Sunday, 09 July 2023 16:56

ፍም፣ እፍፍ ሲሉት ይነዳል እንትፍ ቢሉበትም ይጠፋል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 በጥንት ዘመን እድሜውን በሙሉ በመድከምና በመልፋት ሃብት ያፈራ ባለፀጋ ሁለት ልጆች ወልዶ በአንድ አገር ይኖር ነበር። ልጆቹም አንዱ ብርቱና ጎበዝ ሲሆን፣ ሌላው ግን ሰነፍና ደካማ ነበር።
ባለፀጋው ወደ ሽምግልና ዕድሜው ሲደርስ ልጆቹን አስጠራና መመካከር ያዙ።
“ልጆቼ እንደምታዩኝ እርጅና እየተጫጫነኝ ነው። እግዚአብሔር ይመስገንና ባገሪቱ ካሉት ከበርቴዎች አንዱ ብሆንም የኔ ሃብት የኔ ሆኖ የሚቆየው ልሰራበት የሚያስችል ዓቅምና ስልጣን ኖሮኝ ስገኝ ብቻ ነው። ያለበለዚያ ግን ሃብቴም ይባክናል፣ እናንተ ልጆቼም በማመስገን ፋንታ “ኤጭ ወዲያ” ብላችሁ ሞቴን ትመኙልኛላችሁ ሲል፡-
ልጆቹ አቋርጠውት በአንድነት “አባባ ምነው ያለወትሮህ እንዲህ ያለ አስፈሪ ነገር ትናገራለህ?” ብለው ጠየቁት።
“አደራ ልጥልባችሁ ነው” አለና ቀጠለ አባት። “እስከዛሬ ካፈራሁት ሃብት ግማሹን አኑሬ ግማሹን ለሁለታችሁ ላካፍላችሁ ወስኛለሁ”
ልጆቹም በየተራ “አባታችን ስለአሰብክልን እናመሰግንሃለን ከቃልህም አንወጣም” አሉና ጉልበቱን ሳሙ።
አባትየውም የሃብቱን ገሚስ ለሁለት ከፍሎ እኩል እንዲካፈሉ የፈረመበትን ሰነድ ሰጣቸውና፣ መርቆ ወደፈለጉበት አገር ሄዶ ሰርቶ ከመኖር ነፃነት ጋር አሰናበታቸው።
ከዚያን ቀን አንስቶ ሁለቱም ወደተለያየ ቦታ ተሰማርተው፣ ትዳር መሥርተው መኖር ጀመሩ። ልጆች ወልደው በተናጠል አባታቸውን እየጠየቁ እነሱ ግን ሳይጠያየቁ ዓመታት አለፉ።
ሁለቱ ልጆች በአንድ ሳምንት ውስጥ ተከታትለው ሞቱና አንዱን ቀን መርዶአቸው ለሽማግሌ አባት መጣለት። ሀዘኑን ባገር ወግ ተቀምጦ ሰነበተና መርዶ አምጪዎቹን ስለልጆቹ ያሟሟት ሁኔታ ጠየቀ። ብርቱው ልጁ በእህል ጥጋብና በቁንጣን፣ ደካማው ደግሞ በስንፍናና በችጋር መሞታቸው ተነገረው።
ሽማግሌውም ይኸንን የልጆቹን ባህርይ ቀድሞ ለምን እንዳላሰበበት ሲቆጭ ሰነበተና፤ “ሰነፉ ልጄ የሞተበት ብርቱው ልጄ የሞተበት ለሰነፉ ልጄ ´መድሐኒት´ ሊሆናቸው ሲገባ ወየው ልጆቼ ያለመጠያየቃችሁና ያለመተሳሰባችሁ ጎዳችሁ” በማለት አንብቦ አዘነ።
ቀጥሎም ስለ ልጅ ልጆቹ ጠባይና አመል ጠየቀ። የሰነፉ ልጅ በተቃራኒው ብርቱ መሆኑንና የብርቱው ልጅ እንዲሁ ሰነፍ መሆናቸው ተነገረው።
የእግዚአብሔር ተዓምር አያቅም እያለ ሲገረም ከቆየ በኋላ፣ ከአጠገቡ ሳይርቁ እንዲኖሩ አዝዞ እየሰራችሁ እደጉ በማለት የተራረፈውን ንብረት አካፈላቸው።
የልጅ ልጆቹም በየፊናቸው የየአባታቸው ሞት ጥልቅ ሀዘን እየተሰማቸው፤ አባቱን በጥጋብ የሞተበት የአባቱ አይነት ሞት እንዳይደርስበት እስኪጠግብ ከመብላት እራሱን አግዶ፤ በችጋር መኖር ስለጀመረ እየከሳና እየጠወለገ መስራትም እያቃተው ይሄድ ጀመር።
አባቱ በችጋር የሞተበት ደግሞ የአባቱ አይነት አሟሟት እንዳይገጥመው ያለመጠን እየበላ ያለቅጥ በመወፈሩ መስራት አቃተውና እቤት ዋለ።
አያታቸውም እንደዚህ የሆነበት ምክንያት ቢጠይቅ ሁለቱም አባታቸው የሞቱበት ምክንያት ለመከላከል በወሰዱት እርምጃ ነበር።
አያታቸው መጀመሪያ ለሰነፉ “የብርቱውን አባትህን ሞት ፈርተህ አካልህን ምግብ ብትከለክለው የሰነፉ አጎትህ ሞት ያጋጥምሃል፡፡” አለው። ቀጠለና ለብርቱው “የሰነፉን አባትህን ሞት ፈርተህ አካልህን ያለቅጥ ብትመግበው የብርቱው አጎትህ ሞት ያጋጥምሃል” ካለ በኋላ ለሁለቱም፤”ልጆቼ ጨርሰው ሲራቡም ጨርሰው ሲጠግቡም ሞት ይከተላል። ከአባታችሁ ሞት ተማራችሁ? የሚባለው በልክ ሰርታችሁ በልክ መመገብ ስትችሉ ብቻ ነው። መፍራት ያለባችሁ የራሳችሁን ተግባር እንጂ የአባቶቻችሁን ሞት አይደለም። መፍራት ያለባችሁ የአባቶቻችሁን ያለመጠያየቅና ያለመከባበር ነው። ማለት ያለባችሁ እኔ የአባቴንም የአጎቴንም ጥፋት አልደግመውም ነው” አላቸው ይባላል።
***
የኢትዮጵያ ህዝብ በቋንቋው ቢለያይም በመከራው ግን በደም፣ በባህል፣ በስነ-ልቦና፣ በታሪክ… ወዘተ አንዱ የአንዱ የሥጋ ዘመድ ነው። ወይ አጎት፣ ወይ አክስት፣ ወይ ዋርሳ፣ ወይ አያት፣ ወይ የአያት ልጅ ነው። ሲቀናቀን ቢኖር እውነታው ከዚህ አይዘልም። ንግግሩ ከሚዛን እንዳይዘናበልበት አባቴ ምን ደረሰበት? ብቻ ሳይሆን አጎቴስ? የማለት ባህርይ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ እዚህ አድርሶታል።
“ማሩን ለራስ መርዙን ለጎረቤት” እንዳንባል የራስን ብቻ ሳይሆን የአጎትንም ጨምሮ ማየት አስተዋይነት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የአጎቱንና የአባቱን መከራ አዛምዶ እያጤነ፣ ከተሞክሮ እየተማረ፣ ዛሬም ሳይነጣጠል እጅ ለእጅ ተያይዞ ለመራመድ እየጣረ ነው።
ፓርላማው የዚህ ጥረቱ ዓቢይ ምሳሌ ነው። ፓርላማው ከነጉድለቱ የአገሪቱ ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪ መሆኑ ታውጇል።
“የምትጠጣበትን ጉድጓድ ደንጊያ አትጣልበት” እንዲል መጽሐፉ፤ በዚህ በተከበረ የሕዝብ ሸንጎ ፊት የሚደረግ ስላቅ እልህና ዘለፋ የሀገሪቱን ግርማ ሞገስ ዝቅ አድርጎ የሚያስንቀን እንዳይሆን መጠንቀቅ ይበጃል።
የምክር ቤቱን አባላት “የተከበሩ አቶ/ወ/ሮ እገሊት” ብለን የምንጠራቸው የግል ፍቅራችን አነሳስቶን ሳይሆን ለወከሉት ህዝብ ያለንን አክብሮት ለመግለጥ ጭምር ነው። ፓርላማውን የሚያከብር አባላቱን ያከብራል። አባላቱን ማክበር ማለት የመረጣቸውን ህዝብ ማክበር ማለት ነው። አባላቱን ስናሽሟጥጥና በእነሱ ላይ ስንሳሳቅ የላካቸውንና የወከላቸውን ህዝብ ምን እያልነው እንደሆን ከወዲሁ ማጤን ይገባል።
አባቴ ሲቆጣ አጎቴን እያሰበ ካልሆነ፣ በዓይነቱ የተጠየቀው በዚያው በዓይነቱ ካልተመለሰ ወደ ስድብና ናጫ ያመራል። አበው ሲሸመግሉ “እምባጓሮና የውሃ ሙላት ከጨመሩባቸው ይበረታሉ” የሚሉትም ለዚህ ነው። ያበለዚያ ግን “ዓሳማ ንጹህ መሆኑን ለማሳየት እግሩን ያነሳል” መባል ይከተላል።
“ጀግና ማለት በመጀመሪያም በመጨረሻም የገዛ ባህርይውን ያሸነፈ ነው” ማለት ይህን ይመስላል። ቁጣ፣ እልህ፣ መገሰልና ሌሎችን መናቅ፣ የጎበዝ ምልክት አይደለም። ቧልትና ተሳልቆ በቤተ-መቅደስ ውስጥ ሲካሄድ “ቅዳሴው ሲያልቅበት ቀረርቶ ሞላበት”ን ያስተርታል። “የጀግና ሰው ጌጡ ትህትናው ነው” እንዲል መጽሐፍ  ከዘለፋው ትህትናው ሊቀድም ይገባል። ምክር ቤት የገባው አባል የአባቴም የአጎቴም ወኪል ነው እናም ወኪሌና ወኪላቸው ሲነጋገሩ “ዳኛ ሆነህ ስትሰየም እንደ ጠበቆች አትሁን” የሚለውን ብሒል ሳይዘነጉ መሆን አለበት።
የሚያስቆጣውና ዘለፋ ውስጥ የሚያስገባው የሌሎች ሀሳብ መስጠት ከሆነ፣ ሌሎችን አላዳምጥም ማለት የት እንዳደረሰን የእራሳችንን ታሪክ ማስታወስ ይበቃል።
ቡድን እንደ ደንጊያ ክምር ነው። በተለይም ያ! ቡድን በጉልበተኛና በማን አህሎኝ የሚመራ ከሆነ የቡድኑ አውራ ሲመዘዝ ክምሩ እንደሚናድ መጠራጠር አይገባውም። ስልጣንና ክብር በራሳቸው እግር ሲቆሙ ያዛልቃሉ። ምርኩዝ ግን ምንጊዜም ምርኩዝ ነው።
ጎበዝ ያነሰበትን ሰፈር እያሸሟቀቁ የደካሞች ዓለቃ፣ የሰነፎች አውራ ላለመሆን ልብ ያለው ልብ ይበል። ለፍቶና ደክሞ ያለፈለት ሰው ድኅነት፤ ሳይለፋ የበለጸገውን ሰው ትክክለኛነት አያሳይም። “የተቆለፈ ደጃፍ በቶሎ አይከፈትም” እንዲሉ፣ የሚጠራኝ ይበዛል ብሎ ለገመተ የሚወደድበትን ብልሃት ቢያዘጋጅ ይበጀዋል።
“የሰው ልጅ ጊዜውን እቃም ቦታውን ሳያገኝ አቀርምና ሁሉንም አትናቅ” እንዳለው መጽሐፈ ምሳሌ… አነሰ በዛ፣ ጠቆረ ቀላ፣ ሳንል ትህትናንና አክብሮትን በማስቀደም ምሳሌ መሆን ካሻን “ፍም እፍፍ ቢሉትም ይነዳል፣ እንትፍ ቢሉትም ይጠፋል” ማለትን እንልመድ!! እንከተል!!Read 1526 times