Saturday, 05 August 2023 12:28

ኪነጥበብና ባህልን ለሥራ ፈጠራ ካልተጠቀምን ሥራ አጥነት አይቀረፍም ተባለ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ኪነጥበብና ባህልን ለሥራ ፈጠራ በአግባቡ ካልተጠቀምን የተንሰራፋውን ሥራ አጥነት መቅረፍ እንደማይቻል ተገለፀ፡፡ ይህ የተገለፀው ከትላንት በስቲያ ሀምሌ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ረፋድ ላይ ሰላም ኢትዮጵያ “ኪነጥበብና ባህል ለሥራ ፈጠራ” በሚል መርህ በቫይብ ሆቴል ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ነው፡፡
የሥራ አጥ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱ በፓናል ውይይቱ ላይ የተነሳ ሲሆን፤ ለዚህ ችግር መባባስ መንግስትም ሆነ ማህበረሰቡ ለኪነ-ጥበብና ለባህል ትኩረት አለመስጠታቸው ብሎም ለዘርፉ ያለው አመለካከት መዛባት መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
በኢትዮጵያ የህዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ባለበት በአሁኑ ወቅት ኪነ-ጥበብና ባህልን ለስራ ፈጠራ አለመጠቀምና ዘርፉን ችላ ማለት ለስራ አጥነቱ መባባስ አስተዋፅኦ ማድረግ ነው ሲሉ ተወያዮቹ አሳስበዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኪነጥበብና ባህል በሥራ ፈጠራ ረገድ ያለው አሰራር ኋላቀርና አመርቂ ሥራ ያልተሰራበት ከመሆኑም በላይ በመንግስት በኩል የህግ ማእቀፍ ያልተዘጋጀለትና የተዘነጋ በመሆኑ ለሥራ ፈጠራና ለአገር እድገት ሊያበረክት የሚገባውን  እንዳላደረገ ነው በውይይቱ የተነሳው፡፡ በተጨማሪም በሀገሪቱ ያሉት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የባህልና ሥራ ፈጠራን የሚያግዝ አሰራር የላቸውም የተባለ ሲሆን፤ እነዚህ ኮሌጆች ከስር መሰረታቸው ተሃድሶ እንደሚያስፈልጋቸው ተጠቁሟል፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከሌሎችም ተቋማት የተውጣጡ ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈው የመፍትሄ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል የፓናል ውይይቱ ያዘጋጀው ሰላም ኢትዮጵያ፤ በባህልና ኪነ-ጥበብ ላይ የሚሰራና ከ25 ዓመት  በፊት በስዊድን ሀገር የተመሰረተ ዓለም ዓቀፍ ተቋም ሲሆን በኢትዮጵያ ቢሮ ከፍቶ በበርካታ የኪነጥበብና ባህል ጉዳዮች ላይ እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

Read 1322 times