ገና ከእንቅልፋችሁ ስትነቁ የተፈጥሮ ድምፅ ከጆሯችሁ ስር፤ “ዛሬ ያንተ/ያንቺ ቀን ነው” ብላችሁ አታውቅም? እንደው …አለማት በሙላ ለናንተ ሲሉ ደፋ ቀና እያሉ መሆኑን ተረድታችሁ የነቃችሁበት ቀን አይታወሳችሁም? የትኛውንም አይነት ውድቀት ላለማስተናገድ፣ ጭንቅላታችሁ ከብረት የጠነከረ እምነት ይዞ አይናችሁን ከተሰደደበት ህልም ጠርቶትና አንቅቶት፣ ለቀናችሁ አስረክቧችሁ የሚያውቀውን እለት እንዴት እረሳችሁት?
ሰይፉ እነዚህ ስሜቶች እየተሰሙት ነው፣ ከእንቅልፉ የተነሳው፡፡ ምን እንደሆነ በቅጡ ያላወቀው መንፈስ፣ በግድ በሚመስል መልኩ ከአቅም በላይ የሆነ ደስታ ውስጥ ከቶታል። አልጋውን አንጥፎ የማያውቀው ሰውዬ፣ ድንገት ዛሬ ላይ የጥላሁንን ዘፈን እያፏጨ፣ አልጋውን በማንጠፍ ላይ ነው፡፡ እንደ መደነስም የሚያደርገው ነገር አላጣም፡፡ ዛሬ ላይ አይኖቹን ከገለጣቸው ጀምሮ ያለው ህይወቱ፣ ምንም አይነት እንቅፋት እንደማይገጥመው አድርጎ የሚያሳምነው አይነት፣ የደስታ መብከንከን ውስጥ ከተቶታል፡፡
ድንገት እስከዛሬ እየተመተመው የመጣው ህይወቱን ወደደው፡፡ እስካሁን ያለቀሰባቸውን ሀዘኖቹን ላሁኑ እድገቱ እንዳበጁት አድርጎ፣ እንደ መምህር ቃል ተቀበላቸው፡፡ ያስቀየሙትን ሰዎች ሁሉ እያስታወሰ በልቡ ይቅር አላቸው። እስከዛሬ ሲያናድዱት የነበሩትን የህይወቱን ገጠመኞች እያስታወሰ፣ ይስቅና ያላግጥባቸው ጀመር፡፡ ከዛሬው ቀን ጀምሮ ማንም ቢሰድበው እንኳን በሳቅና ጨዋታ ለማሳለፍ ብሎ እስከዛሬ ተሸክሞት የነበረውን የንዴት እብደት እንዳያገኘው አድርጎ፣ ከአዕምሮው አውጥቶ ወደማይታወቀው ጠፈር ውስጥ ወረወረው፡፡ ይህን ሁሉ…እድሜን የሚፈጅ የራስን ማንነት የመቀያየሩን ሂደት፣ ፈገግ እያለና ክፍሉ ውስጥ እየደነሰ ደረሰበት፡፡
ማንም ሳይሆን ቀኑ በራሱ የሰጠው የስጦታ መንፈስ ውስጥ ያለ ሰው እንደሆነ አያሰበ፣ ክፍሉን ለቆ ሊወጣ ሲል አንድ ጊዜ ዞሮ ተመለከተው። አንድ ነገር ብቻ እንደሚጎለው ገባው...ቤቱ ውስጥ፡፡ እስከ ዛሬ ታይቶት አያውቅም ነበር። ሁሉም የሚፈልገው ነገር ከስሩ እንዳለና፣ ምንም ከህይወት እንዲጨመርለት የማይፈልግ ሰው አድርጎ ነበር ራሱን ያሰለጠነው፤ ሆኖም አሁን በአዲስ አይን አለምንና ህይወቱን መመልከት ጀምሯል፡፡ አዎ…በዛ ክፍል ውስጥ ህይወት መግባት አለበት። አንዲት ሴት መከሰት አለባት ብሎ አሰበ፡፡ ብቻውን ለምን ያህል ጊዜ እንደኖረ ሲታወሰው፣ ፍፁም ራስ ወዳድና ከተፈጥሮ ጋር የተጣላ ሆኖ ይኖር እንደነበረ ተገነዘበ፡፡ የእውነትም ስራው ላይ ብቻ ሲያተኩር ከርሞ ከሴት ጋር የመሰንበቻ እድሜውን ግጦ እንደጨረሰው ታወሰው። ለምን ይሄን እንዲያስታውስ ቀኑ ነገረው? ምናልባት የገዛ ማንነቴንና ደስታዬን የለገሰኝ ይህ ቀን፤ ሚስቴንም ሊያመጣልኝ አስቦ ነው ብሎ ተረጎመው፡፡ ይህን እያሰበ ቤቱን ለቆ ወጣ….
ስራ መግባት አልፈለገም፡፡ ስለዚህ እንዴት አድርጌ ቀኔን ልጋልበው ብሎ ሲያስብ፣ ቁጭ ብሎ ብቻውን ከዚህ በኋላ የሚገነባውን ህይወቱን እያሰላሰለ ድራፍት መጠጣት ፈለገ። መጠጥ ከጠጣ ቆይቷል፡፡ የሚበላውም የሚጠጣውም ስራውን ብቻ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ሊኖር አስቧል፡፡ ምናልባትም ሚስቴን እዛው እየጠጣሁ አገኛት ይሆናል ብሎ በማሰብ፣ ከሰፈሩ ራቅ ብሎ ያገኘው አንድ መጠጥ ቤት ውስጥ ጎራ አለ፡፡
ገና ግቢው ውስጥ እንደገባ፣ ከአንዲት ብቻዋን ከተቀመጠች ሴት ጋር አይን ለአይን ተገጣጠመ። ወዲያው ግን አንገቱን አቀርቅሮ እሷን ለማየት እንዲመቸው አድርጎ ፊትለፊቷ ተቀመጠ፡፡ ቀስ ብሎ ቀና አለ…ተደብቃ እያየችው አያት፡፡ በጣም ታምራለች፡፡ የሚወዳት አይነት ሴት ናት፡፡ አሁን እየተከሰተ ያለውን ነገር የትኛውም የአስትሮሎጂ ተመራማሪም ሆነ ደብተራ ሊመሰጥርለት አይችልም…ይሄ ሚስጥራዊ የህይወት ህግ ነው፤ እዚህ ድረስ ያለወትሮው እየጎተተ ያመጣው፡፡ እርግጠኛ ነው በሚያየው ነገር፡፡ አሁንም እንደምንም ብሎ…አንገቱን አስጨንቆ ዞሮ ተመለከታት፡፡ ልክ እንዳያት አቀረቀረች፡፡ አሁን እርግጠኛ ሆነ፡፡ የምሯን አይታኛለች ብሎ አሰበ፡፡ ስለዚህ ቀጥሎ ለሚመጣው ሂደት ቀመር እንዳለበት ገባው፡፡
እንዴት አድርጎ እንደሚያናግራት ማሰላሰል ጀመረ፡፡ ፊቷን ወደ ሌላ አቅጣጫ ስታዞር ጠብቆ፣ አይኖቿን ብቻ ነጥሎ በማየት፣ ማንነቷን ለመረዳት ሙከራ ማድረግ ጀመረ፡፡ በዚሁ ሰዓት ላይ ጭንቅላቱ ምንም አይነት ነገር ቢነግረው የተነገረውን በሙሉ ለማድረግ፣ የስሜት ህዋሶቹን እንደሚያዛቸው እርግጠኛ ሆኗል፡፡
አይኖቿ ጎላ ጎላ ማለታቸው ምናልባት የራስ መተማመንን መንፈስ፣ በአይኖቿ ስፋት ልክ ተፈጥሮ እንደሰጠቻት ገመተ፡፡ ስለዚህ ቀርቧት ከመለፋደድ ይልቅ፣ ልክ እንደሷ እሱም ምን ያህል በራሱ የሚተማመን አይነት ሰው እንደሆነ ሊያሳያት፣ የመጀመሪያውን ቀመር መቀመር ጀመረ፡፡
ቀረብ ብሏት የሷን አስተያየት ሳይጠብቅ ዝም ብሎ አጠገቧ ሊቀመጥ አሰበ፡፡ ተቀምጦም ለጥቂት ደቂቃዎች ምን እያደረገ ነው ብላ ስታስብ፣ እሱ ግን ምንም ሳይናገር ዝም ብሎ ወደ ሌላ አቅጣጫ በማየት ትኩረት ሊነሳት አሰበ፡፡ ሚስጥራዊና ምንነቱን ለመረዳት የሚያጓጓ የወንድ አይነት፣ ሴቶች ይወዳሉ ብሎ ስለሚያስብ፣ ከፊቷ ተገስጦ ሚስጥር ሊሆንባት ወሰነ፡፡
ከቆይታም በኋላ ሲጨንቃት፤”ይቅርታ የኔ ወንድም ሳታስፈቅደኝ ነው የተቀመጥከው?” ብላ እየተሽኮረመመች ስትጠይቀው በህሊናው ታየው፡፡ ያን ሰዓት ላይ ነው ዞሮ አይኖቿን ሊመለከት ያሰበው፡፡ ዞሮም ለተወሰኑ ሰከንዶች ቃላት በምላሱ ሳያመርት ዝም ብሎ ያያትና …
“አይኖችሽ ይጣራሉ፡፡:” ብሎ ሲመልስላት፣ በአይነ ህሊናው ታየው፡፡ በገዛ ማንነቱ መቅናት ጀመረ፡፡ በጣም የሚፈለግ ሰው መሆኑን ተረድቶ፣ አንድ ጊዜ ቀና ብሎ አያት፡፡ ልጅቷ እሱን ማየት አቁማ ጉጉት በላዩ ላይ ያዘለው አይኖቿን በር ላይ ጥዳ በሀሳብ ሄዳለች፡፡ ሰይፉ ልክ እንደሱ፣ ስለ እሱ እያሰበች እንደሆነ ጠረጠረ፡፡ እንዴት ግን በአንድ ጊዜ ከኔ ፍቅር ሊይዛት ይችላል ብሎ አሰበ፡፡ ለዚህ ጥያቄ መልስ አጣለት፡፡ መልሱ ያለው በጠዋት ወትውቶ ያነቃው የተፈጥሮ ሚስጥር ውስጥ እንደሆነ ገመተ፡፡
ጃንቦ አዘዘ…
ደገመ…
ደጋገመ….
መጠጥ አግኝቶ የማያውቀው …የአልኮል በርሀ የሆነው ጭንቅላቱ፣ ከሚያስበው ፍጥነት በላይ ያሳስበው ጀመር፡፡ ይህች ሴት አንዴ እሱን፣ አንዴ በሩን እያየች አምታታዋለች። ቅድም ያቆመውን ሀሳብ፣ የስካር መንፈስ በሚጎትተው ጭንቅላቱ ማሰብ ጀመረ፡፡ እንዲህ ብላ የምትመልስለት መሰለው…
“እንዲሁ ሳይህ ስላንተ ማወቅ ፈለኩ፡፡ ስትታይ ሚስጥራዊ ሰው ነው የምትመስለው፡፡ አይኖችህ ነፍስን መመዘን የሚችሉ ይመስላሉ። አለባበስህ ለህይወት ያለህን ክብር ይናገራል። ስትገባ ገና ያየሁት አረማመድህ ደግሞ ምን ያህል በራስህ የምትተማመን ሰው እንደሆንክ ይተርካል፡፡ ምንም ባትናገር ራሱ የመልክህ ሰሌዳ ቃላት ሆኖ ሀሳብህን ይሰብክልሀል… “እያለች ልትቀጥል ስትል፣ የሚያቋርጣት ይመስለዋል… እንዲህ ብሏት….
“ስምሽን እስካሁን ያልጠየኩሽ ስምሽን እየሰማሁ ከእንቅልፌ ስለነቃሁ ሊሆን ይችላል። የት ነው የተወለድሽው ብዬ የማልጠይቅሽ፣ ብርሀን የሞላው ልቤ ውስጥ…ውበት የተፀነሰበት ህሊናዬ ውስጥ…አለምን መሸከም የሚችለው ትከሻዬ ላይ አድርጌሽ ከፈጠርኩሽ ስለቆየሁ ነው፡፡ ሳትወለጂ ነው የወለድኩሽ--" የሚላት ይመስለዋል፡፡ ይህንንም ስናገራት አይኖቿ በእንባ ይሸፈናሉ ብሎ አሰበ፡፡: ከዛም በግራ ጉንጯ በኩል ብቻ አንድ የእንባ ዘለላ የደስታዋን ሀዲድ ተከትሎ ዝምም እያለ ሲወርድ ይመለከታል። በቀስታ ተነስቶም እንባዋ ያልጎበኘውን የቀኝ ጉንጯን በቀዘዘዝታ ሲስማት፣ በህሊናው ፍንትው ብሎ ታየው፡፡ ምንም ሳትናገር እያያት ብቻ አሳዘነችው፡፡
ከበፊቱ ጎላ ጎላ ማለት የጀመሩት አይኖቹ፣ በሙሉ ድፍረት ልጅቷ ላይ ማፍጠጥ ጀመሩ። በዚህ ሰዓት ላይ ልጅቷ ግራ እየገባት ነበር ሰይፉን የምትመለከተው፡፡ የሱ ጭንቅላት ውስጥ በእርግጠኝነት መንፈስ የተፈበረኩትን ቅዠቶች፣ ይህች ሴት አታውቃቸውም፡፡ ሰይፉ ከፊቷ ተቀምጦ…በተመስጦና በስካር ድንዛዜ ምን እያሰበ እንደሚመለከታት ብታውቅ፣ ለሁለቱም መልካም መንፈስ በፈጠረ ነበር፡፡ ሆኖም እሷ ምንም የምታውቀው ነገር የለም…ያልተከሰተውን ህይወት…ያልተነገሩ ቃላት መካከል ቁጭ ብሎ የምሩን እየኖረ ያለው ሰይፉ ብቻ ነው፡፡
እዛው መጠጡን እየጠጣ በተቀመጠበት የሚደፋ መሰለው፡፡ ለካስ እሷን እያሰበ ድብን ብሎ ሰክሯል፡፡ በስሜት ውስጥ ሆኖ በፍጥነት ሲጠጣው የነበረው ድራፍት፣ አናቱ ላይ ሌላ ሀሳብ ሆኖ ጉብ ማለት ሲጀምር ታወቀው፡፡ ስለዚህ በፍጥነት የሆነ ውሳኔ መወሰን እንዳለበት አሰበ፡፡ ሆኖም ተፈጥሮ ለሱ ብቻ የለገሰችውን ታሪክ በድል ለመወጣት፣ የታሪኩን ፍፃሜ እዛው በተቀመጠበት ጨርሶት ነው፣ ተነስቶ ወደ እሷ መሄድ ያለበት፡፡
ልጅቷ እዛ ቦታ ላይ ከተቀመጠች አሁን ሁለት ሰዓት አልፏታል፡፡ ድፍረት አግኝቶ እስኪያናግራት ድረስ ነው፣ እየጠበቀችው እንደሆነ አድርጎ እያሰበ ያለው፡፡ እርግጥም ነው ከቆይታ በኋላ ሰይፉ፣ ሙሉ ለሙሉ ልጅቷ ላይ ማፍጠጡን ተያያዘው፡፡ ሳያስበው እርግጠኛ ሆኗል…ሳያስበው ለሱና በሱ ብቻ የተፈጠረች አድርጎ ነው እየተመለከታት ያለው…ከዚህ በፊት የማያውቃት እንግዳ ሴት መሆኗን እዛው በተቀመጠበት ረስቶት ቁጭ ብሏል፡፡ ምን ጉድ ውስጥ ጭንቅላቱን እንደከተተው የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ የሚገባው አንድ ነገር ብቻ ነው። እስካሁን ሲያኳትነው የከረመው ህይወቱ፣ ለልፋቱ መልስ እየሰጠው እንደሆነ ብቻ ነው እያሰበና እያመነ ያለው፡፡ ከዚህ በኋላ ራሱን ማዳን አይችልም ፡፡ ቃላትም ሆኑ የምድር ሀይሎች አሁን ያለበት እምነቱ ላይ ምንም አይነት ተፅዕኖ ማሳደር እንደማይችሉ ነው የሚያውቀው፡፡
ስካሩ ከፍ ስላለበት ሀሳቡ ጡዘቱን አክርሮት፣ ለራሱ በራሱ እንግዳ የሆኑ ቅዠቶችን ማምረት መጀመሩን መረዳት ጀመረ፡፡ ከዚህ በኋላ ቢጠጣ አንደበቱ ክዶት እንደሚያመልጠው ገመተ፡፡ ስለዚህ ትንፋሹን ሰብስቦ ሄዶ የወደፊት የፍቅር አጋሩን… ህይወት ልፋቱን አይታ የከፈለችው ደሞዙን፣ ጊዜው ሳይዘገይ በፍጥነት መቀበል አለበት፡፡
ሰይፉ ከተቀመጠበት እንደ ቁስለኛ ወታደር እየተሳበ ተነሳ፡፡ ልክ እሱ እንደተነሳ ልጅቷ በር በሩን እያየች ፈገግ ስትል ተመለከተ፡፡ ደስታዋ ቅርቧ እንደሆነ ሲመለከት፣ ጣዖቱን ማንም ሳይነካበት ቶሎ ሊከልላት መራመድ ሲጀምር፣ አንድ ወጠምሻ የሚያክል ፍጥረት፣ ፈገግ እያለ መጥቶ ከልጅቷ ጋር ተቃቀፈ፡፡ ከስሯም ተቀምጦ ስልኩን በማውጣት ያናግራት ጀመር…
“ተመልከች ያገኘሁልሽን ቬሎ? አያምርም?...ይህን ቬሎ ለብሰሽ ለማየት መላዕክት፣ ከሰማይ አምፀው መጥተው ሰርጋችን ላይ የሚታደሙ ይመስለኛል፡፡”
ልጅቷ ከተቀመጠችበት ተነስታ የወጠምሻው ሰው ወጠምሻ ከንፈሮች ላይ ከንፈሮቿን አተመቻቸው፡፡ ከሰይፉ ፊት ለፊት ሆነው ነገር አለሙን ረስተውት ለጥቂት ጊዜ ተሳሳሙ፡፡ ሰይፉ የሚያየውን ነገር ማመን ከብዶት፣ በሰላም ፍቅር የሚለዋወጡት እንግዳ ሰዎች ላይ ማፍጠጡን ተያያዘው፡፡
የምር የሱ እንደነበረች አድርጎ አምኖ ነበር፡፡
የምር ህይወት ልጅቷን ከተኛችበት ቀስቅሳ ወደ እሱ እንደላከቻት ልቡ ተቀብሎ ነበር፡፡ እንደዚህም አድርጎ ካመነ ረዥም ጊዜ አሳልፎታል፡፡ ሆኖም ሁሉም ነገር አይኑ እያየ ሲፈራርስ ተመለከተ…በተስፋ መቁረጥና በሀያል እምነት ውስጥ ሆኖ ከዚህ በፊት ተዋውቋቸው የማያውቃቸው እንግዳ ሰዎች ላይ ተቆጥቶ ተናገረ…
ልጅቷ ላይ አፍጥጦ…”የት ነው የምታውቂው?” ብሎ ጠየቃት፡፡
ሁለቱም ፍቅረኛሞች ዞረው ግራ በመጋባት ተመለከቱት፡፡ ደግሞ ጠየቃቸው…
“የት ነው የምትተዋወቁት ነው እኮ የምለው?” መስከሩን ረስቶታል፡፡ ሁሉንም ነገር ረስቶት ቁጭ ብሏል፡፡
የልጅቷ እጮኛም ከተቀመጠበት ተነስቶ ከሰይፉ ፊት በመቆም፣ አሁን ያለበትን ሀሳብና እምነት ከጭንቅላቱ ውስጥ በአንድ ቡጢ ሊያባርርለት ተዘጋጀ…ሆኖም አንድ ጊዜ ዞሮ ልጅቷን ቆጣ ብሎ ጠየቃት…
“ከዚህ በፊት ታውቂዋለሽ?”
ልጅቷ ግር ብሏት ሰይፉን በጭንቀት እያየችው …”አረ ያለ አሁን አይቼውም አላውቅ።” አለች፡፡
ሰይፉ ከስካሩ መንቃት አቃተው፡፡ እስካሁን ያመነውን እምነት መሸሽ አቃተው፡፡ የወደፊት ሚስቱን…የተፈጥሮ ስጦታውን ዝም ብሎ ማጣት አልፈለገም፡፡
“አንተ ራስህ ማነህ?” ብሎ ወጠምሻውን ሰው ሊጠጋው ሲል ብቻ፣ ያለው ትዝታ ነው የሚያስታውሰው…
ካልጋው ላይ ሆኖ…
ጠዋት ሲነቃ…
የበለዘው አይኑን በመስታወት እያየ…
ትላንት ዘላለም እስኪመስለው ድረስ ለማስታወስ እየሞከረ…
ምን ያህል የተረገመ ቀን እየጀመረ እንደሆነ እየተረዳና እያመነ ሲነቃ ነው፣ የመጨረሻው ትውስታው ከጭንቅላቱ የተቀላቀለው፡፡
ህይወትን ያዳመጠበትን ጆሮውን ቆርጦ ቢጥለው ወደደ…ለፍላጎቱና ለአጉል እምነቱ አሳልፎ የሰጠው አይኑን ጎልጉሎ ቢያወጣው ተመኘ…ትላንት የሚባለው…ትውስታ ውስጥ ብቻ ቦታ ይዞ የሚቀመጠውን የጊዜን ልጅ ቢያገኘውና ነገው ድረስ ቀጥቅጦ ቢያጠፋው ወደደ፡፡ ዛሬና አሁን ብቻ ትላንትን መግደል እንደሚችሉ አስቦ አስቦ ከደረሰበት በኋላ፣ ዛሬውን ራሱ ጠልቶት ቁጭ ስላለ… የዛሬው ቀን ደግሞ ሌላ አጉል ፍላጎት ከጭንቅላቱ እንዲያመነጭ ከማድረጉ በፊት ብሎ፣ ጊዜ ሳያባክን፣ ጥቅልል ብሎ አልጋው ውስጥ በመግባት፣ የህልምን አለማት የሚያስተዳድረው አምላኩን፣ በፍጥነት በሩን እንዲከፍትለት በመማጠን፣ አይኖቹን እንዳይነቁበት አድርጎ ከደናቸው፡፡
Saturday, 12 August 2023 20:48
አዲስ ዓይን - አዲስ ህይወት
Written by በኪሩቤል ሳሙኤል
Published in
ልብ-ወለድ