በአዲስ አበባ የመንገድ ላይ ፍተሻዎች፣ እስሮች፣ ማዋከቦችና እንግልቶች እየተፈጸሙ ናቸው- ኢሰመጉ
በአዲስ አበባ የፀጥታ ኃይሎች የሕግ አግባብ በሌለው መልኩ የመንገድ ላይ ፍተሻዎች እስሮች፣ ማዋከቦችና እንግልቶችን በዜጎች ላይ እየፈጸሙ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) አስታወቀ።
ኢሰመጉ ሰኔ 7 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፤ እነዚህ እስሮችና እንግልቶች በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉት የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል፣ በአዲስ አበባ ተከታታይ የተቀናጀ ኦፕሬሽን እንደሚያደርግ ማስታወቁን ተከትሎ እንደሆነ አመልክቷል፡፡
የኢሰመጉ መግለጫ ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ቀርቧል፡፡
መግቢያ
በአዲስ አበባ ከተማ በተደጋጋሚ የከተማዋን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚል መንግስት ከአዲስ አበባና ከፌደራል ፖሊስ የተዋቀረ ግብረ ሃይል በማቋቋም፣ ደኅንነት የማስከበር ስራዎችን እንደሚሰራ ይታወቃል። እነዚህ ሰላምና ደኅንነትን ለማስከበር ተብለው በመንግስት የሚሰሩ ስራዎችና የሚከተሏቸው ስነ-ዘዴዎች አንዳንድ ጊዜ የህግ ስነ-ስርዓትን ያልተከተሉና የሰዎች ሰብዓዊ መብቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚጥሉ ሆነው ይገኛሉ።
አምስት አካላትን የያዘው የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል፣ የተለያዩ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍጠር የተዘጋጁ ኃይሎች እንዳሉ በመግለጽ፣ በአዲስ አበባ ውስጥ ተከታታይ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ሊካሄድ መሆኑን ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ የሚታወስ ነው። ሰላምና ጸጥታን ለማስከበር ትኩረት ተሰጥቶት መሰራቱ አግባብ ቢሆንም የእዚህን አይነት ይዘት ያላቸው ለህግ አስፈጻሚው አካል ከፍ ያለ ስልጣን የሚሰጡ እርምጃዎች በህግ ከተደነገገው ውጪ በሚፈጸሙበት ወቅት በሂደቱ የሚሳተፉ አካላት የህግ ስነ-ስርዓትን ያልተከተሉ ድርጊቶችን ለመቆጣጠርና ሰዎች ህጋዊ፣ አስፈላጊና ተመጣጣኝ ባልሆነ መልኩ ሰብዓዊ መብቶቻቸው እንዲገደቡባቸው ሲያደርጉ የሚስተዋል በመሆኑ ሰላምና ጸጥታን የማስከበር ሂደቱ ላይ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ህግና ስርዓትን የተከተለ አሰራር እንዲኖር ያስፈልጋል።
ይህን ኦፕሬሽን ተከትሎ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ላይ በጸጥታ አካላት የህግን ስነ-ስርዓት ያልተከተሉ የመንገድ ላይ ፍተሻዎች፣ እስሮች፣ ማዋከቦችና እንግልቶች በሰዎች ላይ እየተፈጸሙ መሆኑን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ ይህ የጋራ ግብረ ሃይል መደበኛውን የህግ ሥነስርዓት በመከተል ሊንቀሳቀስ የሚገባው ቢሆንም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ከመደበኛው የህግ ስነ-ስርዓት ከፍ ያለ ስልጣን እንዳለው በማሰብ ስልጣንን አላግባብ የመጠቀም ሁኔታዎች ተስተውለዋል።
ተያያዥ የህግ ግዴታዎች
የህዝቦችን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ የአንድ መንግስት ተቀዳሚ ኃላፊነት መሆኑን ከሰብዓዊ መብቶች አንጻር የመንግስት ኃላፊነት ተብለው ከተቀመጡት ሰብአዊ መብቶችን የማክበር፣ የማስከበርና የማሟላት ኃላፊነቶች መገንዘብ ይቻላል። ነገር ግን የህዝቦች ሰላምና ደኅንነትን መንግስት በሚያስጠብቅበት ወቅት ሊከተላቸው የሚገቡ በህግ የተቀመጡ ሥነ-ስርዓቶች ሊኖሩ ይገባል። ይህም ማለት ለምሳሌ በተለመደው የህግ የማስከበር ስርዓት ለመቋቋም የማይቻሉ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲፈጠር ለህግ አስፈፃሚው አካል ሰፋ ያለ ስልጣን በመስጠት ለመቆጣጠር ይሞከራል፡፡ ይህ ሲሆን ግን ህግ አስፈፃሚው አካል ስልጣኑን ለጥጦ በመጠቀም የሰዎችን ሰብአዊ መብቶች እንዳይጥስና አላግባብ እንዳይገድብ መቆጣጠሪያና ተጠያቂ ማድረጊያ መንገድ ሊኖረው ይገባል፡፡ የህጋዊነት፣ የተመጣጣኝነት፣ የአስፈላጊነት፣ አድሎ አለማድረግ፣ ግልፀኝነት፣ የተጠያቂነትና ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች መርሆዎች ሊከበሩ ይገባል፡፡
ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን ከላይ የተጠቀሰው አይነት በመንግስት እየተተገበረ ያለ የተቀናጀ ኦፕሬሽን፣ የተለያዩ ሰብአዊ መብቶች ላይ ማለትም እንደ የመዘዋወር መብት፣ የነፃነት መብት፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት፣ የመሰብሰብ መብት፣ የግል ህይወት የመከበር መብቶችና ሌሎችም ሰብአዊ መብቶች አላግባብ ሊገደቡና አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ፡፡
የኢሰመጉ ጥሪ
የፀጥታና ደህንነት የጋር ግብረኃይል በአዲስ አበባ ውስጥ እያካሄደ ያለው ተከታታይና የተቀናጀ ኦፕሬሽን የታሰበለትን ሰላምና ደህንነት ማስከበር እንዲችል የህግ ስነ-ስርዓትን የተከተለ እንዲሆን፣
የፀጥታ አካላት ይህን ኦፕሬሽን በሚፈፅሙበት ወቅት የሰዎችን ሰብአዊ መብቶች አላግባብ እንዳይገድቡና እንዳይጥሱ ተገቢውን የህግ ስነ ስርዓት እንዲከተሉና ያልተመጣጠነና አላስፈላጊ የሆኑ ኃይሎችን ከመጠቀም እንዲቆጠቡ፣
የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረኃይል በሚያካሄደው ኦፕሬሽን ስልጣናቸውን አላግባብ የሚጠቀሙ በሂደቱ የሚሳተፉ አካላትን የሚቆጣጠርበትና በህግ ተጠያቂ የሚያደርግበትን ሥርዓት እንዲዘረጋ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
Saturday, 17 June 2023 00:00
”ሰላምና ደህንነትን የማስጠበቅ እንቅስቃሴዎች ሰብአዊ መብቶችን እንዳይጥሱ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል”
Written by Administrator
Published in
ዜና