Saturday, 22 July 2023 00:00

“ዘመን አንተን ትመስላለች”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     አንጋረ ፈላስፋ መፅሐፍ ላይ እንዲህ ይላል፡- “አንድ ንጉስ ለህዝቡ፤ ‘ዘመን እንደ ምን አለች?’ ብሎ ይጠይቃል፡፡ ህዝቡም፤ ‘ዘመን ማለት አንተ ነህ፤ አንተ ሰላማዊ ስትሆን ሰላማዊ ትሆናለች፤ አንተ የከፋህ እንደሆነ ትከፋብሀለች’ ሲሉ ለንጉሱ መለሱለት።”
ምንም እንኳን ዘመንን የሚያበጀው እሱ ፈጣሪ ቢሆንም፤ ሰው መልካም ከሆነ በመልካም ስራው ፈጣሪውም የተሻለውን ይሰጠዋል። ንጉስ ዳዊት ባደረገው ነገር ሁሉ ተፀጽቶ በእንባ እያለቀሰ ፈጣሪውን በመለመኑ፣ ፈጣሪም ይቅር ባይ አምላክ ነውና ይቅር ብሎትም አልቀረም፤ “ከልጅ ልጅህ እወለዳለሁ” በማለት ትልቅ ፀጋን ሰጥቶታል። በቃሉም መሰረት ከድንግል ማርያም ተወልዶ የዓለምን ሀጢያት ሁሉ ደምስሶ ወደ ዘላለም ሕይወት እንድንገባ አድርጎናል። ሰው ወደ መልካም ነገር ከተጠጋ ጠማማውን ያቀናል።
ህዝቡ ማንን ይመስላል? መሪውን! መሪው ማንን ይመስላል? ህዝቡን! ጥሩ መሪ፤ ጥሩ ተመሪ ህዝብ ያመጣል። ጥሩ ህዝብ፤ ጥሩ መሪን ያስገኛል። ከላይ “ዘመን አንተን ትመስላለች” እንዳሉት፣ መሪ ጉልበትን ሳይሆን ጥበብንና እውቀትን መላበስ አለበት። እንደ ጥበበኛው ኢትዮጵያዊ ዮቶር መሆንን ያሻል። ዮቶር ለሙሴ ስርዓትን አስተማረ። የዛሬን አያድርገውና ለካ እኛ ኢትዮጵያዊያን የአስተዳደር ጥበብን ገና በዓመተ ዓለም ዘመን ጀምሮ የታደልን ነበርን! “መሪነት ህዝብን ብቻ ሳይሆን እራስንና ቤተሰብንም በአግባቡ መምራት ነው” የሚሉ በርካቶች ናቸው። መሪነት ከስር ከመሰረቱ መጀመር፣ “በትንሹ የታመነ ለትልቁ ይታመናል” እንደሚባለው ሁሉ፣ እራሱን መምራት የቻለ አካባቢውንም ሆነ ሌሎች ሀላፊነቶችን መሸከም ማስተዳደር ይችላል። አንዳንድ የድርጅትም ሆነ የሌላ አመራሮች፣ ሰራተኛ ቁጭ ብድግ ስላለላቸው ብቻ የመሩና የተከበሩ ይመስላቸዋል።… በስርዓቱ ያስተዳደሩም እየመሰላቸው በዚህ ባህሪያቸው ይቀጥላሉ።
…”ዘመን አንተን ትመስላለች” እንደተባለው፣ ቤተሰብም ሆነ መስሪያ ቤት፣ ሀገርም ጭምር የሚመራውን ይመስላል። መንግሥት የሚመራው ህዝብ ድሀና ደካማ ከሆነ፣ የዚያ አገር መንግሥት በሌሎች ሀገራት እይታ ደካማ ነው። መንግሥት በህዝቦቹ ላይ የቱንም ያህል ሃያልና አምባገነን ቢሆንም፣ በሌሎች ዘንድ ደካማነቱ አይሸፈንም። ጠንካራና በኢኮኖሚ የፈረጠመ ሀገርና ህዝብ ያለው ደግሞ ተፈሪና ተከባሪ ነው። “ሥርዓት ከሌለው ብዙ ህዝብ ይልቅ ሥርዓት ያለው ጥቂት ህዝብ ይበልጣል” ያሉት ባልሳሳት ፊታውራሪ ተክለ ሐዋሪያት ይመስሉኛል፡፡
ለምሳሌ የአፍሪካ አገራት መሪዎች በደካማ አስተሳሰባቸው ላይ ደካማ ህዝብና ያልሰለጠነ ማህበረሰብ ይዘው፣ ግን ደግሞ በሀብት የበለጸገ ሀገር ይዘው እድሜ ልክ እርዳታ ተቀባይ ለማኝ ሆነው ይኖራሉ። እያንዳንዱ የአፍሪካ ሀገር በተለያየ ማዕድን የበለፀገ፣ ለግብርና አመቺ፣ ለኢንዱስትሪም ምቹ ቢሆንም፣ ጠንካራ የስራ ልምድና ባህል ባለመኖሩ፣ እንኳን ለነገ ይቅርና ለዛሬም የሚሆን የዕለት ጉርስ የሌለው ህዝብ ነው።
ከድህነታችን የባሰው ደግሞ ደካማ አስተሳሰባችን ነው። በጎሳና በብሄር ተከፋፍለን እርስ በርስ መታኮስና መገዳደል፣ አንዱን ጥሎ ሌላው መንግስት ለመሆን በጦርነት ሀገሩን ማተራመስ፣ ህዝብን ለስደትና ለርሀብ መዳረግ፣ በራሳችን ሃብት የገነባውን ማቃጠልና ማውደም የእለት ተዕለት ስራችንና ልዩ መታወቂያችን አድርገነዋል…።
ስልጣን ያለው መንግስትም ስልጣኑን በራሱ ዘመድ፣ ጎሳ፣ ብሄር ብቻ ወንበሩን በማጥለቅለቅ በብልሹ አሰራርና በሙስና በመዘፈቅ ይታወቃል። ሌላውን ጎሳና ብሄር በመጨቆን የራስን ወገን ብቻ ተጠቃሚ በማድረግ፣ ሌላው የሀገሩ ገጸ በረከት ተካፋይ ሳይሆን ምፅዋተኛ እንዲሆን በማድረግ የአፍሪካ መንግስታት የተካኑ ናቸው። “ለምን!?” ብሎ የሚጠይቅን በመግደል እንዲያም ሲል በማሰርና በመደብደብ ለስደት በመዳረግ እነሱ ብቻ በሀገሩ ላይ አድራጊ ፈጣሪ ይሆናሉ። የባለስልጣኖች ከህግ በላይ መሆን፣ የሀገር ገንዘብ ማባከን፣ የነሱ ልጆችና ቤተሰቦች ከሀገር  ወጥተው በአውሮፓና በአሜሪካ በውድ ትምህርት ቤት እንዲማሩ መደረግ፣ እነሱ በህዝብና በሀገር  ሀብት የቅንጦትና የተንደላቀቀ ኑሮ ሲመሩ፤ ሌላው በሀገሩ እንደ  ስደተኛ የቁም እስረኛ ሆኖ ነፃነቱን ተገፎ እንዲኖር በማድረግ፣ ህዝቡን ለአመፅና ለመንግስት ግልበጣ እንዲነሳሳ ያደርጉታል። ይህ የአፍሪካ መሪዎች የሚታወቁበት መለያ ታርጋ ቁጥራቸው ነው።
ምርጫ በመጣ ቁጥር የተፎካካሪ (ተቃዋሚ) ፓርቲዎች ደጋፊዎችን በማሰር፣ በመደብደብ፣ ለስደት በመዳረግና በመግደል የሚጀምረው የምርጫ ቅስቀሳ፣ ኮሮጆ በመስረቅና ድምፅ አጭበርብሮ “አሸንፌያለሁ”     በሚል የአምባገነናዊ ንግግር ይደመደማል። በዚህ የተነሳ ለተወሰነ ወራት ወይም ዓመታት “ድምፄን ተነጥቄያለሁ” በሚል ሌላኛው ተፎካካሪ ሃይል ጦርነት ይጀምራል። በዚህ የተነሳ የሚጀመረው ጦርነት ህዝብን ለስደትና ለረሀብ እንዲሁም የአማፅያኑን ጎሳ በማሳደድ ይቀጥላል። በዚህ ሁኔታ አፍሪካ ጥገኛ የሆኑ ደካማ መንግስታትን ተሸክማ አሁንም ድረስ እየተጓዘች ትገኛለች። ለምሳሌ ያህል ደቡብ ሱዳንን፣ ዋናዋ ሱዳንን፣ ሱማሌን ወዘተ የመሳሰሉት ሀገራትን መመልከት በቂ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያም ከእነዚህ አገራት የምትደመር እየሆነች መጥታለች፡፡
እናም “ዘመን አንተን ይመስላል” እንዳሉት፣ እውነትም ዘመን መሪውን እንደሚመስል የደቡብ አፍሪካን መሪ ኔልሰን ማንዴላን ለዚህ አባባል መጥቀስ ይቻላል። ዘመን እሱን መስላ አገሩን ለተሻለና ህዝብ ለመረጠው መሪ በማስረከብ ወይም “እኔ እዚህ ጋ በቃኝ ሌላ ሰው ደግሞ ሀገሩን ይምራ” በማለት ሰላምና የተረጋጋ ሀገርና ህዝብ መፍጠር ይቻላል። “ዘመን አንተን ይመስላል” ማለት ይህ ነው  እንግዲህ።
(ከጋሻው ሙሉ “ሹመት እና ቁመት” መፅሐፍ የተቀነጨበ)


Read 1365 times