ሽምግልና ሳያውቀኝ (ሳልደክም) በፊት፣ ያጣሁትን መጽሐፍ ፍለጋ፣ ወደ መርካቶ አቀና ነበር። የልጅነት ጉርምስናዬ ላይ የካህሊልን The prophet መጽሐፍ መርካቶ ገዝቼ ስራመድ፣ ከብዙ መኪና ጋር እየተጋፋሁ፣ የመጽሐፉን ቅጠል እየገለጥኩ አነብ ነበር። ካህሊል እንደ ፍላፃ ወደ ልቤ የሚወረውራቸው ቃላት፣ ምናቤን የገለጡ ጣፋጭ ወይን ያጠጡኝ ነበር።
ወጣትነቴም እንደ ልጅነቴ፣ በመጽሐፍ አክናፍ፣ የምናብ ሰማይ ላይ መብረርን ይወዳል። በነሲብ አንድ መጽሐፍ ከዚሁ ቦታ ገዝቼ ነበር።
መጽሐፉ ብዙም አላስደሰተኝም (ርዕሱና ደራሲው ይቆዩኝ)። ከስንት ጊዜ በኋላ እያዘገምኩ ስጨርሰው፣ ከጀርባው የተተዉ አራት ባዶ ወረቀቶች ላይ በእጅ የተፃፈ አስደንጋጭ ፅሁፍ አየሁ። ማንበብ አልፈለኩም፤ ግን አነበብኩት። ንፁህ ሆሄያት፣ ቃላትና ጥልቅ ሀሳቦች ውብ በሆነ ጥቁር ቀለም ብዕር ተፅፈዋል።
ውበት የበዘባቸው ነገሮች ህመም የበዛባቸው ናቸው። አደባባይ ላይ መቆም የቻለ ሀዘንተኛ፣ በሕቡዕ ደስታ የሰከረ ነው። ለዓይን ያጓጓ፣ ለልብ አደጋ ነው የሚል ተረት መሰል ሥነልቦናዊ ፍራቻ አለኝና፣ እየሰጋሁ ማንበቡን ጀመርኩ።
“ለመሞት የወሰንኩት ለመኖር ተስፋ ጎድሎኝ አይደለም (በዚህ ደረጃ ደደብ አይደለሁም)። ለመሞት የፈለግሁት እንደ ሌላው ሥነ-ልቦናዊም ... አካላዊም ችግር ገጥሞኝ አይደለም። ሞትን ለዓመታት አጥንቼዋለሁ። ወደ ሞት የሚሄዱ ሰዎችን መርምሬያለሁ። ሁሉም ሞትን ይፈራሉ። ከመሞታቸው ጥቂት ደቂቃ በፊት ደግሞ ሞትን እራሱ በውስጠኛው አይናቸው ይመለከቱታል። ሞትን ግን አያውቁትም። በህይወት እያሉ ያዩታል ግን አይገልፁትም። ሰው የአካልና የነፍስ ጥምር ስሪት ነውና አካሉን ስላላየን ብቻ ጠፋ፣ የለም ለማለት አንደፍርም። በግሪክ ሥነ-ተረት ውስጥ ቀድሞ የተፈጠረው የፍቅር አማልክት ኤሮስ ነው። ከአንዲት ጥቁር አክናፍ ካላት ወፍ እንቁላል፣ የፍቅር አማልክት ተፈጠረ። ይህቺ ወፍ ዘመኗን ጨለማ ላይ ያሳለፈች ናት። ታላላቅ እውነቶች የአፈ ታሪክ ልጆች፣ የተረት ደግሞ የልጅ ልጆች ናቸው። እውነት የለም - ያለው አሳማኝ ውሸት ብቻ ነው። እግዜር ዓለምንና ሰዎችን ፈጠረ። ብርሃንን ዘረጋ። ህይወት ያላቸውንና የሌላቸውን ሁሉ አቆመ። እሱስ ከየት መጣ?
ከእግዜር ጋር የነበረው ጨለማ ብቻ ነበር፤ በአይሁድ ብሉይ ዘፍጥረት ውስጥ። ጥንት የግብፅ ሰዎች፣ ቅድመ ዓለም ላይ የነበረው፣ የጨለማና የውሃ ውህድ ነው ብለው ያምናሉ። የግሪክ ሥነ-ተረት፣ ቅድመ ዓለም ላይ ጨለማ ብቻ እንደነበር ፣ ያም ጨለማ ላይ አንዲት ወፍ ስለመቀመጧ ያምናል። ብዙ ተረቶች፣ ጨለማ የእግዜር ከዓለም በፊት የነበረ ወዳጅ ስለመሆኑ ቢያምኑም፣ መነሻዬ ናቸውና ገለታ ይግባቸው። ጨለማ ግን ጨለማ ብቻ አይደለም። እግዜር ህይወትንና ዓለምን ከመፍጠሩ በፊት የኖረው ከጨለማ ጋር ብቻ ነው (ይቅርታ፤ እግዜር ከመወለዱ በፊት እና በኋላ እያልኩ በአልቦ ዘመን ጊዜን ከፈልኩ እንጂ ጨለማ የእግዜር አያት እንጂ አባት አይደለም) ምናልባት ለሺህ አሊያም ለእልፍ አዕላፍ ዘመናት (ይቅርታ ቅድመ ዓለም ላይ ዘመን የለም - ግን ዘመንን ለመፍጠር እንገደዳለን) የእግዜር ጓደኛ (አያት) ጨለማ ብቻ ነበር። ጨለማ አልቦ ብርሃን ነው። በዚህ መንገድ፣ ብርሃን የህይወት መፈጠር ትዕምርት ነው። ያለ ብርሃን ህይወት አይገለጥምና፣ ብርሃን የህያው መነሻ ነው። ህይወት ከብርሃን ማሕፀን ነው የተወለደው። እግዜር ከአፈር ለሰራው ግዑዝ የህያውነትን ትንፋሽ ሲዘራ፣ የብርሃንን ዘንግ በረቂቅ መለኮታዊ ቅብብሎሽ መስጠቱ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ህይወት ብርሃን ነው ካልን ጨለማ ሞት ሊሆን ነው። ይሄ ግልብ ፍካሬ የሚወስደን ግን ወደ ላቀ እውነት ነው። የላቀ እውነት ደግሞ ሁሌም ተረት ነው። ተረት ያልተረዳነው ረቂቅ እውነት ብቻ ነው። ግን ተረት እንደወረደ (በቀጥታ) እውነትነቱን አይገልፅም። ሀቆቹን በምሳሌ የመሸፈን ልማዱ... ሌላም ትዕምርታዊ ንግርቱ ተድበስባሽ ብቻ አያደርገውም።
ህይወት ከብርሃን ተወለደ ካልን፣ ሞት ከጨለማ ተወልዷል ማለት ነው። ሁሉም የተቃርኖ ውጤት ፍካሬ ነውና። ሞት ደግሞ ድብቅ የእግዜር ቅድመ አለም ሁነት ነው። መሞት አለመኖር አይደለም መለኮትን የመጨበጥ፣ ልዕለ ተፈጥሯዊነትን የመላበስ ረቂቅ እውነት እንጂ። በዓለም ላይ ሞት እግዜርን ሆኖ ዳግም የመወለጃ ፍኖት (ማሕፀን) ነው። ቅድመ ዓለም ሞት አለመኖር ነው - ክስተተ ዓለም ላይ ደግሞ እግዜርን ሆኖ መወለጃ።
እግዜር የተፈጠረው የሞት የዘር ፍሬ ለሁለት ተቃራኒ (የማይዋኻዱ የሚመስሉ) ፈሳሾች ተከፍለው በነበረበት ጊዜ፣ ሞት ተቃርኖውን አንድ አድርጎ ባያያዘበት የገዛ ናጥራዊ ማሕፀኑ ውስጥ ነው። ይሄ ማሕፀን አላረጠም። እልፍ እግዜሮችን ፀንሶ ሊወልድ ለእልፍ ጊዜ ያምጣል ግን አይወልድም። ምክንያቱም የበኩር ልጁ ሞት (በቅድመ ዓለም ሞት አለመኖርን ይወክላል) ነው ተከታይ ልጁን (እግዜሩን) ለታላቅ የእግዜርነት ብቆታ የሚቀባው። ሞት ደግሞ የጨለማ ልጅ ነው። ጨለማስ?
ጨለማ የአልቦነት ፅንፍ መገኛ ነጥብ ነው።
እና እራሴን በእራሴ ገድዬ ስሞት እንዳያችሁ አታልቅሱ። ሞተ ብላችሁ አትዘኑ። ከሞት የተወለደው የሞት የበኩር ልጅ ር እግዜር ታሞ ለህልፈት እያጣጣረ ነውና ሞቱ እኔን እግዜር አድርጎ የመውለጃ ተፈጥራዊ ሁነት ስለሆነ አታልቅሱ።
የመጪው ዘመን እግዜር እኔ ነኝ። የምሞተው ለእርካሽ ተስፋ ጎድዬ አይደለም። የምሞተው እግዜርን ሆኜ ለመወለድ ነው። የመጪው ብልሁ አምላክ እኔ ነኝ። የምሞተው ለነገው ታላቅ አምላክነት ተቀብቼ ነው።
ዓለምን በቃሌ አፀናለሁ። ብርሃን ለጨለማ መስታወሰው አቆማለሁ። ህይወት በፍቃዴ ይታነፃል።
Saturday, 12 August 2023 21:02
ጨለማ | ሞት | እግዜር
Written by አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Published in
ጥበብ