Monday, 14 August 2023 20:18

የጦርነትን መጨረሻ ማን ያያል?

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(1 Vote)

ቆሜ መንገዱን ስቃኝ፥
ድንገት ስሜት ቢደቃኝ፥
ዓይኔን ገልጬ አየሁት፥ ጊዜ ጃርትን ይመስላል፥
ሲኼድ በአውራ ጎዳናው፥ገላው እሾህ ይጥላል።
መቼ ነው ይኼን ግጥም የጻፍኩት? ለምንስ ዛሬ ደገምኩት? የተሻሻለ ነገር ስለሌለ መሆን አለበት። የ”ነበር” ስሜቶችን በ “ነው”ካገኘናቸው፣ብሎም ወደ “ይሆናል” ካሻገርናቸው መኖር ብላሽ።
‘Every end is a new begining’
አንደኛው የዓለም ጦርነት፣ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ወለደ። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት፣ የቀዝቃዛውን ጦርነት ወለደ። እያንዳንዱ ዳርቻ አዲስ ውጥን ይዞ ይመጣል። አለቀ ያልነው ጦርነት፣ በአዲስ ውጥን ተከስቷል። ነገርዮሹ “ጠፈር አልፎ ጠፈር፣ ሰማይ አልፎ ሰማይ” ዓይነት  ነው።
የጦርነትን መጨረሻ፣ «የሞተ ብቻ ነው የሚያየው»። በሕይወት ሳለን ከጦርነት ማምለጥ የሚቻል አልሆነም። የሲቪል ጦርነት፣ የሳይበር ጦርነት፣ የወዶ ፈቅዶ ጦርነት ...ሁሉም በየዓይነቱ ሲያንዣብቡ ይታያሉ።
መኖርም ይደክመኝ ይዟል።
ሁቱ ቱትሲ አንብበው፣ የሶሪያን ታሪክ ዘግበው፣ የመጀመሪያውና የሁለተኛውን ዓለም ጦርነት ጠቅሰው፣ አና ፍራንክን ምሳሌ አድርገው፣ ቀይ ሽብር ገለመሌን ተረድተው ስለ ጦርነት ጉዳት ከሚናገሩት  በላይ ይሰማኛል። ለምን? ቀንደኛ ተጠቂ ነኛ። ብዙ የዋጥኩት ሰቆቃ፣ ብዙ በሳቅ የምሸነግለው ኀዘን፣ ብዙ ቤተሰቦቼንም እንዳጣሁበት የማውቅ እኔ ብቻ ነኝ።
«የሞተው ወንድምሽ
የገደለው ባልሽ
ኀዘንሽ ቅጥ አጣ
ከቤትሽ አልወጣ»
ይሏታል ያቺን ሴት_ ይበልጥ ሊያሳዝኗት። ሟች በመሞቱ አይጠየቅም፣ ገዳይ በመግደሉ ግን ፍርድ ይጠብቀዋል። ምላስ ውስጥ የገባ ስም ቀን ይጠብቃል። እንደ ፋሮ (በቶሎ መዞር የማይችል አውሬ) ወደፊት ብቻ የሚመድር ሳያይም ሆነ አይቶ የሚያልፋቸው ደቂቅ ሕይወቶች ይኖራሉ። ያልታዩት ግን ጠቃሚዎች ናቸው። መታየትን የመሰለ ጠላት ምን አለ?
«በፍራሻችን ሥር ፤ ቃሬዛ ተጣብቆ
በልብሳችን ገበር ፤ከፈን ተደብቆ
የአዳሩ ጥሩምባ ፤ከሙዚቃ ልቆ
በዘንድሮ ጣቶች ፤ከርሞ ላይነካ
ደህና ሰንብች ማለት፤ዘበት ኖሯል ለካ»
ይላል በዕውቀቱ _ለአጣት እህቱ። ዘበት ሆነብን ስንብት። እንዲሁ ነው ይገርማልን ያጣሁት። ጣቴ ጣቱን የነካ የተመረቅኩ ሰሞን ነበር። ደህና ሁን እንኳ እንዳልለው ከል የሆነኝ “የዝሆኖች ጸብ” ነበር።
የጦርነትን መጨረሻ የሚያየው የሞተ ብቻ ነው፤ በፕልቶም አፍ ይውጣ በማን ትልቅ ሐቅ አዝሏል። ቅዱስ ያሬድ ያያት ትል፣ ስድስት ጊዜ ሞክራ በሰባተኛው የወጣችዋ የት ደረሰች በሞቴ? የወጣችው ዛፍ ላይኮ ነው። ዛፉ ደግሞ አቀበት ነው፤ ለእሷ። ታዲያ ሌላ ሰባት ሙከራዎች በየቦታው እንደምታደርግ ለምን ዘነጋን። «አንኳኩ ይከፈትላችኋል ፤ስትገቡ ሌላ በር ይጠብቃችኋል» ነው ነገሩ። ሰላም ሰላም በሉ ሰላም ይወርዳል፤ በማግስቱ ጠብደል ጦርነት ይወልዳል እንደማለት።
የሀገራችንን ሰላም ከጦርነት ለይቼ አላየውም። መበሻሸቅ ይበዘዋል። የቱም እንዳያምርብን ማን ረገመን? ይቺ ሰፈር እኮ «ወንድ አይወለድብሽ» ተብላ ተረግማለች ያሏትን መንደር አስታወስኩ። ባሰፋው ሃገራችንን «ሰላም አይመርብሽ» ያላት ማን ይሆን?
በጎኔ ከያዝኩት ኮረጆ ትዝታ እየዘገንኩ ነው። አሁንም «ይገርማል» ላይ ነኝ። ፍጥነቱ፣ ኩሸቱ አይረሳኝም። በእናቱ ዓይኖች ዙሪያ የተጠለሉ እንባዎችን ሳይ ህመሜ ያገረሻል። ወደ ሌሎች እናቶች ሊዛመት የቃጣውን ኀዘን ሳይ አዝናለሁ።
ስሙና ግብሩ ተመሳሰለ_ይገርማል። የጦርነትን መጨረሻ አይቶ ይሆን? ወይስ ቦታ ከለልሎን?_ዘበት ነው ቁርጡን ማወቅም። ደርግ የበላቸው ሁለቱ አጎቶቼ ፤በፎቶ የማውቃቸው ይቆረቁሩኛል። ስሜቱ የደረሰኝ በእናቴ በኩል ነው። ኀዘን ይወረስ የል? ወንድም አልባ ሲያደርጋት፣ ያ አረመኔ ጥርሴን ነከስኩበት (ጥሩ ሥራዎቹ ሳይናቁ)። መሪ ሊታረቅ የኗሪ መተላለቅ ይከነክነኛል።
እናቱ አይናዲስ ትደውልልኛለች። አነሳለሁ፤ እንባዬን እየተቆጣጠርኩ።
«የልጄን አድራሻ አጣሁ እኮ»
«አይዞሽ ይገኛል!...» እላትና ስሜቱን አልችለውም። እናት መከረኛዋ። በዚች ምድር አበሳዋን እንድታይ የተፈረደባት የሴት መለኮት እናት።
ተላላ ነው ተላላ ነው
የእናት ሆድ አይችልም
ይሞታል ነው እንጅ
ይገድላል አትልም።
እስኪ እንደ እናት ይሞታልን ልመዱ። ፍርሃት ጥሩ ነው በቦታው። ይገርማል በወንድሜ ላለመመታቱ ምን ያህል እርግጠኛ ነኝ? ሁለቱም ተቃራኒ ተፋላሚዎች ናቸውና። ህመሙን የሚያከብደው ይኼ ነው። አንድ ቤት ያደጉ ልጆች የተቃራኒ ጦር አባል መሆን።
ስንወለድ እናለቅሳለን፤ስንኖርም አናጣው።
ስንወለድ እርቃን ነን፤ስንሞት ልንደግመው።
በመሐል መኖር አለች። ለምጻችንን ሸፍነን የምንቆይባት_የኪራይ ሕይወት። «እኔም የእኔ አይደለሁ»ን በቀላል ለምን አየነው? ነፍስ ሥጋን ተከራይታ መኖሯ እሙን ነው። የተከራይነት ዕድሜዋ ሲያልቅ ሥጋን ለአፈር፣ ለዘመዱ ትታው ትኼዳለች። አካላችንን እንኳ በንብረትነት ማቆየት ያልቻልን ሰዎች መሆናችንን ብናውቅ ለትርፉ ባልተጨነቅን።
የይገርማል አባት አናጺ ነው።
በሌሊት ተነስቶ ወደ ሥራ ይኼዳል። ይገርማል እንደጅራት ይከተለዋል። በቶሎ ሙያ ለምዶ አባቱን ማገዝ ችሎ ነበር። ሙያን በቶሎ የመልመድ አባዜው ምናልባት ሞትን በቶሎ አስለምዶት እንዳይሆን እሰጋለሁ። አባቱ፣ ባለቆቡን ምስማር እያሳየ (ስለ ሲመ˙ቱ መጥበቅ)፣ ቋሚውን እየጠቆመ (ስለ ሃገር ምሰሶነት)፣ ማገሩን እየነካ (ስለ ሕዝብ አስፈላጊነት)፣ ስለ አውራጅ፣ ዝንቦ እና ክፈፍም ያለውን ብሎት ነበር። ይኼው ለመጥበቅ ሲል ይመታውን በትር ፍለጋ ወጥቶ ቀረ።
እዘኑላት ለሴቷ።
ያለ ልጅ፣ ያለ አባት፣ ያለ ባል ለምትቀረዋ። ጥቂት ህጻናት ቢቀሯት እንኳ በዚህ ዘመን መኖርን ያህል ከባድ ሸክም ለምትሸከመዋ፣ ለሞተው ሁሉ አድግድጋ ፊቷን ስትነጭ ለምትውለው ለእሷ ‘ራሩላት።
የጦርነት መነሻ ሐሳቡ በብዙኀኑ ፍላጎት ቢሆንም እንኳ፤ ጉዳቱ ለየግል ነው። የይገርማል እናትን ለቅሶ ማን አገዛት? ብቻዋን አልቅሳ በጉንጯ ስርጉድ እንባ ስትሰፍር ስትውል ማን ዞሮ አያት? ነገሮች ሁሉ ከመጨረሻው ቢጀምሩ (start from the end) ቢሆን ደግ ነው። ጨለማ ጨለማን አያስወግድም፤ ብርሃን እንጂ፤ ጥላቻም በጥላቻ አይጠፋም በፍቅር እንጂ! (‘Darkness can’t drive out darkness, only light can do that. Hate can’t drive out hate, only love can do that’)
ይገርማል የእግር እሳቴ።
ሰፊ ሱሪ ለብሰህ በጆንያ ውስጥ ያለች ሰንደል መስለሃል ስልህ፣ ጥሩ መዓዛ ባለው ወከልከኝ ያልከውን ልርሳ? ቻው ትልበትን እጅ ቃታ ያስጨበጡትን እስከ መቼ ልርገም? እንስሳት እንኳ ቢጤውን አይገድልም፤ ያለውን ጆርጅ ኦርዌል ስንቴ ልድገም? ምነው ራቅከኝ ወዳጄ።
ቢጤዎችህ መሣሪያቸውን ይዘው ይዘው፣ ሞታቸውን ከወንድማቸው ሊቀበሉ ሲኼዱ  ባየሁ ጊዜ አነባሁ፡፡ እንዴት እንደሚተኩስባቸው አላውቅም። የሰው ልጅ አረመኔ ነው የምለው፣ ይኼን ትራጀዲ ሳይ ነው። አና ፍራንክ ቢጨንቃት ነው፣ “ምንም ቢሆን የሰው ልጅ መልካም ነው” ያለችው። የሰውን ልጅ እንዴት ነው ማልመድ የሚቻለው? ውሻውን የከዳ ውሻ ይሆናል፤ ትዝ አለኝ። ከውሻ እንኳ እያነስን ነው።
ቆሜ መንገዱን ስቃኝ፥
ድንገት ስሜት ቢደቃኝ፥
ዓይኔን ገልጬ አየሁት፥ ጊዜ ጃርትን ይመስላል፥
ሲኼድ በአውራ ጎዳናው፥ ገላው እሾህ ይጥላል።
አዎ! እግር መርጦ ይቁም። የተደገፉት ኹሉ ምርኩዝ አይደለም። መንገዶች ሁሉ ጥሩ ፍጻሜ የላቸውም። ገና ከእንቅልፉ እንደተነሳ ”ና ፓድ እንምታ” ይለኝ ነበር ይገርማል። ወደ ግዑዝ ሳኮ እና ፓድ ስንሰዳቸው የቆዩት እጅና እግሮች ሕይወት ወደ አለው...ወደ ወንድም እየመጡ ናቸው።
ዛፍና  ሌላ ዛፍ ...
ይደጋገፋሉ...ከተቀጥላ ጋር
እኛም ለአመላችን...
እንገፋፋለን፥ ለአንድ ጀንበር አዳር።
ይገርማል_የእግር እሳቴ።
ወንድምህ በጥይት ተመቶ ተርፏል። የአውራ ጣቱ ምርቅዝ የሚቆሰቁሱበትን ጥዝጣዜዎች እርሱ ያውቃል። እያንዳንዷ ህመም ወደ ትዝታው ትረዝማለች። “ባልሆነ” የሚለው ይበዛል። የአንተን የእግር ዳና ስንቴ ጠበቅን። ተረት እየመሰለ ስንት እውነት በአንተ በኩል ተነገረ። አናጺው አባትህ ያቆመው ቤት እርቃኑን ነው፤ ያለሰው ምንስ ሊሆን።
የድሮ ጨዋታችንን የምንከልስበት ቦታ ያዝ ለማንኛውም።
የተዋጋ ብቻ አይሞትም፤ ሰላምን የሰበከም እንጂ። ጥይቶች ሰው አይመርጡም፤ ቃታ ሳቢዎችም ለመለየት ጊዜ የላቸውም። እኔም የጦርነትን መጨረሻ አይ ዘንድ ይርዳኝ። በሌላ ሕይወት እስክንገናኝ እጓጓለኹ።

Read 818 times