Saturday, 15 July 2023 20:41

ለ2 ዓመት የሚያገለግል የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

ከዚህ ቀደም በነበረው እትም ስለ ዓደይ የሚታጠብ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ አመሰራረት እና በውስጡ ስለሚገኙ ምርቶች ለንባብ በቅቷል። ቀጣይ ክፍሉም በዚህ እትም ቀርቧል።
በዩኒሴፍ መረጃ መሰረት የወርአበባ ቁስ ድህነት ማለት ሴቶች በወርአበባ ወቅት የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁስ ማግኘት አለመቻል፣ የመግዛት አቅም አለመኖር እና የግንዛቤ እጥረትን ያካተተ ነው። ይህ እጥረት ከሚስተዋልባቸው ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ይህን ችግር ለመፍታት ዓደይ የሚታጠብ የንፅህና መጠበቂያ እንደተቋቋመ የዓደይ የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ መስራች እና ባለቤት ወ/ሮ ሚካል ማሞ ተናግረዋል። እንደ ባለቤቷ ንግግር የዓደይ ምርቶች ሙሉበሙሉ ከጥጥ የተሰሩ ናቸው። የአደይ የንፅህና መጠበቂያ እየታጠበ እስከ 2 ዓመት ድረስ አገልግሎት መስጠት ይችላል። ለዚህም አንዲት ሴት አንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግለውን የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ስትጠቀም በሁለት ዓመት ውስጥ ከ1ሺ በላይ የምታወጣውን ወጪ ወደ 240 ብር ዝቅ እንዲል ያደርጋል። በከተማ አከባቢ ለሚኖሩ ሰዎች የንፅህና መጠበቂያ ችግር እምብዛም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በት/ቤቶች እና በገጠራማ ስፍራዎች ችግሩ ከፍተኛ ነው። እንደ ወ/ሮ ሚካል ንግግር የሚታጠብ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ከገንዘብ ጋር ለተያያዘ ችግር ብቻ ሳይሆን ከአወጋገድ አንፃር ለአከባቢ ንፅህና የተሻለ ነው።
በጊዜያዊ መጠለያ እንዲሁም በተለያየ እርዳታ በሚያስፈልግበት ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሴቶች ከምግብ እና መሰል ጉዳዮች ጋር በተመሳሳይ መልኩ የንፅህና መጠበቂያ ሊያገኙ ይገባል። የወርአበባ ተፈጥሯዊ እንደመሆኑ ሴቶች በሚገኙበት በየትኛውም ስፍራ እና ሁኔታ የንፅህና መጠበቂያ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል ወ/ሮ ሚካል ማሞ። ከንፅህና መጠበቂያ በተጨማሪ የመፀዳጃ ክፍል እና ንፅህና ለመጠበቅ የሚያስፈልጉ ሌሎች ቁሳቁሶችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል። እንዲሁም ህመም ለሚሰማቸው ሴቶች እረፍት የሚያደርጉበት ቦታ ማመቻቸው ተገቢ መሆኑን ወ/ሮ ሚካል ተናግረዋል።
እንደ ወ/ሮ ሚካል ማሞ ንግግር የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሳይሰራ ሴቶችን በስራ ገበታ ማብቃት እና ተማሪዎችንም ፍሬያማ ማድረግ አይቻልም። አንዲት ሴት ተማሪ በአማካይ ከ3 እስከ 5 ቀናት ከትምህርት ገበታ እንደምትቀር ይገመታል። ማለትም በአንድ ዓመት ውስጥ ከ50 ቀናት በላይ ይባክናሉ። ስለሆነም “ሴቶችን እናብቃ የሚለው ነገር የንፅህና መጠበቂያ ከመስጠት ነው የሚጀምረው” ብለዋል ወ/ሮ ሚካል ማሞ። ሴቶች የወርአበባ ንፅህና መጠበቂያ ባለማግኘታቸው ለጤና ጎጂ የሆኑ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ይጠቀማሉ። አመድ፣ ፌስታል እና ጉድጓድ ላይ መቀመጥ፤ ኩበት፣ ንፅህናው ያልጠበቀ ጨርቅ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን መጠቀም ተጠቃሽ ናቸው። ንፅህናው ያልተጠበቀ ቁሳቁስ መጠቀም ደግሞ ለተለያዩ በሽታዎች ያጋልጣል። ከዚህም ውስጥ ኢንፌክሽን እና የማህፀን ካንሰር ይጠቀሳል። ስለሆነም በሽታ ከማጋጠሙ አስቀድሞ የንፅህና መጠበቂያን ተደራሽ ማድረግ የተሻለ ነው።
ለጤንነት ጎጂ በሆነው በወርአበባ ወቅት ጉድጓድ ላይ የመቀመጥ ሁኔታ መኖሩን በተመሳሳይ መልኩ የተናገሩት እድገታቸው በገጠር ከተማ ውስጥ የሆነው እና ኑሯቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉት ወ/ሮ ባዩሽ ዳንኤል ናቸው። ወ/ሮ ባዩሽ ለመጀመሪያ ጊዜ የወርአበባ ካዩበት ወቅት ጀምሮ የወርአበባ ማየት እስካቆሙበት ድረስ ንፅህና ለመጠበቅ የተጠቀሙት ጨርቅ ነው። ነገር ግን የውስጥ ሱሪ የሌላቸው ሴቶች ጉድጓድ ላይ ይቀመጣሉ። ወ/ሮ ባዩሽ ስለወርአበባ ንፅህና መጠበቂያ(ሞዴስ) ለመጀመሪያ ያወቁት ከ15 ዓመት በፊት ነው። ሁኔታውንም “ጊቢዬ ውስጥ ተከራይ የነበረች አንዲት ሴት ለወሊድ ወደ ህክምና ተቋም ስትሄድ አብሬያት ሄድኩ። በቦታው የነበረች የህክምና ባለሙያም ሞዴስ ገዝተሽ ነይ አለቺኝ። እኔም ምን እንደምትል ስላልገባኝ ደግሜ ጠየኳት።” በማለት አስታውሰውታል። ወ/ሮ ባዩሽ የህክምና ባለሙያዋ እንዲገዛ ስለጠየቀችው የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ምንነት ካወቁ በኋላ ድንጋጤ እና ንዴት ተሰማቸው። “እስካሁን ድረስ ሳስበው ያናድደኛል። ለእራሳችን የሚጠቅም ትልቅ ጉዳይ ላይ ቸልተኝነት ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ይባላል።” በማለት ተናግረዋል ወ/ሮ ባዩሽ። የሁለት ሴቶች ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ባዩሽ እስከ 12ኛ ክፍል ተምረዋል። በት/ቤት ቆይታቸው በወርአበባ ወቅት ንፅህና ለመጠበቅ ስለሚያገለግል የጨርቅ ንፅህና መጠበቂያ እውቀት አግኝተዋል። ነገር ግን በዘመናዊ መልክ ስለሚዘጋጀው የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ መረጃው የላቸውም። ከሴት ልጆቻቸውም ጋር በወርአበባ ዙሪያ ውይይት አድርገው አያውቁም። “ከእናቴ ጋር ስለዚህ ጉዳይ ተነጋግረን አናውቅም። ከታናሽ እህቶቼም ጋር ሆነ ከልጆቼ ጋር አንነጋገርም። ሁላችንም በየፊናችን ነው የምንወጣው። ይህም የሆነው የሚያሳፍር ነገር ስለሚመስለን ነው” ብለዋል።
የወ/ሮ ባዩሽ ልምድ በብዙ ሴቶች ላይ የሚስተዋል ነው። ያነጋገርናቸው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሌላ እናትም የነገሩን ታሪክ ተመሳሳይ ነው። ከክፍለሀገር ለስራ ወደ ከተማ በሄዱበት አጋጣሚ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተመለከቱ። “የስራ ባልደረቦቼን አጠቃቀሙን እንዲያሳዩኝ ስጠይቃቸው ያሳዩኝ ፊት ግን እስካሁን ያላዋቂነት እና የበታችነት ስሜት እንዲፈጥርብኝ አድርጎኛል” በማለት ተናግረዋል። እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያውን መጠቀም ከጀመሩ በኋላ ዋጋው ስለከበዳቸው የንፅህና መጠበቂያውን ለመተው ተገደዋል። እናም የሚታጠብ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ቢበራከት በማለት ሀሳብ ሰተዋል።
የዓደይ የሚታጠብ የንፅህና መጠበቂያ መስራች እና ባለቤት ወ/ሮ ሚካል ማሞ እንደተናገሩት ወደ 17 የሚሆኑ የሚታጠብ የንፅህና መጠበቂያ አምራች ድርጅቶች አሉ። በትስስር መድረክ አማካኝነት እነዚህ አምራቾች በጋራ በመሆን በምስራት ይገኛሉ። እንደ ወ/ሮ ሚካል ንግግር የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ እጥረት በመኖሩ ንፅህናው ያልጠበቀ የንፅህና መጠበቂያ እንዲመረት እና እንዲሰራጭ ምክንያት ሆኗል። ነገር ግን በህጋዊ መንገድ ለሚንቀሳቀሱ የንፅህና መጠበቂያ አምራቾች መንግስት ትኩረት ሰጥቶ በጋራ ቢሰራ(ቢደግፍ) ችግሩን ለመቀነስ ይረዳል። ወ/ሮ ሚካል “በሀገርአቀፍ ደረጃ 72 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የንፅህና መጠበቂያ የማግኘት ችግር አለባቸው። እንደ ዓደይ ይህን በመቅረፍ ሂደት ውስጥ አስተዋፅኦ ለማድረግ(አሻራ ለማሳረፍ) እየሰራ ይገኛል” ብለዋል። ይህም ስራ ብዙ አካላትን የሚያሳትፍ ጉዞ መሆኑን ወ/ሮ ሚካል ጠቁመዋል።
የዓደይ የሚታጠብ የንፅህና መጠበቂያ ምርት ላይ እንቅፋት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ቀረጥ ተጠቃሽ ነው። የንፅህና መጠበቂያው ላይ ከሚደረግ ቁልፍ ጀምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ከሌሎች ሀገራት እንደሚያስገቡ የዓደይ ባለቤት ተናግረዋል። ስለሆነም ቀረጥ መኖሩ የምርቶቹ የሽያጭ ዋጋ ላይ ተፅዕኖ አድርጓል። ወ/ሮ ሚካል ከጀግኒት ኢትዮጵያ፣ አይኬር እና መሰል አካላት ጋር በመሆን ‘ሰብአዊነቴን አትቅረጡ’፣ ‘ቀን ይወሰንልን ዋጋ ይተመንልን’ እና ሌሎች የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ላይ ትኩረት ያደረጉ እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ ‘አበባ አየሽ ወይ ትምህርት ቤት ትሄጃለሽ ወይ’ በሚል እንቅስቃሴ ለተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያ እንዲያገኙ አድርገዋል።
የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የመጀመሪያው ተግባር ግንዛቤ መፍጠር ነው። የግንዛቤ ለውጥ ሲባል ደግሞ የማህበረሰቡ ግማሽ አካል የሆኑትን ወንዶች ያካተተ መሆን እንደሚገባው የሚያጠያይቅ አይደለም። ወ/ሮ ሚካል እንደተናገሩት በአንዳንድ ት/ቤቶች ላይ የስርአተ ፆታ አስተማሪዎች ለወንድ ተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በመስራታቸው ለውጥ ተገኝቷል። “አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኝ አንድ ት/ቤት ውስጥ ወንድ ተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያ ከእኛ ተቀብለው ለሴት ተማሪዎች እስከመስጠት እና ሴቶቹም ሳያፍሩ እና ሳይሸማቀቁ ይዘው እስከመንቀሳቀስ ደርሰዋል” ብለዋል ወ/ሮ ሚካል። ለተማሪዎች ከሚሰጠው የግንዛቤ ስራ በተጨማሪ ለአካልጉዳተኞች የሚሆን በምልክት ቋንቋ እና በድምፅ የተዘጋጀ የግንዛቤ መስጫ ዘዴዎች በአደይ ውስጥ ይገኛሉ።
የወርአበባ ቁስ ድህነት አንገብጋቢ ችግር መሆኑን በመረዳት በ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያ በማጣት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ ማድረግ እንደሚገባ ወ/ሮ ሚካል ተናግረዋል። የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ችግሩን ለመቅረፍ ትኩረት በማድረግ እንዲሰሩ እና ትብብር እንዲያደርጉ በማለት የዓደይ የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ መስራች እና ባለቤት ወ/ሮ ሚካል ማሞ መልዕክት አስተላልፈዋል።


Read 1130 times