ባቢሎንን ከወደቀችበት አንስቼ ሕይወት ዘርቼባታለሁ።የፈራረሰውን ጠራርጌ ገንብቻታለሁ። ግርማዊነቷን እንደገና
አጎናጽፌያታለሁ።አቻ የለሽ ገናና ዝናዋን አድሼላታለሁ…
ይላል ናቡከደነፆር።ኩራቱ ናት - መናገሻይቱ ከተማ ታላቂቱ ባቢሎን።
ናቡከደነፆር፣ ከቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ወጥቶ ታላቂቱን ከተማ ይቃኛል። በሕንጻዎቿ ከፍታ ይደነቃል። ሌላው ይቅር። በከተማዋ ዙሪያ የተሰሩት ግንቦችና በሮች ያስገርማሉ።
በዚያ ዘመን፣ የግንብ አጥር የሌለው ከተማ በሰላም ማደር አይችልም። የወራሪዎች መጫወቻ ይሆናል። የፍርስራሽ ክምር ያደርጉታል። እስከ ወዲያኛው ከታሪክ መዝገብ ይሰረዛል። ባቢሎን ግን የታሪክ ባለጸጋ ናት። ማንም የማይደፍራቸው ግንቦች ተሰርተውላታል።
በከተማዋ ዙሪያ 80 ሜትር ስፋት ያለው “የመከላከያ ቦይ” ተቆፍሯል። በውኃ ተሞልቷል። ታጣፊ የመሻገሪያ ድልድዮች ተሰርተውለታል። ድልድዮቹን አጣጥፎ ማንሳት ይቻላል። መከላከያውን ቦይ ተሻግሮ የሚመጣ ወራሪ፣ ከፊት ለፊት የኮርቻ ግንብ ይጠብቀዋል።
የመጀመሪያው ግንብ “ካር-ኡ” ይባላል።
ሰፊውን ቦይ እያካለለ በከተማዋ ዙሪያ የተሰራው ኮርቻ ግንብ፣ የ2.3 ሜትር ውፍረትና የ7 ሜትር ቁመት አለው። ከላይ በሁለት ሜትር ቁመት የጥበቃ ዘቦች ምሽግ ተጨምሮበታል። 225 ማማዎች ከፍ ብለው ተሰርተውለታል። ጠላት ይህንን ጥሶ ቢገባ… ከሀያ እርምጃ በላይ አልፎ አይራመድም። ትልቁ የዳርቻ ግንብ ይጠብቀዋል።
ሁለተኛው ግንብ፣ “ዱር-ኡ” ይባላል።
በከተማዋ ዳር በዙሪያዋ የተገነባው ዋና ግንብ ውፍረቱ 6.5 ሜትር ነው። ቁመቱ 14 ሜትር። የምሽግ ቆጥ ሲጨመርበት 16 ሜትር ይሆናል። ከ300 የሚበልጡ ረዣዥምና ትላልቅ ማማዎች አሉት። ይህም ብቻ አይደለም። ከአጠገቡ ሌላ ግንብ አለ።
ሦስተኛው ግንብ፤ “ሳል-ኡ” የሚሉት ነው። በ3.7 ሜትር ውፍረት በጡብ የተሰራው ግንብ፣ ከነ ቆጡ 10 ሜትር ቁመት አለው። እንደ ሰንሰለት ለከተማዋ ዐጥር ሆኖ ይጠብቃታል።
ናቡከደነፆር፣ ተጨማሪ አራተኛ ግንብ በጠንካራ ሸክላዎች ዙሪያውን ደርቦበታል - በ3 ሜትር ውፍረት፣ በ7 ሜትር ቁመት።
በከተማይቱ ዙሪያ በአራት ጥምጥም የተሰሩት ግንቦች፣ እያንዳንዳቸው ከ7.5 ኪሎ ሜትር በላይ ይረዝማሉ።
ይህም ብቻ አይደለም። ንጉሥ ናቡከደነፆር ከተማይቱን በእጥፍ አስፋፍቶ፣ አዳዲስ ድርብርብ ግንቦችን ሰርቷል። የከተማ ዳር ግንቦች ይሏቸዋል።
እንደተለመደው በውኃ የተሞላ የመከላከያ ቦይ በዙሪያው አለ - በ80 ሜትር ስፋት።
ቀጥሎም ደንዳና የዳርቻ ግንብ አለ። “ዳሩ ዳኑ” ይሉታል። ደንዳናነቱ ውፍረቱና ውኃ የማይበግረው መሆኑ ነው። በእሳት ተጠብሶ የተዘጋጀ ሸክላ ተደርቦበት በ11 ሜትር ውፍረት የተሰራው ግንብ፣ 13 ሜትር ቁመት አለው። ርዝመቱ 7.5 ኪሎ ሜትር ነው።
ከዚሁ አጠገብ ሌላ ግንብ ጨመረበት። በ7 ሜትር ውፍረት የተሰራው ግንብ ከነ ቆጡ በ15 ሜትር ቁመት አለው። ይሄኛውም 7.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው።
የባቢሎን የመከላከያ ግንቦች፣ ከ1400 በሚበልጡ ረዣዥም የጥበቃ ማማዎች ተጠናክረው የተሰሩ ናቸው። ናቡከደነፆር በዚህ ሁሉ ግንባታ እጅግ ቢኮራ አይገርምም። በእርግጥ፣ ከሱ በፊትም ባቢሎን ለበርካታ ሺ ዓመታት የዘለቀች ትልቅ ባለታሪክ ከተማ ናት። ቢሆንም ግን፣ ነቡከደነፆር በብዙ ዕጥፍ አሳድጓታል።
ከናቡከደነፆር በፊት… የባቢሎን ከተማ ግንቦች በአጠቃላይ 2 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ያህል ነበረ።
በናቡከደነፆር ዘመን… 7.5 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ደርሷል። (የሕዳሴ ግድብ 75 በመቶ ያህል ማለት ነው።)
የመጠን ጉዳይ ብቻ አይደለም። የግንባታ ጥራቱም በብዙ ዕጥፍ አድጓል።
ከናቡከደነፆር በፊት… አብዛኛው ግንባታ “በጡብ” ነበር። በፀሓይ የደረቀ የጭቃ ጡብ ማለት ነው። በእሳት የተጠበሰ ጠንካራ ሸክላ እንደ ልብ አይገኝም ነበር። ከግንባታው 15 በመቶ ያህል ብቻ ነው በሸክላ የተሰራው።
በናቡከደነፆር ዘመን ግን፣ የከተማዋ የመከላከያ ግንባታ ከሦስት ዕጥፍ በላይ አድርጓል። አብዛኛው ግባንታ ደግሞ በሸክላ ሆኗል (65 በመቶ ያህል)።
በሌላ አነጋገር፣ ከናቡከደነፆር በፊት ለከተማዋ ግንቦች 22 ሚሊዮን ሸክላዎችን ተጠቅመዋል።
በናቡከደነፆር ዘመን ግን ከ380 ሚሊዮን በላይ ሸክላዎች በከተማዋ ዙሪያ ዐጥር ግንብ ለመስራት ውለዋል። ልዩነቱ ከ15 ዕጥፍ ያልፋል። ባቢሎን ቀድሞውንም ተአምረኛ ከተማ ናት። በናቡከደነፆር ዘመን ደግሞ፣ የራሷን የቀድሞ ታሪክ “የሚያስንቅ” አዲስ ተአምር አይታለች።
ይሄስ መታበይ አይደለም?
በእርግጥ፣ የቀድሞ ገናና ታሪኮችን ማናናቅ ይቅርና፣ ቸል ማለትም እንደ ትልቅ ኀጢአት ነበር የሚቆጥሩት። የባቢሎን ንጉሦች የራሳቸውን የግንባታ ገድል ለታሪክ ሲያስመዘግቡ፣ የቀድሞ ግንባታዎችን ሳይጠቅሱ አያልፉም።
ናቡከደነፆርም በአባቱ ዘመን የተሰሩ ግንቦችን በክብር አንድ በአንድ እየዘረዘረ ገልጿል።
የራሱንም ግንባታ ጽፏል።
ምናለፋችሁ! ባቢሎን የዓለማችን ገናና ከተማ ሆናለች። ከአጠገቧ የሚደርስ ሌላ ተፎካካሪ አልነበረም። በጉልበት የሚያንበረክካት ሌላ ኃያል አገር የለም። ያን ሁሉ አስተማማኝ ግንብ ጥሶ የሚገባ ከየት ይመጣል?
ቀን ከሌሊት ክረምት ከበጋ ባቢሎን የሰላም ምድር ናት።
በከተማዋ መሐል የኤፍራጥስ ወንዝ ዓመቱን ሙሉ በእርጋታ ይጓዛል። ሲያምረውም እየጋለበ ይጎርፋል። በታሪክ የተነገረላቸው ግዙፍ ግንባታዎች የሚገኙትም ከወንዙ በስተቀኝ በኩል ነው። በወንዙ ዳርቻ ከተገነቡት ወፋፍራም ግንቦች አጠገብ፣ ሁለት ትልልቅ ቤተ መንግሥቶች ተሰርተዋል።
አንደኛው ቤተ መንግሥት የእረፍት ጊዜን ዘና ብሎ ለማሳለፍ የሚያመች ነው። የአትክልት ስፍራዎች፣ መናፈሻዎችና ሰው ሰራሽ ፏፏቴዎች ተሟልተውለታል።
ሁለተኛ ቤተ መንግሥት ትልቅ ነው። 600 አዳራሾችና ክፍሎች እንደነበሩት በተመራማሪዎች ቁፋሮ ተረጋግጧል። መደበኛ የንጉሡ መኖሪያዎችንና የመንግሥት ቢሮችን ያካትታል።
ትልቁ ቤተ መንግሥት ሸክላ የተነጠፈላቸው ግቢዎች (የደጀ ሰላም ቦታዎች) አሉት። ከመሐል የሚገኘው ደጀ ሰላም ከሌሎቹ ሰፋ ይላል። 60 ሜትር በ50 ሜትር ነው። የንጉሡ ደጀ ሰላም ነው። እዚህ ከደረስን…
የዙፋን አዳራሽ ፊት ለፊት ይታየናል። ከንጉሡ ዋና ቢሮ ደጅ ላይ ቆመናል ማለት ነው።
በጌጠኛ ሸክላዎች የተገነባው አዳራሽ ትልቅ ነው። በጥበብ የተዛነቁት ጌጠኛ ሸክላዎች በኅብረ ቀለማት እንደ “ሴራሚክ” ያብረቀርቃሉ።
የዙፋን አዳራሹ ሦስት በሮች አሉት። ግራና ቀኝ በሮቹ 3.8 ሜትር ስፋት አላቸው። ከመሐል ደግሞ ዋናው በር፣ በ5.8 ሜትር ስፋት የተሰራ ነው - ቁመቱ ከዐሥር ሜትር ይረዝማል።
የአዳራሹ ስፋት 52 ሜትር በ17.5 ሜትር ነው። ከ900 ካሬ ሜትር ይበልጣል።
የግድግዳዎቹ ውፍረት ሲጨመርበት 1500 ካሬ ሜትር ይሞላል።
ከጎን በኩል የግድግዳው ውፍረት 2.8 ሜትር ነው። በሌላኛው ጎኑም እንደዚያው።
የፊትና የኋላ ግድግዳዎቹ ደግሞ እያንዳንዳቸው በ6 ሜትር ውፍረት የተገነቡ ናቸው።
እንግዲህ ናቡከደነፆር እንደ አዲስ የገነባቸው የቤተ መንግሥት ሕንጻዎችና ማማዎች ላይ ሆኖ ነው ከተማይቱን የሚቃኛት። ከአጠገቡ ሰፋፊ የክብረ በዓል መንገዶችና ትላልቅ ቤተ መቅደሶች አሉ። የከተማዋ ትልቁ የመግቢያ በር ከበስተግራ በኩል ይታየዋል።
ኢሽታር በር ይባላል። ራሱን የቻለ ሕንጻ ነው ቢባል ይሻላል። የግንቡ ቁመት አራት ፎቅ ያክላል። ውፍረቱ 50 ሜትር ነው። ስፋቱ ከ50 ሜትር ይበልጣል። አሰራሩ እንደ ቤተ መንግሥት ነው። ሸክላዎቹ እንደ ሴራሚክ በጌጠኛ ቀለማት ያብለጨልጫሉ።
ዛሬ በጀርመን በርሊን ሙዚዬም ውስጥ አምሳያውን ገንብተው ለጎብኚዎች ያሳያሉ። በሺ የሚቆጠሩ ጌጠኛ ሸክላዎች ከቦታው በቁፋሮ እንደተገኙና በድብቅ ወደ ጀርመን እንደተጓጓዙ ታሪክ ጸሐፊዎች ይገልጻሉ።
ናቡከደነፆር ግን የከተማዋን ሕንጻዎች የሚቃኘው እንደ ጎብኚ አይደለም። አዝመራውን በኩራት የሚመለከት ነው የሚመስለው።
በስተቀኝ በኩል ደግሞ፣ “ዝነኛው ግንብ” አለ። “የባቢሎን ግንብ” ሲሉ አልሰማችሁም? የባቢሎን ደብር ልትሉትም ትችላላችሁ። ወይም ደብረ ባቢሎን።
ደብረ-ባቢሎን።
ከ2600 ዓመታት በፊት፣ በናቡከደነፆር ዘመን በከተማዋ ዕንብርት ተሰርቶ የተጠናቀቀው ደብር ‘ፒራሚድ’ የመሰለ ቅርጽ አለው።
ስፋቱ ከኳስ ሜዳ ይበልጣል።
91 ሜትር በ91 ሜትር ነው። ቁመቱም 91 ሜትር።
ከ30 ሚሊዮን በላይ ሸክላዎችን ፈጅቷል።
በእርግጥ፣ እዚህም ላይ ናቡከደነፆር ነባር ጅምሮችን ሳይጠቅስ አላለፈም። ደብረ ባቢሎን ከሱ በፊትም ተሰርቷል። ነገር ግን አርጅቶና ፈራርሶ ነበር። የናቡከደነፆር አባት እንደ አዲስ ግንባታውን እንዳስጀመረ፣ ግንባታውንም 15 ሜትር ቁመት ላይ እንዳደረሰው በታሪክ ተመዝቧል። ናቡከደነፆርም ይህን መስክሯል። ከዚያም የግንባታውን ጥራት አሻሽሎ ቁመቱንም 91 ሜትር አድርሶ አጠናቅቆታል። ከ20 ፎቅ በላይ ይሆናል። ከአናቱ ላይም ትልቅ ቤተ መቅደስ ተሰርቶለታል (በአብረቅራቂ ሰማያዊ ሸክላዎች)።
በእቶን እሳት ተጠብሰው በጥራት የተዘጋጁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የናቡከደነፆር ዘመን ሸክላዎች፣ እስከ ዛሬ ድረስ በምድረ ኢራቅ ለቪላ ቤት ግንባታ ተመራጭ መሆናቸውን አስቡት።
አዎ፣ ንጉሥ ናቡከደነፆር በብዙ ጦርነት ትልልቅ ነገሥታትን አሸንፎ ጥሏል። ሰፋፊ ግዛቶችን በወረራ አስገብሯል። እውነት ነው። ይበልጥ የሚኮራው ግን በባቢሎን ግንባታ ነው። በጦርነት ካገኛቸው ድሎች ሁሉ ትበልጣለች።
ሰፋፊ መንገዶቿ፣ የውኃ መተላለፊያ አውታሮቿ፣ የመስኖ እርሻዎቿ… ድንቅ ናቸው።
በባቢሎን ግንባታዎች ላይ ሰፊ ጥናት ማካሄዱና መጽሐፍ ያሳተሙ ተመራማሪዎች ብዙ ናቸው። ዛሬ ዋናው ተጠቃሽ መጽሐፍ Olof pedersen, “Babylon-The great city” በሚል ርዕስ ያሳሙት መጽሐፍ ነው።
Published in
ነፃ አስተያየት