Saturday, 27 May 2023 17:04

“ያልጠረጠረ፣ ተጠረጠረ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)


        እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ...መቼም ያለንበት ጊዜ...አለ አይደል...እንደምታውቁት አስቸጋሪ ነው፣ በሙሉ ልብ ራቅ ብሎ መሄድ የማይቻልበት፡፡ አሀ ልክ ነዋ...በፊት እኮ...አለ አይደል... “ዊክኤንድ ለምን ከከተማ ወጣ ብለን አናሳልፍም!” ይባል ነበር፡፡ አሁን፣ አሁን ግን ብዙ ጊዜ አንሰማውም፣  ቢባልም እንደበፊቱ በሙሉ ልብ ሳይሆን በመጠራጠር ነው፡፡
ይቺን ስሙኝማ... በዕድሜ የገፉት ሴትዮ ምርመራ ለማድረግ ሆስፒታል ሀኪማቸው ዘንድ ይሄዳሉ፡፡ “ዶክተርዬ ልትረዳኝ ይገባል፣ ምን እንደማደርግ ግራ ገብቶኛል፡፡ ምንም ነገር ማስታወስ አቅቶኛል፡፡ የሰማሁትን ነገር ደቂቃ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ነው የምረሳው፡፡ ምን እንደማደርግ ምከረኝ፣” ይሉታል፡፡
በዚህ ጊዜ ዶክተሩ ምን ብሎ ‘ቢመክራቸው’ ጥሩ ነው... ”የሚደረጉልሽን ምርመራዎች ሙሉ ሂሳቡን አስቀድመሽ ክፈይ፡፡” እናማ ዶክተርዬም ቢሆን ላያምናችሁ ይችላል ለማለት ያህል ነው፡፡
የሚገርም እኮ ነው፡፡ ደግሞላችሁ...በአንድ ጫፍ አይደለም ከከተማ ወጣ ስለማለት ማሰብ የጥንቷ፣ የጠዋቷ ከተማ ውስጥ እንኳን ራቅ ወዳለ ሰፈር መሄድ ብዙም  ምቾት የማይሰጥበት ጊዜ ውስጥ ነን፡፡ በሌላኛው ጫፍ ደግሞ (‘ጫፍ’ ቢሉ ቅርብ የሆነ ‘ጫፍ’ መሰላችሁ እንዴ!) እናላችሁ....“በል/በይ...” ባላቸው ጊዜ፣ የዓይናችን ቀለም ባስጠላቸው ጊዜ፣ የሆነ ከበድ ያለ ነፋስ የመጣ በመሰላቸው ጊዜ አውሮፕላን ላይ እንጣጥ ብለው ሽው ማለት የሚችሉ ሰዎች መአት ናቸው ይባላል፡፡ ...ባለ ፍራንኮች፣ ባለ ቦተሊኮች፣ ባለ ‘ታላላቅ ወንድሞች’...ባለ መጠባበቂያ ፓስፖርቶች...ጨምሩበትማ፡፡ ግን፣ ፌይር አይደለም፡፡
አሁን ጊዜው ከፍቷል፤ አዳዲስ ወዳጆች የሚፈለጉበት ሳይሆን ቀድሞ የነበሩ መልካም ወዳጆችን አጥብቆ መያዣ ነው፡፡ (‘መልካም’ የሚለው ቃል ይሰመርበትማ!)
ስሙኛማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ከዚህ ቀደም እንዳወራናት አሁንም የማናምናቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ያውም ከበፊቱ ባይብስ ነው! ለምን ቢባል... ምክንያቶች ይኖሩናላ!  ምክንያቱም ቃል ተግባር ላይ ሲውል ማየት ናፍቆናልና! አሀ..ልክ ነዋ! ከላይ እስከ ታች የማናምናቸው ነገሮች፣ የማናምናቸው ቡድኖች፣ የማናምናቸው ስብስቦች፣ የማናምናቸው ግለሶቦች፣ የማናምናቸው መግለጫዎች... እየበዙብን ነዋ!
 “ጆሮ አይጾምም፣ ዓይን አይጠግብም...” የሚሉት ነገር አለ አይደል...ተወደደም ተጠላም መስማታችን፣ ማየታችን አልቀረም! እናማ...ሰዋችን በብዙ ነገሮች ተጠራጣሪ ቢሆን አይፈርድበትም፣ ስንትና ስንት ጉድ ያለበት ዘመን መሰላችሁ! (እንትና...ይሄ ‘የሮቦት ዋይፍ’ ምናምን ስለሚሉት ነገር...ሰምተሀል! ምን መሰለህ...አይ ማንም መክሮኝ ወይም ገፋፍቶኝ አይደለም፡፡ አንተ ደግሞ... “ያልጠረጠረ ተመነጠረ!” ቢሉህ አይነት አለዋ! እናልህ፣ “ሁልጊዜም አዲስ ነገር መሞከር እወዳለሁ...” የምትለው ነገር ስላለህ፣ አዲስ የሆነውን የሮቦት ዋይፎች ነገር ሞክረህ ንገረንማ!
ለምሳሌ በስሎው ሞሽን እየተራመደ ያለ የሚመስለውን ሰው ገና እንዳገኛችሁት ሰላም ብላችሁ እንኳን ሳትጨርሱ ተጣድፎ “በኋላ እደውላለሁ፣” ብሎ ሽው ካለና፣ ይደውላል ብላችሁ ከጠበቃችሁ ‘ፕራንኩ የተሠራው’ (ቂ...ቂ...ቂ...) እናንተ ላይ ነው ማለት ነው! ልከ ነዋ... እስቲ በዚህ መልክ አግኝታችኋቸው “እደውላለሁ..” የሚል ሰው ስንት ጊዜ እንደገጠማችሁ አስቡትማ፡፡ ደግሞ ስንቱ  ቃል ገብቶ  ቃሉን ጠብቆ እንደደወለ ሂሳብዬዋን ሥሯትማ፡፡ መጨረሻ ላይ እኮ የፈረደባችሁ እናንተው ናችሁ የምትደውሉት፡፡ ሰውየው የእናንተን ጥሪ ከመለሰ ከሁለት ነገሮች አንዱ ነው... ወይ ቁጥሩን አላየም፣ ወይም ቁጥራችሁን ጭራሽ አያውቀውም፡፡
“ሀሎ!
“ሀሎ እደውላለሁ ብለህ ጠፋህብኝ...”
“ማን ልበል!” ምን! ሰውየው ምንድነው ያለው? እኔ እነግራችኋለሁ... “ማን ልበል!”  ነው ያለው፡፡
“ጆኒ ነኝ፣ የስድስት ኪሎው ጆኒ...”
“ጆኒ! ጆኒ...ይቅርታ አላስታወስኩህም!” ‘እየፈጩ ጥሬ’ የሚለውን ተረት፣ ወይም የዚሁ ተረት ‘የዘር ግንድ’ ያለው ሌላ ተረት ብታውቁ ይሄኔ ነበር የምትጠቀሙበት፡፡ አለ አይደል...ይሄን  ጊዜ በ‘ሂዩመን ስፒሽየስ’ ውስጥ መፈጠራችሁን ብትረግሙ አያስወቅስም፡፡ ጭራሽ “ማን ልበል!” ይበላችሁ! “እመኑኝ ንቋችኋል፣ ደፍሯችኋል፣ ብታምኑም ባታምኑም ከእነመፈጠራችሁም ረስቷችኋል፡፡” (ቦለቲካ እንደ እነእንትና ጠባይ ጥምም ባለበት፣ እኛም ዘንድ ሆነ ሌላ ቦታ በጣም ባስጠላበት ቀሺም ዘመን ለይቶልኝ ቦተሊካ፣ ቦተሊካ አሰኘኝ እንዴ!)
“አንቺ ዛሬ ጸጉርሽ እኮ የአንቺ የተፈጥሮ ጸጉር ሳይሆን ከሆነች አሪፍ የሆሊዉድ ተዋናይ የተበደርሽው ነው የሚመስለው፡፡ እንዴት እንደሚያምር አልነግርሽም!”
“ይሄን ያህል አምሮብኛል!”
“ማማር ብቻ!”
እንትናዬ ቆይ ለመዝለል አትቸኩይማ፡፡ አሀ... ላንቺ ብዬ ነዋ! “ዝለይ፣ ዝለይ፣” ቢልሽ እኮ አብሮሽ አይዘልም፡፡ እኔ የምለው... “ከንፈሩን ያሞጠሞጠ ሁሉ የሚሳም አይደለም...” የሚል ተረት ይሁን ማስጠንቀቂያ ትዝ ያለኝ የሆነ ሰው ነግሮኝ ነው ወይስ የበቀደሙ ‘ሂስቶሪካል’ ቅዠቴ ተረፈ ምርት ነው!
እኔ የምለው...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ብርቅርቅታው ለእኛ ለእግረኞች መከራ የሆነ የተወለወለ መኪና ይዘው “የእኔ ሀብት ሕዝቡ ነው” የምትለዋን ‘ፕራንክ’ ምናምን ነገር አሁን፣ አሁን ብዙም አንሰማትምማ! ማለትማ በሌላ ተለወጠች እንዴ! ማለትማ... ነገርዬዋ የተፈጥሮ ሂደት ጨርሳ ከሰመች ወይስ ‘ዲሊት’ ተደረገች፡፡
 “የጻፍከው ጽሁፍ እኮ እንዴት አሪፍ እንደሆነ የሚገርም ነው፡፡” ኸረ በህግ አምላክ! እናንተ እኮ የጻፋችሁት በጣም ቀሺም ሆኖባችሁ “ጽሁፉ ከታተመ በኋላ ሀክ መደረግ ተጀመረ እንዴ!” ምናምን እያላችሁ ሊሆን ይችላል፡፡ ደግሞላችሁ...የቅርብ አለቆች እኮ “ይህን ጽሁፉ የጻፈው የትኛው መጠጥ ቤት እየጠጣ እንደሆነ ይጣራ፣” ምናምን ለማለት ምንም አልቀራቸው፡፡ እናማ ምን እንደሠራችሁ እየተዋወቃችሁ “አሪፍ!” ምናምን የሚል ሰው ወይ ‘የዋህነቱ’ በዚች ዓለም ላይ የማይሠራ ነው፣ ወይ ‘ጮሌነቱ’ በዚች ዓለም ሊሠራም፣ ላይሠራም የሚችል ነው፡፡ ቂ...ቂ...ቂ...  እናም “ይህች ጸሁፍህ  ለታሪክ መቀመጥ ያለባት ነው፣” ሲላችሁ “አይ ይቺ ሰውዬ ተናግራ፣ አናግራ እኔኑ ታሪክ ልታስደርገኝ ነው እንዴ!” ብትሉ አይፈረድባችሁም፡፡ “ከተናግሮ አናጋሪ ጠብቀኝ...” የሚባለው እኮ በምክንያት ነው፤፡
እናማ...አለቦታቸው የሚገቡ የአድናቆት፣ ጭብጫቦ አይነት ነገሮችን በጥርጣሬ የሚያይ መአት ህዝብ እንዳለ ልብ ይባል ለማለት ነው፡፡
ለምሳሌ “ትወደኛለህ?” ብላ ስትጠይቀው ጠብ፣ ጠብ የሚለው አይነት፡፡ “አዎ እወድሻለሁ!” “እንጥሌ ዱብ እስክትል ነዋ የምወድሽ!” ቂ...ቂ...ቂ... (እንጥል ‘ላቭ’ ውስጥ ድርሻ እንዳለው ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰበት ቀን፡፡) እንደማለት “እንዴት እንዲህ አይነት ጥያቄ ትጠይቂኛለሽ?” ብሎ ጠብ፣ ጠብ የሚያሰኘው፡፡
ስሙኝማ...ለስንብት ይቺን እዩልኝማ...ልክ እንደ እኛ ሥራ ማግኘት ቀላል ያልሆነበት ቦታ ነው አሉ፡፡ እና አንድ የህክምና ዶክተር ቧንቧ ይፈነዳበትና ቧንቧ ሠሪ ያስጠራል፡፡ ቧንቧ ሠሪውም በአጭር ጊዜ ውስጥ ነገርዬውን አስተካክሎ ጨረሰ፡፡
“ሂሳብህ ስንት ነው?” ሲል ባለቤት ጠየቀው፡፡
ቧንቧ ሠራተኛውም “ስድስት መቶ ዶላር ብቻ ነው፣” ይላል፡፡ ይሄኔ ዶክተሩ ብው ይላል፡፡
“ምን! ስድስት መቶ ዶላር?”
“አዎ፣ ስድስት መቶ ዶላር፡፡”
“ይሄ እብደት ነው፡፡ እኔ የህክምና ዶክተር ሆኜ እኮ ይህን ያህል ገንዘብ አላገኝም፣” ይላል ዶክተር ሆዬ ንዴቱ ሳይበርድለት፡፡ ቧንቧ ሠሪው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው...
“እኔም የህክምና ዶክተር የነበርኩ ጊዜ ያን ያህል አላገኝም ነበር፡፡” አሪፍ አይደል፡፡
እናማ...ባለንበት ያለመተማመን ዘመን ያልጠረጠረ፣ እሱ ባይጠረጥርም፣ ራሱ ተጠርጣሪ እንደሆነ እየረሳ ነው ነገሮች የሚበላሹት፡፡ ሀሳብ አለን...“ያልጠረጠረ ተመነጠረ፣” ከሚለው ጎን ለጎን “ያልጠረጠረ ተጠረጠረ!” የሚል ይግባልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1364 times