Sunday, 09 July 2023 16:56

ዓደይ የሚታጠብ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

በዓመት ውስጥ ለ10 ወራት፤ በሳምንት ቢያንስ ለ5 ቀናት የማደርገውን የተለመደ ተግባር እየከወንኩ ባለሁበት ቅፅበት የ7ኛ ክፍል መምህር የሆነው አስጨናቂ ቁና ቁና እየተነፈሰ፣ እጆቹን እያማታ እና የሆነ ነገር እያጉተመተመ ወደ ቢሮዬ መጣ። “አሞኝ ስለነበር ነው የቀረሁት ፈተና አታጥፍልኝም፤ ቤተሰቦቼ ገጠር ስለሄዱ ቤት ጠብቂ ተብዬ ነው የቀረሁት፤ ኧረ ሁለተኛ አልቀርም! ወላጆቼ ለቅሶ አጋጥሟቸው ነው። እንዴት ብዬ ወላጅ አመጣለው። ላሁን ብቻ እለፈኝ፤ የሚሉ ልምምጦች እና ውትወታዎች እንደ አንድ አስተማሪ የተለመዱ ሊሆኑ ይችላሉ። ግን የሰሞኑ በጣም በዛ! እኔ ሰልችቶኛል! ተማሪዎቹ ለምን እና የት እንደሚቀሩ በደንብ ጥናት መደረግ እና እርምጃ መወሰድ ያለበት ይመስለኛል። አለበለዚያ በዚህ ሁኔታ መቀጠሌን እኔንጃ!” ብሎ በመጣበት አካሄድ ተመልሶ ሄደ።
ሀና እባላለው። ተወልጄ ያደኩት በአነስተኛ የገጠር ከተማ ውስጥ ነው። ከልጅነቴ ጀምሮ የማልመው እና የምመኘው የመምህርነት ሙያ ውስጥ ከገባው ረዥም ዓመታትን አስቆጥሬያለው። በርዕሰመምህርነት ወደ አዲስአበባ ከመምጣቴ አስቀድሞ ብዙውን የመምህርነት ጊዜዬን ያሳለፍኩት በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ ነው። ለዚህም ተማሪዎች ከት/ም ገበታቸው ሲቀሩ መመልከት ለእኔ የተለመደ ነገር ነው። ነገር ግን ችግራቸው ስለሚታወቅ መፍትሄ ለመፈለግ ይቻል ነበር። አሁን ግን በዚህ በትልቅ ከተማ ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ምን ሊያስቀራቸው እንደሚችል በጭራሽ ማወቅ አልቻልኩም። የእኔም ሆነ የብዙዎች መምህራን ግምት የአፍላነት ቅብጠት ወይም አልባሌ ልማድ ይዟቸው ይሆናል የሚል ነው። ግን ደግሞ ከወንዶቹ ይልቅ ሴቶቹ ናቸው በብዛት የሚቀሩት። ለምን.....? እያልኩ ከእራሴ ጋር ስሟገት ጊቢ ውስጥ የሚጯጯህ ድምፅ ሰማሁ።
አንዲት የ8ኛ ክፍል ተማሪ እና መምህር አስጨናቂ ቆመው ይጨቃጨቃሉ። የሁኔታውን ምንነት ለማጣራት እየተጠጋሁ ባለሁበት ቅፅበት ተማሪዋ “የፈለጋችሁትን አድርጉ እኔ ግን ወደ ቤት እሄዳለው” ብላ ወደ ውጪው በር አመራች። ከመምህሩ ጋር የነበረው ግብግብ ከጥበቃ ሰራተኛው ጋር ቀጠለ። ይህ ግብግብ በጉልበት እንደማይቆም ስለገባኝ እንድትሄድ እንዲፈቅድላት ለጥበቃ ሰራተኛው ነገርኩት። ይቺ ተማሪ እና መሰሎቿ ከትምህርት ገበታ የሚቀሩበትን ምክንያት ለማወቅ ልጅቷን መከተል እንዳለብኝ ስለገባኝ በርቀት ተከተልኳት። ልጅቷ የሄደችው እንደፈራሁት ወይም እንደገመትኩት በተለያዩ ሱስ የተጠመዱ ሰዎች ወደሚሄድቡበት ቦታ ሳይሆን ወደ ቤቷ ነበር። ለተወሰነ ሰአታትም ተመልሳ ከወጣች ብዬ ጠበኩ። ምንም አልነበረም። ከዚህ በኋላ የነዚህ ተማሪዎች ጉዳይ ይበልጥ ጥያቄ እየሆነብኝ መጣ። በዙሪያዬ ያሉ መምህራን እንደሚሉት ወላጅን ማናገር ‘ብቻ’ መፍትሄ መስሎ አልታየኝም። በዚህ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች ከወላጅ ይልቅ ጓደኛ ወይም እንደጓደኛ የሚቀርባቸውን ሰው እንደሚሰሙ አውቃለው። ትክክለኛ መፍትሄ የሚገኘውም ከእውነተኛው ችግር ነው። ልጅነቴን ለማስታወስ ሞከርኩ። ከት/ቤት ለምን ነበር የምቀረው......? ቤተሰቦቼ ስራ ካዘዙኝ ወይም ቤት ጠባቂ ከሆንኩ፣ የወርአበባዬ ሲመጣ እና አንድአንዴ ደግሞ እንስሳቶችን የሚያግደው ልጅ በሆነ ምክንያት ከሌለ እሱን ስለምተካ ነበር። ግን የእኔ ልጅነት እና የእነዚህ ተማሪዎች ህይወት አይገናኝም። ምክንያቶቼ ለገጠር እንጂ ለከተማ ተማሪ የሚሆን አልመሰለኝም።
ለብዙ ሳምንታት በዚህ ሀሳብ ተወጥሬ ሰነባበትኩ። ግን ችግር እንጂ ምንም መፍትሄ ላገኝ አልቻልኩም። ከተለመዱት ቀናት በአንዱ ፈጣሪ የተማሪዎቹን እና የእኔን ጭንቀት ተመልክቶ አንዷ ተማሪ እራሷን አሳልፋ እንድትሰጥ አደረጋት። እየተጣደፈች ወደ ቢሮዬ መጣች እና “እኔ ምለው መምህርት አንቺም ሴት ነሽ አይደል” አለችኝ። “አዎ” አልኳት ድፍረቷ ቢገርመኝም እያደነኳት። “እና ታዲያ እኔ ፔሬዴ መጥቶ ልብሴ ስለነካ ሲሳቅብኝ እና መማር ሲያቅተኝ ለምን ዝም ትያለሽ” በማለት ከተል አደረገች። “ኧረ እኔ ዝም አላልኩም! ማን ነግሮኝ! ቆይ ማን ነው እንዲህ ያለሽ። ነይ አሳዪኝ...” ብዬ በጀብደኝነት ልሄድ ስል “ይቅርታ መምህርት ግን አሁን ሄደሽ መናገርሽ ብቻ ለውጥ አያመጣም። አብዛኛቹ ሴት ተማሪዎች ይበልጥ አፍረው እንዲቀሩ ያደርጋቸዋል” በማለት ያልጠበኩትን ነገር ነገረቺኝ። “የወርአበባ አየን ብላችሁ ከት/ቤት ትቀራላችሁ እንዴ” አልኳት። ችግሩ ያልደረሰብኝ ይመስል። “አዎ አብዛኞቹ ተማሪዎች ሞዴስ መግዛት ስለማይችሉ ይቀራሉ። እስካሁን አልሰማሽም እንዴ?” አለችኝ። ቀጠል አድርጌ “ቤተሰብ ደብተር፣ እስኪሪብቶ እና ሌላም ነገር ሲገዛ ለንፅህና መጠበቂያ የሚሆን ገንዘብ ያጣል” አልኳት። እሷም “ የገንዘብ ብቻ ሳይሆን ለዚህ ጉዳይ ያላቸው አስተሳሰብ ልክ አይደለም፤ ከ13 ዓመት በታች ፔሬድ መጣ ሲባል ደግሞ ያለማመን ነገርም አለ። አንዷ ጓደኛችን ከክፍሏ ልጅ ጋር አይተዋት ስለነበር ግንኙነት አድርገሻል ብለው ገርፏት” በማለት ይበልጥ ግራ አጋባችኝ። ግን አሁን ላይ ችግሩንም ይሁን መፍትሄውን ያወኩ ይመስለኛል። ለልጆቹ የወርአበባ ንፅህና መጠበቂያ እንዲያገኙ ማድረግ ዋነኛው ጉዳይ ቢሆንም በተፈጥሯዊ ጉዳይ ላይ የተስተካከለ አመለካከት በሴት እና በወንድ ተማሪ እንዲሁም በቤተሰብ ላይ መፍጠር ከመማር ማስተማሩ ጎንለጎን የምሰራበት ጉዳይ መሆን አለበት።
በዓለምአቀፍ ደረጃ ወደ 5መቶ ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች በወርአበባ ወቅት የሚያስፈልግ ቁሳቁስ እንዲሁም የመፀዳጃ ቤት አገልግሎት ማግኘት አይችሉም። ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ 22 ሚሊዮን ሴቶች የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ አያገኙም። እንዲሁም ስለሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ሙሉበሙሉ ግንዛቤ(እውቀቱ) የላቸውም። ይህን ችግር ለመቅረፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ(ከሚመረቱ) የንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ውስጥ ዓደይ የሚታጠብ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ አንዱ ነው። የዓደይ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ መስራች እና ባለቤት ወ/ሮ ሚካል ማሞ ይባላሉ። ወ/ሮ ሚካል በንግድ አስተዳደር ምሩቅ ናቸው። ዓደይ የሴቶች የሚታጠብ የንፅህና መጠበቂያ ከመመስረቱ አስቀድሞ በድርጅቱ የሚመረተው የልጆች አልባሳት ነበር። ወ/ሮ ሚካል የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ለማምረት መነሻ የሆናቸውን ሀሳብ ያገኙት በቅርብ ጓደኛቸው አማካኝነት ነው። ነገር ግን እንደ ወ/ሮ ሚካል ንግግር ሀሳቡን በሰሙበት ወቅት ለጉዳዩ ትኩረት አልሰጡትም ነበር። ምክንያታቸው ደግሞ ለስራው አዲስ ስለነበሩ ስጋት ስላደረባቸው ነው። “እኔ ውልደቴም እድገቴም ከተማ ውስጥ በመሆኑ እና በዚህ ችግር ውስጥ ስላላለፍኩ የወርአበባ የንፅህና መጠበቂያ ችግር አላውቅም ነበር” ብለዋል ወ/ሮ ሚካል ማሞ። ወ/ሮ ሚካል የተለያዩ ጥናቶችን ከተመለከቱ እና በድርጅቱ አከባቢ(ለገጣፎ) ባሉ ት/ቤቶች ውስጥ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ችግር መኖሩን ካስተዋሉ በኋላ ወደ ስራው ለመግባት ችለዋል። ዓደይ የሚታጠብ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ የተመሰረተው እ.ኤ.አ በ2017 ሲሆን በውስጡም ከ80 በላይ ሴት ሰራተኞችን ይዟል።
ከተለመደው የመሸጥ እና የመለወጥ ስራ ወጥተው በጎ ተፅዕኖ የሚያሳድር(Social entrepreneur) ስራ እንደሚሰሩ የተናገሩት ወ/ሮ ሚካል ማሞ በዚህ ስራ ለ4 ዓመታት ያህል ቆይተዋል። እንደ ዓደይ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ መስራች እና ባለቤት ንግግር ንፅህና መጠበቂያው አደይ የሚለውን ስያሜ ያገኘው ምርቱ ሀገርበቀል ስም እንዲኖረው በማሰብ ነው። እንዲሁም ዓደይአበባ የሚያምር፣ በዓመት በተወሰነ ወቅት የሚታይ እና ለመድሀኒትነት የሚውል በመሆኑ ነው። የአደይ የሚታጠብ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ምርቶች; በተለያየ መጠን የተሰሩ ከ18 እስከ 24 ወራት እየታጠበ አገልግሎት የሚሰጥ የወርአበባ የንፅህና መጠበቂያ፣ የወርአበባ የውስጥ ሱሪዎች(ንፅህና መጠበቂያው ከውስጥ ሱሪ ጋር አንድ ላይ የተሰራ)፣ ለአካል ጉዳተኞች የሚሆን የንፅህና መጠበቂያ፣ በገዳም ውስጥ ለሚኖሩ እናቶች የተዘጋጀ የንፅህና መጠበቂያ እና ብርቄ ባልዲ ናቸው። ብርቄ ባልዲ በአይምሮአዊ ንብረትነት የተመዘገበው በጀግኒት ኢትዮጵያ እና አይኬር ሲሆን በተባባሪነት አደይ የሚታጠብ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ግብአቶቹን ያዘጋጃል። ከላይ ከተጠቀሱት የዓደይ ምርቶች በተጨማሪ ሳሙና፣ ፎጣ እና የውስጥ ሱሪዎች በአደይ ምርቶች ውስጥ ይገኛሉ። እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያ አገልግሎት ላይ ከዋለ በኋላ ወይም ተጨማሪ የንፅህና መጠበቂያ ለመያዝ የሚያስችል ቦርሳ ይገኛል። ይህ ቦርሳ ጥቁር ቀለም ያለው፣ ውሀ የማያስገባ እና መጠኑ አነስተኛ በመሆኑ ለአያያዝ አመቺ ነው።ዓደይ የሚታጠብ የንፅህና መጠበቂያን ማግኘት የሚቻለው (ለሽያጭ የሚቀርበው) ድርጅቱ በሚገኝበት በለገጣፎ አከባቢ ነው። ነገር ግን በብዛት ለሚወስዱ አካላት የመጓጓዣ ወጪ ሳይከፍሉ ያሉበት ቦታ ድረስ የማድረስ ሁኔታ መኖሩን ባለቤቷ ተናግረዋል። አራት ጥቅል የሚይዘው(3 መካከለኛ እና 1 ትልቅ መጠን ያለው) የዓደይ የንፅህና መጠበቂያ በ120 ብር ነው የሚሸጠው። እስከ 2 ዓመት ድረስ ማለትም ለ100 ያህል ጊዜ እየታጠበ አገልግሎት ይሰጣል።
 እንዲሁም እስካሁን ሙሉበሙሉ በእርዳታ እየተሰጠ ያለው የብርቄ ባልዲ ለ60 ሺ ሴት ተማሪዎች መድረስ ይችሏል። የዓደይ የንፅህና መጠበቂያ፣ የውስጥ ሱሪ፣ ሳሙና፣ የቀን መቁጠሪያ እና መምሪያ(በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጀ) ብርቄ ይዛለች። እንደ ወ/ሮ ሚካል ማሞ ንግግር ባልዲው በእራሱ ለማጠብ እና ለማስቀመጫነት እንዲውል ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ወ/ሮ ሚካል ማሞ “ተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያውን ሲያገኙ የተረጂነት ስሜት እንዲሰማቸው አንፈልግም። ድርሻዬ ነው ብለው እንዲጠይቁ ነው ምንፈልገው” በማለት ተናግረዋል። ስለሆነም እንደ ወ/ሮ ሚካል ማሞ ንግግር ሴት ልጆች ሳይፈሩ እና ሳይሳቀቁ የንፅህና መጠበቂያ እንዲያገኙ የግንዛቤ ስራ በመስራት እና ግብአቱንም በማቅረብ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጀምሮ እያንዳንዱ ግለሰብ ግዴታ አለበት።


Read 455 times