Saturday, 20 May 2023 21:25

ከማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  “ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረበት ቦታ የምታገኘው መንግሥትን ብቻ ነው!”

        አሜሪካ ውስጥ በአብርሃም ሊንከን ዘመን የነበረ ሆስፒታል ዛሬም አለ። እንግሊዝ ሀገር በሄድኩ ጊዜ የዛሬ ስንትና ስንት መቶ አመት አካባቢ ሼክስፒር በጠጣበት ቡና ቤት ጠጥቼ፣ ሼክስፒር በሸናበት ታዛ ስር ሸንቼ ወደ ሀገሬ የመመለስ ዕድል ገጥሞኛል። ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ያለ ዕድል ማግኘት አይታሰብም። ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረበት ቦታ የምታገኘው መንግሥትን ብቻ ነው። ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ከሳምንት በፊት ጤና ጣቢያ የነበረው ከሳምንት በኋላ ፖሊስ ጣቢያ ሆኖ ታገኘዋለህ፤ እናም በሽተኛ ለመጠየቅ ያመጣኸውን ፍራፍሬ እስረኛ ጠይቀህበት ትመለሳለህ። በዚህ አይነት፦ ከሳምንት በፊት ሙዚየም ከሳምንት በኋላ ጅምናዚየም። ከሳምንት በፊት ላይብረሪ ከሳምንት በኋላ እኔ ነኝ ያለ ግሮሰሪ። የሰውም ለውጥ ፍጥነት እንዲሁ ነው፦ ከወር በፊት ተላላኪ፣ ከወር በኋላ አስመጭና ላኪ። ከአመት በፊት የከባድ መኪና አሽከርካሪ፣ ከአመት በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ። ከአመት በፊት አድማ በታኝ፣ ከአመት በኋላ የኳስ ተንታኝ ሆኖ ታገኘዋለህ። በነገራችን ላይ የኳስ ነገር ሲባል አንድ ነገር ትዝ አለኝ። ከሦስት ወራት በፊት መሰለኝ በአትሌቶችና በባለስልጣናት መካከል በአዲስ አበባ ስታዲየም የኳስ ግጥሚያ ተደርጎ ነበር። እና ኮመንታተሩ አትሌቶች ኳስ ሲይዙ ‘ኦ ••••• ቀነኒሳ ኳስ በእጁ ነክቷል አደገኛ ስህተት ‘ እያለ ትችት ሲያዘንብባቸው ይቆይና፣ ባለሥልጣኖች ኳስ ሲይዙ ይቅለሰለሳል። ‘አሁን ጀነራል ኳስ ይዘዋል ‘•••• ጀነራል አታለው አለፉ ለማለት ፈለገና፣ አታለው የሚለው ቃል ክብር የሚነካ ስለመሰለው ‘ጀነራል መስዋዕትነት ከፍለው አለፉ...!’
(በእውቀቱ ስዩም)

_________________________________________________

                   የዘንድሮው በጀት በጥልቀት ይመርምር!!

          “የፌደራልና የክልል ተቋማት በበረታ የበጀት እጥረት ውስጥ ወድቀዋል” የሚለውን ዘገባ አደመጥኩ።
የበጀት ዓመቱ መገባደጃ ላይ ሆነን ስለ በረታ የበጀት እጥረት መናገር ትርጉሙ ምንድን ነው?  የበጀት ጉድለቱ ከርሞ ከነበር እንዴት ተከሰተ? እስከ አሁን ድረስ የበጀት እጥረቱ እንዴት ተካካሰ? ስራስ እንዴት ይሰራ ነበር?  በርካታ ጥያቄ የሚያጭር ዘገባ ነው፡፡
ለተቋማቱ የተበጀተላቸው በጀት ከእቅዳቸው በታች ነበር ?  በጀታቸውን በአግባቡ ስለማያውቁና ስላልቀመሩ ጉደለት ገጠማቸው ? በጀታቸውን አዳዲስና ውድ ተሽከርካሪ በመግዛት፣ ለውሎ አበልና ለነዳጅ ወጭ በመክፈል፣ ለቢሮ ማስዋቢያና ውድ የቢሮና የግል ቁሳቁስ በመግዛት አባከኑት ? በበጀት የተመደበላቸውን ገንዘብ ከእቅድ ውጭ ለፕሮጀክቶችና ለእርዳታ ለገሱት ? በግሽበቱ ምክንያት የዋጋ ንረቱን መቋቋም አቃታቸው? መንስኤው የቱ ነው ? ይገለጽ !!
የማቀድ አቅም ማነስ፣ የበጀት አፈጻጸም ድክመት፣ በጀትን ከእቅድ ውጭ ማድፋፋት፣ ዝርክርክነትና ብክነት ከሆነ ተጠያቂነትን ሊያስከትል ይገባል። የተወካዮች ምክር ቤት ከወዴት አለህ ? የዘንድሮው በጀት በጥልቀት ይመርምር፣ የሚቀጥለው ዓመት በጀት በቅጡ እንዲታቀድ ጥብቅ መመርያ ይሰጥ!!
(ሙሼ ሰሙ)
_________________________________________________________

                      ቤተ መንግሥት እንደ ማስቀየሻ ?
                          

       (የግል አስተያየት)
የቤተ መንግሥት ግንባታን የመሰሉ ቅንጡ ፕሮጀክቶች ፍላጎት ጀርባ፣ እንደ ሀገር ኢኮኖሚያችን ያለበትን አጣብቂኝና አሁናዊ ሁኔታ በጥቂቱ ለማሳየት ያህል፦
- በዘንድሮው ዓመት ከጸደቀው 786 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ በጀት ውስጥ ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ የበጀት ጉድለት ያለበትና በልመና ከሚገኝ እርዳታ ይሞላል ተብሎ የተያዘ ነገር ግን እስካሁን ያልተገኘ ነው።
- በዚህ ወቅት የፌዴራልና የክልል መንግሥት ተቋማት በከባድ የበጀት እጥረት እየተፈተኑ ነው፤
- መንግሥት ለበርካታ ፕሮጀክቶች መክፈል የነበረበት ገንዘብን መክፈል አልቻለም፤
- በመንግሥት የወጡ የግዥ ጨረታዎች በገንዘብ እጥረት ምክንያት በርካቶቹ ተሰርዘዋል።
- በበጀት እጥረት መደበኛ የመንግሥት ሥራዎችን በአግባቡ ማከናወን አዳጋች ሆኗል።
- በአንዳንድ ክልሎች ለመንግሥት ሠራተኞች መከፈል ያለበት ደሞዝ ለወራት አልተከፈለም።
- በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች በጦርነቱ የወደሙትን መሠረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት ዓመታትን ሊፈጅ ይችላል። (ያውም ገንዘቡ ከተገኘ) በዚህ ሁሉ የኢኮኖሚ ምስቅልቅል  ውስጥ ባለች ሀገር ውስጥ “ቅንጡ ቤተ መንግሥት ካልገነባን ሞተን እንገኛለን” የሚሉት “ፖለቲከኞች”፤ ትንሽ ማመዛዘን ቢችሉ ኖሮ፣ የመንጋ ድጋፍ ለመሳብ የፉክክር ፕሮጀክት እየመዘዙ የሀገር ሀብትን መጫወቻ ከሚያደርጉ ቢያንስ እንወክለዋለን ለሚሉት በችግርና በችጋር ለሚቆራመደው ደሀ ገበሬ ማዳበሪያ ባቀረቡለት ነበር። የብልጽግና ሹማምንት በፖሊሲ ችግር፣ በሙስናና በብልሹ አሠራር የተዝረከረከው ቢሮክራሲ፤ ሕዝቡን ለኑሮ ውድነትና የሰላም እጦት ስለዳረገው ተቃውሞ እንደተነሳባቸው ገብቷቸዋል። ይህንን የሕዝብ ተቃውሞ ለማርገብ፣ ከጽንፈኛ ዘውጌ ብሔርተኞች ድጋፍ ለማግኘትና ማኅበራዊ መሠረታቸውን በመሳብ ኃይል ለማሰባሰብ አዲስ አበባ ላይ የማደናገሪያ ፕሮጀክቶችን አጀንዳ አድርገው ማቅረብ የተለመደ ማስቀየሻቸው ነው፡፡ በእኔ እምነት፣ አሥራ ሁለቱም ክልሎች አዲስ አበባ ላይ ቤተ መንግሥታቸውን ቢገነቡ ብዙም ችግሩ አይታየኝም። ምክንያቱም በዘር ልዩነት ላይ መሠረቱን ያደረገው ኋላቀር “የድንጋይ ዘመን ፖለቲካ” ስለሚፈራርስ፣ ወደፊት የአረጋውያን መጦሪያ ወይንም ሆስፒታሎች ሆነው ሊያገለግሉን ይችላሉ።
  (ዮሐንስ መኮንን)

_____________________________________________________

                       ተራራ ያልበገራቸው እጆች !

       በሚኖርበት መንደር እብዱ እያሉ ይጠሩታል፡፡ ዳሻራት ማንድሂ ይባላል፡፡ ህንዳዊው ገበሬ እበድ ያስባለውን ሀሳብ ወደ ተግባር ለመለወጥ ያነሳሳው፣  ነብሰ ጡር ባለቤቱ ባንድ ወቅት ባጋጠማት ያልታሰበ አደጋ ህይወቷ በማለፉ ነበር፡፡ የሚኖሩበት አካባቢ መንገድ የለውም፡፡ ነዋሪው ከአንዱ መንደር  ወደ ከተማው  መጓዝ ሲፈልግ  የግድ  ተራራና ገደል ማቋረጥ ግድ ይለው ነበር፡፡የዳሻራት ማንድሂ ነብሰ ጡር ባለቤት እንደተለመደው ከመኖርያ ቤቷ በማለዳ ወጥታ  ውሃ ለማምጣት በገደሉ አፋፍ ስትጓዝ፣ ድንገት ያዳልጣትና ወድቃ ክፉኛ  አደጋ ይገጥማታል፡፡  ክፉኛ የደነገጠው ማንጂሂ፣ ከመንደሩ በቅርበት ወደሚገኝ ሆስፒታል ለመሄድ የሚኖርባትን መንደር ከአዋሳኝ ኩታገጠም ከተማ ጋር የለያየውን ተራራ በመተው  ዙርያ ጥምጥም 70 ኪ.ሜ አድካሚ የእግር ጉዞ ማድረግ  ግድ ብሎት ነበር፡፡ አርፍዶ ህክምና ቦታ የደረሰው ማንጂሂ፣ በተራራው ሳቢያ ሚስቱን አካለ ስንኩል ብቻ አይደለም ያደረጋት፤ ቆይቶም ሕይወቷን ጭምር እንድታጣ ምክንያት ሆነ፡
ይህ ጥቁር ጠባሳ ልጆቿን ጥላለት በሄደችው በሚስቱ ማቆሚያ ሊበጅለት ይገባል ያለው  ህንዳዊው ገበሬ፤ እብድ ያስባለውን ሀሳብ እ.ኤ.አ በ1960  የነበሩትን ሦስት ፍየሎች በመሸጥ አንድ  ዶማ፣ አንድ ሽብልቅ፣ አንድ መሮ ይዞ  ሀሳብን ወደ ተግባር ፣  አይቻልምን ወደ ይቻላል ለመቀየር ስራውን ሀ ብሎ ጀመረ፡፡
በህንድ ገጠራማው መንደር አይነኬውን የጌህሉርን ተራራን አፍርሶ፣ ከተራራው ወዲያ ማዶ ዙርያ ጥምጥም ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለንግድ ብዙ ቀናትን የሚጓዙ የመንደሩ ሰዎችን በቅርበት ለማገናኘት ያለመ ስራውን ጀመረ፡፡ ማንጂሂ  ሥራውን ሲጀምር አብዛኞቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ሊሳካ እንደማይችል ደግመው ደጋግመው ቢነግሩትም እሱ ግን አሻፈረኝ ብሎ 110 ሜትር ርዝመት ፣ 8 ሜትር ከፍታና  9 ሜትር  የጎን ስፋት ያለውን የጌህሉርን ተራራን መናዱን ተያያዘው፡፡
ቀናቶች አለፉ፡፡ እብዱ ገበሬም የመንገድ ግንባታ ሥራው ፈር እየያዘለት ሄደ፡፡ በቆይታ ብዛትም አዳዲስ ፈጠራን ይሞክር ጀመር፡፡ ለምሳሌ አልፈነቀል ያለ ቋጥኝ ሲገጥመው  በእሳት እየለበለበ ቀጥሎም ውሃ እየረጨ፣ አለቱን ወደ ኮረት የሚለውጥበት ብልሃት ፈጠረ፡፡ ተራራውም  እየተለወጠ መንገድ መምሰል ሲጀምር ፊታቸውን ያዞሩ የመንደሩ ሰዎች ሁላ ተደስተው ድጋፋቸውን በማሳየት፣ ምግብና ውሃ ያቀርቡለት ጀመር፡፡ ወዲያው እብዱ የሚለው መጠሪያውም ተለውጦ “የተራራው ሰው” የሚል ስም ወጣለት፡፡
ከ22 ዓመታት አድካሚ ስራ  በኋላ እ.ኤ.አ በ1982 የመንገድ ሥራው ተጠናቀቀ፡፡  “የተራራው ሰው” 70 ኪ.ሜ ዙርያ ጥምጥም ጉዞን አዲስ በቀደደው መንገድ ወደ 1 ኪ.ሜ አሳጥሮ ታሪክ አደረገው፡፡ ዛሬ ላይ በትንሷ ቀዬው የሚኖሩ ነብሰ ጡር እናቶች፣ትንንሽ ህጻናት ያለ ምንም እንግልት ሲሻቸው በእግር፣ ሲሻቸው በአውቶሞቢል ይጓዙበታል፡፡
ደሻርዝ ማንዲ በአንድ ዶማ፣በአንድ ሽብልቅና በአንድ መሮ  ሀሳብን ወደ ተግባር ፣  አይቻልምን ወደ ይቻላል ቀይሮ  ከመንደሩም አልፎ ለአለምም ምሳሌ ሊሆን በቃ፡፡
ከዚህ በመነሳት ውድ አንባቢዎች፡- በተሰማራችሁበት ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን በእያንዳንዱ ውሳኔያችሁ ሂደት ላይ ውጤታማነታችሁን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡ ውጤታማ መሆናችሁ ምኞታችሁን ለማሳካት ይጠቅማችኋልና ነው፡፡ አብዛኞቹ ስኬታማ ሰዎች በውጤታማነት የተካኑ ናቸው፡፡ ምክንያቱም በብልጠት ስለሚሰሩ፣ አላስፈላጊ  ልፋትን  ስለሚያስቀሩና ጊዜያቸውን ስለማያባክኑ ነው፡፡
 ለነገሮች ፅኑ አቋም ከሌለንና በሚፈጠሩ ድንገተኛ አጋጣሚዎች ስኬታማነትን እናግኝ ብንል በቀላሉ ልንቀዳጅ አንችልም፡፡
 አብዛኞቹ ስኬታማ ስራ ፈጣሪዎች በቀላሉ አይወድቁም ወይም በውሳኔያቸው ሂደት ላይ መዝረክረክ አይታይባቸውም፡፡
ምክንያቱም ከውሳኔያቸው በፊት ግባቸውን በጥልቅ የመመልከት፣ የማዋቀርና ሙሉ በሙሉ የመዘጋጀት ልምድ ስላላቸው ነው፡፡ አንድ ነገር ጨርሰው የሚቆሙም አይደሉም፡፡   
(ኢሳያስ መብራቱ)


Read 1408 times