ምርጫ ቦርድ ሀዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ (ህውሃት) በሚል ስያሜ አዲስ ክልላዊ ፓርቲ ለማቋቋም የቀረበውን የቅድመ እውቅና ፍቃድ ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ፣ ጥያቄ አቅራቢዎቹ የምርጫ ቦርድን ውሳኔ በመቃወም ፣ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በማቅረብ ክስ እንደሚመሰርቱ አስታውቀዋል።
ቀደም ሲል “ፈንቅል” በሚል ስም የተቋቋመውንና ሕውሐትን በመቃወም የወጣቶች እንቅስቃሴን በማድረግ ላይ የነበረው ፓርቲ መሪዎች በህውሃት ስም አዲስ ክልላዊ ፓርቲ ለማቋቋም ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቅርበው ነበር።
ህዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ (ህውሃት) በሚል መጠሪያ ክልላዊ ፓርቲ ለመመስረት ግንቦት 21 ቀን 2015 የቅድመ እውቅና ጥያቄ እንደቀረበለት ቦርዱ ይፋ ባደረገው ደብዳቤ ገልፆ፤ በህውሃት ስም አዲስ ፓርቲ ቢቋቋም መራጮችን የሚያደናግር በመሆኑ የቀረበልኝን የቅድመ እውቅና ጥያቄ አልቀበለውም ብሏል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ህዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ (ህውሃት) በሚል መጠሪያ የአዲስ ፓርቲ መቋቋምን የማይቀበለው ቀደም ሲል መሰረቱን ትግራይ ክልል አድርጎ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሲንቀሳቀስ የነበረና በቦርዱ ህጋዊ ሰውነቱ እንዲሰረዝ የተደረገ ፓርቲ በመሆኑ በመራጮች ዘንድ ግርታን ሊፈጥር የሚችል በመሆኑ ጥያቄውን እንደማይቀበል አስታውቋል። ይህንኑ ቦርዱን ውሳኔ በመቃወም “ታሪካዊውን የህውሃት ፓርቲ ለመውረስና ፓርቲው የትግራይ ህዝብ ታሪክ ስለሆነ ወደ ህዝቡ ለመመለስ ስለምንፈልግ ጥያቄያችን አናቆምም” ያሉት የአዲስ ፓርቲ ቅድመ እውቅና ጥያቄ አቅራቢዎቹ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ የማይሰጠን ከሆነ በምርጫ ቦርድ ላይ ክስ እናቀርባለን ብለዋል።
ህውሃት ቀደም ሲል ሚያዚያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ፤ በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ህውሃት ፓርቲ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን ጠቁሞ፤ ቦርዱ ከዚህ ቀደም በፓርቲው ላይ የጣለውን የህጋዊ ሰውነት ስረዛ ውሳኔ እንዲያነሳለት ጠይቆ ነበር። ቦርዱ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ ጥያቄውን አለመቀበሉን በመግለጽ፣ የተሰረዘውን የፓርቲውን ህጋዊ ህልውና እንደማይመልስ አስታወቆ የነበረ ሲሆን የህውሃቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል፤ ይህንኑ የቦርዱን ውሳኔ እደማይቀበሉት ማሳወቃቸው ይታወሳል።
Published in
ዜና