አድካሚ ቀን ነው ያሳለፈው፡፡ ያለወትሮው ብዙ ታካሚዎችን ሲያክም ነው የዋለው፡፡ ስራው ሳይካትሪስትነት ነው፡፡ ቀኑን የሚያሳልፈው ልክ እንደ ካህን፣ የሰዎችን የነፍስ ሚስጥር በማዳመጥ ነው፡፡ ያውቀዋል… የትኛውንም ያህል የእውቀት ባለቤት ቢሆን፣ የሰው ልጅን ሀዘንና ደስታ ቀርቶ የራሱን ስሜት እንኳን ጠንቅቆ እንደማይረዳው ያውቀዋል…ያውቀዋል…የመለኮታዊ ቀውስነትንና ሀይማኖታዊ እብደቶችን ባጠናው የሳይኮሎጂ እውቀት ሊፈታቸው እንደማይችል። ሆኖም ይሞክራል፡፡ ይጥራል፡፡ ለማከም፡፡ ለማዳን፡፡
ብዙዎቹ ታካሚዎች ያሳዝኑታል። አብዛኞቹ ከኋላ ታሪካቸው ተከትሏቸው በመጣው የማንነት ቀውስ የሚሰቃዩና ፈቅደው እያደረጉት፣ ፈቅደው የሚሰቃዩበት ሱስ ውስጥ የተዘፈቁ ናቸው፡፡ ራሳቸውን ከሚረዱት በላይ እሱ ምንም ማድረግ እንደማይችል ያውቀዋል፡፡ የሰው ልጆችን አጥብቆ ይወዳል፡፡ አዕምሯቸውን እንደ ፈጣሪ ማንበብ ቢችልና እንደፈጣሪ መልስ መስጠት ቢሞክር ምኞቱ ነበር፡፡ ሆኖም የሰው ልጅ ብቻ ነው፡፡ የሰው ልጅን የሀዘን ሚስጥራዊ ምንጭ በተሸከመው ጭንቅላቱ ብቻ ተረድቶ መፍትሄ ማምጣት አይችልም፡፡ እናም አንዳንድ ጊዜ ታካሚዎቹን በተመረጡ ቃላት ብቻ ለማከም ሲሞክር፣ እየሸወዳቸውና የማይጨብጡትን ተስፋ እያነፈሰባቸው እንደሆነ ተረድቶ፣ የምሩን እያለቀሰ የሚያዝንበትም ቀን አለ፡፡
ዛሬ ግን ድክም ብሎታል፡፡ ከታካሚዎቹ መካከል አንዱን የሆነ ነው የመሰለው፡፡ ሆኖም አንድ የመጨረሻ ታካሚ ማስተናገድ አለበት። ቶሎ ብሎ ጨርሶ ቶሎ ወደ ቤቱ በመሄድ፣ በፀጥታ ጨለማ ውስጥ መቀመጥ ነው የፈለገው።
በሩ በዝግታ ተንኳኳ…
“ይግቡ” አለ፡፡
አንዲት ሴት ወደ ውስጥ ዘለቀች፡፡ ለሳይካትሪስቱ ዘላለም ግን በሩን እንደከፈተችው፣ ዘላ ልቡ ውስጥ የገባች ነው የመሰለው፡፡ በሱ መስፈርት እጅግ የተዋበች ሴት ናት የገባችው። እንደሌሎቹ ታካሚዎች አይኖቿ ላይ ምንም አይነት የሀዘን ጭንብል አላጠለቀችም፡፡ ህይወት የሚያንጸባርቁት አይኖቿ፣ እሱን ሊያክሙት የመጡ መሰለው፡፡
ተቀመጪ ለማለት ጊዜ አላገኘም፡፡ ጊዜና ቦታ የሚሰወሩበት የአዕምሮው ክፍል ውስጥ ተደብቆ ለብቻው እያያት ነው፡፡ ሰሎሜም ብትሆን በዘላለም ላይ የሚስተዋለውን ስሜት ተረድታዋለች፡፡ ሲመለከታት ወዲያው እንደሚደነግጥ ታውቅ ነበር… እውቀቱ እንዲሰወርበት አድርጋም ብታወራው፣ የቃላቶችዋ ግዞተኛ እንደምታደርገው ታውቃለች፡፡ ሆኖም አሁን ላይ ለማድረግ ለምትሻው ነገር ውበቷ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ተገንዝባለች፡፡
ተቀመጪ እስኪላት ድረስ ቆማ በስስ ፈግታና በፍፁም የራስ መተማመን መንፈስ ውስጥ ሆና ጠበቀችው፡፡
ዘላለም ከሄደበት ዘላለም የሚመስል ትካዜ ውስጥ ተንቦጫርቆ እንደምንም ከወጣ በኋላ ምራቁን ለመዋጥ እየታገለ እንድትቀመጥ በእጁ ምልክት አሳያት…
“እባክሽ ተቀመጪ?”
“አመሰግናለሁ” ብላ ከፊት ለፊቱ ተቀመጠች፡፡
በትኩረት ሲመለከታት ከቆየ በኋላ ማስታወሻ መፃፊያውን አውጥቶ ጥያቄውን ጀመረ፡፡
“ሰሎሜ ነው አይደል ስምሽ?”
“አዎ፡፡”
“ምን ልርዳሽ እሺ ሰሎሜ?” አላት…ለመርዳት ሳይሆን ለመረዳት በሚመስል ድምፀት፡፡
“ዝግጁ ነህ?” አለችው ሰሎሜ …ከቅድሙ ፈገግታዋ በላይ ቀዝቀዝ ያለና ትንሽ ፍርሀት በሚተነፍስ አንደበት፡፡
“አልገባኝም? …ለምኑ ነው የምዘጋጀው?”
“ህይወት ለመስራት…የፈጣሪን ሀላፊነት ለመወጣት?”
ዘላለም፤ ሰሎሜ ምን እያለችው እንደሆነ ለመረዳት ቸግሮታል፡፡ ሆኖም የአዕምሮ ህሙማን በማንኛውም ሰዓት ምንም አይነት ነገር ሊናገሩ እንደሚችሉ ስለሚያውቅ፣ ሀሳብዋ በፈሰሰበት ሊፈስላት ራሱን አዘጋጅቶ፣ ሰሎሜ አለም ውስጥ ሊገባ ሙሉ ትኩረቱን እሷ ላይ አደረገ፡፡
“የምትይኝን ለመስማት ዝግጁ ነኝ፡፡”
ሰሎሜ የመጨረሻዋን ፈገግታ ለግሳው መልኩዋን በቅፅበት ወደ ጨለማነት ቀየረችው፡፡ በተቀመጠበት በአንድ ጊዜ አይኖችዋ ላይ ገነትን እና ሲዖልን ተመለከታቸው፡፡ ሰሎሜ መናገር ጀመረች፤
“በጥንቃቄ እንድታደምጠኝ እፈልጋለሁ። ስትሰማኝ ደግሞ እየፈራኸኝ መሆን አለበት። አለበለዚያ የማወራቸው ነገሮች በሙሉ ህልምና ቀልድ ሊመስሉህ ይችላሉ፡፡ መፍራት ትችልበታለህ?”….ኮስተር ብላ ጠየቀችው፡፡
ዘላለም ተገርሞ ሲያያት ከቆየ በኋላ አንድ ጊዜ በሀይል ሳቀ፡፡ ሰሎሜ መልክ ላይ ግን ምንም አይነት የስሜት ለውጥ አልታየም፡፡
“መፍራት እችልበታለሁ ብዬ አምናለሁ።” አለ ዘላለም፤ እጅግ በመደነቅ ስሜት ሰሎሜን እያያት፡፡
ሰሎሜ ከቦርሳዋ ውስጥ ብዙ አይነት ዚፖች ስትከፋፍት ከቆየች በኋላ፣ አንድ አነስ ያለ ሽጉጥ አውጥታ ደቀነችበት፡፡ ዘላለም ከተቀመጠበት ተስፈንጥሮ ለመነሳት ሲሞክር፣ ከጥልቁ የምድር ማህፀን ውስጥ እየተግተለተለ የሚወጣ በሚመስል የቁጣ ድምፅ ባለበት እንዲቀመጥ አደረገችው፡፡
“አንድ እንዳትንቀሳቀስ! አይዞህ እንድትፈራ ብፈልግም…መፍራት ያለብህ ግን እኔን ሳይሆን ራስህን ነው፡፡ ራስህን ፈርተህ በምታመጣው እውቀት እኔ መዳን እችል ይሆናል፡፡ ሀሳቤን ግልፅ ያደረኩልህ ይመስለኛል፡፡”
“ምን…እንዴት…ምን አድርጌሽ እንደሆነ ብቻ ነው ማወቅ ያልቻልኩት? ምን እንዳደርግልሽ ነው የምትፈልጊው?”
ሰሎሜ፣ ነፍሱን እንደ መፅሐፍ ገልጣ ያነበበችበት እስኪመስለው ድረስ አፈጠጠችበት፡፡
“ዛሬውኑ ራሴን እንድገድል የሚያደርግ ምክንያት እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ … ይህን ማድረግ ካልቻልክ ግን እኔ እገድልህና ጨዋታችን እዛ ጋ ያበቃል፡፡ ጨዋታውን ግን ስትጫወተው በኔና ባንተ መካከል ምንም አይነት የጊዜም ሆነ የቦታ ልዩነት እንደሌለ አምነህ ነው፡፡"
“ምን…?” አላት ዘላለም በሚሰማው ነገር ፍፁም ተገርሞ፡፡
“ራሴን እንዳጠፋ ማድረግ ካልቻልክ አጠፋሀለሁ፡፡ አሁን ሁሌም እንደምታደርገው ስራህን ጀምር፡፡ ጥያቄዎችህን ቀጥል፡፡ ገድለህ አድነኝ! “
ዘላለም የሚናገረው ጠፍቶት የሚንቀጠቀጠው እጁን ለማረጋጋት እየሞከረ ነው፡፡ ለቅፅበት ያክል ፍቅር መሳይ መሳሳብ የፈጠረችበት ሴት… ለድንገት ያህል ለኔ ብትሆን ብሎ የተመኛት ሴት… ውበትን የትም ቢያስስ የሷ አይን ላይ ሄዶ እንደሚያበቃ በደቃቅ ሰከንዶች ውስጥ ሲያስባት የነበረችው ሴት … ራሷን እንድታጠፋ እየጠየቀችው ነው፡፡ ዛሬ ብቻ እንዲያያትና ከዛሬ ጀምሮ እንዲረሳት የፈለገችውን አስገራሚ ሴት… እንዴት አድርጎ እንደሚያዋራት ከሀሳቡም ከእውቀቱም ሲያምጥ ከቆየ በኋላ ጥያቄውን ጀመረ፡፡
“በህይወት እየኖርሽ እንደሆነ ስታስቢ ምን አይነት ስሜት ይሰማሻል?”
ሰሎሜ ከተቀመጠችበት ሶፋ ላይ ራሷን ካደላደለች በኋላ፣ ለተጠየቀችው ጥያቄ መልስ መስጠት ጀመረች፡፡
“በመጀመሪያ በህይወት መኖር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ላለማሰብ ብዙ ተጉዣለሁ። ምናልባትም ይሄን ጥያቄ ለራሴ መመለስ ከጀመርኩ በኋላም ሊሆን ይችላል ራሴን ለማጥፋት የወሰንኩት፡፡ በአጭሩ መኖር የማልፈልገው ነፃነትን ፈልጌ ነው፡፡ ነፃ መሆን የፈለኩት ደግሞ ከራሴ ነው፡፡ ገፀባህሪው ግራ እንዳጋባው ተዋናይ የምመላለስ የምድር መድረክ ላይ ያለሁ እንግዳ ፍጥረት ነበርኩ ብልህ ይገልፀኛል፡፡ በህይወት ለመኖር እምነት ያስፈልግ ይሆናል …በምንም የምድርም ሆነ የሰማያት አለማት ላይ ባሉት ነገሮች እምነት የለኝም፡፡ በውሸትና ለሙከራ ተብሎ በተሰራ የምድር ቀፈት ውስጥ የተፈጠርኩ ስህተት አድርጌ ነው ራሴን የማየው፡፡ እውነት ነው እስካሁን ኖሬያለሁ…ግን ኖሬያለሁ? እሱን እኔም ለመረዳት ይከብደኛል፡፡”
“አሁን የምትይኝን ማንነት መቼና እንዴት ጭንቅላትሽ ውስጥ እንደተፈጠረ ልትነግሪኝ ትችያለሽ?” ዘላለም በሰሎሜ መልስ እጅግ ተገርሟል፡፡ ቀጥሎም ምን ልትመልስ እንደምትችል ማወቅ ስለተሳነው፣ መረዳቱን ከፊት አስቀምጦ በአይኖቹ እየጠበቃት ነው፡፡
“እዚህ ላይ የደረስኩት የአማልክቱን ተንኮል የተረዳሁ እለት ነው፡፡ የፈጠሩን ተንኮለኞች ናቸው፡፡ ምንም አይነት እጣፈንታም ሆነ ነፃ ፍቃድ የተባለ ቅዠት እንደሌለ ስረዳ ነው ጥልቅ የሆነ መሰላቸት ውስጥ የገባሁት፡፡”
“እጣፈንታም ሆነ ነፃ ፍቃድ የተባለ ቅዠት የለም ስትይ ምን ለማለት ፈልገሽ ነው?”
“አስተውለህ ስማኝ፡፡ እንደምታየኝ ሴት ነኝ…በጥሩ ኑሮ ላይ ያለሁም እንደምመስልህ አልጠራጠርም፡፡ ይሄ ሁሉ የሆነው እኔ መርጬ ይመስልሀል? የገጠመኞች ጥርቅም አንተን መፍጠር አቅም ካላቸው…የአንድ የልቤ የምትለው ሰው ሀሳብ መንገድህን መቀየስና ማስቀየር ከቻለ…ሰይጣንም በለው ቅዱስ መንፈስ እየተፈራረቁ በሀጥያትና በፅድቅና ጉዞ ውስጥ እየነከሩና እያወጡህ የማንነት ቀውስ ውስጥ በፍጥነት የሚዘፍቁህ ከሆነ…አደኩኝ አወኩኝ ባልክበት የእድሜህ ዘመን ውስጥ ውታፉ የማይሞላ ስፋቱ የማይደረስበት የማያልቅ እውቀት ውስጥ እንዳዲስ ራስህን የምታገኝበት አለም ላይ የምትኖር ከሆነ…እያኖርኩህ ነው ብሎ ቃል የገባልህ የምድር መንግስት መኖርህን እስክትጠላ ድረስ የእሱን እኔነት እያጠባህና እየጋተህ መተንፈስህን እስክትጠላ ካደረገህ….ሴትነቴ በምድርም ህግ ሆነ በሰማያዊውም እውቀት ውስጥ ያነሰና ለዘር መራቢያነት ብቻ የሚጠቀምብኝና በዚሁ መልክ ብቻ በሚያየኝ ማህበረሰብ ውስጥ የምኖር ከሆነ…. ይህ ሁሉ እየሆነብኝ እንደማንም ፈዛዛ ፍጥረት አብሬ ስፋዘዝና ሁሉም ለአዕምሮዬ የምገብረው እውቀት ህሊናዬን እየገባ የሚሞነጫጭርብኝ ከሆነ…..” ድንገት መናገር አቆመች፡፡
ዘላለም በጥልቀት ተመለከታት፡፡ የምር መሞት እንደምትፈልግ አመነ፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻለ እንደምትገለው …ጥልቀትን ብቻ የሚናገሩ አይኖቿ ውስጥ ገብቶ ተረዳት፡፡ ስለዚህ አንድ ነገር ማድረግ አለበት፡፡ ሰውን ማዳንና ሰውን መግደል ያላቸውን ልዩነት የሚያሰላስልበት ጊዜ ላይ አይደለም፡፡
ሰሎሜ በምድር ላይ ለመኖር ምክንያት ያጣችበትን ያክል፣ ለመሞትም በቂ ምክንያት የሌላት ሴት እንደሆነች አውቋል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚያወጣቸው ቃላት ወይ የሱን ወይ የሷን ህይወት እንደሚፈፅመው እርግጠኛ ሆኖ መናገር ጀመረ፡፡
“ሰሎሜ፤ እጅግ እንግዳ የሆነ ነገር ውስጥ ነው የከተተሺኝ፡፡ ሆኖም ለሰማሁት ነገር አስተያየት መስጠት ስላለብኝ እናገራለሁ፡፡ እንደሰማሁሽ ከሆነ ከህይወት ምንም አይነት ትርፍ እንደማይገኝ እያሰብሽ ነው ያለሽው፡፡ ይሄን ደግሞ ሊያግዙንና መፍትሄ እንዲሰጡን ካበጀናቸው መንገዶች መካከል ሀይማኖትና ፍልስፍና ናቸው፡፡ አንቺ ደግሞ ሁለቱንም በርብረሽ መፍትሄ አላገኘሽባቸውም፡፡ በምድር ላይ ለመኖርሽ ምክንያት ለመፈለግ በእውቀትሽ ብትባዝኝም እውቀትሽ እየወሰደ የሚያገናኝሽ መሰልቸትሽ ጋር ነው፡፡
ሆኖም ለመኖርም ለመሞትም ምክንያት የምትፈልጊ ከሆነ እና ምንም አይነት አጥጋቢ መልስ ካላገኘሽ፣ ምናልባት የነዚህ ሁሉ ምክንያቶች መጥፋት ምክንያቱ አንቺ ልትሆኚ እንደምትችይ አላሰብሽም፡፡ በምድር ላይ ያጋጠሙሽና የሰው ልጅ የሚያየውን አበሳ ካንቺ በህይወት መገኘት ሚስጥር ጋር አዳቅለሽ፣ ለህይወትሽም ለሞትሽም ምክንያት መፈለግሽ ላይ ጥያቄ አለኝ፡፡ በህይወትና በሞት መካከል ያለውን ፀጥታ ግን እንዴት አድርገሽ ነው ለማድመጥ እየጣርሽ ያለሽው?”
ሰሎሜ በመሳሳት ስሜት ውስጥ ሆና ስትመለከተው ከቆየች በኋላ ጥያቄውን በጥያቄ መለሰችው፡፡
“ልክ ስገባና ስታየኝ በመጀመሪያ የተሰማህ ስሜት ምንድነው? የእውነትህን ብቻ ንገረኝ?”
ዘላለም ልቡ መቅለጥ ሲጀምር ታወቀው፡፡ ፀጥ ብሎ ዘላለም ቢመለከታትና ከዘላለም በኋላ ጥያቄዎቿን ቢመልስላት በወደደ ነበር፡፡ ሆኖም ሰሎሜ እሱን ከምድር እንዲሰርዛትና ፈጣሪዋን ደግሞ ዘላለሟን እንዲቀማት ነው እየተማፀነች ያለችው፡፡ በነዚህ ፅንፍ አስተሳሰቦች መካከል ያለውን ፀጥታዋን ተረዳላት፡፡ የሱን ፍልስፍና ተፈላስፋው የጨረሰች የመጨረሻዋ ሴት መስላ ታየችው፡፡ ምንም ነገር ቢነግራት ሁሉም ተስፋን ሳይሆን እውነትን የሚሰብኩ መሆን አለበት፡፡
“እንዳየሁሽ ፍቅር ነው የተዋሀደኝ፡፡ መረጋጋት ነው ቀድሞ የጎበኘኝ፡፡ ልታድኚኝ እንጂ ላድንሽ እንዳልመጣሽ ነው የገባኝ፡፡ አይኖችሽ የሞተ ማንነት ላይ ህይወት መተንፈስ ይችላሉ፡፡ ሰሎሜ….ሰሎሜ….. በፍቅር የተሰራሽ ፍጥረት ነሽ፡፡ ማየት እስክችል ድረስ አይቼሽ ፍቅር ብቻ አድምጬ ነው የተመለስኩት፡፡”
ሰሎሜ ያልጠበቀችው እንባ ጉንጩዋ ላይ በሀዘን እየነቀሰ መውረድ ጀመረ፡፡ ሆኖም ልትጠርገው አልፈለገችም፡፡
“ሰሎሜ…?” አለ ዘላለም፡፡
“የልብሽ ብሽቀት ድረስ ደርሼ ስመለከትሽ ራስሽን መግደል ሳይሆን የምትፈልጊው፣ አንቺ ውስጥ ያለውን…ምክንያት አምጪ እያለ የሚነዘንዝሽን…ምክንያት አልባ ማንነትሽን ነው መግደል የፈለግሺው፡፡ አለበለዚያ ከሞትሽም በኋላ ለምን ሞትኩ ማለትሽ አይቀርም፡፡ ያለፈቃዳችን የመጣንበት አለም ለስሜቶቻችን ደንታ እንደሌለው መረዳት አለብሽ…እኛ ነን ለህይወት ምክንያት የምንሰጣት እንጂ ህይወት ለኛ የምትሰጠን ነገር የላትም ብዬ ነው የማምነው፡፡ መልሱ የሚርቅ ከመሰለን ምናልባት እጅግ ቅርባችን ስለሚሆን ሊሆንም እንደሚችል መጠርጠር አለብሽ፡፡ ስለዚህ ሰሎሜ ልነግርሽ የምችለው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ እኔ ጋ የመጣሽው ለመሞት ምክንያት ፍለጋ ሳይሆን ላለመሞት ካለሽ ጉጉት ነው። ሞትን ስላልተረዳሽው ብቻ አይደለም መሞትሽን የፈለግሽው …ነገር ግን ህይወትን መረዳት ውስጥ የተደበቀ ሞት እንዳለ አውቀሽ ሞትን በሞት የምትሽሪው መስሎሽ ነው የመጣሽው፡፡ ሁለቱንም ብታደርጊ ሞትንም ህይወትም ድል አትነሺም… ድል ተነስተሽ ፈተናውን ትወድቂያለሽ እንጂ፡፡ ስለዚህ ሰሎሜ አትሙቺ፡፡ ኑሪና ሞትን ግደይው፡፡ እስካሁን ያሉትን ምክንያቶችሽን ገለሽ ራስሽን ፍጠሪው። ቅንድብ ለአይን ቅርብ ሲሆን አይን ግን ቅንድብን ማየት አይችልም የሚለውን አባባል ታውቂው እንደሆነ ባላውቅም፣ አንቺንም ግን በዚሁ አባባል ውስጥ ነው ያገኘሁሽ፡፡ ራስሽን እንድትገዪ ማድረጉ አቅቶኛል ባልልም አንቺ ውስጥ ያሉትን ጥርጣሬዎችና ምሬቶችን ገድዬ እንደማድንሽ ቃል እገባልሻለሁ፡፡ አለበለዚያ ግን አሁኑኑ ግደይኝ እና የሁለታችንንም የህይወት ምዕራፍ ዝጊው፡፡”
ዘላለም ይህን ተናግሮ…እንደጉድ የሚደልቀውን የልቡን ትርታ ለመቆጣጠር እየሞከረ በእንባዋ የብዕር ቀለም የተተረከውን የአይኗ ላይ ሀዘን እየተመለከተ ተጠባበቃት…ጠበቃት….ጠበቃት….ጠበቃት…..
ሰሎሜ በትካዜ ከምታየው ዘላለም ላይ አይኖቿን ነቅላ፣ ሽጉጡን ካወጣችበት ቦርሳዋ ውስጥ መልሳ ከተተችው፡፡ ከተቀመጠችበት ረጋ ብላ ተነስታ….
“ሰሎሜ አትሙቺ ነው ያልከኝ?” ብላ ጠየቀችው፡፡
“አዎ ሰሎሜ አትሙቺ፡፡” አላት ድምፁን ጠንከር አድርጎ፡፡
ሰሎሜ ምንም ሳትናገር ክፍሉን ለቃ ወጣች። ዘላለም እንደደነገጠ በሩ ላይ ፈዝዞ ለሰዓታት ተቀመጠ፡፡
ሰሎሜን ከዛን ቀን ጀምሮ አይቷት አያውቅም፡፡ በህይወትና በሞት መካከል ያለ ፀጥታ ነች…ሰሎሜ፡፡ ትሙት ትኑር የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ሆኖም በህይወት ውስጥ ምክንያት ማጣት የት ድረስ ህሊናን እየጎተተ ምን ውስጥ እንደሚሰትረው ጥርት አደርጎ ተምሯል…ከሰሎሜ፡፡ ተጀምሮ ያላለቀ መፅሐፍ ሆናበት ተሰወረች፡፡ ያላለቀውን መፅሐፍ የሚጨርሰው እሱ እንደሆነ ያውቃል …የሚጨርሰው በቃላት አይደለም…በመኖር ነው፡፡
Saturday, 22 July 2023 00:00
“ሰሎሜ ….አትሙቺ…?”
Written by ኪሩቤል ሳሙኤል
Published in
ልብ-ወለድ