Print this page
Saturday, 20 May 2023 21:26

ለመጥመምም ለመለመጥም ጊዜ አለው?

Written by  -ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 “የኛ ጎራ” ለብቻው፣ በጨዋ ደንብ፣ ለእውነት በፅናት እንዲቆም መጠበቅ የዋህነት ነው ብሎ ያስባል-ብዙ ሰው፡፡ ስነ-ምግባርን ማክበር አያዋጣም ብሎ ይደመድማል። እጅን አጣጥፎ በዝምታ የጥቃት ሰለባ ለመሆን በፈቃደኝነት አንገትን እንደ መስጠት ይሆንበታል-ስነምግባርን ማክበር፡፡ ሽንፈትን መጋበዝና ለጠላት መመቸት እንደሆነ ያምናል፡፡
    

         “መጥመም” ማለት፣… የአላማና የአቋም ፅናት ይመስላል። ግን አይደለም። በጭፍን አፈንጋጭነት ላይ ድርቅናንም ይጨምርበታል- “መጥመም” ማለት። የመግባባት አቅም የጎደላቸው ሰዎች፣… አንዳች የምክክር ሙከራ ሲያዩ ይሻክራቸዋል። ጠማማ ይሆንባቸዋል። ወይም ያጣምሙታል።
ስህተትና ጉድለት እየታያቸው፤ ዝም ይበሉ ማለት አይደለም።… ደግሞም ከበቂ በላይ የመከራ መዓት በአገሬው ሞልቷል። ያዩትን የችግር ወይም የብልሽት ብዛት ቢናገሩና ቢታወቅ፣ መንገድ የሳተውን ለማስተካከል፣ የጎደሉትን ለማሟላት ይጠቅማል።
እንዲሁ፣… በባዶ መጥመምና ማጣጣል ነው ችግሩ።
ምን ይሄ ብቻ!  የዚሁ ግልባጭ፣… የመጥመም ሌላኛው መንትያ ገፅታ፣… ተቀናቃኙና እኩያው የሆነ ሌላ ችግር አለ። መጥመም እንደ ረጋሚ አስለቃሽ ነው። ሸንጋይ አጫዋች ወይም አዝማሪ ደግሞ ግልባጩ ነው።
መለመጥና መተጣጠፍ፣… የመግባባት ፍላጎትና ብልሃት ይመስላል። ግን አይደለም። በጭፍን እየሄዱና እየተለጠፉ፣ ለባለስልጣን እየዘፈኑ ተቀናቃኞችን የማብሸቅ “ጥበብ” ነው።
መንግስት “አልደራደርም” ብሎ ከተናገረ፤ “የድርድር ወረዳው” ብለው ያስጨፍራሉ። መንግስት፣ “ምክክርና ድርድር” ብሎ በማግስቱ ከተናገረም፤ “ምክክር የአገር ክብር” ብለው  ያስተጋባሉ።
 “ምክክር፣ ውይይት፣ መግባባት”፣… የሚሉ ቃላት ስለተደጋገሙ ብቻ፣… ለሁሉም ጉዳይ መፍትሔ የተገኘለት የሚመስላቸውና የሚያስመስሉ ሰዎች ሞልተዋል። እልልታና ጭብጨባ እንጂ፣ ትችትና የማስተካከያ ሃሳብ በጭራሽ መስማት አይፈልጉም። እንደ ጥላቻ እንደ ቅራኔ ይቆጥሩለታል። በጭፍን አፈንጋጭነትና በጠማማ ስሜት፣ ሁሉንም ነገር የማንቋሸሽ ዘመቻ የመጣባቸው ይመስላሉ፤ ያስመስላሉ።
ያዩትን መንደርና አገር ሁሉ፣ “ከመቀመቅና  ከሲኦል ይብሳል” ብለው የሚያማርሩ እሳት የላሱ በረዶ የሚያዘንቡ አስለቃሾች አሉ። ግልባጮችስ?  
ጉራንጉሩንና ሸንተረሩን ሳይቀር  ከኤደን ገነትና ከሥልጣኔ ሰገነት አስበልጠው የሚያሞግሱ አጫዋቾች አዝማሪዎችም ሞልተዋል።
ሁለቱም መንትዮች ናቸው። “አቤት ተዓምረኛ መዓት” እያሉ በጭፍን የሚያስለቅሱና፤ “አቤት ተዓምረኛ ሲሳይ” እያሉ በጭፍን የሚያጫውቱ፣… እኩያሞች ናቸው። ከመቀመቅ ለመዳንም ወደ ሰገነት ለመድረስም አይጠቅሙም። አቅሙ የላቸውም። እውነታውን ለመገንዘብ ያልቻሉና ያልፈለጉ ጭፍን ሰዎች፤ ለወደፊት ምን እንደሚሻል የማወቅ እድላቸውን ዘግተውታል።
አስለቃሽና አጫዋች እያልን ስለ ሁለት ዓይነት ሰዎች ብንነጋገርም፤ “የጭፍን ሰው፣…ሁለት የጭፍንነት ገጽታዎች” ብለን ብናስባቸው ይሻላል።
የምክክርና የመግባባት ፀሐይ ወጣች እያለ ትናንት ሲያወድስና ሲያስጨፍር የነበረ የጭፍን ስሜት ፊታውራሪ፤ በዚያው አይዘልቀም። አመሻሽ ላይ ድንገት ተጠምዝዞ፣ ባልተጠበቀ ፍጥነት ዛሬ መልኩን ቀይሮ፣ “ፅልመት ነግሷል” እያለ አገር ምድሩን የሚያጨልም መርዶ ይናገራል። እልልታው በዋይታ ይቀይረዋል።
ከማዶ በኩል፣ የእሪታ አስተባባሪ የነበረ የቅራኔ አጋፋሪ፤ በእልህ ስሜት ተገልብጦ፣ “የውይይትና የፍቅር ዘመን መጣች” እያለ የሚያዳንቅ አዝማሪ ሆኖ ያድራል።
አንዱ ተከርብቶ፣ ተቀናቃኙ ተገልብጦ፣ ቦታ ይለዋወጣሉ።
ያልተቀረው ነገር፣ የጭፍንነት ቅኝታቸው ነው። በጭፍን የደገፈ፣ በጭፍን ይቃወማል። እንደ ልብስ ሁለት ማንነቶችን እየለዋወጡ ይለብሳሉ ልንል እንችላለን። መሰረታዊ የጭፍንነት ባሕርይ ወይም ማንነት ግን አልተለወጠም። ጭፍንነት ነባር ባሕርይ ነው። ሁለት የጭፍንነት ገፅታዎቹም ነባር ናቸው።
ታዲያ ለምን እንግዳ ይሆንብናል?
አንዱ የጭፍንነት ገፅታ ላይ ብቻ ስለምናተኩር ነው፤ ግልባጩ ሲመጣ እንደ አዲስ የሚሆንብን። አስቡት።
መደገፉና መቃወሙ አይደለም ዋናው የማንነት ባሕርይ። ጭፍንነት ነው። ሲደግፍም ሲቃወምም በጭፍን ነው። በጭፍን እየደገፈ፣ ተቀናቃኞችን ግን በትክክለኛ መርህና በሐቅ ሚዛን ይተቻል ማለት አይደለም።
በጭፍን የሚያዳንቅ፤ በጭፍን ያንቋሽሻል።
ነገር ግን፣ የምንደግፈውን በጭፍን ሲደንቅልንና የማንደግፈውን በጭፍን ሲሰደብልን፣… ቅር አይለንም። ቅር ቢለን እንኳ አንናገርም። “በጭፍን ሳይሆን በአግባቡና በልኩ ነው ማድነቅ ያለበት። በመረጃና በጨዋ ደንብ ነው መተቸት ያለበት” የሚል ቅሬታ አይፈጠርብንም። ቢፈጥርብን እንኳ፣ ፊት አንሰጠውም።
በጭፍንም ይሁን በፈጣጣ፣… እንደ ውጤታማ አስተዋፅኦ እንቆጥርለታለን።
ጭፍንነቱና ፈጣጣነቱ የማይመቸን፣… ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ የተገለበጠ ጊዜ ነው።  ወይም ደግሞ፣ ከኛ ጋር አብሮ ያልተገለበጠ እንደሆነም፣… ጭፍንቱና ፈጣጣነቱ እንደ አዲስ ይታየናል- ለዚውም ገዝፎ።“ውሸታምና ጋጠወጥ ተሳዳቢ፣ ጠማማና ተንኮለኛ ነው” ብለን ክፉኛ የምንጠላው የወዲያኛው ጎራ አዝማሪ፣ ድንገት የወዲህኛው ጎራ አስለቃሽ ሲሆንስ?… አነጋገሩ ባይለወጥም፣ የውሸትና የስድብ ኢላማው ስለተቀየረ፣ ባለውለታ እንጂ ነውረኛ ሆኖ አይታየንም፡፡
ጠማማነቱና ተንኮሉ፣ “ለበጎ አላማ ስለሆነ”፣ እንደ ጥፋት ሳይሆን እንደ ጥበብ፣ እንደ ክፋት ሳይሆን እንደ ብቃት ልንቆጥርለት ብዙ ሰበብና ማመካኛ እንፈጥራለን፡፡  ወራዳው እንለው ነበር። “ወንዳታ” እንለዋለን፡፡
ለዚህ አዙሪት ተጠያቂው ማን ነው? ተቀናቃኙ ጎራ ነዋ! እልም ያለ አሉቧልታ፣ አስፀያፊ የስድብ መዓት የሚያጎርፉ “አጥቂ ጠላቶች” በየእለቱ እየዘመቱብን!
 “የኛ ጎራ” ለብቻው፣ በጨዋ ደንብ፣ ለእውነት በፅናት እንዲቆም መጠበቅ የዋህነት ነው ብሎ ያስባል-ብዙ ሰው፡፡ ስነ-ምግባርን ማክበር አያዋጣም ብሎ ይደመድማል።  እጅን አጣጥፎ በዝምታ የጥቃት ሰለባ ለመሆን በፈቃደኝነት አንገትን እንደመስጠት ይሆንበታል-ስነምግባርን ማክበር፡፡ ሽንፈትን መጋበዝና ለጠላት መመቸት እንደሆነ ያምናል፡፡
እናም፣ ለአድማጭ ለተመልካች፣ ለይስሙላና ለታይታ ያህል “የስነ-ምግባር ሰው” መምሰል እንጂ፣ ከልብ የቅንነት  መርህን መከተል አያዋጣም ብሎ ያምናል- ብዙ ሰው፡፡
በሌላ አነጋገር፣ “በተቀናቃኝ ጎራ የሚርመሰመሱት ጋጠወጦች ብዙ ናቸው። ከነሱ የበለጡና የባሰባቸው ባለጌዎች በወዲህኛው ጎራ ቢበዙልን ይሻላል” ብሎ ያስባል፡፡
እናም፣ ጭፍን አስለቃሾች እና አጫዋቾች እንደሆኑ እያወቀም፣ ከወዲህኛው ጎራ ውስጥ ሲገቡ፣ ይደግፋቸዋል። ቢያንስ ቢያንስ በይሁንታ ያቅፋቸዋል፡፡
“በወዲያኛው ጎራምኮ እልፍ ባለጌዎች ሞልተዋል” በማለት ለወዲህኞቹ ባለጌዎች ተከላካይ ጠበቃ ይሆናል፡፡ በሌላ አገላለፅ፣ አብዛኛው ጨዋ ሰው ለጋጠወጦች ምቹ መፈልፈያ ነው፡፡
ጋጠወጥ ተሳዳቢ መሆን የማይፈልግና የማይደፍር የአገራችን ጨዋ ሰው፣ ጋጠወጦችና ተሳዳቢዎች መድረኩ እንዲቆጣሩትና ገናና እንዲሆኑ ግን መንገድ ይከፍታል፡፡ እዚህ ላይ፣ “በአገሩ አዋቂዎች የሉም ወይ?” የሚል ጥያቄ ሊመጣባችሁ ይችላል።
ጋጠወጦችና ባለጌ ተሳዳቢዎች፣ አስለቃሽና አጫዋች አዝማሪዎች በአገሬው ሲነግሱ፣ መጥመምና  መለመጥ ፖለቲካውን ሲዘውሩት፣… አዋቂዎች ምን ይላሉ?
“ለጊዜው ብቻ ነው” ብለው ራሳቸውን የሚያታልሉ “አዋቂዎች” ሁሌም አሉ፡፡
 “አገር እስኪረጋጋ ድረስ”፣
“ትግሉ ለድል እስኪበቃ ድረስ”፣
“ለውጡ መልክ እስኪይዝ ድረስ”፣
“እስክናሸንፍ ድረስ”…
የትኛውም አይነት ድጋፍ… ጨዋም ሆነ ጋጠወጥ ማሰባሰብ፣
 ተቀናቃኞችን የሚጠላ ጭፍንም ሆነ ፈጣጣ ተቃዋሚ ማቀፍ የግድ ነው ይላሉ፡፡
ከድል በኋላ፣ ጋጠወጦችንና ጭፍን ፈጣጦችን ጠራርጎ ማጥራት አይከብድም ብለው ራሳቸውን ለማሳመን ይጥራሉ፡፡ አደጋውን እያባባሱና እያከበዱ እንደሆነ አይገባቸውም? እንዲያውም አደጋውን እያከበዱት እንደሆነ ላለመገንዘብ ነው ሰበብና ማመካኛ የሚደረድሩት። ባዶ የተስፋና የመፅናኛ እንተፈቶን ሲፈትሉና ሲሸምኑ የሚያድሩት፡፡ራሳቸውን የሚያታልሉ “አዋቂዎች”፣… “ለጊዜው ብቻ ነው” እያሉ ጋጠወጦችንና ጨካኞችን ካገነኑ በኋላ፣… ማጣፊያውና መላው የሌላቸው አቅመቢስ ይሆናሉ። ለዚያም ነው፣ በየዘመኑና በየአገሩ ብዙ እልቂትና ትርምስ፣  የሚከሰተው። ለዚያም ነው፤ አገር የጨካኝ አምባገነን ወይም የጨካኝ አመፀኞች መጫወቻ የሚሆነው፤ ምድር ሲኮል የሚፈጠረው፡፡ “ለጊዜው ብቻ ነው” ብሎ ራሱንና ሌሎችን በባዶ ተስፋ የሚያታልል አዋቂ ጠፍቶ አያውቅም። ሁሌም በሁሉም አገር ይኖራል። በዚያው ልክ ነው፤ ሁሌምየጥፋት ታሪክ በየአገሩ እየተደጋገመ የሚከሰተው፡፡
በእርግጥ፣ የጋጠወጥነትና የስድብ ፉክክር፣ እንደ ጊዜያዊ ጨዋታ፣ ብልጠታቸውን የሚያስመሰክሩበት የትርፍ ሰዓት “ጌም”፣ እለታዊ የመዝናኛ ወሬ፣ የሳቅና የቧልት ገበያ ሆኖ የሚታያቸው አላዋቂዎች አሉ፡፡
መጫወቻ ለመሆን ነው ሩጫቸው። ከትንሽ ጊዜ በኋላ፣ “ብልጠት የጎደላቸው” የለየላቸው ፈጣጣ ጋጠወ
ጦችና ለከት የሌላቸው ተሳዳቢዎች፣ መድረኩን ሲቆጣጠሩት፣ ብልጦቹ ቀልደኞች፣ ከጨዋታ ውጭ ይሆናሉ። ወይ ተዋርደው ይሸሻሉ፣ ወይ አዝማያውን አይተው ድምፃቸውን ያጠፋሉ፡፡



Read 3494 times