Saturday, 27 May 2023 17:00

በአንዋርና በኒን መስጅዶች የመስጅድን ፈረሳ የሚቃወም ሰልፍ ተደረገ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(9 votes)

 በተቃውሞው ከመንግስት ሃይሎች በተተኮሰ ጥይት የቆሰሉ ሰዎች አሉ
                     
       በሸገር ከተማ አስተዳደር እየተፈፀመ ያለውን የመስጂድ ፈረሳ ተግባር የሚቃወም ሰልፍ በመርካቶ አንዋር መስጂድና በኒን መስጂዶች ትናንት ተካሂዷል፡፡ የተቃውሞ ሰልፉን ለመበተን ከመንግስት የፀጥታ ሃይሎች በተተኮሰ ጥይት የተጎዱ ሰዎች መኖራቸውንና በአስለቃሽ ጭስም ጉዳት መድረሱን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ተቃውሞ ላይ በሸገር ከተማ አስተዳደር እየተከናወነ ያለው የመስጂድ ማፍረስ ተግባር እንዲቆምና የፈረሱት መስጂዶችም በአስቸኳይ እንዲተኩ ተጠይቋል፡፡ ይህንኑ የተቃውሞ ድምፅ ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ አድማ በታኝ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ በስፍራው በነበሩ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱንና በጥይት የተመቱም ሰዎች መኖራቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ፖሊስ ሰልፈኛውን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተጠቅሞ የነበረ ሲሆን ይህም በአካባቢው በነበሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሰ መሆኑም ታውቋል፡፡
አካባቢው በፀጥታ ሃይሎች እየተጠበቀ ሲሆን አመሻሹን ከተቃውሞው ጋር ተያያዥነት አላቸው የተባሉ ሰዎችም በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው ተብሏል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከፖሊስ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡
በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር ውስጥ እየተከናወነ የሚገኘውን የመስጂድ ፈረሳ ተግባር በመቃወም የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ መግለጫ ያወጣ ሲሆን ምክር ቤቱ የጁምዓ መልዕክት ጥሪ አስተላልፎ ነበር፡፡
የፌደራል መጅሊስ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ለዛሬ ግንቦት 19 ቀን 2015 ዓ.ም አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራቱ ይታወቃል፡፡

Read 2517 times