Sunday, 09 July 2023 17:35

“ሀዲስን ፍለጋ”

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(0 votes)

የክቡር ዶ/ር ደራሲና ዲፕሎማት ሀዲስ አለማየሁ ሁለተኛው የኢጣሊያ ወረራ የጦር ግንባር እና የአርበኝነት ትግል ተሞክሮ ነው፤ የዚያን ዘመን ህይወታቸውን የሚያወሳ አንድ እራሱን የቻለ ገጽታም ጭምር ነው - ትዝታ፡፡ በርግጥም የጦርነቱን ሙሉ ታሪክ ብቻ ቀንብቦ የያዘ ሰነድ ነው ልንለው አንችልም፡፡ ምክንያቱም ሀዲስ ከሽሬ ግንባር በየቀኑ የተደረገውን እና የሆነውን ሁሉ እየተከታተሉ ዝርዝር ማስታወሻ የያዙበት ደብተራቸው በሁለት ጥሩ ባልሆኑ አጋጣሚዎች ጠፍቶ መቅረቱን በመቅድማቸው ገልፀዋል፡፡
እንግዲህ ከዚያ ሁሉ የተረፋቸው አንዳች ባይኖርም፤ ከአይምሯቸው ያልጠፋውን ከብዙ ጥቂቱን አስታውሰው ያኖሩልን የዘመን ትዝታ ውስን ማህደራቸው ናት፤ ለዚህም ነው ትዝታ ሲሉ የሰየሟት፡፡…“በጣም የማዝነው መጀመሪያ የጻፍሁት ማስታወሻ በመጥፋቱና ደባጉና በተባለ ቦታ ጠላት ሰፈራችንን ባይሮፕላን በደበደበበት ጊዜ ድንኳኔና በውስጡ የነበረው ሁሉ በቦምብ ሲቃጠል አብሮ ተቃጠለ፤ መጽሐፉን የጻፍሁት፣ የጦርነቱም የግዛቱም ጊዜ ካርባ አመታት በላይ ካለፈ በሁዋላ በመሆኑ፣ የብዙ ጀግኖችን ስምና ስራቸውን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቦታ ሰጥቼ ከተከታታይ ትውልዶች ጋር ለማስተዋወቅ ሳልችል ስለቀረሁ ነው፡፡“ (ገጽ.6) ምንም እንኳን ትዝታ ግላዊ ህይወታቸውን በተመለከተ የተሟላ ስዕል መስጠት የሚችልና ዝርዝር ነገር በበቂ አሟልቷል ባይባልም፣ በማስረጃ የተደገፉ ነባር ታሪኮች እና ተረኮችን፤እያሰባጠረም-እያመሳከረም እሚተርክ ሁለንተናዊ ጠቀሜታው የበዛም፣ ሚዛን የሚያነሳም ድንቅ ማስታወሻ ነው፡፡ በነቢብም፤ በገቢርም የዘመኑን ማህበራዊና ስነልቦናዊ ሁነት ከፋሽስት ኢጣሊያ የጦርነቱ ክስተት ጋር አጣምራ የምትተርክና የምታንፀባርቅ የዚያ ትውልድ መስተዋትም ናት፡፡ የሀዲስ የወጣትነት ሀሳቦቻቸው፣ ለነፃነት ያደረጉት ተጋድሎዋቸው፣ የጋለ የሀገር ፍቅር ጥማታቸው፣ የጦር ሜዳ አስገራሚና አስደንጋጭ ገጠመኞቻቸው፣ ለሞት የሚዳርጉ የነበሩ ውሳኔዎቻቸው እንዲሁም በጥበብ ስራዎቻቸው ላይ፤ በተለይ በቴአትሮቻቸው ህዝቡን ለማንቃት የሄዱበት ርቀትና እልህ አስጨራሽ ፍትጊያዎቻቸውን ሁሉ አካትተው የቀነበቧት ድርሳናቸው ናት፡፡
“አርበኛው ደራሲ”
ሀገሬ ተነስታ ካልጨበጠች እርካብ
ነገራችን ሁሉ የምቧይ ካብ-የምቧይ ካብ
ይህን ያሉት የዚያ አንፀባራቂ ትውልድ አባላት የምንላቸው (የእነ-ዮፍታሔንጉሴ፣ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ፣ ሀዲስ አለማየሁ) ኢትዮጵያዊያን ነበሩ፡፡ ከያ ትውልድ ጥቂት ቀደም ብሎ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ብቅ ያሉ፣ በቁጥራቸው አነስተኛ ግን በሀገሪቱ የዘመናዊነት ግስጋሴ ጉልህና ወሳኝ ሚና የነበራቸውና ዘመናዊ ትምህርት የቀሰሙ ወጣት ኢትዮጵያዊያን ደግሞ አሉ፡፡ እኚህ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን አይናቸውን እንደገለጡ ገዝፎ የታያቸው በአጥጋቢና አርኪ ሁኔታ ያልተቋጨው ሀገር ግንባታ ነው፡፡…“ልብ አድርግ ከኢትዮጵያ ክፉ ልማድ ለጌታው እንጂ ላገሩ አይደለም፡፡ ይህ ማለት ክፉ ልማድ መለወጥ የሚገባው መሆኑ መቼም የታወቀ ነው! ነገር ግን ክፉም ቢሆን ልማድ ሆኖ፣ ስርዓት ሆኖ አገራችንን እስከ ዛሬ በነፃነት ያቆያት ስለሆነ ታማኝነት ላገሩና ለባንዲራው የሆነ ካልሆነ የነበረውን ማድከም ወይም ማፍረስ፣ ባዶ እጅ የሚያስቀር ነው፡፡ ዛሬ ያለንበት ሁኔታ ከጥቂቱ በቀር ተሰናድቶ ሳይተካ የጥንቱ የተደከመበት ነው፡፡ ለዚህ ነው፤ እንኩዋንስ ከጥንቱ ልንበረታ እንዲያውም ደክመናል ያልሁህ”፡፡ (ገጽ.20) ሀዲስና መሰሎቻቸው የኢትዮጵያ አገራዊነት እውን ሆኖ በማያሻማ መንገድ ተጠብቆ እንዲኖር ነው እንጂ፤ ሌላ ጫናና ተግዳሮቶችን ተቋቁመው ስለ መዝለቃቸው እርግጠኞች ነበሩ፡፡ (ስለእኚህ ትንታግ ወጣቶች በስፋትና በዝርዝር ለመረዳት እውቁ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “ፋና ወጊ የለውጥ አቀንቃኞች በኢትዮጵያ” በሚል ያቀረቡትን ጥናታዊ ስራ በማየት ስለ ጉዳዩ  በይበልጥ መረዳትይቻላል)
ከዘመኑ ትንሽ ፈቅ አልን፡፡ የሀገር ግንባታው ህልምም ቀጥሏል፡፡ ውጥኑን ከመሰረቱ የሚያደናቅፍ እንቅፋት በወረራ ሳቢያ ተከሰተ፡፡ ኢጣሊያ ዳግም ኢትዮጵያን ወግታ በአንድ በኩል ድል ለመቀዳጀት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የአድዋን ቂም ለመበቀል…ከዚያ ባሻገር ደግሞ  አይነተኛ ግብዋ ወደሆነው ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛትዋ ለማድረግ በነበራት ፅኑ ፍላጎት፤ መጀመሪያ ለዚሁ ግብዋ ፖሊሲ አድርጋ ከነደፈቻቸው መካከል፤ ከፍ ሲል የጠቀስኳቸው ምሁራንን እና የተማሩ ኢትዮጵያውያንን የማጥፋት ዘመቻ ነበር፡፡ (ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ ይህ የወጣት ሀገር ወዳድ ምሁራን እልቂት የታሰበውን ሀገር ግንባታ ፕሮጀክት ያለባለቤት አስቀረው! ሲሉ በትካዜ የጻፉትን ከአመታት በፊት ከአንድ ጋዜጣ እንደዘበት ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡) በእርግጥ ከአንድ ምዕተ-ዓመት በፊት ተነስተው የነበሩትና በጅምር የቀሩት ወጣቶች አቅደውና ጀምረውት የነበረው የኢትዮጵያን አገራዊነት ግንባታ በጊዜው አለመጠናቀቅ አሁን ላለንበትም፤ ለገባንበትም ውስብስብ ቀውስ ዳርጎናል! የሚሉ ዘመኑ ላይ የጻፉ፣ ጊዜውን በተጨባጭ ያጠኑ ምሁራን ጥቂት አይደሉም፡፡ ከዚያ እልቂት በዕድል የተረፉት እንደ ሀዲስ አለማየሁ ያሉ የዚያ ትውልድ አባላት የሀገር ግንባታው ሂደት በአጭር መቀጨቱን፣ ወረራው የሀገሪቷን እድገት ወደ ኋላ መጎተቱን፣ በአናቱም የንጉሱ ከአገር ለቆ መውጣት መራር እውነታነቱን…በይበልጥ ተገነዘቡ፡፡ ግንዛቤያቸው ቁጭትም ነበረው፡፡ ቁጭት ያዘለው ህልማቸው ተጋድሎዋቸውን ተስፋ አስቆራጭ አደረገባቸው፡፡…“ንጉሳችሁ አገር ለቀው ወጡ እኮ ይሉናል፡፡ ያለመሪ ከሀይለኛ ጠላት ጋር ጦርነት መቀጠል እንዴት ይሆንላችኋል?“ ይሉናል፡፡ ንጉሱ ያገራችንን ሸለቆዎችና ጫካዎች ይዘው አልሄዱም፤ ሸለቆዎቻችንና ጫካዎቻችን ለጠላት አጋልጠው አይሰጡንም፤ በጉያቸው አቅፈው ለመጨረሻ ድል ያበቁናል፡፡ ስለዚህ እዚያ ጫካ ምሽግና አውሮፕላን በሌሉበት የፋሽስትና የኢትዮጵያ ወታደሮች ብቻ ለብቻ በሚገጥሙበት ጦርነት፤ እኔ ባየሁት መጠን ድሉ የኛ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም! ደግሞም አገር ካቀፈ በዘመናዊ መሳሪያ የሚወጋን ጠላት ባርበኝነት ከመከላከል የተሻለ መንገድ የለም”፡፡ (ገጽ.128) ሀዲስ ይህን ይበሉ እንጂ በዚህ ወኔያቸው እና ቆራጥነታቸው አገራቸውን ከወራሪ በአርበኝነቱ ለመታገል መርጠው ከመዝመታቸው በፊት መወሰን አቅቷቸው እያወጡና እያወረዱ ከራሳቸው ጋር ብዙ መሟገታቸውን ከትዝታቸው ያወጉናል፡፡ በመጨረሻ ለመዝመት ቆርጠው አለቃቸው ራስ እምሩን ለማስፈቀድ በለመኑ ጊዜ ሳይቀበሏቸው መከልከላቸውን እንዲሁ በየምዕራፉ ያስነብቡናል፡፡ አንዴ ልባቸው ወደ ጦሩ ቀጠና ለማቅናት የተነሳሳው ሀዲስ፤ ከእንግዲህ ቢቀሩም የመንፈስ እረፍት እንደማይኖራቸው ሲረዱ ስራቸውንም ተረጋግተውና በሙሉ ልብ መስራት እንደማይችሉ የበላዮቻቸውንበማሳመን ተፈቅዶላቸው ለመሄድ ችለዋል፡፡
“ምን ያለው ፈሪ ነው፤ ምን ያለው ወራዳ
እኛን ገፍቶ ሰድዶ ወደ ጦሩ ሜዳ
እሱ ተሸሸገ ገብቶ ከእናቱ ጉዋዳ!”
ባምስት ፈጅ አንካቦ ጠላውን ከልብሶ
ተነስቶ ሲፎክር ግንባሩን ከስክሶ፣
አይኑን ደም አጉርሶ
ጀግና መስሎን ነበር፣ ጠላት አሸባሪ ምሽጉን ጣጥሶ
ጦር መጣብህ ቢሉት አእምሮው ተቃውሶ
ሆዱ እየተንጉዋጉዋ እንደጠጣ ኮሶ
ተሸሸገ እማጀት የናቱን መቀነት ለብሶ!
ሀዲስ በወቅቱ በስልጣናቸው ዲፕሎማት ከመሆናቸው ትይዩ በሀገርና ህዝብ ጉዳይ ላይ አያሌ ሀላፊነቶች ነበሩባቸው፡፡ ይሁንና ከኃላፊነት ይልቅ ስልጣናቸውን አጉልተው የሚያሳዩ ሰው አይደሉም፡፡ ይህም ሀገር ከማስቀደም ይልቅ ለስልጣን አጽንኦት እንደማይሰጡ አመላካች ነው፡፡ ማህበረሰቡ ለስልጣን ካለው ተገዥነት፣ ለአስተዳዳሪዎች ከስልጣን ጋር ብቻ አያይዞ የሚሰጣቸው ላቅ ያለ ቦታ ሳያሳስባቸው ዝቅ ብለው ለአገር አንድነትና ነፃነት (ለአንዲት ነፍሳቸው ሳይሳሱ በመዝመት) የከፈሉትን ዋጋ ስናጤን ለዚህም የደራሲነት ስስ ነፍሳቸው ሳትጠቅማቸው እንዳልቀረች ያስጠረጥረናል፡፡ ሀዲስ በውስጣዊ የስብዕና እሴታቸውና በምክንያታዊ ዕሳቤዎቻቸው በእጅጉ የላቁ የዘመኑ ምሁር ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ በመሰረቱ ውስጣዊ እሴት ስንል፣ አንድ ነገር በራሱ በሌሎች ነገሮች ላይ ያልተመሰረተ ለራስ ያለ ከፍ ያለ ዋጋ ነው፡፡ ለምሳሌ ዜጎች የአካል ጉዳትም ሆነ ሞት የሚያስከትል ቢሆንም በእርግጠኝነት ስሜት ለአገርና ወገን ለመሰዋት ፈቃደኛ የሚሆኑት ወይም የራሳቸውን ጥቅም ወደ ጎን በማድረግ በሰብአዊነት ስሜት ሌሎችን ለመርዳት የሚነሳሱት አርበኝነትና ሰብዓዊነት በራሳቸው ባላቸው በዚህ የውስጣዊ እሴት ዋጋ የተነሳ ነው፡፡ አንድ አርበኛ እርሱ ሞቶ ሌላው ወገኑ እንዲኖር ቆርጦ ሲነሳ፤ በውትድርና የመሰማራት ፍላጎቱ፣ እንቅስቃሴው እና  አድራጎቱ ሁሉ ባለው የባህሪ ሁኔታ ላይ የተመረኮዘ መሆኑ በስነ-ባህሪ አጥኚዎች ዘንድ ይታመናል፡፡ ይህ አይነቱ ምክንያታዊ የባህሪ እሴት ለሀገር እድገትም ሆነ ኋላቀርነት ያለው አንድምታ ከፍ ያለ ነው፡፡ ሀዲስ በእድሜም ሆነ በእውቀት እንዲሁም በአእምሮ ብስለት ከመሰሎቻቸው የተሻሉ ስለነበሩ ባላቸው ፅኑ ያገር ፍቅር ምክንያት፤ የህዝቡን ስነልቦና ጠልቆና አስተውሎ ከመረዳት ባለፈ ጥሩ አስተማሪም ሆነ መሪ መሆን የሚችሉ የበቁ ድንቅ የእውቀት አባት መሆናቸውን…በመጽሐፋቸው ውስጥ በሚያነሷቸው የበቁ የአመራር ጥቆማዎች፣ የተፈተኑ የመፍትሔ አቅጣጫዎች፣የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች የሚያስተናግዱበት መንገዶች፣ክፉና ደጉን የሚመዝኑበት አመለካከቶችና ማሰብ የሚጠይቁ አካሄዶችን…በአንክሮ ስንመረምራቸው በወጉ ያስረዱናል፡፡…“አየህ ልክ አይደለም፡፡ ህዝቡ ስላልተማረ የኢትዮጵያ መንግስት ቢገዛው የኢጣሊያ መንግስት ቢገዛው ልዩነት ያለው መስሎ አይታየውም፡፡ መቼም የሚበዛው የኢትዮጵያ ህዝብ ጦርነቱ የሁለት ንጉሶች ወይም የሁለት ገዢዎች ጦርነት መሆኑንና የሱ ተግባር እግዚአብሔር ረድቶት ድል ላደረገው መገዛት ብቻ መሆኑን የሚያምን ነው! የኢትዮጵያ ህዝብም በረጅም ታሪኩ ከውጭ ጠላቶቹ ጋር ብዙ ጦርነቶችን ሲያደርግ ነገስታቱ ብቻቸውን ሄደው የተዋጉበት ጦርነት የለም፡፡ ሁልጊዜ ሰራዊቱ ወይም ህዝቡ በጀግንነት ተዋግቶ ጠላቱን ድል እያደረገ ነው ነፃነቱን አስከብሮ የኖረ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ የጠላት መንግስት ባገሩ ላይ የሚያደርገውን ጦርነት በንጉሱ ላይ እንደሚያደርገው መመልከት የለበትም፡፡ የውጭ መንግስቶች አገሩን ለመያዝ የሚያደርጉትን ጦርነት የንጉሱ ጉዳይ ነው! ብሎ በግዴለሽነት የሚመለከት ከሆነ ለምን በብዙ ጦር ሜዳዎች ደሙን እያፈሰሰ ያገሩን ነፃነት ሲያስከብር ኖረ! ስለዚህ ልክ አይደለም፡፡ (ገጽ.138)  በአንድ ወቅት እውቁ አሜሪካዊው ፈላስፋና ገጣሚ ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን፤ ለእያንዳንዱ ታላቅ ሰው ለትልቅነቱ መልካም ባለውለታዎቹ በቀደመው ትውልድ ለእርሱ የተተውለት የመጻሕፍት ርስቶች ናቸው!…ሲል ተናግሮ ነበር፡፡ አዎ፤ የእነ-ሀዲስ አለማየሁ፣ ኅሩይ ወልደ ስላሴ፣ ከበደ ሚካኤል፣ ማሞ ውድነህ…የመሳሰሉ ነባር ደራሲያን መጻሕፍቶቻቸው ቀድመውን ያለፉ የአሳቢና አሰላሳይ ሰዎቻችን የአንጎል ንቃት ንዝረቶች ናቸው፡፡ ልዩና በጎ የአእምሮ ትሩፋቶቻቸውን፣ ጠሊቅ ሀሳቦቻቸውን፣ ምግባሮቻቸውን እና ራዕዮቻቸውን፣ ድሎቻቸውንም ጨምሮ ወደኛ የሚያንቆረቁሩባቸውና በትርታችን ውስጥ የሚያርገበግቡባቸው የደም ስሮችም ጭምር ናቸው፡፡ የእነ-ገብረህይወት ባይከዳኝ፣ ተመስገን ገብሬ፣ ግርማቸው ተክለ ሀዋርያት፣ አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ…የእነዚህ ባለተሰጥኦ ነፍሶች የከበረ ህሊና ወደ አእምሮአችን በማስረግ በእነርሱ አይን እንድናይ፣በሀሳቦቻቸው እንድናስብ፣ በጥንካሬአቸው እንድንበረታና በመንፈሳቸው ክንፍ ወደ ላይ እንድንመነጠቅ ያደርጉናል፡፡ (በቀጣይ ሳምንት በከፊል ቴአትሮቻቸውን፣ በሙሉ ደግሞ ተረት ተረትን ለመቃኘት እመለሳለሁ፡፡)


Read 477 times