Saturday, 03 June 2023 19:54

በቡዳፔስት 2023

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 * ሐንጋሪ ለዝግጅቱ እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር አውጥታለች
       * ከ180ሺ በላይ ትኬቶች ተሸጠዋል። ከ2500 በላይ አትሌቶች ይሳተፋሉ።
            
       በሐንጋሪ መዲና ቡዳፔስት  ከ77 ቀናት በኋላ 19ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ይጀመራል። ሻምፒዮናው በምስራቅ አውሮፓ ሲካሄድ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።  የዓለም አትሌቲክስ ማህበር እንዳስታወቀው ሻምፒዮናው በስታድየም ተመልካቾች ብዛት ክብረወሰን ሊመዘገብበት  ይችላል። ከ180ሺ በላይ ትኬቶች መሸጣቸው እየተገለፀ ሲሆን ዋጋቸው ከ8 እስከ 27 ዶላር መሆኑ ታውቋል።
ከ203 አገራት የተውጣጡ ከ2500 በላይ አትሌቶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል ።  ከ8,000 በላይ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች፤ ባለድርሻ አካላት፤ ሚዲያዎችና ሌሎች እንግዶች በሐንጋሪ መንግስትና አዘጋጅ ኮሚቴው ግብዣ ተደርጎላቸዋል። የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከኦሎምፒክና ከዓለም ዋንጫ ቀጥሎ የሚታወቅ ግዙፍ የስፖርት መድረክ ነው። ቡዳፔስት ይህን ሻምፒዮና ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ በማስተናገድ በአውሮፓ አህጉር የአትሌቲክስ መናሐርያነት ለመጠቀስ ትበቃለች።
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ከዓለማችን ታላላቅ የስፖርት መድረኮች አንዱ መሆኑ ይታወቃል ። ባለፈው በአሜሪካ ኦሬጎን ግዛት ዮጂን ላይ የተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመላው ዓለም በቲቪ ስርጭት ለ1.12 ቢሊዮን ሰዓታት ዕይታ ያገኘ ነው። ኔልሰን በሰራው ሪፖርት መሠረት ሻምፒዮናውን ዮጂን ከተማ በመገኘት 150ሺ ስፖርት አፍቃሪዎች ተከታትለዋል። በቲቪ ስርጭቱ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ተመልካች እንደነበረው ተረጋግጧል። የአሜሪካዋ ዮጂን ከተማ በሻምፒዮናው ከ153 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማንቀሳቀሷን የጠቀሰው ጥናታዊ ዘገባው ከማስታወቂያ ከ19 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሠብሰቡን አመልክቷል። በአጠቃላይ የኦሬጎን ግዛት በቲቪ ስርጭት ብቻ ከ59 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቱም ተገልጿል። የዓለም ሻምፒዮናው በአፍሪካ ከፍተኛ ተመልካች ማግኘቱን የጠቀሰው ደግሞ የስፖርት ኤክዛማይነር ሐተታ ነው።  በአህጉሪቱ ሻምፒዮናው መዘጋጀቱን እንደሚያዋጣ የገለፀው የዓለም ሻምፒዮናው ከፍተኛ የቴሌቭዥን ተመልካቾች ቁጥር ተሠዝግቧል በሚል ነው። የዓለም ሻምፒዮናው ከቡዳፔስት በኋላ በ2025 እኤአ የምታዘጋጀው የጃፓኗ ቶኪዮ ናት። የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በ2027 እኤአ ላይ የሚያዘጋጀውን አገር በቡዳፔስቱ መስተንግዶ ዋዜማ ላይ የሚገልፅ ይሆናል።  ኬንያ በ2029 “እኤአ ላይ 22ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለማዘጋጀት  ማቀዷ ተወስቷል። የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በየሁለት ዓመቱ ሲካሄድ እስከ 3 ቢሊዮን ተከታታይ በዓለም ዙርያ የሚያገኝ ሲሆን ውድድሮችን የሚመለከቱ 1 ቢሊዮን ይሆናሉ።
ሃንጋሪ በቡዳፔስት ከተማ 19ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለማዘጋጀት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ ማድረጓን ሃንጋሪቱዴይ ዘግቦታል። በቡዳፔስት እምብርት ላይ የሚገኘውና 35 ሺ ተመልካች የሚያስተናግደው ዘመናዊው ብሔራዊ የስፖርት ማዕከል  ባለ9 መም ትራክ ተነጥፎበታል።  በአውሮፓ አትሌቲክስ የሪኮርድ ቀይ ምንጣፍ የተባለው ሞንዶ ትራክ ተነጥፎበታል። የስታዲየሙ አሰራር የትራክ ላይ ሩጫዎችንና የሜዳ ላይ ስፖርቶችን በአንድ ላይ  ለመመልከት ምቹ መደረጉም ተገልጿል።  ከ500 በላይ ጋዜጠኞችን የሚያስተናግድ የሚዲያ ትሪቡን መያዙም ታውቋል። እንደ ሐንጋሪ ቱዴይ ገለፃ በዓለም ሻምፒዮናው የሚሳተፋ ዓለምአቀፍ የፕሬስ ሚዲያዎችን በተሟላ የስፖርት ልማት ለማስተናገድ የቡዳፔስት አዘጋጅ ኮሚቴ ሰርቷል። ከ120 በላይ ጋዜጠኞችን የሚይዝ የጋዜጣዊ መግለጫ አዳራሽ የተገነባ ሲሆን የሚዲያ ማዕከሉ እስከ 400 የሚዲያ ባለሙያዎችን ያስተናግዳል።
ለዓለም ሻምፒዮናው  የሚደረገው ዝግጅት በየአገራቱ እንደቀጠለ ነው። በአትሌቲክስ የሚታወቁት አሜሪካና ኬንያ የአትሌቲክስ ቡድናቸውን በአገር አቀፍ ሻምፒዮናዎች ላይ ይወስናሉ።  ከ2 ሳምንት በፊት ብሔራዊ ሻምፒዮና ያካሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በረጅም ርቀትና በማራቶን በሚመርጣቸው አትሌቶች ላይ እየሰራ ይገኛል። በማራቶን የሚኒማ ማስመዝገበያው ጊዜ ባለፈው ሰሞን ያበቃ ሲሆን በመካከለኛ ርቀት፤ በ5ሺ ሜትርና በ10ሺ ሜትር ውድድሮች ሚኒማ ለማሟላት እስከ ሐምሌ አጋማሽ ጊዜ ተሰጥቷል። በዓለም አትሌቲክስ ለዓለም ሻምፒዮናው በወጣው ሚኒማ መሠረት   በማራቶን በወንዶች 2 ሰዓት ከ09 ደቂቃ በሴቶች 2 ሰዓት ከ28 ደቂቃ ማሟላት ይጠበቃል። በ5ሺ ሜትር በወንዶች 13.07 ደቂቃዎች በሴቶች 14.57 ደቂቃዎች እንዲሁም በ10ሺ ሜትር በወንዶች 27 ደቂቃዎች በሴቶች 30.4 ደቂቃዎች እንደ ሚኒማ ተቀምጧል። የኢትዮጵያን ቡድን በዓለም ሻምፒዮናው የተሳካ ተሳትፎ እንዲኖረው በመካከለኛና በረጅም ርቀት ውድድሮች እንዲሁም በማራቶን አትሌቶችን በጥንቃቄ መመልመል ያስፈልጋል። ፌዴሬሽኑ ብቁ አትሌቶችን ለማሰለፍ ከቴክኒክ ኮሚቴው፤ ከአትሌቶች ፤ ከአሰልጣኞች ፤ ከማናጀሮች፤ ከህክምና ሌሎች ባለሙያዎች ጋር ተቀናጅቶ መሥራት አለበት። በማራቶን በኩል  በትልልቅ ማራቶኖች ያሸነፋ ፤ በዓለም አቀፍ የፈጣን ሰዓት ደረጃ ላይ የሚገኙና በወቅታዊ ብቃታቸው ተሽለው የሚገኙትን ይዞ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት መሥራት ይጠይቃል። በውደድር ዘመኑ ላይ በማራቶን ምርጥ ብቃት ላይ ያሉና የዓለም ሻምፒዮና ሚኒማ የሚያሟሉ የማራቶን አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች ከ10 በላይ ናቸው። በረጅም ርቀት ደግሞ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይ ተሳትፈው የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ፤  በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ደረጃና ሰዓት የዓመቱን ጠንካራ ውጤት የያዙ፤ በዳይመንድ ሊግና በዓለም አትሌቲክስ የዙር ውድድሮች ላይ በመሣተፍ ሚኒማውን ካሟሉ በርካታ አትሌቶች መካከል ምርጡን ቡድን ለመለየት መንቀሳቀስ ተገቢ ነው። አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ከዚህ ቀደም በሆላንድ ሄንግሎ ብዙ ወጭ አድርጎ በ10ሺ ሜትር የሚያካሂደውን የዓለም ሻምፒዮና ማጣርያ ዘንድሮ በሐዋሳ ለማድረግ ማቀዱ ቢገለፅም እርግጠኛ መሆን አልተቻለም። አሰልጣኞች ፤አትሌቶችና ማናጀሮች  ውድድር በአውሮፓ ምናልባትም በስዊድን እንዲሆን ጠይቀዋል። የሐወሣ ስታድየም ትራክ አመቺ ቢሆንም የአየር ሁኔታው በረጅም ርቀት  የሚፈለገውን ሚኒማ ለማሳካት ፈታኝ እንደሚሆን እየተገለፀም ነው። በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ በኩል ቢያንስ በአንድ  ወር ውስጥ ሙሉ ቡድኑን በማወቅ ወደ መጨረሻው የዝግጅት ምዕራፍ መግባት ይኖርበታል ። በኬንያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለአትሌቲክስ ቡድናቸው ምርጫ የሰጡትን ትኩረት መጥቀስ ይቻላል። ኬንያ አትሌቲክስን የሚመሩት ለዓለም ሻምፒዮናው እጪ ያደረጓቸውን አትሌቶች ከመጋቢት ወር ጀምሮ እየተከታተሉ ናቸው። ለዓለም ሻምፒዮናው ቡድን ለመብቃት ሚኒማ ማማሟላት፤ በጠንካራ የልምምድ መርሀ ግብር መቆየትና በዶፒንግ ምርመራና የክትትል ሂደት ውስጥ መግባት ወሳኝ መሥፈርት መሆኑን አሳስበዋል። የዓለም ሻምፒዮናውን ለመሳተፍ እጩ የሆኑ አትሌቶች ከሻምፒዮናው በፊት ሶስት በሻምፒዮናው ወቅት አንዴ የዶፒንግ ምርመራ ማድረግ አለባቸው።
ባለፈው ሻምፒዮና ላይ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኙ አራት አትሌቶች ወደ ቡዳፔስት በሚሄደው የኢትዮጵያ ቡድን በቀጥታ መግባት ይችላሉ። በሴቶች 10 ሺህ ሜትር ለተሰንበት ግደይ ፣ በወንዶች ማራቶን ታምራት ቶላ ፤ በሴቶች ማራቶን ጎይተቶም ገብረስላሴና በሴቶች 5ሺ ሜትር  ጉዳፍ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማስገኘታቸው ይታወቃል፡፡ የሻምፒዮንነት ክብራቸውን ለማስጠበቅ በቀጥታ የመሰለፍ እድል አላቸው። በዮጂን ኦሪገን ተካሂዶ በነበረው  18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ  ኢትዮጵያ አራት ወርቅ፣ አራት ብርና ሁለት የነሐስ  ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከአሜሪካ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ መጨረሷ ይታወሳል።
Read 605 times