Saturday, 17 June 2023 00:00

ለየቅል አደርን

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 (በድሉ ዋቅጅራ)


 (በድሉ ዋቅጅራ)
ወንድምን ከወንድሙ ቢለዩት፣
አልቦ ስጋ - ደም፣ ነፍስም አልቦ፤
ጮጮ ላይሞላ፣ ታልቦ ታልቦ፤
ልምሻ ሊጥለው፣ አቅም ሰልቦ፡፡
ወልነት ያጣው፣ የኛም ቃል፤
ሲዘረጋ ይጠቀለላል፤
ሲያወፍሩት፣ ደርዙ ይሰላል፡፡
የሰው ልጅ ንፉግ ህይወቱን፣
ለነገ ቸርነት ሲያጨው፤
ያልተጨበጠ ድንግዝ ምኞቱን፣
በዛሬ ብርሀን እያየው፤
ተስፋ አለና ሰየመው፡፡
ችግሩ ከተስፋችን ስር፣
 ያቆጠቆጠው ቁልቋል፤
ደምቶ አዳምቶን ደርቋል፤
ለነገ ያልነውም ጥሪት፣
 ሻሞ ብለነው አልቋል፡፡
እንዴት ነው?
የነገ ድርሳን፣ በዛሬ ብርሀን ተነቦ፤
‹‹የብር ጥልፍ፣ ወርቀዘቦ››፤
ተብሎ ሚወደሰው?!
እንዴት ነው?
የተማመንበት እርሻ እንኳ፣
በተስፋ ዘር የሞላነው፤
አሸተ እንጂ፣ መች አጨድነው?
ቆጥ ሳናቆም ወንጭፍ ይዘን፣
ለወፍ አይደል የዳረግነው?
እና ይኸውልን . . .
አክታን - ከስስት እንትፍታ፤
ምኞታችን እያማታ፤
መሻታችንን - ከተስፋ፤
ስስታችን እያጋፋ፤
የጨበጥነው መቅኖ አጣ፣
ያኘክነውን አልዋጥነው፤
የዋጥነውም እድሜ አልሆነን፣
 ለየቅል አቀርሽተነው፡፡
ያንተን ባላውቅም ወንድሜ፣ . . . . .
ጭንቅ ሲለኝ አንዳንዴ፤
ሲዘቅዘኝ የሀሳብ ውርዴ፤
ሌላ መደለል ያምረኛል፡፡
ብቻ ምናኔ ያሰኘኛል፡፡
ይኸውልን . . .
እንደአራስ ጥብቆ፣
የትናንት ሀሳባችን፣
ለዛሬያችን እያጠረው፤
ምኞታችን መልህቅ አጣ፣
 ከማእበል የሚያስጥለው፡፡
ተስፋችን ቅዠት ከለለው፡፡
በኔ ይሁንብህ! ግድ የለም!
 . . . . . . . . . . የዛሬን እንተወው ጓዴ፤
በዛሬ ምሬት፣ ጣእማችንን?
በዛሬ ቅዠት፣ ህልማችንን?
. . . . . . . . . . . ምን ብለህ?
እንዴት አድርጌ?
እኔን ግን የሚቆጨኝ፣. . . .
እንደጥንት መርከበኛ፣
 የጊዜ መስፈሪያ አሸዋ፤
አለ ስንለው ተንሸራቶ፣
ፍቅራችን እንደተሰዋ፤
ልብህ እያወቀ፣ ሹክ ሳትለኝ፣
ልቤ እያወቀ፣ ሳላጫውትህ፤
እኔም ከአድባር መገለሌ፣
አንተም ከእድሬ መውጣትህ፡፡
አይቆጭህም?!
------------
(“የተስፋ ክትባት!”)



Read 1182 times