Saturday, 03 June 2023 13:22

የ‘ነገር’ ፉርኖ ቤት!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ....ኸረ ምስኪኑ ሀባሻ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አ...አቤት አንድዬ! አቤት!
አንድዬ፡- ተኮራረፍን እንዴ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ለምን እንደሱ አልክ! አስደነገጥከኝ...
አንድዬ፡- ቆይ አስጨርሰኝ እንጂ፡፡ ሌላ ጊዜ ገና እዚህ ሳትደርስ ከስንትና ስንት እርቀት እየተጣራህ አልነበር እንዴ የመትመጣው! ዛሬ እኮ ምን እንደተገኘ እንጃ፣ ዝም ብለህ ዘው ብለህ ነው የገባኸው! ቁልፍህ ሰጥቼህ ነበር እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- አላስቀልድ አትበለኛ! እናንተ ቀልድና ቀልድ እያስመሰላችሁት ያለው ቁም ነገራችሁ ተምታቶባችሁልና፣ ቀልዴንማ አትውሰድብኝ፡፡ እና...ምነው እንደቀድሞው ሰላም አላልከኝምሳ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ይቅርታ አንድዬ፣ እራሴንም እየረሳሁ ነው! ይቅርታ!
አንድዬ፡- እፎይ...አሁን ልቤ መለስ አለች፡፡ ዝም ብለኸኝ  ዘው ብለህ ስትገባ እኮ ሰጋሁ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ለምን አንድዬ! እኔ ምስኪኑን ምን ያደርገኛል ብለህ ትሰጋለህ አንድዬ!
አንድዬ፡- ድንገት መጥተህ  ከገዛ ቤቴ አፈናቅለህ፣ ወንበሬን ልትወስድብኝ መስሎኝ ነዋ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ...
አንድዬ፡- ግዴለም ይቅር፡፡ ምላድርግ ብለህ ነው ምስኪኑ ሀበሻ! እኔ እኮ እንደው ቁጭ ብዬ ስታዘባችሁ አይሆንም፤ ሊሆን አይችልም የሚባለው ነገር ሁሉ የሚሆንባት የእናንተዋ ሀገር ብቻ ትመስለኛለች፡፡ ደግሞ እኔን ከወንበሬ ማንሳት አይሆንም፣ ሊሆን አይችልም፣ አይታሰብም አይደል የሚባለው! ምናልባት፤ “እሱ ማን ስለሆነ ነው፣ ለዘለዓለም ወንበሩን ይዞ. የሚኖረው” ብላችሁ በአብላጫ ድምጽ ወስናችሁብኝ፣ አንተን ልከውህ እንደሆነ ብዬ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ እያስፈራራኸኝ ነው!
አንድዬ፡- እሱን እንኳን ተወው ምስኪኑ ሀበሻ፣ እሱን እንኳን ተተው፡፡ ይልቅ ዋናው ነገር ዛሬ ሁሉ ነገርህ ተለዋውጦብኛል፡፡ እንደው ትንሽ እነኛ ከፊትህ አልፋቅ ያሉ መስመሮች ባይሮ ኖሮ ሌላ ሰው ትመስለኝ ነበር፡፡ ደህና ነህ? ማለቴ ጤና ነህ አይደል!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣...ምን ጤንነት...
አንድዬ፡- ምን ጤንነት አለ ልትለኝ አይደል!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አዎ አንድዬ፣ ምን ጤንነት አለ! አሁንማ  አእምሮዬ ሁሉ በትክክል ማሰብ አቁሟል፡፡
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፤ አሁን ቁም ነገር አመጣህልኝ፡፡ እኔንም ግራ የገባኝ ነገር ነው፡፡ እኛን አለመታዘብ ሥራ የለህም ወይ እንዳትለኝ እንጂ እዚህ ሆኜ ስታዘባችሁ፣ ብዙዎቻችሁ ነገረ ሥራችሁ ሁሉ ይሄ...የአእምሮ ምንድነው የምትሉት...ይሄ የሰው አእምሮ እንኳን የመሥራት አቅም ሲያጣ...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- የአእምሮ መቀንጨር ነው የምንለው አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- ግን ምስኪኑ ሀበሻ ሁሉ ነገራችን ውስጥ ጥልቅ ይላል እንዳትለኝ እንጂ፣ መጨንቀር የምትለዋን ቃል እንደው ምን ስትሉ ነው የፈጠራችኋት!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ልቦና ኖሮን እንዲህ እንዲህ አይነት ነገር ብናውቅ ኖሮማ፣ በማን ዕድላችን! ሲሉ ሰማን እኛም ማለት ጀመረን፡፡
አንድዬ፡- ግን እኮ ምስኪኑ ሀበሻ እንደው ለጨዋታ ያህል ፍቀድልኛና፣ ለዘፈን ጥሩ ቃል አትመስልህም! ለምሳሌ “በአንቺ ፍቅር አሳሬን በልቼ አእምሮዬ ጨነቀረ” ምናምን አይነት...ተወው፣ እርሳው  ምስኪኑ ሀበሻ፡፡ ከምን የዋለች ጊደር አይደል የሚባለው...ከእናንተ ብሼ ቁጭ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ! አንድዬ...  ስማኝማ አንድዬ!
አንድዬ፡- ተረጋጋ እንጂ፣ ምስኪኑ ሀበሻ፡፡ በአምስተኛ ማርሽ ተንደረደርክብኝ እኮ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ምን፣ ምን መሰለህ...ካላስቸገርኩህ ቅድም ያልካትን ድገምልኝማ!
አንድዬ፡- ለመደግም የሚበቃ ምን አልኩና!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ...በፍቅርሽ አእምሮዬ ጨንቅሮ ምናምን የምትለዋን፡፡
አንድዬ፡- ጎሽ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ጎሽ! ቀስ ብለህ ደግሞ እስክስ እያልክ ዝፈንልኝ ልትለኝ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ ምን ቆርጦኝ አንድዬ! ምን ቆርጦኝ!
አንድዬ፡- ይልቅ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ይቺ የአእምሮ መጨንቀር የምትባለዋን ነገር፣ መዘላለፊያ  እያደረጋችኋት ነው ልበል!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ አትታዘብኝና ዘንድሮ የእኛ አእምሮ ያልጨነቀረ፣ ምን ይጨነቅራል ብለህ ነው፡፡ የሆነ ነገርማ ሆነናል፡፡
አንድዬ፡- ቆይ፣ ቆይ ምስኪኑ ሀበሻ...እኔ ለቀልድ ያህል ጣል አደርግሁ እንጂ ቁም ነገር ነው ብዬ አይደለም፡፡ እናንተ ኢምንቱንም ነገር ሁሉ ተራራ ማሳከል አልለቅ ብሏችሁ ነው እንጂ እኔስ ስቀልድ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ይቅርታ አንድዬ፣ አሁን ያልከውን እቃወማለሁ፡፡ እኛን እንዳይከፋን ብለህ ነው እንጂ የአእምሮ መጨንቀር ነገርማ...አንድዬ የሚሆነውን ነገር ሁሉ እያየህ! የሚባለውን ነገር እየሰማህ! እና አንድዬ፣ እውነት ማለቂያ የሌለው ይህ ሁሉ ጉዳችን በትክክል ከሚያስብ ከጤነኛ አእምሮ የሚመጣ ነው!
አንድዬ፡- ቆየኛ ምስኪኑ ሀበሻ...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ...ደፍሬ ላቋርጥህና እንዴት አሰላኸው አትበለኝ እንጂ፣ ከየአስራችን ሰባታችን፣ አአምሯችን የጨነቀረ ይመስለኛል፡፡
አንድዬ፡- አንተም አበዛኸው፣ በጣም አበዛኸው ምስኪኑ ሀበሻ፡፡ ብቻ እኔ ምን አገባኝ...ነገራችሁ ሁሉ ወይ ወዳጅ፣ ወይ ጠላት አይነት ጥቁርና ነጭ ነገር ስለሆነ፣ ለጨዋታ ብዬ ተናገሬ፣ እኔ እጄ በሌለበት ነገር ጠላት አላበዛም፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ አላበዛሁትም፡፡ እንደውም አሳንሼ ነው አንድዬ! ይህ ሁሉ ነገር በግራ በቀኝ፣ በላይ በታች ወጥሮ ትንፋሽ አሳጥቶን፣ መፈናፈኛ አሳጥቶን፣ እርጋታ አሳጥቶን፣ ሰላም አሳጥቶን፣ የእኛ አእምሮ ያለጨነቀረ የማን ይጨነቅራል! አንድዬ...ሁላችንም እኮ ሁለት አይነት ህይወት ነው ያለን፡፡
አንድዬ፡- ማለት ምስኪኑ ሀበሻ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ማለትማ አንድዬ የጓዳናና የአደባባይ ህይወት ነው ያለን፡፡
አንድዬ፡- ጓዳስ አደባባይስ ያው እናንተው አይደላችሁ እንዴ! ምን የሚጨመር፣ ምን የሚቀነስ ኖሮ ነው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን መሰለህ አንድዬ፣ በአደባባይ አሁን እኔን እንደምታየኝ፣ ተብለጭልጨን አምሮብን፣ ከዓይን ያውጣችሁ የምንባል ነን፡፡
አንድዬ፡- የጓዳውስ...?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- የጓዳውማ አንድዬ፣ የጓዳውማ ሆድ ይፍጀው ነው፡፡
አንድዬ፡- ሁሌም ሲከነክነኝ የኖረና የሚኖር፣ ሁሌ ሲገርመኝ የኖረና የሚኖር ነገር ነው ያነሳህልኝ፣ ምስኪኑ ሀበሻ፡፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን አንድዬ?
አንድዬ፡- ሆድ ይፈጀው ያልከው ነገር፡፡ እንዲህ ስትሉ ለራሴ ምን እንደምል ታውቃለህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን ትላለህ አንድዬ?
አንድዬ፡- እንደው እነኝህ ሰዎች ዘላለማቸውን ሆዳቸው ሁሉንም ነገር ፈጅቶ ፈጅቶ አለመክሰሉ እላለሁ፡፡ አጠፋሁ እንዴ ምስኪኑ ሀበሻ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- በጭራሽ አንድዬ!
አንድዬ፡- እሺ፣ ለመሰናበቻ አንድ ነገር ልጠይቅህ ምስኪኑ ሀበሻ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ጠይቀኝ አንድዬ፡
አንድዬ፡- ሆዳችሁን የነገር ፉርኖ ቤት ማድረግ የምታበቁት መቼ ነው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሱማ አንድዬ፣ እሱማ...
አንድዬ፡- ግዴለም ምስኪኑ ሀበሻ፤ ግዴለም፡፡ ሌላ ጊዜ ስትመጣ ትመልስልኛለህ፡፡ በሰላም ግባ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ! አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1079 times