ሰዉ ትርፍና ኪሳራዉን አስልቶ የሚኖር ፍጡር ነዉ (man is rationally calculative being) በአመክንዮዉ ላይ የሚሰለጥን ክፉ ደዌ ነዉ፡፡ አፍቃሪ ሰዋዊ ፍቅር ዘላለም የማይዘልቅ ወረት (faddish) መሆኑን እያወቀ እንኳ የሚወደዉን በማምለክ መገዛትን ይመርጣል፡፡ እንደ ፍቅር በሰዉ ላይ የሚሰለጥን ኃያል ነገር የለም ይለናል አዩብ፡፡


Read 1167 times