Saturday, 05 August 2023 11:17

"ሰበበኛ ድህነት ከማለዳ ይጀምራል"

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ዓለም ገና እንደተፈጠረችና ጊዜ መቆጠር ሲጀምር ማንከስ የተባለችው የቤት ድመት ጭራ ነበራት ይባላል። በጣም ግሩም

ጭራ። ረዥም፣ እንደ ነብር ዥንጉርጉር፣ የሚያኮራና የሚያጎማልል።
ማንከስ ድመት ኩሩ ናት። ጭራዋን ሽቅብ አቁማ ቀና ብላ ስትጎማለል ኩራቷ በማንም እንስሳ አይደረስበትም። ስታድንና

ስትተኛ በስተቀር ጭራዋን አትሸመልለውም።
የማንክስ ድመት ጠባይ ከመጠን ያለፈ ልበ-ሙሉነት፣ ከልክ-ያለፈ ራስን በራስ በማኖር ማመን፣ በፍፁም በሌሎች

አለመመራትና የራሷን ደመ-ነብስ መከተል ነበር።ታዲያ አንድ ጊዜ አደገኛ የጥፋት ውሃ ሊመጣ ሆነ። አምላክ በሰው ልጆች ድርጊት ተቆጥቶ ነው ይህ ጥፋት የሚደርሰው።
ስለዚህም ይማሩ ዘንድ ይሄ ጥፋት ውሃ መጣ።አምላክም ኖኅ መርከብ እንዲሰራና ከየእንስሳቱ ሁለት ሁለት እየያዘ በመርከቡ እንዲያመልጥ አዘዘው። ኖኅ መርከቡን ሠራ።
ለመሄድም ዝግጁ ሆነ። አምላክ ለሁሉም እንስሳት እንዲህ አለ፤ “ሁላችሁም ሁለት ሁለት እየሆናችሁ ወደ ኖኅ ሂዱ። ወደ መርከቡም ግቡ። እስከ ጎርፉ ፍፃሜ ቀን እሱ ይንከባከባችኋል” አላቸው።
ሁሉም እንደታዘዙት ፈጸሙ። አንዲት እንስሳ ብቻ ትዕዛዙን አልሰማ አለች። ይህች እንስሳ ማንከስ ድመት ናት።
“የምሰራው ስራ ስላለኝ ለመምጣት አልችልም። ገና አደን አለብኝ። ለምግቤ አይጥ ልፈልግ እሄዳለሁ” አለችና ወደ አደኗ
ተሰማራች። ሌሎቹ እንስሳት በመርከብ ተሳፈሩ።
ጥቂት ዝናብ ማካፋት ጀመረ። ኖኀ ያልገቡትን በማስገባት ሥራ ተጠመደ። ማንከስ ድመትንም “አይርፈድብሽ፣ በጊዜ ነይና
ተቀላቀይ። አሁኑኑ ነይ” አላት።
ማንከስም፤ “አሁን እንኳን ለመምጣት ዝግጁ አይደለሁም። ደግሞም አንተ በፈለግህበት ሰዓት ሳይሆን እኔ በፈለግሁበት ሰዓት
ነው የምሄደው” አለችና ጢሟን እያሸች፣ እየተጎማለለች ሄደች።ኖኅ የመጨረሻዎቹን እንስሳት ሲያስገባ ዝናቡ ዶፍ መጣል ስለ ጀመረ የመጨረሻ ጥሪ አደረገላት- ለማንከስ ድመት። በሩን
መዘጋጋት ቀጠለ። ልጆቹና  ቤተሰቦቹ መርከቡን እየጎተቱ ማንቀሳቀስ ጀመሩ።ማንከስ ድመት ጸጉሯን ዝናብ ሲያበሰብሰው ታወቃት። ቀዝቃዛና ዶፍ የቀላቀለ ዝናብ ነበር። ፍርሃትና ራዕድ አስከተለባት።
ይሄኔ ኖኅን አለመታዘዝ ጅልነት ነው ብላ አሰበች። ከሌሎቹ እንስሳት ጋር ወደ መርከቡ ካልሄደች የጎርፍ ሲሳይ እንደምትሆን ገባት።ዘላ ወደ መርከቡ ጥልቅ አለች። በሩ የመጨረሻውን ክፍተት እየዘጋ ነበር። ማንከስ ድመት ገብታ ከጨረሰች በኋላ ጭራዋ ታንቆ ቀረባት። በጣም አሳመማት። ስቃይ ሲበዛባት መጮህ ጀመረች። ኖኅ አዝኖ አከላትዋን አስለቀቀላት። ሆኖም ውቡን ጭራዋን
ሊያድንላት አልቻለም። እንደ ነብር ጅራት የተዥጎረጎረ ጭራዋ ተጎምዶ ወደቀ። በተጠራች ሰአት ያልመጣችው የማንከስ
ድመት ዘለአለሟን ጎራዳ ጭራ ሆና ቀረች።

***
ለማንኛውም ነገር ማርፈድ ጎጂ የመሆኑን ያህል፤ በምንፈለግ ሰዓት አለመምጣት እጅግ በጣም ጎጂ ነው። የጥፋት ውሃ

እስኪመጣ መጠበቅ ኋላ የእውር ድንብር መሄድን ያስከትላል። ወቅታዊ የሀገር ጥሪ ወቅታዊ ምላሽ ይፈልጋል።
የግለሰብ፣ የድርጅት ወይም የፖለቲካን ፍላጎት፣ ከሀገር ፍላጎት ማስቀደም የብዙሃንን ችግር ያወሳስባል። የብዙሃንን ብሶት

ያባብሳል። አልፎ ተርፎም ለውድቀት ይዳርጋል። የሕዝብን በደል ጩኸት፣ የህዝብን ወዮ ጥሪ አለመስማት የሀገርን ጉዳይ ቸል

ከማለት አንድ ነው። የገቡትን ቃል አለመፈጸም ለሀገር ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ ከማለት አንድ ነው። በዲሞክራሲያዊነት ስም ኢ-

ዲሞክራሲያዊ መሆን የሀገርን አደራ ከመብላት አንድ ነው። ሲፋጅ በማንኪያ፣ ሲቀዘቅዝ በእጅ መብላት ከአታላይነት አንድ

ነው። ፍትሐዊነትን እንደ መመሪያ እየጠቀስን፣ አድልዎን በየፋይሉ ላይ ከፈረምን የጥፋት ውሃው አካል ነን ማለት ነው።

በመላው አገር ላይ የተንሰራፋውን ድህነት፣ ከአናት እስከ ግርጌ የወረረንን በሽታ፣ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የለከፈንን ሙስና፣ በበር

ስንሸኘው በመስኮት የሚገባውን ጦርነት፣ ልማት እያወራ ልፋት የሚያስከትለውን ዋልጌ ሃላፊ፤ ወዘተ የምናስወግድበትን

መንገድ በጋራ ለመቀየስ በልባዊ ዲሞክራሲያዊ ስሜት ካልተነሳሳን እንደ ድመቷ ጅራታችንን ተቆርጠን እንኳን የምንድንበት

የኖኀ መርከብ አይኖረንም።  ከየፖለቲካ ድርጅቱ  ከየቡድኑ ከየአይነቱ  ሁለት ሁለት ሰው ጭኖ ከጥፋት ውሃ የሚያድን

መርከብ እንኳ ከቶም የለንም። ሁሉም የጥፋት ውሃው ተሰምቶት ካልተረባረበ፣ በአንድ ኖኅ ቀርቶ በሺህ ኖሆች ሊሰራ የሚችል

መርከብ ከቶ አይኖረንም።
በእርዳታ ሊገኝ የሚችልን ገንዘብ ለማግኘት አለመቻል አንድ ጥፋት ነው። በእርዳታ የተገኘን ገንዘብ በአግባቡ አለመጠቀም

ከባድ ጥፋት ነው። በእርዳታ የተገኘን ገንዘብ በዚህም ሆነ በዚያ ምክንያት  ከነጭራሹ ሳይጠቀሙ መቅረት የጥፋት ውሃ ነው።

ህዝብ በበሽታ እያለቀ በህዝብ ስም የተገኘን ገንዘብ በቢሮክራሲያዊ ሰበብ ስራ ላይ አለማዋል አንድ ትውልድ ላይ ወንጀል

እንደመፈጸም የከፋ እኩይ ተግባር ነው።  
ለወቅታዊ ጥሪዎች ወቅታዊ ምላሽ ሊሰጡ የሚችሉ የፖለቲካ አውሎ ንፋስ በማነሳሳት “ጨሰ! አቧራው ጨሰ” የሚሉቱ

ሳይሆኑ፣ የሀገርና የህዝብ ችግር የሚቆረቁራቸው አስተዋይ ወገኖች ብቻ ናቸው። አስተዋይ ያልሆኑቱ በወቅታዊ ምላሽ ፈንታ

ወቅታዊ ምላስ ነው የሚሰጡት። ዛሬ ባለንበት ሁኔታ ለሀገሩ ቀና አሳቢውን ሃላፊነት የሚሰማውን፣ ለቅርብ ፍላጎት ሳይሆን

ለሩቅ እድገት የተነሳውን፣ ለጊዜያዊ ግምገማ ሳይሆን ለዘላቂ ግብ የቆመውን፣ ለድርጅት ስሜት የሚደሰኩረውን ሳይሆን ለሀገር

በመስጋት የሚቃጠለውን፣ አበጥሮ ለማየት አያዳግትም። “እንደምነህ አትበል ፊቱን እየው” ነውና።
አዲስ ሹም በመጣ ቁጥር ከዜሮ የመጀመር ፈሊጥ ሌላው የጥፋት ውሃ ማባባሻ ነው። በተጣለ መሰረት ላይ የቆመን ጠማማ

ማገር ማቃናት ወይም መንቀል አንድ ነገር ነው። መሰረቱን አልፈልገውም ብሎ እርጥብ-ከደረቅ ማንደድ ግን ሌላ ነገር ነው።  

ጎጂ ነው። “አይብ አይተው አሬራ ይደፋሉ” እንዲሉ አዲስ ሀሳብ ብልጭ ባለ ቁጥር በእጅ የያዙትን ሁሉ በትኖ ሆይ ሆይ ማለት

ብዙ መንገድ አያስኬድም። ስር የያዘን ነገር ማስተዋል ለማገርም ለጣራም አቅም ይሆናል። በአንጻሩ አዲስ ሹም አዲስ ስለሆነ

ብቻ ደግሞ ጭፍን ጥላቻ ማሳደር በጭራሽ አግባብነት የለውም። በአሮጌ አስተሳሰብ እንደ መኩራራት የሚያደነቁር

አመለካከት የለም። አዲስ ሹም፤ መዋቅርን፣ የሰው ሃይልን፣ አሮጌ አተያይን በአዲስ መልክ ለማሻሻል መጣሩ ነገን ለመቅረጽ

አንዱ ተስፋ ነው- ፍትሃዊ እስከሆነ ድረስ። ዲሞክራሲያዊ ባህል እስካለው ድረስ። ርቱእነትና ግልጽነት እስካልጎደለው

ድረስ። ለትክክለኛው ቦታ ትክክለኛ ሰው እሱ እስከሆነ ድረስ። “ጨካኝ እንጂ ሹም አትፍራ” የሚባለውም ይሄኔ ነው።
ሀገርን ከጎረቤት ሀገር፣ ሀገርን ከዓለም የሚያኖራት ዲሞክራሲያዊ ብስለትም ነው። ዲፕሎማሲያዊ አደራ የሀገር ጥሪ ነው።

ከመቼውም ጊዜ በላይ ዲፕሎማሲያዊ ብልህነት የሞትና ህይወትን መስመር የሚለይበት ወቅት ቢኖር ዛሬ ነው። የሀገር ጥሪን

መወጣት ከጥፋት ውሃ መዳን ነው። በጊዜ የኖኅ መርከብ መስራት ነው። በአጭር ጊዜ የኖኅ መርከብ መስራት ቢሳን ብዙ

ታንኳዎችን እየሰሩ መንገድን ማቀላጠፍ ነው። አቅም ግንባታ፣ ያለንን አቅም ከመጠቀም ነው የሚጀምረው። ሜዳው ላይ

መሮጥ ሳይቻል ተራራ መውጣት ዘበት ነውና። እንደ ጥንቱ፣ ሹሙ ሀገር ውስጥ ጥፋት ሲበዛበት የውጪ ዲፕሎማት አድርጎ

ገለል ማድረግ፣ ዛሬ ዘዴ ሳይሆን ሀገርን መበደል መሆኑ ፍንትው ብሎ የታየበት ዘመን ነው።
የተወሳሰቡት ችግሮቻችን አንዱ ካንዱ ጋር የተጠላለፉ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዳቸው ስር የሰደዱ መሆናቸው ነው

አልነቀል እንዲሉ የሚያደርጋቸው።  በችጋር ላይ ችጋር እየተደራረበ ከድህነት በታች አድርጎናል። እጅግ ጥልቅ ድቀት

በመሆኑና የድህነታችን ቅርንጫፎች በመብዛታቸው ለድህነታችን ተጠያቂው እንኳ ማን እንደሆነ በውል ለመለየት ያቃተ

ይመስላል። ዛሬ ጫፉ ላይ የደረሰውን የኢኮኖሚ መቆርቆዝ የሰበቡን ምንጭ ካላየንና ካልፈታን የአናቱን ችግር አንቀርፈውም።

መፈክር እያሰገርንና በዘመቻ ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮች ናቸው እያልን በምንረባረብባቸው ጉዳዮች ላይ ብዙ ሃብትና የሰው

ኃይል ከመፍሰሱ በፊት አስቦ፣ አበጥሮ የሚያይ አዋቂ ያሻቸዋል። ድህነት ስር መሰረት እንዳለው፣ የሚናገር ሳይታክት

የሚፈትሽ በአንድ አቅጣጫ እያየ ምርምር ጨርሻለሁ የማይል፣ ሆደ-ሰፊና አዕምሮ ብሩህ ሰው ያስፈልገናል። አሁንም አዲስ  

መንገድ ለመቀየስ የሚደፍር አዋቂ ሊኖር ይገባል።
አዋቂው “ሰበበኛ ድህነት ከማለዳ ይጀምራል” የሚለውን ተረት በቅጡ ለማጤንና ለማሳየት ዕውቀትም፣ ድፍረትም አያጣምና!

Read 1725 times