Saturday, 12 August 2023 20:52

እርግዝና ከመፈጠሩ አስቀድሞ የሚሰጥ ህክምና. . .

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 በህዝብ ማመላለሻ መኪና (ታክሲ) ውስጥ ከአሽከርካሪው አጠገብ ተቀምጫለው። በመኪናው የድምፅ ማጉያ ጆሮን በሚያስይዝ የድምፅ ከፍታ ራዲዮ ተከፍቷል። ከራዲዮው ውስጥ “የአደንዛዥ እፅ እና የአልኮል ሱስ ያለባችሁ እንዲሁም ሰውነታችሁ አስፈላጊውን ንጥረ ነገር ባለማግኘቱ ምክንያት የተጎዳችሁ....” የሚል ንግግር ወደ ጆሮዬ ገባ። ንግግሩ ገና ሳያልቅ ከጎኔ የተቀመጠች አንዲት ወጣት ወደ እኔ ሠርቅ አርጋ እያየች “በገዛ ሰውነታችን ምን አድርጉ ነው የሚሉን....” አለች። ግራ በተጋባ ስሜት ፈገግ ብዬ ዝምታን መረጥኩ። ቀጠል አድርጋም “ሰው በማይመለከተው ጉዳይ ለምን ይገባል?” አለች። “እንዴት?” አልኳት። እሷም በዙሪያዋ ካሉ ሰዎች ጋር በመሰባሰብ በቁሳቁስ እና በተለያዩ ነገሮች ድጋፍ እንደምታደርግ ነገር ግን በሚሰጠው ድጋፍ ላይ የአንዳንድ ሰዎች ምላሽ እንደሚያስገርማት ነገረቺኝ። ፈገግ ብላ እና ትንሽም እንደመናደድ ኮስተር እያለች “አንድ በእድሜያቸው ጠና ያሉ ሠው እርዳታ በምንሰጥበት ስፍራ እርዳታ ለመውሰድ መጡ። እኛም ልናስተናግዳቸው ተጣደፍን! እሳቸው ግን የስድብ ናዳ ያወርዱብን ጀመሩ...” ብላ ንግግሯን ሳትጨርስ “በምን ምክንያት” በሚል ጥያቄ አቋረጥኳት። ስለ እኒህ ሰው ማንነት እንደሰማችው ከሆነ በእድሜ የልጅልጃቸው የምትሆን ሴት በመጥለፍ አግብተዋል።  የሲጋራ (ትንባሆ) እና የአልኮል መጠጥ ሱሰኛ ናቸው። ይህ የትንባሆ ሱስ እና የአባላዘር በሽታ ከእሳቸው አልፎ በባለቤታቸው እንዲሁም በተፀነሰው ልጅ ላይ ጉዳት አድርሷል። እናም በዚህ ጉዳይ ከሚደርስባቸው ወቀሳ ለመመሸሽ አስቀድመው ለመከላከል ‘ባህላችንን ለማበላሸት ትምህርት፣ ህክምና እና ምግብ እያላችሁ በብጫቂ ነገር ልትደልሉን አትሞክሩ” በማለት ይናገራሉ።
አጠገቤ የተቀመጠችው ሴት ይህን ታሪክ ስትነግረኝ ከአፏ የትምባሆ እና ምንነቱ ልለየው ያልቻልኩት ጠረን ተቀላቅሎ ወደ አፍንጫዬ ገባ። ሳላስበውም “አንቺስ?” አልኳት። “አዎ እኔም ሲጋራ አጨሳለው። ነገር ግን የጎዳሁት እራሴን እንጂ ሌሎችን አይደለም” አለቺኝ። “ታዲያ ሰውዬውስ ምን አጠፉ” አልኳት ነገረስራዋ ግራ ቢያጋባኝ። “በእሳቸው ምክንያት የሚስታቸው እና የልጃቸው ጤና ተጎድቷል። ሌሎች የተጎዱ ሰዎች ከጉዳታቸው እንዳይወጡ እንቅፋት እየሆኑ ነው። እኔ ግን ሌላ ሰው አልጎዳሁም፤ እኔ የማደርገውን አድርጉም አላልኩም፤ የምችለውን እርዳታም እሰጣለው። ነገር ግን የግል ምርጫዬ መከበር አለበት” አለች። እኔም “ሬዲዮው እያለ የነበረው ሴቶች ከመፀነሳቸው በፊት ሊያደርጉ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ነው። እና ልጅ ለመውለድ አታስቢም?” አልኳት። “አልወሰንኩም” አለች ፈርጠም ብላ። “በመውለዱ?” አልኩ ለምን የማወቅ ፍላጎት እንዳደረብኝ ባይገባኝም። “እኔንጃ” ብላ ፊቷን ወደ መስኮቱ አዞረች። ‘ታዲያ እሷ ማትፈልገውን፤ ያላመነችበት ነገር እንዴት ለሌላ ሰው ልትመክር ትችላለች’ አልኩኝ በውስጤ። ምንም እንኳን እንደማንኛውም ሠው ግለሰባዊ ምርጫ ቢኖራትም እያወቁ እራስን መጉዳት ግን በሽታ እንጂ እንዴት ምርጫ ሊባል ይችላል!? እራስን መጉዳት ተፈጥሯዊ መብት ቢሆን እራስን ማጥፋት ወንጀል ባልሆነ ነበር!
“ምን ሆና ነው፤ አሟታል እንዴ” የሚል ድምፅ እና ትከሻዬ ላይ ያረፈው የአሽከርካሪው እጅ ግራ ከተጋባሁበት ስሜት አነቃኝ። “ማን” አልኩት ፊቴን ወደሱ መልሼ “አብራችሁ አይደላችሁም እንዴ” አለ ድንጋጤ በተሞላበት ድምፅ። አጠገቤ ያለችው ሴት እራሷን እንደመሳት ብላለች። ለካ አስተውዬ አላየኋትም እንጂ በሱሱ ይሁን በሌላ ምክንያት ሰውነቷ በጣም የገረጣ ነው። አሽከርካሪው ወደ ረዳቱ ዞሮ “እስቲ ውሀ ነገር ካለ” በማለት ጠየቀ። አጠገቤ ያለችው ሴትም እንደመንቃት ብላ “ሀኪም ቤት...” አለች። አሽከርካሪውም በአከባቢው ወደሚገኝ የህክምና ተቋም ይዞን ሄደ። ተሳፉሪውም ባቀደው ሰአት ካሰበበት ቦታ ባለመድረሱ መነጫነጭ ጀመረ። እኔም ከአሽከርካሪው እና ከታማሚዋ መሀከል በመቀመጤ እንዲሁም ለደቂቃዎችም ቢሆን ከእሷ ጋር በመነጋገሬ ከሌላው ሰው የተሻለ የቅርብ ሰውነት ማዕረግ ስላሰጠኝ አፍ አውጥቼ አልተናገርኩም እንጂ ‘ወዳ እና ፈቅዳ መጎዳትን ለመረጠች ሴት...’ እያልኩ በውስጤ እያጉረመረምኩ ነው። ነገር ግን ማጉረምረሜ ከተሳፋሪው “ቢያንስ አንድ ሰው እንኳን አብሯት ቢሆን” ከሚል ሀሳብ፣ ከአሽከርካሪው እና ከረዳቱ የትዝብት አይን እንዲሁም ከእራሴ ህሊና ሊያስጥለኝ አልቻለም። ቤተሰቦቿ እስኪመጡ ድረስ የህክምና ተቋም ውስጥ ቁጭ ብዬ የህክምና ውጤቷን መጠባበቅ ጀመርኩ። ውጤቷን እና ታሪኳን ከሰማሁ በኋላ የፈረደባት ልቤ ያዝንላት ጀመረ።
ወላጆቿን በሞት የተነጠቅችው ገና በአስራዎቹ መጀመሪያ እድሜ ላይ ነበር። ከቤተሰቦቿ ጋር መካከለኛ የሚባል ኑሮ ትኖር የነበረ ቢሆንም ቤታቸውን ጨምሮ ያላቸው ንብረት በእዳ ስለተያዘ በሀራጅ ተሸጠ። እሷን እና ወንድሟን በማደጎ የወሰዷቸው የአባቷ የቅርብ ጓደኛ ነበሩ። የአባቷ ጓደኛ ከልጆቻቸው ጋር በተመሳሳይ መልኩ ቢያሳድጓቸውም ኑሯቸው ዝቅተኛ ስለሆነ የቤተሰቡን ህልውና ለማስቀጠል ከትምህርቷ ጎንለጎን ስራ መስራት ነበረባት። ከስራ በተጨማሪ ልክ እንደ እሷ ያሉ ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ተማሪዎችን በትምህርት እና በአንዳንድ ቁሳቁሶች ማገዝ ጀመረች። ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል በትምህርትም በስራም አብሯት የሚያግዛት አንድ ሰው አገኘች። ከዚህ ሰው ጋር የነበራት ቅርርብ ከፍ ብሎ የፍቅር ግንኙነት ተጀመረ እና ፀነሰች። በነበረችበት ሁኔታ ልጅ ወልዶ ማሳደግ የማይሞከር ነበር። እናም ፅንሱን አቋረጠች። አሳዳጊዋ ይህንን ሲሰሙ ከቤት አባረሯት። የተፀነሰው ልጅ አባት ወደ ክፍለሀገር ስለሂደ ልታገኘው አልቻለችም። ለተወሰኑ ዓመታት ቤት ተከራይታ እየሰራች ትምህርቷን ብትቀጥልም ኑሮውን መቋቋም ስላልቻለች ትምህርቷን ለማቋረጥ ተገደደች። ታናሽ ወንድሟ ነፃ የትምህርት እድል አግኝቶ ከሀገር ወጣ። ለተወሰነ ወራት በስልክ ከተገናኙ በኋላ ግንኙነታቸው ተቋረጠ። ይኑር ይሙት የሚታወቅ ነገር የለም። ከኑሮ ጋር ከምታደርገው ትግል ይበልጥ ተስፋ መቁረት አሸነፋት። ለጊዜው ህመሟን ለሚያስረሳ እፅ እና መጠጥ እጅ ሰጠች። ምንም እንኳን አሁን ላይ ኑሮን ታግላ አሸንፋ ለሌሎች ብርታት መሆን ብትችልም፤ በሱስ ግዞት ውስጥ መኖሯ እንደቀጠለ ነው። ታክሲ ውስጥ ያገኘኋት ይቺ ሴት በአሁኑ ወቅት ባለትዳር ስትሆን በህክምና ውጤቷም መሰረት ነፍሰጡር ናት። የህክምና ተቋም ውስጥ የተነገረኝ ዜና ግን ይህ ብቻ አልነበረም። ወላጆቿን ለሞት ያበቃው የስኳር ህመም እሷ ላይም ተገኝቷል። ትንባሆ አጫሽ እና አልኮል ጠጪ መሆኗ ደግሞ አይደለም ለነፍሰጡር በማንኛውም ሰው ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የሚያጠያይቅ አይደለም። የህክምና ባለሙያዎቹ እንደነገሩን ከሆነ ፅንስ ከመፈጠሩ አስቀድሞ የህክምና ክትልል ማድረግ ነበረባት። አይምሮዬ ላይ ሲመላለስ የነበረውን ጥያቄ ጠየኳት። “እኔ ምልሽ አሁንስ ወሰንሽ ማለቴ ሱሱን.... እእእእእ.... ባንቺ ሰውነት ማንም ባይመለከተውም.... ያው” ተንተባተብኩ። ፈገግ እንዳለች “አዎ በሰውነቴ ማንም አይመለከተውም” አለች። ንዴቴ ለእራሴም እስኪያስገርመኝ ድረስ ድምፄን ጮክ አድርጌ “ፊትሽን እንኳን በቅጡ ያላየሽ ያ ሁሉ ተሳፉሪ፣ የህክምና ተቋሙ የጥበቃ እና ሌሎች ሰራተኞች የደከሙልሽ፣ የህክምና ባለሙያዎቹን እንኳን ምን ብዬ እነግርሻለው። አንቺው ምስክር ነሽ! እሺ ሌላው ቢቀር ባለቤትሽ እስከመታመም የተሰቃየው፤ ሆድሽ ውስጥ ያለው ፅንስ የተጎዳው.... ባንቺ ሰውነት ባይመለከትልቸው ነው!” በማለት ተናገርኩ። ትኩር ባላ ከተመለከችኝ በኋላ በተረጋጋ መንፈስ እና ፈገግታ  “ያን ንግግር ስናገር በሙሉ ቀልቤ አልነርኩም። ነገር ግን በሆዴ ያለው ፅንስ ያለፈውን ቁስሌ አክሞ ተስፋ ሰቶኛል። ባለቤቴም ከእኔ ጋር ሲሰቃይ ነው የኖረው። አሁን ሁላችንም እፎይ እንላለን። እናንተንም አደከምኳችሁ። አመሰግናለው” አለች። ይቺ ሴት አሁን ላይ ከነበረባት ሱሶች ተላቃ፣ ልጇን በሰላም ወልዳ፣ የምትመኘውን ሰላማዊ እና ደስተኛ ህይወት እየኖረች ትገኛለች። በመጥፎ አጋጣሚ የተመሰረተው ግንኙነታችንም አድጎ ቤተሰብ ሆነናል። የእሷን አጋጣሚ መነሻ በማድረግ እኔም ከባለቤቴ ጋር የቅድመ እርግዝና የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኛለው።
በጤና ሚንስቴር በእናቶች እና ህፃናት፣ አፍላ ወጣቶች ስራ አስፈፃሚ የእናቶች ጤና ዴስክ እስፔሻል ሲኒየር ኤክስፐርት የሆኑት ታከለ የሺዋስ እንደተናገሩት ቅድመ እርግዝና የህክምና አገልግሎት ማለት ልጅ መውለድ በሚቻልበት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ሰው የሚያገኘው የህክምና አገልግሎት ነው። “ከእናቶች እና ጨቅላ ህጻናት ጋር ቁርኝት አለው” በማለት ባለሙያው የተናገሩ ሲሆን ይህም ቁርኝት አገልግሎቱ የእናቶች እና የጨቅላ ህጻናትን ሞት በመቀነስ በሚያበረክተው አስተዋጻኦ የሚገለጽ ነው።
እናቶች የቅድመ እርግዝና የህክምና ክትትል ባለማድረጋቸው ምክንያት ከእናት ወደ ልጅ የተለያዩ በሽታዎች ሊተላለፉ እና በተጸነሰው ልጅ ላይ የአፈጣጠር ችግር ሊያስከትል ይችላል። ስለሆነም ችግሩን አስቀድሞ ለመከላከል እርግዝና ከመፈጠሩ አስቀድሞ የህክምና ክትትል ማድረግ ይመከራል።
እርግዝና ከመፈጠሩ አስቀድሞ ጥንዶች ማድረግ ያለባቸው ጉዳዮች; የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ የፎሊክ ንጥረነገር ያላቸውን እንደ ኣሳ፣ ቆስጣ፣ ጎመን ያሉ ምግቦችን መመገብ፣ ተከታታይነት ያለው የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ የተመጣጠነ ክብደት እንዲኖር ማድረግ [ከመጠን በላይ ውፍረት እና አነስተኛ ክብደት ለእርግዝና አይመከርም] ፡ በቅድመ እርግዝና ወቅት የሚወሰድ የቫይታሚን እንክብል መውሰድ፣ የአልኮል መጠጥ እና ሲጋራ እንዲሁም አደንዛዥ እጾችን ማቅም ተጠቃሽ ናቸው። በተጨማሪም ማንኛውም አይነት መድሀኒት አለመውሰድ (አስገዳጅ ከሆነ የህክምና ባለሙያ ማማከር) ያስፈልጋል።
በኢትዮጵያ በግለሰብ ደረጃ ካልሆነ በቀር ለሁሉም ተገልጋዮች የተመቻቸ በጤናተቋማት የሚሰጥ የቅድመ የእርግዝና ክትትል አለመኖሩን ባለሙያው ተናግረዋል። ጤና ሚንስቴር ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ከ15 እስከ 49 ዓመት የእድሜ ክልል ለሚገኙ ሴቶች እና እንዳስፈላጊነቱ ለወንዶች ይህን አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመስጠት እየሰራ ይገኛል። “ማንኛዋም እናት ለሌላ የህክምና አገልግሎት ወደ የህክምና ተቋም ስትሄድ የቅድመ እርግዝና ዳሰሳ እና ምርመራ ይደረግላታል” በማለት ባለሙያው ተናግረዋል። ለምሳሌ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት፣ የስኳር፣ የልብ እና የኤች አይ ኤድስ ህክምና ለማግኘት ወደ ህክምና ተቋም የሚሄዱ ተገልጋዮች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ። በሀገርአቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ የታሰበው የቅድመ እርግዝና የህክምና አገልግሎት ለ1ዓመት ወይም ለ1 ዓመት ከ6 ወር ሙከራ ከተደረገበት በኋላ ተግባራዊ እንደሚደረግ ባለሙያው ተናግረዋል። ስለሆነም በሀገር አቀፍ ደረጃ የቅድመ እርግዝና የህክምና አገልግሎት ተግባራዊ ሲደረግ እናቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በጤና ጥበቃ ሚንስቴር በእናቶች እና ህፃናት አፍላ ወጣቶች ስራ አስፈፃሚ የእናቶች ጤና ዴስክ እስፔሻል ሲኒየር ኤክስፐርት የሆኑት ታከለ የሺዋስ ጥሪ አድርገዋል።

Read 1014 times