Saturday, 27 May 2023 17:01

አይጧ ከሌለች ጉድጓዱ ከየት መጣ?! (ርያማ ዲኖና ጡሉ ማሚኒ ዳይ) የሲዳማኛ ተረት

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 ከብዙ አመታት በፊት ሁለት ለአካለ ትግል የደረሱና በተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥ ይታገሉ የነበሩ ጓዶች ነበሩ፡፡ ከተወሰነ ወቅት በኋላ የነበሩበትን ፓርቲ ትተው ዓላማቸውን ቀይረው በጊዜው ወደነበረው መንግሥት ገቡ፡፡ በዚያ መንግሥት ውስጥም እንደ አንድ ኮሚቴ ሆነው እንዲሰሩ በመወሰኑ በኮሚቴ ሃላፊነት አንድ ሻምበል ተመድቦላቸው የፖለቲካ ጥናታቸውን ቀጠሉ፡፡ ተጠመቁ፡፡ አመኑ፡፡ መልካም ኑሮ ያገኙ መሰሉ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከሁለቱ ወጣቶች አንደኛው ወደ ወዳጅ አገር ወደ ኩባ ለአጭር ጊዜ ስኮላርሺፕ አገኘና ሄደ፡፡
ተምሮ፣ ተመራምሮ፣ የፖለቲካ ንቃቱን አዳብሮ፣ አንቱ ተብሎ፣ በስኮላርሺፕ የሚቆይበት ጊዜ አልቆ ወደ እናት አገሩ ተመልሶ መጣ፡፡ ወደ እናት ኮሚቴው ለመግባትም አገር ውስጥ ይጠብቀው ወደነበረው ጓደኛው  ሄደና አገኘው፡፡
ሆኖም ሰብሳቢያቸው የነበረው፤ የኮሚቴያቸው መሪ ሻምበል ዛሬ የለም፡፡ ከኩባ የመጣው ወጣት እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የቆየውን ወጣት “ኧረ የሆነስ ሆነና ጓድ ሻምበልስ ወዴት አለ?” ሲል ጓደኛውን ጠየቀ፡፡
ጓደኛውም እያመነታ፤
“ለካ አልሰማህምና! ጓድ ሻምበል እኮ ታስሯል” ይለዋል ሲፈራ ሲቸር፡፡
ከኪዩባ የመጣው ወጣት ክው አለ፡፡ ግራ ገባው፡፡ “እንኳን አሰሩት” እንዳይል ነገ ምን ሊከተል እንደሚችል፣ ጓድ ሻምበል ይፈታ አይፈታ፣ ተፈቶም ወደ ኮሚቴው ይመለስ አይመለስ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ በአንፃሩ “እሱን የመሰለ ጓድ እንዴት ይታሰራል?” ብሎ እንዳይሟገት ደግሞ ገና እሥሩ አላበቃም፡፡ በማን ላይ እንደሚቀጥል ስለማይታወቅ ያስፈራል፡፡ ስለዚህ ጥንቃቄ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ጓደኛው ምን ይል ይሆን እያለ እየጠበቀ አፍ-አፉን ያየዋል፡፡
ያም ከኩባ ተመላሽ ሲጨንቀው ቆይቶ እንዲህ አለ፡-
“አቤት የአብዮታችን ፍጥነት!!”
****
አለመተማመንና ጥርጣሬ የነገሰበት ወቅት የፍርሃት እናት ነው፡፡ ሰው የልቡን አያወራም፡፡ ጓደኛና ጓደኛ በጎሪጥ ይተያያል፡፡ መከዳዳት የእለት - የሰርክ ጉዳይ ይሆናል- እንደውም ይለመዳል፡፡ ጠብታዋ ነገር ሰፍታ ጎርፍ ትሆናለች፡፡ በጦርነት ከሚረታው በወሬ የሚረታው ይበልጣል፡፡ የበታች የበላዩን ይፈራል እንጂ አያከብርም፡፡ ይታዘዛል እንጂ አያምንም፡፡ የበላይ የበታቹን በትንሽ-በትልቁ ይጠራጠራል፡፡ ያሴርብኛል እንጂ ያግዘኛል የሚል እምነት የለውም፡፡ አለቅየው ቅንጣት ታህል ጥፋት ሲያይ ከምድር-ከሰማይ ጉዳይ ጋር አገናኝቶ በእኔ ላይ የተቃጣ ተንኮል ነው ሲል ይደመድማል፡፡ ሁሉ ነገር ወዴት እንደሚያመራ ስለማይታወቅ በጥንቃቄና በፍርሃት መካከል ልዩነት ይጠፋል፡፡ ሰላምታው ስድብ፣ ስድቡ ሰላምታ የሚመስልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ፈሪው ከፍርሃቱ ብዛት ጀግና ይሆናል፡፡ እንቅፋቱ ሁሉ ለሞት ያበቃኛል ስለሚል የተከላከለ መስሎት አጥቂ ይሆናል፡፡ “የሚያባርረኝ ጣሊያን እንቅፋት መትቶት በሞተ አርበኛ ነህ አሉኝ እንጂ እኔስ አርበኛ አደለሁም!” እንዳለው የሃገራችን ሰው መሆኑ ነው፡፡ ጀግናው ደግሞ ከጥንካሬው ብዛት ፈሪ ይሆናል፡፡ ትንኟን በአቶሚክ ቦንብ ይገድላል፡፡ ለዚህም አላጨበጨባችሁልኝም ብሎ አገር ምድሩን ያኮርፋል፡፡ መጨካከን እንደ ዋዛ ይለመዳል፡፡ ስርቆትና ምዝበራ “ቢዝነስ ተሰራ” ይሰኛል፡፡ ከእያንዳንዱ ሃብት ጀርባ ያለው ወንጀል እንደ ጥበበኛነትና እንደ ጀብድ እንደሚቆጠር ሁሉ፤ በእያንዳንዱ መሸናነፍ ጀርባ ያለው ደግሞ እንደ አላማ ፅናት፣ ቆራጥነት፣ መስዋእትነት ይታያል፡፡ በዚህን አይነት ሰአት ብዙ ክስተት የድንገቴና የዱብ-እዳ እንጂ በሂደት የመጣ አልመስል ይላል፡፡ አብዛኛው ነገር የማይታይ ፍልሚያ (The invisible conflict እንዲል መፅሐፍ) አይነት ይሆናል፡፡ ህቡኡ የአደባባይ አዋጅ ፣ የአደባባይ አዋጁ ህቡእ የመምሰል ባህሪ ያመጣል፡፡ ወዴት እየሄድን ይሆን? የሚለው ጥያቄ የሁሉ ሰው ጥያቄ ይሆናል፡፡ የአለቃም የምንዝርም! አንድ ጊዜ አንድ አብዮት አደባባይ ለመሰለፍ የወጡ አሮጊት “የዛሬው ሰልፍ አላማ ምንድን ነው?” ብሎ ጋዜጠኛ ቢጠይቃቸው፤ “ቆይ እንጂ አትቸኩል ገና ሹሞቹ መጥተው መች ነገሩን!” አሉት አሉ፡፡ የሚያገባንን ጉዳይ ሁሉ መስማት መቻል አለብን፡፡ በሃገር ደረጃ የተለየ ችግር የሚፈጥር ካልሆነ በቀር፡፡
ህዝብ በየጊዜው የሚካሄደውን ነገር ማወቅ ይፈልጋል፡፡ በየወቅቱ የሚደረገውን ሃገራዊም ሆነ ከሃገር ጋር የተያያዘ አለም-አቀፍ እንቅስቃሴ እንዲገባው ይፈልጋል፡፡ አፍንጫው-ስር የሚከናወን ድርጊት ላይ አፍጦ አርቆ ማስተዋል እንዳያቅተው፣ ሩቅ ሩቅ እያየ የቆመበት ምንጣፍ ከእግሩ ስር ተስቦ እንዳይወሰድ፤ ማንኛውም ኢንፎርሜሽን ሊነገረው ይገባል፡፡ አለበለዚያ ስለነገ ያለው ተስፋና ግምት በፍርሃትና ጥርጣሬ የተሞላ ይሆንና “አቤት የአብዮታችን ፍጥነት!” ሲል የሚገኝ የራሱ አቋም የሌለውና “ዛሬን እንደምንም ልደር ብቻ” የሚል ዜጋ መፈልፈል ይሆናል እጣችን፡፡ ታመመ ሲሉ ሞተ ፣ ወደቀ ሲሉ ተሰበረ ማለት ቅርብ በሆነበት ዘመን፣ ህዝብ ላለማመን ቅርብ ቢሆን አይገርምም፡፡ አጋጣሚን መሾሚያ መሸለሚያ የሚያደርግ የሚበዛበት ጊዜ ቢፈጠርም አይገርምም፡፡ ሔልሙት ክሪስት የተባለ አንድ ደራሲ፤ The rottener the time the easier it is to get promoted  እንዳለው ነው፡፡ (ጊዜው የበለጠ እየነተበ በመጣ ቁጥር በቀላሉ መሾምና እድገት ማግኘት እየበዛ ይሄዳል እንደማለት ነው፡፡) የቢሮክራሲ ንቅዘት፣ የአመለካከት ክስረት፣ የአዛዥነት አስተሳሰብ፣ የእሺ-ባይነት ኩራት፣ ከሁሉ-በላይ ነኝ የሚል ስሜት፣ የጌታና የሎሌ ግንኙነት፣ የመቻቻል ድህነት፣ የሙስና ጌትነት ወዘተ ሁሉም የተሳሰሩና የተሳሰረ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንዲሁም ታሪካዊ ምንጮች ያሏቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ የህዝብ ጥርጣሬና ፍርሃት ሲከሰትና ነገ ምን ይፈጠር ይሆን? እያለ መስጋትና መጠየቅ ሲበዛ፣ እነዚህን ምንጮች በጥሞና መመርመር ያሻል፡፡ እንደ ሲዳማ ህዝባዊ አባባል “አይጧ ከሌለች ጉድጓዱ ከየት መጣ?” ማለት አለብን፡፡     



Read 1722 times