Saturday, 03 June 2023 13:21

ኢሰመኮ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ለተፈፀመው ጥቃት የመንግስት የፀጥታ አካላት በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባ ገለፀ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(0 votes)

    በሸገር ከተማ ወደ 112ሺ የሚጠጉ ቤቶች መፍረሳቸውንም ገልጿል
                  
       በሸገር ከተማ በመንግስት አካላት ከፈረሱ መስጊዶች ጉዳይ ጋር በተያያዘ ባለፈው አርብ ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ.ም በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ አንዋር መስጊድ ውስጥ  በመንግስት የፀጥታ ሃይሎች በተወሰደ እርምጃ የሰው ህይወት ማለፉንና የአካልና የስነልቦና ጉዳት መድረሱን ኢሰመጉ ገለፀ፡፡ ለሰው ህይወት ህልፈትና አካል ጉዳት ተጠያቂ የሆኑ የፀጥታ አካላት ተለይተው በህግ እንዲጠየቁም አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መበቶች ኮሚሽን ሰሞኑን ከመስጅድ ፈረሳዎቹ ጋር በተያያዘ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በመንግስት የፀጥታ ሃይሎች በተወሰደ እርምጃ የደረሰውን የሰው ህይወት ህልፈትና የንብርት ውድመት በተመለከተ ምርመራ ሲያካሂድ መቆየቱን ትናንት ይፋ ባደረገው መግለጫው አመልክቷል፡፡
የሰሞኑን ተቃውሞ ተከትሎ የደረሱትን ጉዳቶች በተመለከተ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ ከመንግስት የፀጥታ አካላት ሃላፊዎች፣ ከአይን እማኞችና ከተጎጂዎች ማስረጃ ማሰባሰቡንና ክትትል ማድረጉን የገለፅ ኢሰመኮ፤ በምርመራ ውጤቱ መሰረትም የመንግስት የፀጥታ ሃይሎችና የአድማ ብተና ሃይል ወደ ታላቁ አንዋር መስጊድ ግቢ ጭምር በመግባትና አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ፣ ምዕመኑን ለመበተን በወሰዱት እርምጃ በተፈጠረ ሁከት የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን፣ በበርካቶች ላይ የአካልና የስነልቦና ጉዳት መድረሱን አመልክቷል፡፡
በክስተቱ የሞቱና ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ጉዳይ በተመለከተ የሚያደርገውን ምርመራና ክትትል እንደሚቀጥል የጠቆመው ኮሚሽኑ፤ መንግስት ህዝባዊ ሰልፎች፣ ሃይማኖታዊና ሌሎች ስብስቦች ለመበተን አላስፈላጊና ተመጣጣኝ ካልሆነና ሞት ከሚያስከትል የሃይል እርምጃ  እንዲቆጠብ አሳስቧል። ሰሞኑን በተፈጠረው ሁከት ሳቢያ ለደረሰው የሰው ህይወት ህልፈት ተጠያቂ የሆኑ የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ተለይተው በህግ እንዲጠየቁ፣ በቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች ወንጀል ስለመፈፀማቸው በቂ ጥርጣሬ ከሌለና ተአማኒ ክስ የማይቀርብ ከሆነ በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁም አሳስቧል፡፡

Read 1434 times