በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ገለምሶ ከተማ ሰሞኑን የተሰማው ወሬ አግራሞትን የሚያጭር ነው። ሌሊት በጨለማ በመጓዝ የምናውቀው ጅብ በቀትር ከተማይቱ ውስጥ ወደ ሚገኝ አንድ የግል ክሊኒክ ሰተት ብሎ መግባቱ ተሰምቷል።
በገለምሶ ከተማ በሚገኘው ሚልኪ ክሊኒክ የሕክምና ባለሙያ የሆነው አዱኛ አባይነህ፣ የሆነውን እንዲህ በማለት ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ አስረድቷል።
“ጠዋት ወደ አራት ሰዓት አካባቢ ይሆናል። የክሊኒካችን በር ክፍት ነው። እኛም ገና ሥራ አልጀመርንም ነበር። ጅቡ በቀጥታ በተከፈተው በር ገብቶ ወደ ላብራቶሪ ክፍል አመራ።”
የክሊኒኩ ነርስ የሆነው አዱኛ፣ ሰዎች ጅቡን ሲያዩ ተደናግጠው ለመደብደብ ዱላ ማንሳታቸውን ይናገራል።
የክሊኒኩ ባለቤት ግን ሰዎች ጅቡን እንዳይመቱ ተከላከሉ።
“ወደ አምስት ሰዓት አካባቢ የክሊኒኩ ቅጥር ግቢ በሰው ተሞልቶ ነበር። በዚህ ጊዜ በአካባቢው የሚገኙ የትራፊክ ፖሊሶችን ጠርተን ሕዝቡ እንዲረጋጋ አደረግን።”
ጅቡ ግን ላብራቶሪ ክፍል ከገባ በኋላ ጭንቅላቱን አቀርቅሮ እንደተኛ ነበር ይላል፤ አዱኛ። ሁኔታው የታመመ እንጂ ጉዳት ለማድረስ የመጣ አይመስልም ነበር።
“ጅቡ ታሞ እንደሆነ ጠረጠርን። ከዚያም የእንስሳት ሐኪም ጋ ደወልን። እርሱም የፀረ-እብድ ውሻ በሽታ (አንቲ ሬቢስ) መርፌ ስጠው አለኝ። ከዚያም በኋላ መድኃኒት ቤት ሄጄ ገዝቼ ቀስ ብዬ በመርፌ ወጋሁት” ይላል፤ ነርስ አዱኛ።
ነርስ አዱኛ ለጅቡ መርፌውን ለመውጋት ባሰበ ጊዜ ለደኅንነቱ ሰግቶ ነበር። ነገር ግን ጅቡ በጣም ተዳክሞ ለመንቀሳቀስ በማይችልበት ሁኔታ ስለነበረ፣ ሲወጋ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አላደረገም ብሏል። ቢሆንም ግን ለደኅንነቱ የሰጋው ነርስ፤ ጅቡ ተኝቶበት ከነበረው ስፍራ አቅራቢያ የነበረውን ማቀዝቀዣ በከለላነት ተጠቅሞ ነበር መርፌውን የወጋው።
በክሊኒኩ ውስጥ ለአንድ ሰዓት ያህል የቆየው ጅብ፣ መርፌውን ከተወጋ ከ20 ደቂቃ በኋላ ተነስቶ መውጣቱን አዱኛ ይናገራል። “ጅቡ የታመመ ስለሚመስል እኛ አንድ ባዶ ክፍል ልናስገባው ነበር። ነገር ግን እንዳሰብነው አልሆነም። ልክ መርፌውን ከወጋነው ከደቂቃዎች በኋላ ከተኛበት ቦታ ተነስቶ ወጥቶ ሄደ።”
በግል ክሊኒክ መርፌ የተወጋው ጅብ ዳግም አለመመለሱን የህክምና ባለሙያው ያስረዳሉ። ክሊኒኩ ጅቡ ያረፈበትን የላብራቶሪ ክፍል በሚገባ ካጸዱ በኋላ ወደ ቀድሞ ሥራው ተመልሷል። እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ በአካባቢው የተለመደ አለመሆኑንና የአካባቢው ነዋሪዎች መደነቃቸውን የህክምና ባለሙያው አቶ አዱኛ ይናገራሉ።
Published in
አግራሞት