ለኢትዮጵያ አትሌቶች የተደረገው ሽኝት እጅግ አስደናቂ መሆኑን በኢትዮጵያ የሐንጋሪ ኤምባሲ ምክትል ሃላፊ ረካ አጎታ ሲዚ ለስፖርት አድማስ ገልፀዋል። የአትሌቲክ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት፤ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት፤ የባህልና የስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትርና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች አትሌቶችንና ቡድናቸውን በማበረታት ሰንደቅ አለማ አስረክበው በህብረት ሽኝት ማድረጋቸው ለጥሩ ውጤት በጣም የሚያስፈልግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
“በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ በመገኘቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ ምክንያቱም አትሌቶቹ በመካከለኛና በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድር የዓለማችን ምርጦች መሆናቸውን አውቃለሁ፡፡ ታላቅ ክብር ተሰምቶኛል፡ በከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ታላላቅ ሰዎች አትሌቶቹ ከበሬታ ሲያገኙ በማየቴ እጅግ ተደስቻለሁ፡፡ አትሌት ነበርኩ፡፡ ስለዚህም አትሌቲክስን አትሌቶችን እከታላለሁ፤ ልዮ አድናቆትም አለኝ፡፡”ብለዋል
ዲፕሎማቷ እንደገለፁት በሃንጋሪ ሁሉም አይነት ስፖርት ተወዳጅ ነው፡፡ በአትሌቲክ ስፖርት በዓለም አቀፍ ውድድሮች ያን ያህል ስኬት ባይኖርም በአውሮፓ ግዙፉን የአትሌቲክስ ስታድዬም በመገንባት ዓለምን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸው አገራቸው ለስፖርት የምትሰጠውን ክብር የሚያሳይና የሃንጋሪ ህዝብ የዓለም አትሌቲክ ሻምፒዮናዎችን የኦሎምፒክ ውድድሮችን በፍቅር የሚከታተል መሆኑን እንደሚያረጋግጥ አስገንዝበዋል።
“በሃንጋሪ ውጤታማ የሆነው በተለይ በውሃ ዋና ስፖርት ነው፡፡ በሄፕታትሎንም ስኬታማ ሆነናል። በእጅ ኳስም ጠንካራ ቡድኖች አሉን። ምንም እንኳን በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የጎላ ውጤት ባናስመዘግብም እግር ኳስም ለሃንጋሪያውያን እጅግ ተወዳጅ ስፖርት ነው።” በማለት ዲፕሎማቷ ለስፖርት አድማስ አጫውተዋል።
“የዓለም ሻምፒዮናውን ልዩ የሚያደርገው እጅግ ዘመናዊ ስታድዬም በመገንባታችን ነው። ከሻምፒዮናው በፊት ግዙፍ የአትሌቲክ ስታድዬም ሃንጋሪ አልነበራትም፡፡ ስታድዬሙ በመካከለኛው አውሮፓ ግዙፉ የስፖርት መሠረተልማት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ መንግስታችን የዓለም ሻምፒዮናውን በስኬት ለማስተናገድ ሲሰራ መቆየቱ በብዙ መስክ ለምንፈልገው መነቃቃት ወሳኝ ይሆናል። አትሌቲክስ ከዓለማችን ምርጥ የስፖርት ውድድሮች አንዱ እንደሆነ ይታወቃል እንደውም ሃንጋሪ ውስጥ አትሌቲክስን “የስፖርቶች ንግስት” እያሉ ያወድሱታል፡፡ ሃንጋሪያውያን ይህ ታላቅ የስፖርት መድረክ ወደ አገራቸው በመምጣቱ ከፍተኛ ኩራት ተሰምቷቸዋል። ታላቁን የስፖርት ውድድር ከማስተናገድ ባሻገር ሃንጋሪን ለማስተዋወቅ የቡዳፔስት ከተማን የቱሪስት መስህብነት ለማረጋገጥ እድል አግኝተናል፡፡ ቡዳፔስት ከሻምፒዮናው ባሻገር በስነህንዎቿ ውበት፤ እጅግ ታሪካዊና አስደናቂ በሆኑ ሙዚዬሞቿና ሺ ዘመን ባስቆጠረ የፍልውሃዎ አገልግሎቷ ለእንግዶቿ የማይረሳ አጋጣሚ እንፈጥራለን።" በማለትም ረካ አጎታ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያና ሃንጋሪ ባላቸው የዲፕሎማሲ ትስስር በተለይ በትምህርት መስክ ላይ የሚያተኩር መሆኑንም ምክትል አምባሳደሯ አመልክተዋል፡፡ ሃንጋሪ ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የነፃ ትምህርት እድሎችን በመስጠት እንደምትሰራ ጠቅሰው፤ በየዓመቱ ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያን ለነፃ የትምህርት እድል ወደ ሃንጋሪ እንደሚጎዙ፤ የነፃ ትምህርት እድሎች በሁሉም መስክ የሚሰጡ ቢሆንም በህክምና በኢንጅነሪንግና ግብርና መስኮች ሙሉ ደጋፍ በማድረግ እየሰራን ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሃንጋሪ ኤምባሲ ምክትል ሃላፊ ረካ አጎታ ሲዚ በአዲስ አድማስ በኩል ያስተላፉት የመጨረሻ መልዕክት።
“በዓለም ሻምፒዮናው ለሚሳተፋ አገራት በአጠቃላይ የምመኘው ስኬትን ነው። በቡዳፔስት ቆይታቸው ሁሉም ነገር ምቹ እንዲሆንላቸውና የሚያረካ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ተስፋ አደርጋለሁ። ከሻምፒዮናው ተያይዞ የሚጎበኙን የዓለም ህዝቦች የማይረሱት የታሪክ አጋጣሚ ለመፍጠር ነው የሰራነው። ለሻምፒዮናው ከ300 ሺ በላይ ትኬቶች ተሸጠዋል፤ ዋንኛው ምክንያት ከተማዋን በየዓመቱ ለመጎብኘት የሚመጡ የስፖርት ቱሪስቶች የዓለም ሻምፒዮናውን እንደመልካም አጋጣሚ መመልከታቸው ነው፡፡ በየዓመቱ የሚካሄደው የቡዳፔስት ማራቶን በርካታ የስፖርት አፍቃሪዎችን ትኩረት ከመላው አውሮፓ ሲማርክ ቆይቷል፡፡ ከሻምፒዮናው ጋር ተያይዞ በተለይ ከአውሮፓ በርካታ ጎብኝዎችን የምናስተናግደው ከስፖርቱ ጋር ከተማውን የሚጎበኙበት እድል በመፈጠሩ ነው፡፡ ለስፖርት ብለው የመጡ ታሪካዊቷን ከተማ ጎን ለጎን መጎበኘት ይችላሉ፡፡ በስፖርት ቱሪዝም የሃንጋሪ መንግስት ትኩረት አድርጎ እየሰራ የቆየበት ሁኔታን የሻምፒዮናው መሥተንግዶ ያረጋግጣል፡፡”
“በዓለም አትሌቲክ ሻምፒዮናው ለኢትዮጵያ 10 ሜዳልያዎችን እገምታለሁ፡፡ ይህን ምኞቴን ለአትሌቲክ ፌደሬሽኗ ፕሬዝዳንትም ገልጨዋለሁ፡፡ ሃንጋሪያውያን በአትሌቲክ ብዙ ሜዳልያ ለማግኘት ባይሆንላቸውም ኢትዮጵያን በመደገፍ የሜዳልያውን ውጤት ለማጣጣም ነው፡፡”
Saturday, 19 August 2023 20:17
ለኢትዮጵያ 10 ሜዳሊያዎች እጠብቃለሁ በኢትዮጵያ የሃንጋሪ ኤምባሲ ምክትል ሀላፊ ረካ አጎታ ሲዚ
Written by ግሩም ሰይፉ
Published in
ስፖርት አድማስ