Saturday, 27 May 2023 17:00

ዘመን ባንክ አዲስ ያስገነባውን ባለ 36 ወለል ህንጻ አስመረቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ዘመን ባንክ፤ አዲሱን የዋና መሥሪያ ቤቱን ህንጻ ዛሬ ያስመርቃል

         የዛሬ 15 ዓመት፣ በ87.2 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል፣ የባንክ ኢንዱስትሪውን  የተቀላቀለው ዘመን ባንክ፣ አዲሱንና ዘመናዊውን ባለ 36 ወለሎች የዋና መሥሪያ ቤቱን ህንጻ በዛሬው ዕለት  ያስመርቃል፡፡
የዘመን ባንክ  አመራሮች  ከትናንት በስቲያ ሐሙስ፣ በአዲሱ የዋና መሥሪያ ቤት ህንጻ  መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ የባንኩን ያለፉ ዓመታት የሥራ አፈጻጸምና የአዲሱን ህንጻ መጠናቀቅ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባ የፋይናንስ ማዕከል ተብሎ በሚታወቀው ሰንጋ ተራ አካባቢ የተገነባው

የዘመን ባንክ  የዋና መሥሪያ ቤት ህንጻ አምስት ዓመታትን የፈጀ ሲሆን፤የግንባታው አጠቃላይ ወጪ ወደ 1.5 ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ተነግሯል፡፡
የዋና መ/ቤቱ ህንጻ መጠናቀቅ ተበታትነው የቆዩትን የባንኩን የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ወደ አንድ ህንጻ በመሰብሰብ ለደንበኞቹም ሆነ ለራሱ ወጪ ቆጣቢ፣ ቀልጣፋና ምቹ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችለው ተገልጧል፡፡
አዲሱ ህንፃ ባንኩ በየዓመቱ ለህንጻ ኪራይ ሲያወጣው የነበረውን ከ40 ሚ. ብር በላይ እንደሚያስቀርለት የተናገሩት የዘመን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ዘበነ ፤” አዲሱ ህንጻ ለባለአክሲዮኖቻችን ሃብት፣ ለደንበኞቻችን ደግሞ ዋስትና ነው” ብለዋል፡፡የባንኩ ዘመናዊ ህንጻ ሁሉንም የግንኙነት አማራጮችን በቴክኖሎጂ ያቀፈ፣ የመረጃ መሰብሰቢያና ማደራጃ እንዲሁም መተንተኛ ማዕከላት ያሉት ነው ተብሏል፡፡
በ2300 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ያረፈው ህንጻው፤ እስከ 200 የሚደርሱ ተሳታፊዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው የስብሰባ አዳራሾች፣ እያንዳንዳቸው 13 ተሳፋሪዎችን የሚያጓጉዙ አሳንሰሮች፣ 200 ተሽከርካሪዎችን ማቆየት  የሚያስችሉ የምድር ቤትና ፎቅ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችን ይዟል፡፡


ግንባታውን ያከናወነው China W

u Yi CO. LTD የተሰኘ የቻይና መንግሥት ተቋራጭ ኩባንያ መሆኑ ታውቋል፡፡


ባለፈው 2021/22 በጀት ዓመት የባንኩ ትርፍ ከታክስ በፊት 2.1 ቢሊዮን ብር እንደነበር ያስታወሱት የባንኩ አመራሮች፤ ይህም ባንኩ ከተመሰረተ ጀምሮ ካስመዘገበው ትርፍ ከፍተኛው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ያለፉት አምስት ዓመታት የትርፍ ድርሻ በአማካይ 40 በመቶ መድረሱንም አክለው ገልጸዋል፡፡
የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ በአሁኑ ሰዓት ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፤የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱና የተከፈለው ካፒታል መጠን 4.7 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተመልክቷል፡፡ 100 የሚደርሱ ቅርንጫፎች ያሉት ዘመን ባንክ፤ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ጠቅላላ ሃብት እንዳለው  ታውቋል፡፡

Read 2078 times