Sunday, 20 August 2023 00:00

ክብርና ውርደት አለ። ትዕቢትና አንገት መድፋትም አለ።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

ናቡከደነፆር ባቢሎንን ገነባሁ ይላል፤ ሔዋን ደግሞ ሰው ፈጠርኩ ትላለች!


ዮሃንስ ሰ

የንጉሥ ናቡከደነፆር ግዛት እጅግ ሰፊ ከመሆኑ የተነሣ፣ ዐዋጅ ሲያወጣ ለሁሉም አገር ነው። “በመላው ዓለም ለምትኖሩ ሁሉ”…. በማለት ያውጃል።
በመልካም መንፈስ የምስራች ዐዋጅ ሲያስነግር እንዲህ ይላል።
“ከንጉሥ ናቡከደነፆር፣ በምድር ሁሉ ለሚኖሩ ሕዝቦች! ሰላም ይብዛላችሁ” በማለት ዐዋጁ ይጀምራል።
በመቀጠልም ድንቅ ነገር እንደተፈጸመለት ይገልጻል።
“ይህን ስነግራችሁ እጅግ ደስ እያለኝ ነው” በማለት መልእክቱን ያስከትላል (ዳንኤል ምዕ 4)። የናቡከደነፆር መልእክት ምን እንደሆነ ወደ በኋላ እናየዋለን።
ልማቱና ጥፋቱ እየተፈራረቀ እየተደበላለቀ ለሚዛን ያስቸግራል። ገናናነቱ ግን አያከራክርም።
“የነገሥታት ሁሉ ንጉሥ… ከጫፍ እስከ አጽናፍ ዓለምን ሁሉ የሚገዛ” ተብሎ ተጠርቷል።
“የትም ቢሆኑ፣ በሁሉም ላይ ገዥ” እንደሆነ በትንቢተ ዳንኤል ተተርኮለታል (ምዕ 2፣ 38)።
ሥልጣኑ መንግሥታትን የሚጠቀልል ነው። ግዛቱ በሰው ልጅ ሁሉ ላይ ነው ተብሎለታል።
የተጋነነ ይመስላል። ነገር ግን፣ በየአቅጣጫው እየዘመተ ዋና ዋናዎቹን መንግሥታት አስገብሯልና የዓለም ንጉሥ ተብሎ ቢተረክለት አይበዛበትም። ክብሩና ግርማ ሞገሱ ግን በጦርነትና የተገኘ አይደለም። የጦር መሪነቱን የሚያደንቁት ሞልተዋል። ለሱ ግን ከሁሉም በላይ ባቢሎን ትበልጥበታለች።
ሁለት አባባሎችን እናያለን። መጀመሪያ የመታበይ አነጋገር እንመልከት።
ከንጉሡ በፊት ባቢሎን ነበረች።
ባቢሎንን ሲያስብ፣ ሕንጻዎቿን ሲመለከት፣ ለናቡከደነፆር የክብር ዘውድና የኩራት አክሊል ሆነው ይታዩታል። ዳንኤል እንዲህ ጽፎለታል።
…ንጉሡ፣ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ እየተመላለሰ ሳለ፣ “በብርቱ ኃይሌ፣ በገናናው ክብሬ፣ ንጉሣዊ መኖሪያ ትሆን ዘንድ ያሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን ይህች አይደለችምን?” አለ።
ንጉሡ ይሄን የተናገረው፣ “ባቢሎንን እንደ ቅርስ ብቻ ሳትሆን እንደ ፈር ቀዳጅ ሕልም፣ እንደ ነባር ታሪክ ብቻ ሳትሆን እንደ ፋና ወጊ ስኬት” በማሰብ ከሆነ መልካም ነው።
ባቢሎን፣ የሥልጣኔ ታሪክ ያልነበራትና ድንገት በሱ ትዕዛዝ የበቀለች ከመሰለችው ወይም “የሕልም መጨረሻ” ሆና ከታየችው ነው ችግሩ። ይሄ መታበይ ነው።
የናቡከደነፆር ጥፋት ይህ ብቻ አይደለም። በየአቅጣጫው እየዘመተ በርካታ አገራትን የወረረ ጊዜ ብዙ ጥፋት መስራቱ አያጠራጥርም። ብዙ ሰዎች ሞተዋል። እልፍ አእላፍ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
ንጉሡ፣ “የባቢሎን ሕንጻዎችን እየተመለከተ ጣፋጭ የመንፈስ እርካታ ማግኘቱና ኩራት እንደተሰማው መግለጹ” ግን ኀጢአት አይደለም። በእርግጥ እንደ ጥፋት የሚቆጥሩበት ይኖራሉ። “ታበየ” ሊሉ ይችላሉ። የቀድሞ ጠቢባንን ከዘነጋ፣ ነባር ታሪክንና ቅርስን ቸል ካለ፣ የወደፊት ጠቢባንን ከረሳ፣ “ሕልም ሁሉ በኔ ብቻ እውን ሆነ” ብሎ ማሰብ ከጀመረ ግን፣ ሳይታወቀው የስንፍና ጭጋግ ይውጠዋል። ዓይኖቹን ይጋርድበታል። መታበይ ይሆናል። በዚህ ሳቢያ ናቡከደነፆር ከባድ ችግር ደርሶበታል ይላል - የዳንኤል ትረካ።
ናቡከደነፆር ለሰባት ዓመታት፣ እጅግ ከሚያፈቅራት ከባቢሎን ከተማ ተለይቶ፣ ከቤተመንግሥቱ ርቆ፣ ወደ በረሃ እንደተሰደደ በዳንኤል ትረካ ተጽፏል። አእምሮው ተደፍኖ፣ እንደ ሰው ማሰብ አቅቶት፣ በከባድ የጤና ቀውስ ተሰቃይቷል። ከሰው በታች ሆኗል። የ”ሰው”ነት ክብሩ ተዋርዷል። አእምሮ የሌለው እንስሳ ሆኗል።
በእርግጥ፣ የንጉሡ ስህተት የክፋት አይደለም። ጥፋት ቢሰራም “አመል” አልሆነበትም። ጠማማ መንገድ ውስጥ ገብቶ አልቀረም። “ልቡ አልደነደነም”። የስህተቱ ያህል ተጎድቷል። የጥፋቱ ያህል ከባድ መከራ ገጥሞታል።
ደግነቱ ከስህተቱ ተመልሷል። በዳንኤል ምክር ተጨምሮበት ከክፉ መንገድ ወጥቷል። እንደገና ክብሩን አግኝቷል። እንዲያውም፣ “ከቀደሞው የበለጠ ታላቅ ሆንሁ” ይላል ንጉሡ። ቁልፉ ያለው፣ አእምሮ ላይ እንደሆነም ይጠቁማል። እውነት ብሏል። አእምሮ ከሌለ ምን ክብር አለ? ሕይወትም ትርጉም አይኖረውም። ነብይ ዳንኤል እንደሚተርክልን ከሆነ፣ ንጉሡ አእምሮውን ሲያጣ ከሰው በታች ይሆናል። ወደ አእምሮው ሲመለስ፣ ሁሉንም ነገር ያገኛል።
“አእምሮዬ እንደ ተመለሰልኝ፣ ወዲያውኑ፣ ግርማዊነቴና ሞገሴ፣ የመንግሥቴም ክብር ተመለሱልኝ” አለ፤ ታላቁ ንጉሠ ነገሥት ናቡከደነፆር።
የዛሬ 2600 ዓመት፤ የዓለማችን ኃያል ንጉሥ ማን ነበር ቢባል መልሱ አከራካሪ አይደለም። ሌላ ሳይሆን፣ “የባቢሎን ጌታ፣ ንጉሥ ናቡከደነፆር” ነው። የታሪክ መጻሕፍት የንጉሡን ገድል መዝግበውለታዋል። የናቡከደነፆር ስም ለዓለም የተዳረሰው ግን፣ በትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍ ነው።
ሕልሙን ለዳንኤል ይናገራል። ትርጉሙን ይጠይቀዋል። እንዲህ አለው።
እነሆም በምድር ዛፍ ነበር። ቁመቱም ረዥም ነበር። ዛፉም ትልቅ ሆነ። በረታም። ቁመቱም እስከ ሰማያት፣ ቅርንጫፎቹም እስከ ዓለም ዳርቻ ደረሱ። ቅጠሉም የተዋበ፣ ፍሬውም ብዙ ነበር። ለሁሉም የሚሆን ምግብም ነበረው።
ከጥላው ሥር የዱር እንስሳት ያርፉበት ነበር። በቅርንጫፎቹም ላይ የሰማይ ወፎች ይኖሩበታል። ሕያዋን ሁሉ ከእርሱ ይበሉ ነበር።
እነሆም፣ ቅዱስ ጠባቂ ከሰማይ ወረደ። በታላቅ ድምፅም እየጮኸ እንዲህ አለ። ዛፉን ቁረጡ። ቅርንጫፎቹንም ጨፍጭፉ። ቅጠሎቹም ይርገፉ። ፍሬዎቹንም በትኑ። አራዊትም ከጥላው፣ ወፎቹም ከቅርንጫፉ ይሽሹ።
ነገር ግን ጉቶውን በምድር ተዉት።… ዕድል ፈንታውም ከምድር ሣር ከአራዊት ጋር ይሁን።
ልቡም ከሰው ልብ የተለየ ይሁን። የአውሬም ልብ ይሰጠው። ሰባት ዘመናትም ይለፉበት… አለ ቅዱስ ጠባቂ። እኔ ንጉሡ ናቡከደነፆር ይህን ሕልም አልሜያለሁ (ዳንኤል 4፡ 10-18)።
ሕልሜን ፍቱልኝ ብሎ ቢጠይቅም፣ ሌሎቹ ጠቢባን ትርጉሙን ስላላወቁ ሊነግሩት አልቻሉም። ዳንኤል ተጠየቀ። ጥሩ ሕልም አይመስልም። ትረካው እንዲህ ይላል።
ዳንኤል አንድ ሰዓት ያህል በአርምሞ አሰበ። ልቡም ታወከ (ዳንኤል 4፡19)።
እውነትን ለመናገር ፈርቶ አይደለም። ዳንኤል ለንጉሥም ቢሆን እውነትን ለመናገር አይፈራም። ልቡ የታወከው ለናቡከደነፆር የተወሰነ ያህል ክብር ስላለው ነው። ደግሞም እውነት ነው። ናቡከደነፆር ብዙ የሥልጣኔ ታሪኮችን ሰርቷል። ንጉሱ ጥፋት ቢኖርበትም እንዲስተካከል እንጂ በክፉ እንዲወድቅ  ዳንኤል አይፈልግም። ንጉሡም ይህን አይቶ ዳንኤልን ለማበረታታት ሞከረ።
“ሕልሙና ፍቺው አያስጨንቁህ” አለው።
ይሄኔ ዳንኤል ተናገረ።
ጌታዬ ሆይ፣ ሕልሙ ለጠላቶችህ፣ ትርጉሙም ለደመኞችህ ይሁን። ትልቁና ብርቱ፣ ቁመቱም እስከ ሰማያት፣ ቅርንጫፎቹም እስከ ምድር አጽናፋት የደረሰው… ዛፍ፣ ታላቅና ብርቱ የሆንክ አንተ ነህ። ታላቅነህ በዝቷል። እስከ ሰማያት ደርሷል። ግዛትህም እስከ ምድር ዳርቻዎች ድረስ ነው።
…ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ። መኖሪያህም ከአራዊት ጋር ይሆናል። እንደከብቶችም ሳር ትበላለህ። ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል… አለው (ዳንኤል 4፡ 19-26)።
ዳንኤል ከዚህ ቀጥሎ ምክር ይሰጠዋል። ኀጢአትን በጽድቅ ማስቀረት እንደሚችል፣ በንስሓ ንግሥናው ሊመለስለት እንደሚችል ይነግረዋል።
ይህ ሁሉ በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ ይላል ትረካው። ተደናቅፎ መውደቁን፣ ስደቱንና ጉስቁልናውን ያሳየናል። አእምሮ እንደሌላቸው እንደ ዱር እንስሳት ይሆናል። አነሣሡንም ይወጋናል። አእምሮው ተመለሰለት። ንግሥናውም ጸና። ብዙ ክብርም ተጨመረለት ይላል (ዳንኤል 4፡ 29-37)።
ናቡከደነፆር ይህን አስደሳች ታሪክ ነው በዐዋጅ ለዓለም የተናገረው።
ባቢሎን ግንባታ ይሰራል። ነገር ግን የቀድሞ ጥበበኞች የሰሩትን ታሪክ ያከብራል። መነሻ እንደሆኑለት ይዘክራል። (ደብረ ባቢሎን በሚለው ጽሑፍ መመልከት ይቻላል)። ባቢሎን ከወደቀችበት አንስቻታለሁ ይላል- ለጥንታዊ ታሪክ እውቅና ይሰጣሉ።
የእኔነት ክብርና ውርደት አለ። አጉል ትዕቢትና አንገት መድፋትም አለ።
ፍሬያማነትን የወደደ፣ ጎን ለጎን ጥበብንና ትጋትን ማሟላት እንደሚኖርበት የአዳምና የሔዋን ትረካ ይነግረናል። ተጨማሪ ሽልማትም ታገኛላችሁ ይለናል።
ጥበብና ትጋት ለጊዜው ያደክማል እንጂ ለፍሬ ይበቃል።
ፍሬውም ይጣፍጣል። በዚያ ላይ…
የግል ኃላፊነትን እየተወጣን ስለሆነ፣ ይህን  ወደ ማንነት ክብር ይመነዝርልናል።
እግዚሄር “ሰውን ሰራ” ይለናል ትረካው። ሔዋንም የራሷን ድርሻ ትሰራለች። የመጀመሪያ ልጇን ቃየንን ስትወልድ…
“ከአምላክ ጋር እኔ ለራሴ ሰው አገኘሁ” ትላለች።
…she said, “I have got me a man with the LORD.”
የሔዋን አነጋገር፣ “ልጅ አገኘሁ፣ ሰው ፈጠርኩ፣ ልጅ ሰራሁ” የሚሉ ትርጉሞችን ይዟል። በዕብራይስጥ “ቃና” የሚለው ቃል ነው “አገኘሁ” ተብሎ የተተረጎመው። ከሕፃኑ ስም ጋር ይቀራረባል። “ገዛሁ፣ ሰራሁ፣ ባለቤት ሆንኩ” የሚሉ ትርጉሞችን እንደሚያካትት ሮበርት አልተር ይገልጻሉ።
እንግዲህ በጭንቅ ትወልጂያለሽ ተብላለች። የወሊድ ምጥ በሌሎች እንስሳት ላይ አይከሰትም። ለዚህም ይመስላል ማስጠንቀቂያ የተሰጣት። አውቀሽ ግቢበት እንደማለት ነው። ተአምር ለመስራት ነውና “ሸክሙና ስቃዩ ይቅርብኝ” አላለችም።
ፈተናውን በጸጋ ተቀብላ ተወጣችው። ፍሬ አገኘችበት። ይህም ብቻ አይደለም። ፈተናዎችን የምታሸንፍ ሰው መሆኗን አስመስክራለችና፣ የማንነት ክብር ተጨመረላት። ታሪክ ሰርቻለሁ የማለት ሥልጣን በእጇ ለመጨበጥ በቃች። ለዚህም ነው፣ “እኔ ለራሴ ሰው ሰራሁ” ብላ ብትናገር የማይበዛባት።
ድርብርብ ነው የጥበብና የጥረት ሽልማት።
ለውጤት ይበቃል። አብቦ ያፈራል።
እግረ መንገዱም ማንነትን ያንጻል፤ ብቃትን ይገነባል።
የክብር ሽልማትም ይሆናል። የብቃትና የትጋት ምስክርነትን ይሰጣልና።
“እኔ የራሴን ታሪክ ሰራሁ፤ የፍሬ ባለቤት ሆንኩ!” ብሎ ለመናገር የበቃ ሰው፣ በስራው ከብሯል። መልካም የእኔነት መንፈስንና ጥዑም የሕይወት ትርጉምን ያጣጥማል።
“ይሄ ነገር መታበይ አይሆንም ወይ?” የሚል ጥያቄ ሊመጣ ይችላል።
እርግጥ ነው፣ ያስተማሩንን፣ ያሳደጉንን፣ የደገፉንን ሰዎች ከዘነጋን ወደ “ትዕቢት” እናዘነብላለን።  በየዘመናቸው የዕውቀትና የሙያ ጸጋ እየገነቡ ያስተላለፉልንን ጥበበኞች መርሳት የለብንም። እውነተኛ ትጉህ ሰው፣ መነሻ ጸጋዎችን አይክድም። ከቀድሞ ጠቢባን ይማራል። እሱም የራሱን ያክልበታል።
ነባር የሥልጣኔ ጅምሮችንና የቀድሞ ጠቢባንን ከልብ ያደንቃል፤ ያመሰግናል፤ ያከብራል። የራሱንም ጥረትና ውጤት ያከብራል። የራሱን ካላከበረ፣ የቀድሞ ጥበበኞችን ማድነቅ፣ ልሕቀትና ልዕልናቸውንም ማክበር አይችልም።
ራሱን አያራክስም።
የአክብሮት ትክክለኛ መርሕ፣ በሁሉም ሰው ላይ አንድ ነው። ትክክለኛ መርሕ ቀጥተኛ መስመር እንጂ፣ ወዲህና ወዲያ የሚዛነፍ የሚያደላ አይደለም። ጥበብንና ጥረትን፣ ብቃትንና ውጤትን ያዋሓደ ነው የአክብሮት መርሑ፣ የአድናቆት መስመሩ።
 የከበሩና የወረዱ ነገሮችን በመስመር ይለያል። የከበሩ ነገሮች እኩል ስላልሆኑም፣ በሚዛን እያነጻጸረ እንደየልካቸው ያደንቃል።
ፍሬያማ የብቃት አርአያዎችን ካላከበረ፣ ትክክለኛ መርሕና ሚዛን ባይኖረው ነውና፣ የራሱንም ድርሻ በልኩ ማክበር አይችልም።
ነባር ዕውቀትንና የቀድሞ ጠቢባንን አጣጥሎ ራሱን ለማክበር ከሞከረም፣… ወይ በአላዋቂነት ነው። ወይ ራሱን እየዋሸ ነው። ወይ ሰዎችን ለማታለል የሚፈልግ አስመሳይ ነው።
የራሱን ዕውቀት ያላከበረ፣ የጠቢባንን ልሕቀት ማክበር አይችልም። ወገኛ ልሁን ካላለ በቀር። “ራስን ማዋረድ ሕዝብን ደስ ያሰኛል፤ አድናቆትንና ክብርን ያስገኛል” ብሎ በጠመዝማዛ መንገድ ተወዳጅነትን ለማግኘት ካልቋመጠ በቀር፣ ለምን ራሱን ያራክሳል?
ራሱን እያጋነነ ሌሎችን ማናናቅም የለበትም።
የእኔነት ክብር ማለት ከሌሎች ሰዎች በልጦ መገኘት ማለት አይደለም።
ሌሎችን በማዋረድ የሚገኝ አይደለም።
የእኔነት ክብር መታበይን አይፈልግም።
የሌሎችን ብቃትና ድንቅ ታሪክ በመዘንጋት ወይም በማሳነት የእኔነት ክብር አይገኝም - አጉል ትዕቢት እንጂ።
የሌሎችን ብቃት ማክበርና ከትዕቢት መንጻት የሚቻለው ግን፣ ራስን በማክበር ጭምር እንጂ አንገት በመድፋትና ራስን በማዋረድ አይደለም።
ያለጥፋቱና ያለኃጥያቱ ራሱን ለማዋረድ አንገቱን የሚደፋ ሰው፣ ሌሎች ሰዎችም አንገታቸውን እንዲሰብሩ ይጠብቃል። አንገት የሚያስደፉ አምባገነኖች እንዲመጡም ይጋብዛል።
አለኀጢአቱ አንገቱን የሚደፋ ሰውና አለብቃቱ የክብር ዘውድ የሚደፋ ሰው፣ እጅግ የተራራቁ ፍጡራን ይመስላሉ። ነገር ግን እርስበርስ ይዛመዳሉ። ያልተገባ ውርደትና ያልተገባ ክብር በምናባቸው ፈጥረው እንደየዝንባሌያቸው ይከፋፈላሉ።
አንዱ በአጉል ትህትና አለዕዳው ትከሻው ጎብጦ፣ አንገቱን ወደ መሬት አቀርቅሮ ወገቡን ሰብሮ አፈር ላይ ካልተነጠፍኩ ይላል።
ሌላኛው ደግሞ በአጉል ልዕልና በባዶ ትዕቢት ተወጥሮ፣ እግሩ ሥር የተነጠፉ ሰዎች ላይ እየተንጎራደደ ጉራውን ይተረትራል።
ሁለቱም ጠማማ መንገዶች ናቸው። እግር ሥር እየወደቁ መነጠፍና ሰዎችን እየረገጡ መፈንጨት፣ ለሰው ተፈጥሮ አይመጥኑም።
የእኔነት ክብር ለሁሉም ሰው እንደየስራው “ይገባዋል”። የእኔነት ክብር ለሊቃውንትም ለጀማሪዎችም ለሁሉም ሰው ነው፤ ግን እንደየብቃታቸውና እንደየስራቸው ነው።
ያለችውን ዓቅም ተጠቅሞ፣ የሚችለውን ያህል አስቦ፣ በብልኀትና በትጋት የሚጥር ሰው፣… በዚያችው ልክ ፍሬያማ የመሆን ዕድል አለው። በዚያችው ልክ የራሱን ሰብዕና ይገነባል። የእኔነት ክብር ያዳብራል። የሕይወትን ጣዕም በዚያው ልክ ያገኛል።
የወዳጆችን ድጋፍና የስራ ባልደረቦችን ትብብር አይረሳም፤ በአክብሮት ያመሰግናል። ከቀደምት ጠቢባን ጠቃሚ ዕውቀት መማሩንና የጸጋ ወራሽ መሆኑን አይዘነጋም፤ ልሕቀታቸውን ያደንቃል። ነገር ግን ራሱን በማራከስ ቅንጣት ክብር አይጨምርላቸውም። ራሱን በማዋረድ ከፍ አያደርጋቸውም። በጥበባቸውና በስራቸው ከብረዋል፤ በራሳቸው ጥረት ወደ ከፍታ ደርሰዋል፤ ልዕልናን ተቀዳጅተዋል። የሱ ድርሻ በዚያው ልክ ማክበር ነው።
አክብሮቱን በምናብ፣ በቃል ወይም በስግደት ሊገልጽ ይችላል።
የብቃትና የልሕቀት ሰዎች እጅግ ቢበረክቱ በሌሎቻችን ላይ የውርደት ሸክም ያበዙብናል ማለት አይደለም። እንዲያውም ማወቅና መማር ለሚፈልግ ሰው፣ መነሻ ዓቅም ይሰጡታል። ወደ ክብር የሚወስደውን መንገድ ያሳዩታል። ጸንቶ እንዲጓዝም አርአያ ይሆኑለታል።
አርአያና መነሻ ይሆኑለታል ስንል ግን፣ ሕይወቱን ይኖሩለታል ወይም ኑሮውን ይመሩለታል ማለት አይደለም። ኃላፊነቱን ይሸከሙለታል ማለትም አይደለም።
ያገኘውን መነሻ ይይዛል። ለፍሬ የሚበቃው ግን የራሱን ድርሻ በጥበብና በትጋት ከተወጣ ብቻ እንደሆነ ይገነዘባል።
የግል ኃላፊነቱን በውክልና ማስተላለፍ አይችልም።
ሔዋን የእርግዝና ሸክምና የወሊድ ምጥ በራሷ ዓቅም ካልተወጣችው በሷ ስም ፈተናውን የሚጋራት አካል ታገኛለች?
ፍሬያማ ለመሆን የፈለገ ሰው፣ የግል ኃላፊነቱን በጸጋ ተቀብሎ እስከ ጥግ ድረስ የአቅሙን ያህል ይጥራል። ይቅናው አትሉም? የስራ ፍሬውን ያያል። ኑሮውን ለማቃናት ይሞክራል። የስራ ልምድና የሙያ ብቃት ይገነባል። በዚያ ላይ፣ የሕይወትን ትርጉም፣ የሕይወትን ጣዕም ይቀምሳል።
በሌላ አገላለጽ፣ የእኔነት መንፈስና ክብር በውስጡ ነፍስ ይዘራሉ። ውስጣዊው ነፍስ በውጫዊ ቁመናው ላይ ይንጸባረቃል። ከአስተያየቱ ነቃ ከአረማመዱ ቀና ይላል። ነገር ግን፣ በይምሰል ለታይታ፣ በትዕቢት ለጉራ አይደለም። መስመሩንና ሚዛኑን አልሳተምና፣ ሁለት ነጥቦችን በትክክል አዋሕዶ መያዝ ይችላል፡፡
“መነሻ የሆኑልኝ ጸጋዎች ምስጋና ይግባቸውና” ብሎ ለቀደምት ጥበበኞችና ለበጎ ሰዎች አክብሮቱን ይገልጻል። ሁሉንም መዘርዘርና ማመስገን አይቻልም። በጥቅሉ “ይመስገነው” በማለት አሳጥሮ ሊገልጽ ይችላል። ከዚያም…
“እኔም ለራሴ ታሪክ ሰራሁ” ብሎ የራሱን ድርሻ ያከብራል።
የሔዋንን አባባል በማስታወስ ሁለቱንም ነጥቦች አጉልተን ማየት እንችላለን። ከምስጋና ጋር የእኔነት ክብሯን ትገልጽበታለች።
“ከአምላክ ጋር…
እኔ ለራሴ ሰው አገኘሁ” ብላለች ሔዋን።
ፍሬያማነትንና የሕይወትን ጣዕም የወደደ፣ ጎን ለጎን ጥበብንና ጥረትን ይዞ ይቅረብ። በትጋት ለፍሬ ይበቃል። ብቃትንና የእኔነትን ክብር ይቀዳጃል።

Read 1073 times