Saturday, 05 August 2023 11:40

ድምፃዊ ብሥራት ሱራፌል ስለ አዲሱ “ማለፊያ” አልበሙ በተለይ ለአዲስ አድማስ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

“ማለፊያ መንገድ ነው፣ ማለፊያ ጊዜ ነው፣ ማለፊያ ተስፋ ነው”

“ሄድ መለስ” (ወጣ ፍቅር ወጣ) በተሰኘው ስራው ነው ይበልጥ የአድማጭ ልብ ውስጥ የገባው፡፡ “እንደኔ ነወይ” እንዲሁም “ሆንሽብኝ የቤት ስራ” እና ሌሎችም ሥራዎች ተወደውለታል ድምፃዊና የዜማ ደራሲው ብስራት ሱራፌል፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት “ቃል በቃል” የተሰኘውን የመጀመሪያ አልበሙን ለአድማጭ ያደረሰው ተወዳጁ ድምፃዊ፤ እነሆ አሁን ደግሞ “ማለፊያ” የተሰኘ ሁለተኛ አልበሙን ከሰሞኑ ጀባ ብሏል፡፡ ብስራት ሱራፌል “ማለፊያ ሁሉ መኖሪያ አይደለም” እያለ ነው፡፡ ምን ማለቱ ይሆን? አዲሱ አልበሙ ከቀድሞው በምን ይለያል? ሁለተኛ አልበሙን ለማውጣት ለምን አምስት ዓመት ፈጀበት? በሚሉትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቶት ዮሴፍ ጋር በስፋት አውግተዋል፡፡ እነሆ፡-

ወደ አዲሱ አልበምህ ከመምጣታችን በፊት ትንሽ ወደ ኋላ መለስ እንበልና ከህዝብ ጋር በደንብ ያስተዋወቀህ “ወጣ ፍቅር ወጣ” የተሰኘው ስራህ ይመስለኛል፡፡ ልክ ነኝ?
እውነት ነው፤ ማለት ይቻላል። “መንገደኛ” አልበም ላይ ከሰራኋቸው አራት ስራዎች አንዱ ነው… “ሄድ መለስ” ወይም “ወጣ ፍቅር”። ከዚያ በፊት ግን “እንደ እኔ ነው ወይ” የተሰኘ ነጠላ ዘፈን ለቅቄ ነበረ። ዜማው የአባቴ የሱራፌል አበበ ሲሆን፤ ግጥሙ ደግሞ የይልማ ገ/አብ ነው። የሆነ ሆኖ “ሄድ መለስ” የሚለውን ዘፈን ከማውጣቴ በፊት የተለያዩ ስልተ-ምቶች ያሏቸው ዘፈኖችን ነበር የምጫወተው። ይህን ዘፈን ከተጫወትኩ በኋላ ግን የራሴ መለያ የሆነ ስልተ-ምት እንዲኖረኝና ራሴን እንዳውቅ ያደረገኝ ብሎም ከህዝብ በደንብ ያስተዋወቀኝ ስራ ነው እንዳልሽው። ከዚያ በኋላ እንደ “ሆንሽብኝ የቤት ሥራ” አይነት ጥሩ ሥራዎችንም እንድሰራ መንገድ ጠርጎልኛል፤ እናም “ሄድ መለስ” (ወጣ ፍቅር) እውነትም ይህ ነገር ያምርብኛል ብዬ ስልተምት እንድመርጥ እስከማስቻል አቅም የፈጠረልኝ ዘፈን ነው።
የመጀመሪያ አልበምህ “ቃል በቃል” የተሰኘ ነበር። እስኪ ትንሽ ቆይታ እናድርግበት፡፡ የመጀመሪያ አልበምህ የጠበቅከውን ያህል ውጤታማ ነበር ወይስ ነጠላ ዜማዎችህ ተፅዕኖ አሳርፈውበታል?
የመጀመሪያ አልበሜ በጣም ጥሩ ነበር። 12 ዘፈኖችን የያዘ ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ ዜማዎችም የእኔ ናቸው፡፡ ግጥሞቹን ከወዳጆቼ ጋር በመሆን ነበር የሰራናቸው። “ሄድ መለስ” (ወጣ ፍቅር) ሞራል ሆነኝ፤ ትንሽ የገንዘብ አቅምም አገኘሁ። ስቱዲዮ ውስጥ ከፍዬ ማሰራት እንድችል ያደረገኝ ይሄው ስራዬ ነው። “ቃል በቃል” አልበሜ በጥራት እንዲሰራ ትልቅ አስተዋጽኦ ስለነበረው፣ የመጀመሪያ አልበሜም በነጠላ ዜማዎቹ ሳይዋጥ ጥሩ ተቀባይነት አግኝቶ በደንብ ተወድዶ ነው የከረመው። እንዲያውም ከጠበቅኩት በላይ ነበር። የተለያዩ ስቱዲዮዎች ገባሁ፤ እነ አበጋዝ ጋር ለማሰራት አቅም አገኘሁ። በጥራት ተሰራ፤ ጥሩ ተቀባይነትም አገኘ።
ከ”ቃል በቃል” አልበምህ በጣም የተደመጠው “የቤት ስራ” የሚለው ዘፈንህ ይመስለኛል፡፡ ሌሎችስ እንዲህ ነጥረው የወጡ አሉ?
እውነት ነው “የቤት ስራ” በጣም ተደምጧል። ቀደም ብዬ ለቅቄው በኋላ “ቃል በቃል” አልበም ውስጥ ያካተትኩት ጥሩ ስራ ነው። ሌላው ከልጅ ሚካኤል ጋር የተጫወትነው “ኦላላ” እንዲሁም የአልበሙ መጠሪያ የሆነው እራሱ “ቃል በቃል” በደንብ ተወድዶ የተደመጠ ስራ ነው። “ጎዳናው”፣ “አትንኳት”፣ “ወይንዬ”፣ “ዛሬም ከኋላ” “ኢትዮጵያዊ ነኝ” እና ሌሎቹም ጥሩ ናቸው፤ እውነት ለመናገር፡፡
አሁን የተገናኘነው በዋነኝነት ሁለተኛ አልበምህን “ማለፊያ”ን ምክንያት በማድረግ ነው፡፡ ዛሬ አልበሙ ከተለቀቀ አራተኛ ቀኑ ነው፡፡ ግን “ማለፊያ”ን ለማግኘት 5 ዓመት ያስጠበቅከን ማለፊያ የሆነ ሥራ ልትሰጠን ነው? ለምን ይህን ያህል ዓመት ለማለት ነው?
የመጀመሪያውን አልበሜን በለቀቅኩ በነጋታው ይህን አልበም ለመስራት ስቱዲዮ ስራ ጀምሬያሁ። በነጋታው ነው የምልሽ! ስቱዲዮ እንደገባሁ አበጋዝን አገኘሁት፡፡ በእርግጥ የዛን ቀን ለሌላ ሰው የዜማ ድርሰት ለመስራት ነበር የገባሁት፣ እና ሲያየኝ “እንዴ ብስራት ገብተሃል እንዴ ምን እየሰራህ ነው?” ሲለኝ ቀጣይ አልበሜን ጀምሬ ነው አልኩት፤ በጣም ገረመው፡፡
ለአበጋዝ እንደቀልድ ነበር እንደዛ ያልኩት ግን በቃ ጀመርኩት፡፡ ይሄው ሁለተኛ አልበሜም ተለቅቆ እዚሁ ስቱዲዮ ነኝ እንደምታይኝ፡፡ ምክንያቱም ለኔ ሙዚቃ ሥራዬም መዝናኛዬም ነው፣ የት እሄዳለሁ፡፡ የራሴም ባይሆን የምሰራላቸው ልጆች ስላሉ በቅርበት መገናኘት ስራውን መከታተል ግዴታዬ ነው፡፡ የሙሉ ሰዓት ሥራዬም መዝናኛዬም በቃ ሙዚቃ ነው፡፡
አንዳንድ ዘፋኞች በወርም በአንድ አመትም አዳዲስ ስራዎችን ለአድማጭ ያደርሳሉና አንድ አልበም 5 ዓመትና ከዚያ በላይ ጊዜ ወሰደ ሲባል ፌዝ የሚመስላቸው አሉ፡፡ አንተ ሙዚቃ የሙሉ ጊዜ ስራህ ከሆነ እንዴት 5 ዓመት ወሰደብህ?
ምናልባት በ3 ወር የሚለቅ ድምፃዊም ሊኖር ይችላል፣ ነገር ግን ለሰው የምትሰጪው ምንድን ነው የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ ያ ሰው በስምንት ወርም ይሁን በ1 ዓመት ጨርሶ ከለቀቀው በቃ ጨርሶታል። ውስጡ ይሄ ስራ አልቋል ብሎታል ማለት ነው፡፡ አንዳንዴ 10 ዓመትም የሚወስድበት ጊዜ አለ፤ ነገር ግን የዘፈን ጥሩነቱ 10 ዓመት፣ አምስት ዓመት ወይም አንድ ዓመት  ስለቆየ አይደለም። አንድ ስራ ስትሰሪ ግጥምና ዜማው ሊመጣልሽ ይችላል፡፡ ከዚያ ደግሞ ሙዚቃ የሚባለው ጣጣ አለ፡፡ ሙዚቃ የሚባለው ነገር መጥቶልሽ ደግሞ አዘጋፈንን በትክክል ከሙዚቃው ጋር ለመስፋትና ለማዋሃድ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ይሄም ታሽቶ ሲመጣ ሚክሲንግ የሚባለው ጉዳይ ሌላ ራሱን የቻለ ታሪክ ነው፡፡ ምክንያቱም እዚህ አገር ላይ ውስን ሰዎች ናቸው ሚክሲንግ እየሰሩ ያሉት፡፡ አቀናባሪ ብዙ አለ፤ ሚክሲንግ የሚሰሩ ግን ጥቂት ናቸው፡፡ ሚክሲንግ ማለት ድምፅሽን ከሙዚቃ ጋር አጣጥሞ እኩል እንዲሆነና ድምጽሽ ከሙዚቃው፣ ሙዚቃውም ከድምፅሽ እንዳይበልጥ መጥኖ የማዋሃድ ሥራ ነው። ቀጥታ የገቡ የሙዚቃ መሳሪያዎች እንዳይረብሹ አድርጎ የመቀመር ስራ ነው። ይሄ ራሱ ጥንቃቄ፣ ትኩረትና ጊዜን ይፈልጋል። አንዳንዶቹ የሙዚቃ ስራውን የያዙት ራሳቸው ሚክስ ያደርጋሉ። አንዳንዶቹ ለሌላ ሰጥተው ነው የሚያሰሩት። ይህን  ሁሉ  ላሟላ ሥትይ ብዙ ጊዜ ይወስዳል።
የሙዚቃ ስራ ራሱን የቻለ ኬሚስትሪ ነው በለኛ…?
በደንብ እንጂ! ይህን ሁሉ ሥራ በጥንቃቄ አልፈሽ ነው ጥሩ ሥራ ለሙዚቃ አፍቃሪው የምታደርሽው። ሌላው አንድ አልበም አምስትና አስር ዓመት ፈጀ ሲባል፣ በቀን በቀን እየተሰራ አይደለም። በመሃል ሌላ ሥራ ይመጣል። ኮንሰርትንም ጨምሮ ለሌላ ሰው ሙዚቃ ፕሮዲዩስ የማድረግም ነገር ውስጥ ትገቢያለሽ። ይህ ሁሉ ጊዜ ይፈጃል። ታዲያ እነዚህ በ6 ወርና በአንድ ዓመት ሙዚቃ የሚለቁት ሰዎች ይሄ ሁሉ ጫና የለባቸውም ወይ ከተባለ ሁለት ነገር የሚመስለኝን ልንገርሽ። አንደኛ ሌላውን ሥራ እርግፍ አድርገው ወደ ጎን ትተው አልበሙ ሥራ ላይ ብቻ ተጠምደው ሊሰሩ ይችላሉ። በሌላ በኩል የሰሩት ግጥም ዜማና ቅንብር በቅቶታል ብሎ ውስጣቸው አምኗል የሚል ግምት ነው ያለኝ። አንዳንዴ አንድ ሥራ ሰርተሽ ትገመግሚና በቅቶታል ወይ አልበቃውም የሚለውን ነገር መወሰኑ ላይ ነው ጉዳዩ ያለው። እና ይሄ ችግር ነው ብዬ አላስብም።
እኔ እንኳን ጥያቄውን ያነሳሁት ጊዜን በተመለከተ አንዳንድ ሰው ድምጽ ብቻ ኖሮት ግጥምም ዜማም፣ ቅንብርና ሚክሲንግ ከሌላ ሰው ይጠብቃል። አንተ ጥሩ የዜማ ደራሲ ነህ። የሁሉም ዘፈኖችህን ዜማ ሰርተሃል፣ የግጥም ሀሳቦችህንም አንተነህ ለገጣሚዎቹ የምትሰጠው። ይሄ ሁሉ በእጅህ ሆኖ እንዴት ይህን ሁሉ ዓመት ጠበቅን ለማለት ነው። አሁን ተመልሶልኛል…
እውነት ነው። በኔ በኩል ያልሽው ትክክል ነው። እንዳልኩሽ ወደ መድረኩ ሥራ እየገባሁና የሌሎችን ሙዚቀኞች ሥራ ፕሮዲዩስ ወደ ማድረጉ እየሄድኩ፣  ሄድ መለሱ ነው አንድም ጊዜ የሚወስደው። ለምሳሌ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ10 በላይ የሌሎች ሰዎች ሙዚቃዎችን ፕሮዱዩስ አድርገናል።
አዲሱና ሁለተኛው አልበምህ “ማለፊያ” ይሰኛል። አንድ ሰው አንድን ነገር “ማለፊያ” ነው ሲል ቆንጆ ነው ጥሩ ነው ሸጋ ነው፣ የሚል ትርጉም አለው። በሌላ በኩል ማለፊያ፣ መሸጋገሪያ፣ መሄጃ ማለትም ይሆናል። የአንተ አልበም ትርጉም ወደየትኛው ይወድቃል?
ወደ ሁለቱም! ቆንጆ ብትይው ቆንጆ ነው፤ አልበሜ ምን ይወጣለታል? መሸጋገሪያ ወደሚለውም ብትወስጅው ይሆናል። አሁን በብዙ ችግሮች ውስጥ አይደለ ያለነው? ይህ አሁን ያለንበት ጊዜ ወደ መልካም ነገር መሸጋገሪያ ነው። በአልበሙ መጠሪያ ሥር እንዳየሽው “ማለፊያ ሁሉ መኖሪያ አይደለም” የሚል አለ። አሁን በምንም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ማለፊያና መሻገሪያችን ነው። ዛሬ ላይ ሆነን ነው ነገን አሻግረን የምናልመውም የምናየውም። እኔ ለምሳሌ የመጀመሪያ አልበሜን ለመስራት ብዙ ነገር አልፌአለሁ። ፖስተሬ ተለጥፎ ለማየት፣ የራሴን ሲዲ ማጫወቻ ውስጥ ከጥቼ ለማዳመጥ ብዙ ጉጉት  ነበረኝ። ልክ ያንን ይዤው ወደ ኋላ ዞር ስል ብዙ የማልፈልጋቸው ነገሮች አብረውኝ መጥተዋል።
ለምሳሌ ምን ምን ነገሮች?
በጣም ብዙ ነገሮች። ለምሳሌ፡- ለቤተሰብ ጊዜ አለመስጠት ሊሆን ይችላል። በቀላሉ እዚሁ እያለሁ እናቴ ልትናፍቀኝ ትችላለች። እኔ ከእናቴ ጋር ያለኝ ትስስር የተለየ ነው። እንደ እናትም፣ እንደ ጓደኛም እንደ እህትም ጭምር ነው፤ ቅርርባችን፤ ግን ሳላገኛት ውዬ የማድርበት ጊዜ ብዙ ሊሆን ይችላል። ብቻ ብዙ ነገር። አንድን ነገር ይዘሽው ዞር ስትይ ብዙ የማትፈልጊው ነገር አብሮሽ መጥቷል። ነገር ግን አልፈሽዋል። አሁንም ከአንደኛ አልበሜ ወደ ሁለተኛ አልበሜ ስመጣ እንደዛው ነው። አሁንም ይሄንን ይዤ ወደ ሶስተኛው እጓዛለሁ። በአጠቃላይ አሁን ለነገ ማለፊያና መሸጋገሪያ እንጂ መኖሪያ አይደለም የምለው ለዚህ ነው።
ማለፊያ ሲል ነው ማለፊያ
ሰው የማይድን ከሀሳብ ጥድፊያ
ማለፊያ ሲል ነው ማለፊያ
ሰው የማይድን ከሀሳብ ካፊያ
…ይላል ዘፈኑ። አንቺ ቀደም ብለሽ ባነሳሽው “ማለፊያ ጥሩ፣ ቆንጆ ነው” በሚለውም ግን ያስኬዳል። ጥሩ ስራ እንደሰራሁ ይሰማኛል።
ከአልበምህ ሁለት ዘፈኖች ላይ እናውጋ። “ምን ይላል ይሄ” እና “አባብዬ የሚሉት ላይ። “ምን ይላል ይሄ” በሚለው ዘፈን ውስጥ እንዲህ የሚል ስንኝ አለ፡-
ሺህ ዓመት ማን ለኖረበት ለአላፊው ለአጭሩ ኑሮ
ፍቅር እንዴት ይሸሻል የማይሆን ሰበብ ደርድሮ
እንኳንስ ሰበብ ለመፍጠር እንኳንስ ለመጠራጠር
ተስማምቶ አብሮ ለመኖር አልበቃም የጊዜው ማጠር…  
ምን ይላል ይሄ… እያለ ይቀጥላል። ይሄን ዘፈን በማህበራዊ ትስስተር ሚዲያ ላይ ሰዎች የፖለቲካ ቅርፅ ለማስያዝ ሲሞክሩ እያየሁ ነበር፤ ግን ደስ የሚል ሀሳብ አለው አንተ በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ?
“ምን ይላል ይሄን” ሳስብ መጀመሪያ እንዳልኩሽ ብዙ ጊዜ የሚወስድብኝ ሀሳብ ነው። መጀመሪያ ምን ልበል ፣ ምን ልበል የሚለውን አስባለሁ። ከዚያ ሀሳቡን ካገኘሁት በኋላ በምን አይነት መልኩ ልናገር የሚለውን አውጠነጥናለሁ። ለዚህ ምን አይነት ዜማ ይመጥናል? ከዚያ ከእኔ ድምጽ ጋር እንዴት ይዋሃድ? እንዴትስ ብዘፍነው ያምርብኛል? የሚሉት ነገሮች ጊዜ ይወስዱብኛል። “ምን ይላል ይሄን” ስሰራ መጀመሪያ የመጣልኝ ከላይ እንደገለጽሽው “አልበቃም የጊዜው ማጠር” የሚል አለ። ጊዜው በጣም ይሮጣል፤ በዚያ ላይ ያጥራል። ጥድፊያ አለ በቃ ጊዜው አይበቃም። እኔ ዛሬ ላይ ሆኜ ያ “ቃል በቃል” አልበሜ  ከወጣ አምስት ዓመት እንደሆነው ሳስብ ይገርመኛል። በቅርቡ እንደወጣ ነው የሚሰማኝ። እና ይህን አሰብኩና ኢዮቤል ብርሃኑን ኢዮባ ጊዜው እያጠረ ነውና እንኳን ተጣልተን ተናቁረንበት ተዋደንም አልበቃምና በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ነገር እንስራ” አልኩት። እኔ ዜማውን ከስር ከስር እያልኩለት እሱ ግጥሙን ሰራው ማለት ነው። ሰው እንደየመረዳቱ ሊተረጉመው ይችላል። እኔ ግን ባለን አጭር ጊዜ ተዋደን ተደጋግፈን እንኑር ለማለት ነው የሰራሁት።
ሌላው “አባብዬ” የሚለው ዘፈንህ በእጅጉ መሳጭ ነው። አንዳንድ ጊዜ ዘፈኖች ወቅትን ሁኔታን ያስታውሳሉ። ለምሳሌ የአውድ ዓመት ዘፈኖችን ስናስብ ታደሰ አለሙ (ነፍስ ይማር) እንቁጣጣሽን ስናስብ ዘሪቱ ጌታሁን (ነፍስ ይማር) ወደ አዕምሯችን ይመጣሉ። ስለአባት ስናስብ ግርማ ተፈራ ነበር የሚመጣው። አሁን አንተ ተጨምረሃል። ዘፈኑን ለአባትህ አርቲስት ሱራፌል  አበበ ነው የሰራኸው ወይስ ለመላው ኢትዮጵያዊያን አባቶች?
“አባብዬ”  አባቴ ሱራፌል አበበ ለራሱ ሰርቶት ያለፈው ዘፈን ነው። ግጥሙም ዜማውም የአባቴ ነው። ነገር ግን ተጫውቶት የነበረው ድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋዬ ነበር። ጎሳዬ ዘፍኖት የመጨረሻ አልበሙ “ሲያመኝ ያመኛል” ላይ አልተካተተም ነበር።
ለምን ነበር ያልተካተተው?
ዘፈን በብዙ መልኩ ላይዘፈን ይችላል ወይ በሀሳብ ዘፈን ትመርጫለሽ፤ ወይ በሌላ ምክንያት። ብቻ አልተካተተም ነበር። እኔ አንድ ቀን አቤል ጳውሎስ ጋር ሄጄ እየከፈተ እያሰማኝ፣ “ይህን ዘፈን እኮ ጎሳዬ እኔ ጋር ገብቶት ነበር” አለኝ። በጎሳዬ ድምጽ ሰማሁትና ወደድኩት። ከዚያማ የራሴ ዘፈን ነው አልኩኝ። ምንም እንኳን ግጥምና ዜማው የአባቴ ቢሆንም ጎሳዬ ገዝቶ ነው የወሰደውና ባለመብት ነው። ነገር ግን ሳስፈቅደው ጎስሽ ያለምንም ቅሬታ ነው የፈቀደልኝ በዚህ አጋጣሚ ላመሰግነው እወዳለሁ። እኔም ለሱራፌል መዝፈን ነበረብኝ አለኝ። ቀጣይ አልበሙ ላይ ሊያካትተው ሃሳብ ነበረው፤ የሆነ ሆኖ ፈቀደልኝ። እኔም በጣም ስሜታዊ ሆኜ ዘፈኑን ወደ ራሴ አባት ጎትጉቼው ነበር፤ በኋላ ላይ ግን ከስሜታዊነት ትንሽ ወጣ ብዬ ለምን ለሁሉም አባቶች አይሆንም በሚል ጥቂት ሀሳቦች ቀያየርኩና ለሁሉም አባቶች እንዲሆን አድርጌ ሰራሁት። እንደምትሰሚው ቆንጆ የአባቶች ዘፈን ነው።
እውነት ነው ድንቅ ሀሳብ ይዟል አንተም ጥሩ አድርገህ ተጫውተኸዋል?
ስጦታህ ውርሴ ነው ስምህ ማዕረጌ
በጥበብ በጉያህ እግርህ ስር አድርጌ
ከሰማዩ ጌታ ቀጥሎ ከላይ
የቀናው መንገዴ ባንተ አይደለም ወይ
አባብዬ፡ ምክርህ እያቀናኝ ፍቅርህ ያሳደገኝ
አንተን ያገኝሃል እኔን የፈለገኝ… እያለ ይቀጥላል። ጥሩ ስራ ነው።
ልክ ነው በደንብ አዳምጠሸዋል ማለት ነው።
ሌሎች ዘፈኖችህን እናንሳ። እስኪ ምን ምን ሀሳቦች ይዘዋል?
ለምሳሌ “ሀገሬ መልኬ” ጥሩ ዘፈን ነው። ይህ ዘፈን ተስፋ፣ ቁጭትና ፍቅርን የያዘ ዘፈን ነው።
አይዞሽ ሀገሬ ንፋስ ቢለፋም
ኩራዝ ነው እንጂ ፋኖስ አይጠፋም
…ይላል። የፍሬዘር አበበና የምልዕቲ ኪሮስ ግጥም ነው።  ይሄን ዘፈን እንዴት እንደሰራነው ልንገርሽ። መልዕቲ ኪሮስ የሆነ ጊዜ የተከራየችበት ቤት ችግር ገጠማት። ነገሩ የተከሰተው የሰሜኑ የሀገራችን ጦርነት በተከሰተበት ወቅት ነበር። ምልእቲ ኪሮስ የሚለውን ስሟን አከራይዋ በሰሙ ጊዜ በጣም ደንግጠው፤ “እስካሁን እዲህ መሆንሽን ለምን አልነገርሽኝም። በይ በፍጥነት ቤት ፈልጊ” አሏት። ይህ ነገር ከመከሰቱ ከ15 ቀን ወይም ከሳምንት በፊት ይመስለኛል፣ ኢቢኤስ ቴሌቪዥን ላይ ቀርባ “ስለሀገር” የሚያትት ግጥም አቅርባ ነበር። “ኢትዮጵያዬ” ብላ ሀገሯን አወድሳ በተመለሰች በሳምንቱ ይሁን በሁለት ሳምንቱ ነው አከራይዋ
ቤት ልቀቂ ያሏት፡፡ እናም እንዲህ ሆንኩ ብላ ነገረችኝ፡፡ በጣም ከፍቷታል፡፡ እንዲያውም ነይና ዛሬ ስለ ሀገር እንሰራለን አልኳት፡፡ ቁጭ ብለን “ሀገሬ መልኬን” ሰራን፡፡ አስቢው ምልዕቲ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነው፡፡ ምን ሊሰማት እንደሚችል አስቢው፡፡
ከልጅነት ዘመን እስከዚች ቀን ለታ
አይጠፋም ከልቤ የሰጠሽኝ ደስታ
ኑሪልኝ እማ አለም ስቀሽ የኔን ፋንታ
አይጠፋ ከደጅሽ ድግስና ደስታ
የተገፋፋነው በጉያችን ዓለም
እኛ አንሰን ነው እንጂ ጠብበሽን አይደለም
… እያለ ይቀጥላል በጣም ጥሩ ዘፈን ነው፡፡
ሌላው በአልበምህ ውስጥ “ሰሚራ” የሚል ዘፈን አለ፡፡ እኔ ከሙዚቃ ስልተ ምቱ ጀምሮ ስሰማው የሀገራችን የድሬ፣ የሀረሬ፣ የአፋርና የሶማሊያ ቆነጃጅቶች ከነሺቲያቸው እየታሰቡኝ ነው፡፡ እስቲ ስለዚህ ዘፈን ትንሽ አውጋኝ…..
 “ሰሚራ” በስልተምትም በካራክተርም እስከዛሬ ከሰራኋቸው ዘፈኖች ትንሽ ዘወር ያለና ለየት ያለ የፍቅር ዘፈን ነው ከአበጋዝና ከዓለማየሁ ደመቀ ጋር ነው የሰራነው፡፡ በግጥም አቡዲ የሚባል ልጅም አለ፡፡ “ሰሚራ” ዋዛና ጨዋታ የሚመስል ነገር ያለው፣ እንደ ንግግር ያለ ተጨምሮበት የተዘፈነ ነው፡፡ በጣም ተወዷል፡፡ በአልበሙ ላይ “አካላት”  እና “እረፊ” የተሰኙም አሉ፡፡ ብቻ በተቻለ መጠን ለአድማጭ ጆሮና መንፈስ ይመጥናሉ የምንላቸውን ስራዎች ይዘን ቀርበናል፡፡
እስካሁን እንደተነጋገርነው በስራዎችህ ውስጥ ትልልቅ ሀሳቦችን አንስተሃል፡፡ ስለፍቅርም፣ ስለሀገርም፣ ስለአባትም፣ ስለ አብሮነትና መተባበርም፤ ነገር ግን አሁን ትልልቅ ሀሳቦችን የማድመጥ ፍላጎትና ትእግስት ያለው ማህበረሰብ አለን ወይ ሲባል እሰማለሁ፡፡ በተለይ ወጣቱ አካባቢ… ስለዚህ እነዚህ ትልልቅ ሀሳቦች አድማጭ ጋር በአግባቡ ይደርሳሉ ብለህ ታስባለህ?
አዎ! አንቺ ለማለት የፈለግሽው ወጣቱ አብዛኛው የሚከተለውና የሚፈልገው ነገር ገብቶሃል ወይ መሰለኝ፡፡ ለምሳሌ “ሀገሬ መልኬ”ን ስንሰራ ችክችካ የሚባለውን ባህል የሚመስል አድርገን ወጣ አድርገን ነው የሰራነው፡፡ መጀመሪያ ወደ ስድስት ሰባት የሚሆን የሀገር ዘፈን ነበር የሰራሁት፡፡ አልመጣልህ አለኝ፡፡ አልመጣልህ ሲለኝ ሀገሬን አልወዳትም ማለት ነው እያልኩ እናዳደለሁ፡፡  የምሬን ነው፤ የፍቅር ዘፈን እየመጣልኝ ለምንድን ነው የሀገር ዘፈን የማይመጣልኝ ብዬ እበሳጫለሁ፡፡ ጂጂንና ቴዲ አፍሮን ተመልከቻቸው፤ የሀገር ዘፈን በደንብ ይመጣላቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ሀገር በመውደድ ይበልጡናል ማለት ነው ለኔ፡፡ እኔ ስለሆነች ልጅ ዘፍኜ ከመጣልኝ ስለ ሀገሬ ዘፍኜ ሲያቅተኝ እበሳጫለሁ፡፡ ይገርምሻል…. ስድስት ሰባት ዘፈን ነው የሰራነው፤ አይሆንም፡፡ ግጥሙ ሲመጣ ወይ የኔ አዘፋፈን አይመጣም፡፡ የውሸት ይመስላል፡፡ ለሀገር ልዝፈን ብለሽ ስትዘፍኚ ያስታውቃል፡፡ ቴዲ አፍሮ ስለ ሀገር ሲዘፍን ልብ ብለሽዋል? ሲቃ ሁሉ ይይዘዋል፡፡ በእኔ እምነት ሀገሩን በመውደድ ስለሚበልጠን ነው፡፡ በዚህ ሁሉ መሃል “ሀገሬ መልኬ” ተወለደ፡፡ ዘፈኑ  ሞደርን ወጣቱም  ቢሆን በስል-ተምቱ እየጨፈረ ሀገሬ ሀገሬ እንዲል አድርገን ሰራነው፡፡ የእውነት ደግሞ እኔ ራሴ ስሰማው የማለቅስበት፣ ከልብ የመነጨ የሀገር ፍቅር ስሜት ቀስቃሽ ዘፈን ሆነ፡፡ እኔም ሀገሬን በትክክል እንደምወዳት የተረዳሁበት ነው፡፡  ምክንያቱም የሀገር ዘፈን በደንብ ግጥሙም ዜማውም አዘፋፈኑም ስክትክት ብሎ መጣልኛ። ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ሀገር ዘፈን ተሳካልኝ ብየ ደረቴን ነፍቼ መናገር እችላለሁ፡፡
እና ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገርህን መውደድ ጀመርክ ማለት ነው?
ምን መሰለሽ… ስለሀገሬ ልዝፈን ብሎ መዝፈንና የእውነት ከውስጥሽ ተነክተሸ መዝፈን ይለያያል እኮ  በጣም ከባድ ነው፡፡ ስለ አገር፣ ስለ እናት፣ ስለ አባት መዝፈን ተለዋዋጭ ስሜት የለውም፡፡ ለምሳሌ ስለፍቅር ዛሬ የሚሰማሽና ነገ የሚሰማሽ ስሜት ይለያያል፡፡ የምታሳልፊያቸው የፍቅር ጊዜያቶችና ሁኔታዎችም ይኖራሉ፡፡ ትወጃለሽ፣ ትወደጃለሽ፤ ትጣያለሽ በነዚህ ሂደቶች ሁሉ የሚሰሙሽ ስሜቶች የተለያዩ ናቸው፡፡ ከእናትሽ ጋር ግን የፈለግሽውን ያህል ብትጣይ የሚሰማሽ ስሜት አንድ ነው፡፡ ለሀገርሽም ለአባትሽም እንደዛው፡፡ ለሀገርሽ ለእናትሽ ለአባትሽ በተለያየ ተለዋዋጭ ስሜት ውስጥ ብትሆኚም ቋሚ የሆነ ፍቅር ግን አለሽ፡፡ ያ ነገር ተጋብቶብኝ የእውነቴን ዘፍኜዋሁ የሚል ስሜት ተሰምቶኛ “ሀገሬ መልኬ”ን። ሌላ ጊዜ መዝፈን አለብኝ፡፡ በአልበም ውስጥ ስለ ሀገር መካተት አለበት ብለሽ ስትሰሪና የእውነት ስሜቱ መጥቶልሽ ስትሰሪ አንድ አይደለም፡፡
ከሀገሬ መልኬ ውጪ በጣም የወደድከው ዘፈን የትኛው ነው? አንድ የተለመደ አባባል አለ። ድምፃዊያን ይህን ጥያቄ ሲጠየቁ ከጣት ጣት አይበላለጥም፤ እናት ለልጆቿ ፍቅር አታበላልጥም ይላሉ፡፡ ነገር ግን ከጣት ጣት ይበላለጣል፤ እናትም በተለየ መንገድ አብዝታ የምትወደው ልጅ አላት አንተ ከአልበምህ የትኛውን ዘፈን ይበልጥ ወደድከው?
እንግዲህ ካልሽ ምን ይደረጋል! “እና” የሚለው ዘፈኔን በጣም ነው የወደድኩት፡፡ ከዳኘ ዋለ ጋር ነው የተጫወትነው፡፡ ዳኜም እስከ ዛሬ ከተጫወታቸው ስልተ ምቶች ለየት ባለ መልኩ ፊቸሪንግ የገባበት ዘፈን ነው፡፡ ግጥሙ በፊት ሌላ ነበር፡፡ በእውቀቱ ስዩም እዚህ ስቱዲዮ መጥቶ እዛች ጥግ ላይ ቁጭ ብሎ (በጣቱ የስቱዲዮውን መቀመጫ እያሳየኝ) ሰማውና ልምረጥ አለኝ፡፡ እሺ አልኩት፡፡ 30 ደቂቃ መሰለኝ በደንብ ሰማና በሩን ዘግቶ ፃፈልኝ፡፡ እኔ በድምጽ ገባሁት፤ አሪፍ ሆነ፡፡ እሱ ዘፈን በጣም ደስ ይለኛል። እና ግጥሙ የበእውቄ ነው፡፡ ዳኜም በዛ በጎርናና ድምፁ ዝቅ ብሎ፤
አለ አንኳር ጫዋታ አለ አንኳር ጫዋታ
በፍቅር ሲካሱ የማታ የማታ፡፡ …. ሲልበት መቼም ሌላ ነው፡፡
“እና” ሶሻል ሚዲያውን በተለይ ቲክቶኩን የተቆጣጠረ ዘፈን ሆኗል ልበል?
በደንብ እንጂ በጣም ብዙ ሰው ነው የወደደው። ኤላ ቲቪ ዩቲዩብ ላይም በደንብ እየታየ ያለ ነው፡፡
አልበምህን የለቀቅበትን ወቅት እንዴት አየኸው። በፊት በፊት አልበሞች የሚለቀቁት የበዓላትን መቃረብ ተከትሎ በዋዜማዎች ላይ ነበር ያንተን ሳየው ሃምሌ አጋማሽ ላይ ነው የተለቀቀው፡፡ ከምንም በዓል ጋር ግንኙነት የለውም ብዬ ነው
እኔ ዘፈን እንጂ የለቀቅኩት ዶሮ ወይም ቅርጫ አይደለ! ከበዓል መምጣት አለመምጣት ጋር ምን አገናኘው? ዘፈን እኮ ነው፤ በየትኛውም ወቅትና ሰዓት ይደመጣል፡፡ በዚያ ላይ የዓመት በዓል ዘፈን የለኝም፡፡ በፊት በፊት ይመስለኛል የዘፈን ካሴትና ሲዲ ለመግዛት ሰው ያቺን ወቅት ይጠብቅ ስለነበር ነው፡፡ አሁን ላይ ዘፋኙም ዘፈኑም በዝቷል፤ በዓልን መጠበቅ ግዴታ አይደለም፡፡ እኔ ሁሌም ለጓደኞቼ እነግራቸው ነበር፡፡ ይሄ አልበም አልቋል በቅቶታል ብሎ ውስጤ ሲነግረኝ፣ የትኛውም ወቅት ይሁን አወጣለሁ እላቸው ነበር፡፡ እስካሁን ውስጤ አላለቀም ስላለኝ ነበር ያቆየሁት፤ አሁን አልቋል በቅቶታል ተለቀቀ ይሄው ነው፡፡
ስቱዲዮህ የተገናኘነው ዘፈኑ በተለቀቀ በአራተኛ ቀኑ ላይ ነው፡፡ ምናልባት ከአድማጭ በኩል ያለውን ግብረ መልስ ለመጠየቅ ጊዜው በጣም አጭር ይሆናል፡፡ ቢሆንም የአድማጩን አቀባበል የሚያሳይ ፍንጭ አይጠፋምና እንዴት አገኘኸው?
ሁሉም ሰው ሲሰራ ደክሞበት ለፍቶበት ስለሆነ “ጥሩ ነው” ነው የሚለው፡፡ እውነት ለመናገር የጫነው ዕለት በአጫጫን ስህተት ትንሽ ችግር ገጥሞን ነበር። እኔ እከሌ የጻፈው ይህንን ግጥም ነው፤ ዜማው የእከሌ ነው የሚለው ክሬዲት ላይ ስጠነቀቅ ሳውንዱን አልሰማሁም ነበር። አበጋዝ ጋር አሜሪካ ደወልኩ አወራን በፍጥነት ይውረድ ተብሎ ወረደ። 20 ወይም 30 ሺህ አካባቢ ሰው ነበር በትራክ ያየው፤ አውርደን እንደገና ጫንነው። ትንሽ ደንግጠን ነበር። ግን እንደገና ከተጫነ በኋላ በጣም ጥሩ ነው። በተለይ “እና” የሚለውና “እረፊ” በጣም ተወደዋል። ሁሉም ግን በጣም ጥሩ እይታ እያገኙ ነው። በሂደት እናየዋለን።
የአልበም ምርቃትና ኮንሰርት ይቀጥላል አይደል?
አዎ! መጀመሪያ አልበም ሪሊዝ አስበናል። የፍልሰታ ጾም እንደተፈታ አልበም ሪሊዙ ይደረጋል። የኮንሰርቱ ጉዳይ የኔ ስራ አይደለም፤ የሚመለከታቸው ሰዎች አሉ። እነሱ ይህን ሥራ ሂደቱን ይሰራሉ። በሀገር ውስጥም በውጭም ኮንሰርቶች ይኖራሉ፡፡ አብረን የምናየው ይሆናል፡፡
እስካሁን በአዲሱ አልበምህ ዙሪያ ያላነሳነው ነገር ግን መቅረት የሌለበት ሃሳብ ካለ እናንሳና እንሰነባበት……
ማለፊያ ሁሉ መኖሪያ አይደለም ። ማለፊያ መንገድ ነው፣ ማለፊያ ጊዜ ነው፣ ማለፊያ ተስፋ ነው። ስለዚህ አልበሙ ቆንጆና ማለፊያ ነው፤ አድምጡት፤ በሶስተኛ አልበም እስከምንገናኝ አጣጥሙት ነው የምለው። ደሞ ሦስተኛው አልበም አምስት ዓመት አይፈጅም። ምክንያቱም አሁን የራሳችን ስቱዲዮ ስላለን እንደልባችን መስራት እንችላለን። በተረፈ በዚህ አልበም ላይ በግጥም፣ በዜማ፣ በቅንብር፣ በሚክሲንግ፣ በሃሳብና በምክር፣ ጊዜ በመስጠት አሻራቸውን ያሳረፉትን ቤተሰቦቼን፣ ጓደኞቼን፣ የሙያ አጋሮቼን በሙሉ አመሰግናለሁ። ክብር ይስጥልኝ እላለሁ፡፡Read 628 times