Monday, 03 July 2023 08:55

ደቡብ ኮሪያውያን በአንድ ሌሊት ወጣት ሆነው አደሩ!

Written by 
Rate this item
(10 votes)

በሰው ልጆች ታሪክ ሆኖ አያውቅም፡፡ ወደፊትም ሊሆን አይችልም፡፡ በደቡብ ኮሪያ ግን በትክክል ሆኗል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ከ50 ሚሊዬን የሚልቁ ደቡብ ኮሪያውያን ከእንቅልፋቸው የነቁት በአንድ ወይም በሁለት ዓመት ወጣት ሆነው ነው ተብሏል፡፡ ዕድሜያቸው ጨምሮ ሳይሆን ቀንሶ ነው ራሳቸውን ያገኙት፡፡ እንዴት ቢሉ? የአገሪቱ መንግሥት በዕለቱ ዓለማቀፍ የእድሜ አቆጣጠር ሥርዓትን ተግባራዊ በማድረጉ! የደቡብ ኮሪያ ባህላዊ የእድሜ አቆጣጠር ልምድ፤ እያንዳንዱ ህፃን ሲወለድ አንድ ዓመት   እንደሞላው አድርጎ የሚቆጥር ሲሆን ጃንዋሪ 1 በመጣ ቁጥር በእድሜው ላይ አንድ አመት ይጨምርበታል፡፡ ይኼ ማለት ምን ማለት መሰላችሁ? ዲሴምበር 31 የተወለደ ህፃን በቀጣዩ ቀን-ማለትም-ጃንዋሪ 1 ሁለት ዓመት ይሆነዋል፡፡ በተወለዱበት ወርና ቀን ዕድሜን ማስላት ወይም ልደትን ማክበር በደቡብ ኮሪያውያን ዘንድ እምብዛም የተለመደ አይደለም፡፡ ደቡብ ኮሪያ ባለፈው ታህሳስ ወር፣ ባህላዊውን የእድሜ አቆጣጠር ልማድ በዓለማቀፍ ሥርዓት ለመተካት የሚያስችላትን ህግ በፓርላማ ማፅደቋ ይታወቃል፡፡
ይኼን ተከትሎ፣ ባለፈው ረቡዕ፣ በመላ አገሪቱ መተግበር ጀምሯል - አዲሱ ህግ፡፡ ለዚህም ነው “ደቡብ ኮሪያውያን በአንድ ጀንበር በአንድና ሁለት ዓመት ወጣት ሆነው ከእንቅልፋቸው ነቁ” የሚለው መረጃ በስፋት የተሰራጨው፡፡ በእርግጥም የደቡብ ኮሪያውያን ባህላዊ የዕድሜ-አቆጣጠር ዘዴ፣ ሰዎችን በአንድ ወይም በሁለት ዓመት የሚያስረጅ ነው-ያለ ዕድሜያቸው ዕድሜ የሚሰጥ፡፡
 በአዲሱ ህግ ደቡብ ኮሪያውያን የተፈጥሮን ህግ ጥሰው ወደ ልጅነታቸው ወይም ወጣትነታቸው ተመልሰዋል ማለት ይቻላል- በአንድ ወይም በሁለት ዓመት! እርጅናን እንጂ ወጣትነትን ማን ይጠላል? ደግሞም ያለአግባብ በህይወታቸው ላይ የተጫነባቸው እድሜ ነው የተነሳላቸው - ምስጋና ለዓለማቀፉ የእድሜ አቆጣጠር ሥርዓት ይግባውና፡፡
በነገራችን ላይ ደቡብ ኮሪያውያን ህፃን ልጅ ገና ሲወለድ አንድ ዓመቱ ነው የሚሉት ህይወቱ የሚጀምረው በእናቱ ማህፀን ውስጥ ነው ከሚል መነሻ ነው ይባላል፡፡ ጃንዋሪ 1 በመጣ ቁጥር ለሁሉም ያለ አድልዎ የሚታደለው የአንድ ዓመት እድሜ ጭማሪ ግን ተገቢ አይመስልም፡፡ የአንድ ዓመትና የሁለት ዓመት የእድሜ ልዩነት የፈጠረውም ይኼው ልማድ ነው፡፡
“ዕድሜን በማስላት ረገድ ሲፈጠሩ የቆዩ የህግ ሙግቶች፣ ቅሬታዎችና ማህበራዊ ብዥታዎች በእጅጉ እንደሚቀንሱ እንጠብቃለን” ብለዋል፤ የመንግስት ህግ አውጭ ሚኒስትር ሊ ዋን-ኪዩ ባለፈው ሰኞ  ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፡፡
በመስከረም 2022 ዓ.ም በተካሄደ የመንግስት ጥናት መሰረት፤ 86 በመቶ የሚሆኑት ደቡብ ኮሪያውያን፣ አዲሱ ህግ ተግባራዊ ሲደረግ፣ በእለት ተእለት ህይወታቸው ዓለማቀፉን እድሜ እንደሚጠቀሙ ነው የተናገሩት፡፡
“በባህላዊው የኮሪያ የእድሜ አቆጣጠር፣ በቀጣዩ ዓመት 30 ዓመት ይሆነኝ ነበር፤ በአዲሱ የእድሜ አቆጣጠር ስርዓት ግን በሁለት ዓመት ወጣት ሆኛለሁ” ብላለች፤ በሶል የቢሮ ሰራተኛ የሆነችው የ27 ዓመቷ ኢይ ሃዩን-ጂ፡፡ “ወጣት የመሆን ስሜት በጣም ድንቅ ነው፡፡ ከ30 ዓመት ዕድሜ በትንሹ የመራቅ ስሜት ተሰምቶኛል” ስትልም ኢይ አክላለች፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዩን ሱክ ዬኦል፣ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት፣ ዓለማቀፍ እድሜን መደበኛ ማድረግ የመንግስታቸው ቁልፍ ግብ አድርገው ነበር የገለፁት-“ማህበራዊና አስተዳደራዊ ውዥንብርን” እንዲሁም የህግ ሙግቶችን የመቀነስ አስፈላጊነትን በመጥቀስ፡፡ የመንግስት ህግ አውጭ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ግን አዲሱ ህግ የአገሪቱ የመንግስት አገልግሎት አሰራርን ትርጉም ባለው መልኩ እንደማይለውጠው ነው የገለፁት፤ አብዛኞቹ በዓለማቀፍ ዕድሜ ላይ የተመሰረቱ ናቸውና፡፡ የ49 ዓመቷ የመዲናዋ ሶል ነዋሪ፣ ኢይ ኢዩን-ያንግ፣ አዲሱን ህግ በበጎነት ነው የተቀበለችው፡፡ ከዚህ በኋላም እድሜዋን በ50ዎቹ ውስጥ እያለች መግለፅ እንደማያስፈልጋት ተናግራለች፡፡ “ህጉ ተፈጥሮአዊ ወጣትነትን አያጎናፅፍህም፤ ከበፊቱ በአንድ ዓመት ወጣት መባል ከሚፈጥረው ጥሩ ስሜት ውጭ የምታገኘውም እውነተኛ ጥቅም የለም” ያለችው ኢዩን-ያንግ፤ “ነገር ግን ዓለማቀፋዊ ስታንዳርዱ ይኼ ከሆነ መከተሉ ምንም ክፋት የለውም” ብላለች፡፡ ሌላው የሶል ነዋሪ፣ ኦህ ሴዩንግ-ዮዩል ይሄንኑ ሃሳብ-ተጋርቷል፡፡“ወጣት መሆን ሁሌም ጥሩ ነው” ብሏል ኦህ፤ እየሳቀና ከ63 ዓመት ዕድሜ ወደ 61 ያመጣውን አዲሱን ህግ እያወደሰ፡፡
“ልደቴ ዲሴምበር 16 ነው፤ ታዲያ ተወልጄ ወር እንኳን ሳይሞላኝ የሁለት ዓመት ልጅ ሆንኩኝ” ያለው ኦህ፤ “ለዚህ ነው (ባህላዊው የእድሜ አቆጣጠር ዘዴ) ትርጉም የማይሰጠው” ብሏል፡፡በደቡብ ኮሪያ ለውትድርና አገልግሎት፣ ለት/ቤት መግቢያ እንዲሁም የአልኮል መጠጥና የሲጋራ ማጨሻ ህጋዊ ዕድሜን ለማስላት የሚያገለግል ሌላ ሥርዓት አለ፡- በዚህ ሥርዓት ሰው ሲወለድ ዕድሜው የሚጀምረው ከዜሮ ሲሆን፤ ጃንዋሪ1 በመጣ ቁጥር በእድሜው ላይ አንድ ዓመት ይጨመርበታል፡፡ (ይኸ የካላንደር ዕድሜ ተብሎ ይጠራል) የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት፣ ይህ አሰራር ለጊዜው በስራ ላይ ይቆያል ብለዋል፡፡
የእድሜ ነገር በደቡብ ኮሪያ
በደቡብ ኮሪያ ሦስት ዓይነት የዕድሜ አቆጣጠር ዘዴ ይታወቃል፡፡ የደቡብ ኮሪያውያን እድሜ፣ ዓለማቀፍ ዕድሜና የካላንደር ዕድሜ ይሉታል፡፡በደቡብ ኮሪያውያን ባህላዊ የዕድሜ አቆጣጠር ዘዴ፣ ህፃን ሲወለድ በእናቱ ሆድ ውስጥ ያሳለፈው ጊዜ ስለሚቆጠር ገና ይህችን ዓለም ሲቀላቀል አንድ ዓመት ሞልቶታል ተብሎ ይታሰባል፡፡ (ዜሮ ዓመት የሚባል እድሜ የለም)
የፈረንጆች አዲስ ዓመት ጃንዋሪ 1 በመጣ ቁጥር ሁሉም ደቡብ ኮሪያዊ (ከህፃን እስከ አዋቂ) በእድሜው ላይ አንድ ዓመት ይጨምራል- በየካቲትም ይወለድ በታህሳስ ለውጥ አያመጣም፡፡
ዲሴምበር 31 የተወለደ ህፃን፤ በነጋታው ጃንዋሪ 1 ሁለት ዓመት ይሆነዋል፡፡


Read 1850 times