የመጀመሪያው ነው የተባለውና ባለፈው ረቡዕ በስካይላይት ሆቴል የተከፈተው ሃገር አቀፍ የነጋዴ ሴቶች ኤክስፖ፤ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የተካሄደ ሲሆን በትላንትናው ዕለት ተጠናቅቋል፡፡
ኤክስፖውን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በይፋ በከፈቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ በአምራች ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የነጋዴ ሴቶች ኤክስፖን ለማዘጋጀት ብዙ ውጣ ውረድ ማሳለፏንና የዕድሜዋን ሁለት ዓመት ከጥቂት ወራት እንደፈጀባት የገለጸችው የማሌሳ ኤቨንትስ መሥራች ወ/ሮ ሰላማዊት ደጀኔ፤ ኤክስፖው በጋራ ለመስፈንጠር መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን እናምናለን ብላለች፡፡
ለሦስት ቀናት በተካሄደው በዚህ የነጋዴ ሴቶች ኤክስፖ፤ከመቶ በላይ አምራችና ሴት ነጋዴዎች እንዲሁም ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ምርታቸውንና አገልግሎታቸውን በመሸጥና በማስተዋወቅ የተሳተፉ ሲሆን ከ35 ሺህ በላይ ሰዎችም እንደጎበኙት ተገምቷል፡፡
በዚህ ኤክስፖ ላይ ምርትና አገልግሎትን ከመሸጥና ከማስተዋወቅ ባሻገር የፓናል ውይይቶች እንደተከናወኑ፣ የተለያዩ ሥልጠናዎች እንደተሰጡና የልምድና ተሞክሮ ልውውጥ እንደተደረገ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኤክስፖውን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከማሌሳ ኤቨንትስ ጋር በመተባበር ማዘጋጀታቸው ታውቋል፡፡
Published in
ንግድና ኢኮኖሚ