የምድር ቃላት በአንድ ላይ ቢያብሩ በማይተረጉሙት፣ የሀሳብ ጥልቀት በማይደርስበት፣ ጥበብህ የማየውንም ሆነ የማላየውን አለማት የፈጠርክ ፈጣሪ ሆይ እባክህን ሁለንታን በሚገዛው ሚስጥራዊ መንፈስህ ውስጥ ሆነህ አንድ ጊዜ አድምጠኝ፤ ማንነትህን ልፈልግ ሀሳቤን ልዘረጋው ነው፡፡ መልስን አድና እውነትን ልትኖር በፈቀደችው ነፍሴ… እንዲህ አድርገህ የሰራኸኝን ፈጣሪ እየጠየኩህ ላገኝህ… እየገባኸኝ ልሰብክህ…እየናፈከኝ ልፀልይልህ እወዳለሁና…እባክህ ስማኝ!
ማንነትህንና ስራዎችህን ጠቅልዬ ለማወቅ በምድር ላይ ያለኝ እድሜዬ የሚበቃኝ ስላልመሰለኝ… በጭንቅላቴ ሰቅስቄ የያዝኳቸውን የፍለጋ እውቀቶች ለጊዜው አስወግጄ፣ ፊት ለፊት ካንተው አንደበት ሚስጥራቶችህን ልረዳቸውና ልተረጉማቸው እወዳለሁ፡፡
ሆኖም አላውቅህም፡፡ ስላንተም ሰዎች መጥተው ቢጠይቁኝ ከሚስጥራዊነትና ካለመታየትህ ውጭ ልነግራቸው የሚቻለኝ አንዳች እውቀት አጣሁ፡፡ ስለ ተፈጥሮና ተዓምራቶችህ ስንት አመታት ጥናት ሳደርግ፣ ባለቤታቸውን ግን አለማወቄ ሁሌም ቢሆን ነፍሴን የሚቆረቁረው ድክመቴ ነው፡፡ ለምን ግን እስካሁን ድረስ ስፈልግህ ላውቅህ አልቻልኩም? ለምን እንድፈራህና እንዳልመረምርህ ፈጣሪህን እናውቀዋለን የሚሉት ይሰብኩኛል? ለምን እነሱ ብቻ መልዕክትህን እንዲያደምጡ ተደርገው ተሰሩ? ለምን የሁሉም ሀይማኖት ሰይጣናቸው ተመሳሳይ ሆኖ ሳለ፣ ያንተ ማንነት ላይ ግን ተቃረኑ? ፈልገኸው ነው ፈጣሪዬ…?
ገና ለምድር እንግዳ የሆነ ህፃን ልጅ ሆኜ ነው ከዚህ በኋላ የምጠይቅህ፡፡ ምንም ነገር ላይ እውቀት እንደሌለውና በጥበብ ጥማት እንደተሰቃየ ልጅህ ሆኜ ነው ልቀርብህ ያሰብኩት፡፡ አባት እንዳለው ልጅ ሆኜ ሳወራ ደግሞ ነፃነቴን በዛ ውስጥ አገኘዋለሁ…ስለዚህ ነፃነቴ ሊረብሽህ እንደማይችል ይገባኛል፡፡ እንደዚሁ ይገባኛል፡፡
ለኛም እንደሰጠኸን አንተም የራስህ ቃላቶች አሉህና… በቃላቶችህ ንዝረት፣ በእውነትህ ውስጥ እምነቴን እንድሰራው…ማሰቤን ተጠቅሜ አንተን እንዴት እንደማስብህ ለመረዳት፣ ቃላቶችህ የከተሙበትን ክታብ እፈልጋለሁና ከወደዛ ምራኝ?
ምድርን ከእነ ፍጡሮቿ ከፈጠርካት በኋላ ከምናብህ ተፈልቅቀው የወጡት ልጆችህን ታናግራቸው እንደነበር በዛ ያሉ የሀይማኖት መፅሀፍት ውስጥ ለማንበብ ሞክሬያለሁ። ሆኖም ሁሉም በራሳቸው እውነት ውስጥ የፃፉበት መንገድ… የተጠቀሙት የቃላት ጉልበት፣ ለዛም እምነት የሰጡትን ህይወት ስመለከት …የሁሉም መንፈሳዊነት የተጫነውና አምላካዊነትን በመላው ባይሆንም ለሰው ልጅ እንዲገባ አድርገው ለመስበክ የተበጁ ናቸው። ግን የትኛው መፅሐፍ ውስጥ ነው የማገኝህ? ያንተ ቃላት ማንም የሰው ሀሳብ ሳይሰለጥንበት የተከተበው በየትኛው ቅዱስ መፅሐፍህ ውስጥ ነው?
ቃላቶችህን በእውቀት ምጥ ውስጥ ሆኜ ስፈልጋቸው መንገዴ ከነዚህ መፅሐፍት ጋር አገናኘኝ… The Holy Bible, The Holy Quran, The Vedas, Talmud, Kojiki, Bhagavad Gita, Tripitaka, Tanakh, The Lotus Sutra, The Book of Law, …እና ብዙ ብዙ መፅሐፍቶች። የቱ ጋ ተናገርከን ፈጣሪዬ? ሲጠይቁኝ የቱ ጋ ነክ ልበላቸው? ሁሉም መፃሕፍት የራሳቸውን እውነት ከሌሎች እውነቶች ጋር እንዳይደርስ አድርገው አርቀውታል፡፡ ሁሉም ሀይማኖቶች ማንም እንዳይሸሻቸው ይሁን ማንም እንዳይመረምራቸው ከፊታቸው ያንተን ድንቅ ስራ ሳይሆን የፍርድ አቅምህን በመተረክ እንድንፈራህና እንድንከተልህ ነው የሚያደርጉት፡፡ የሀይማኖት ደሞዝ የሰው ልጅ ፍርሀት እስኪመስለኝ ድረስ በእውቀት አልባ ሀይማኖታዊያን ምክንያት ነፍሴን ከጥበባዊ ስራህ እንድትሸሽና ቀርበኸኝ ሳለ ሲያርቁብኝ ባለችኝ እድሜዬ ታዝቤያለሁ፡፡ አንተው ንገረኝ፤ የሁለንታ ገዢና የሁሉም እውቀት ባለቤት የሆንከው… አንተ ብቻ ነህ ይሄን ልትነግረኝ የምትችለው፡፡ የትኛው ቅዱስ መፅሀፍህ ውስጥ ነው የምድር ታሪኬን በእንዴት አይነት መልኩ መፈፀም እንዳለብኝ የሚነግረኝ…የትኛው?
እንዳትጠይቀው ይሉኛል፡፡ አይነግርህም ይሉኛል፡፡ የመረጣቸውን ብቻ ነው የሚያዋራው ይሉኛል፡፡ ዘላለም በሚያፈቅርበት መንፈሱ ዘላለም ሲቆጣህም ይኖራል ይሉኛል፡፡ ይቀናል ይሉኛል፡፡ ይገድላልም ያድንማል ይሉኛል፡፡ ብዙ ብዙ ህጎች አሉት ይሉኛል፡፡ በሰው ልጅ አይን አይታይም ይላሉ፡፡
ለምንድን ነው እንደዚህ የሚሉት የኔ ፈጣሪ? አለማትን ከእነ ውስብስቡ የሰራህ…መቀመጫህ ሁሉም ስፍራ የሆንከው ብቸኛው ፈጣሪ መልስልኝ? እንዲህ እንዲናገሩኝ የሚያደርጋቸው ከነገርካቸው እውቀት ተነስተው ነው ወይንስ የእውቀት እጥረት ውስጥ ባለ ፍርሀታቸው ምዕመናቸውን እንዳያጡ በመስጋት ነው? የምደራደረው በነፍሴ ነውና እንደቀልድ የማልፈው…እንደዘበት የማምንበት ምክንያት አልታየኝምና አንተው ንገረኝ?
ሌላው ጥያቄዬ ውስጥ ስምህን የማወቅ መሻት አለበት፡፡ ስምህ ማነው? አምላክህ ማነው ቢሉኝ ማን ልበላቸው? እርግጥ ነው የዚህን ሁሉ ግዛት ባለቤት እውነተኛ ስም ማወቅ ይገባኛልና እጠይቃለሁ፡፡ በተለያዩ ሀይማኖቶች ውስጥ የተሰጠህን ስም ለማወቅ ፈልጌ እነዚህን በጥቂቱ አገኘሁ… God, Allah, Fuxing, Anubis, Amaterasu, Pantheon, Ravana, Tiber, Bologna, Oya, Zeus, Sol, Veles, Dajjal, Cocidius, Shiva, Sun God, Wodan, Hubert & Jan, Garuda, Shakyamuni Bhuddha, Pashupati, Svaroh, Odin, Tan God, Tridev, Amun Ra, Hadit, Nuit, Hayyi Rabbi, Akal Purakh, Nana Buluku, Unkulunkulu, Dagda, Shangdi, Maria Lionza, Ukko, Baiame, Olorun, Perun, Jesus, Viracocha, Sang-je, Tupa, Trimurti, Sango, Bathala, Yahweh….
ስምህ በያንዳንዱ ሀይማኖት ውስጥ የራሱ ሀይል አለው፡፡ የሰው ልጅ በእያንዳንዱ ስምህ ተፈውሷል፡፡ የስምህ ረቂቅነት ከሀሳብ ውጭ ተግባር ላይም እንዲውል አይቼ አምኛለሁ። ሆኖም ሁሉንም አይደለህም፡፡ ይህም ለኔ የሚገባኝ ነው፡፡ ነገር ግን አንተ ይህ በመሆኑ ምን ይሰማሀል? ያናድድሀል? ወይስ በስምህ ብዛት ልክ አቅምህንም እንደዛው አስፍተህ ስምህን ፈልገው ላገኙት ከነክብርህ ትገለጥላቸዋለህ?
የስምህ መብዛት ውስጥ የምረዳው ነገር፣ የሀይማኖት መብዛትንም ጭምር ነው፡፡ ብዛት ያላቸው ሰባኪያን በሁሉም ሀይማኖት ውስጥ እንደ ሀይማኖቱ ፈጣሪ ተደርገው ይነገርላቸዋል። ያንተንም መልዕክት ለመስበክ ይዘውት የመጡትን ሀሳብ በጥልቀት መመርመር እንዳለብኝ ነፍሴ ትነግረኛለች፡፡ ሁሉም ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው ነገር ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ ሰይጣናቸው ብቻ ነው፡፡ ባለችኝ ጥቂት እድሜ እና እውቀት ቀረብ ብዬ ልማራቸው የሞከርኩት የሀይማኖት ፈጣሪያን እነዚህኞቹ ነበሩ… Jesus Christ, Siddharth Gautama, Prophete Mohamed, Zoroaster, Numa Pompilius, Ajita Kesakambali, Mahavira, Confucius, Pythagoras, Mozi, Zeno of Citium, Plotinus, Eutyches, Bodhidharma, Songtsen Gampo, Ramananda, Martin Luther, Guru Amar Das, John Calvin, Jakob Ammann, John Wesley, Charles Wesley, George Whitefield, Swaminarayan, Bahá’u’lláh, Gerald Gardner, Aleister Crowley…
ገና ብዙ እንደሚቀረኝም አውቃለሁ፡፡ የምድር እና ከምድር ውጭ ባሉ አለማት ላይ ቃልህ ብቻውን የሚገዛና የሚያዝልህ አምላኬ ሆይ ከላይ ከዘረዘርኳቸው የሰው ልጆች መካከል ለየትኛው ይሆን እውነትህን የነገርከው? በያንዳንዱ የሀይማኖት ፈጣሪስ ጀርባ ያለው ምስኪን ምዕመንን እንዴት አድርገህ ነው የነፍስ መቃተታቸውን የምታደምጥላቸው? አንተን ፍለጋ ከሰባኪዎቻቸው አንደበት ስር ቃልህን ሲለቅሙ የሚውሉትና እድሜያቸውን ሙሉ ከእውነት በራቀ እውቀት ሲሞሉ የሚከርሙትን ምስኪን ልጆችህን ምን ሆነው ነው እንደዚህ የሚሆኑት ብለህ እንደ እኔ ትገረማለህ? በእውቀታቸው ማጠር ትኮንናቸዋለህ? ወይንስ በእምነታቸው ስፋት ልክ የጠበበው እውቀታቸውን ይቅር ትልላቸዋለህ?
ጌታዬ ሆይ…እነዚሁ ምዕመን ጋር ተጠግቼ ጥያቄን ሳቀርብ ይቆጡኛል፡፡ መልስን ብቻ…በእውቀትህ ውስጥ ያለው ፍቅርህን ብቻ ፍለጋ ስለ ምንነትህ ስጠይቃቸው መልስ የላቸውም…ሆኖም ከእውቀት ማነስ በሆነ ቁጣ ውስጥ ተዘፍቀው ስምህን ጠርተው ጥያቄዬን ከማስተናገድ ይልቅ የክብርህን አቅም እንዳላውቀው እሱን አታውቀውም… ልታውቀውም አትችልም ይሉኛል፡፡ የት ድረስ ነው ልጆችህ ሲያንቀላፉ እያየህ ዝም የምትለው? አንተ የሰራኸውን ተዓምር በሰው ልጅ አፍ ውስጥ ሆኖ ሲነገር ከመለኮታዊ መገለጥ ይልቅ ጥያቄዎች እየተመረቱ መሄዳቸው አይቀርም፡፡ አንተን ለመተርጎም… ያንተን ሀይል ትርጉም ባለው መልኩ ለማሳየት ቃላት ምንስ አቅም ኖሯቸው ነው... አምላኬ ተናገረኝ እያሉ ያልሰሙትን የሚተነብዩት፡፡ እንዴት እነሱን ታግሰህ ለምዕመኑ ፈተና እንዲሆኑባቸው ተውካቸው? ቁጣህስ የት ድረስ ነው?
አንድ ሀይማኖት መያዝ ካለብኝ ንገረኝ። ከነዚህኞቹ የቱን ልምረጥ?…Hinduism, Atheism, Buddhism, Voodoo, Spiritsm, Judaism, Taoism, Jehovah’s Witnesses, Baha’I, Confucianism, Scientology, Humanism, Jainism, Shinto, Caodaism, Chinese Shamanism, Cheondoism, Khawarij, Zoroastrianism, Tenrikyo, Animism, Wicca, Yezidism, Neo-Paganism, Druze, Brahma Kumaris, Unitarian Universalism, Dao Mau, Rastafari, Korean Shamanism, Jediism, Amish, Juche, Oomoto, Deism, Apsara Ajivika, Chen tao, Mandaeism, Tengrism, Gnosticism, Satanism, Heathenism, Discordianism, Pantheism, Sabians, Pastafarianism, Adidam, Charvaka, Methodism….ወይስ እስካሁን እውነተኛውን ሀይማኖት ገና አልነገርከንም?
ሲጀመር እንዴት በዙ? ለመብዛትስ ያገኙት ምክንያት ምንድነው? የመጀመሪያው የተባለው ሀይማኖት ለምን ሁሉንም ሀይማኖቶች ተክቶ እውነትን አልሰበከም? ወይስ ዘመን በተቀየረ ቁጥር ያንተም ሀሳብ፣ ህግና የመገለጥ አቅም ይቀየራል?
አንድ እና ብቸኛው ፈጣሪ ከሆንክ ስለምን በሁሉም ሀይማኖቶች ውስጥ ስምህና ክብርህ ተለያይቶ ይገለፃል? ወይስ አንተም ብዙ ነህ? ብዙ ሆናችሁ ነው እንዴ የፈጠራችሁን? ይህን መልስ ነፍሴ ትናፍቀዋለች፡፡ አስሳ ባገኘችው ፈጣሪዋ ትረካ ልክ ነፍሴ እውነትን ፍለጋ፣ በያንዳንዱ በሰጠኸኝ የጊዜ ስንጣቂ ውስጥ ያንተን ክብር መገለጥ ትሻለች፡፡
ለምን አንዳንድ ሀይማኖቶች የሰው ልጅ ሲፈጠር ገና ሀጥያተኛና ገሀነም የሚገባው ሆኖ ነው የሚፈጠረው እያሉ ይሰብኩኛል? ምንም ነገርን ጠንቅቆ የማያውቀው ህሊናዬ፣ እንዴት አድርጎ ነው ፈጣሪውን ሊያስቆጣ የሚችልበትን መንገድ ሊፈበርክ የሚችለው? ለምን ማንነቴን ንቄ አንተን ልፈልግ…ስለምን ፍላጎት አልባ ሆኜ አንተን ልፈልግ…?
መቼና እንዴት እንደሰራሁት በማላውቀው ሀጥያት እንዴት አድርጌ ነው፣ ራሴን ልቀጣውና ከፍላጎቱ ላግደው የሚገባኝ? እንድጠይቅ ሆኜ ከተፈጠርኩ እጠይቃለሁ፡፡ ሰይጣንስ ቢሆን ከየት ባመጣው የመጠየቅና የማሳት ብቃቱ ነው የገዛ ውድቀቱ ውስጥ የሰመጠው። የምሬን እኮ ነው አምላኬ ሆይ…ሰይጣንን ማን ሊያሳስተው ይችላል። በራሱ ፈቃድ ተሳሳተ ብል ከመጀመሪያውም የመሳሳትን ጥበብ እስካላገኘው ድረስ በእንዴት አይነት መልኩ ነው ራሱን ሊያስት የሚችለው? እንዲሳሳት አድርገህ ፈጥረኸው ነው?
ሀይማኖት ውስጥ ፍርሀትና ተስፋ አጥራቸውን አጥረው የተቀመጡ ነው የሚመስለኝ፡፡ አንዱ ሀይማኖት ውስጥ ብቻ ለቁጥር የሚቸግር አወዛጋቢ ሀሳቦች በመታጨቃቸው …ተመሳሳይ ሀይማኖት ያላቸው ሰባኪያን እንኳን እርስ በእርስ ሲጋጩ እመለከታለሁ፡፡ ይህንንም በነፍሴ አይን ስመለከት ጥልቅ ሀዘን ውስጥ እሰምጣለሁ፡፡ የፈጣሪን ዘላለማዊ እውቀትና ጥበብን በአንድ መፅሀፍ ውስጥ ቀንብቦ ለማስረዳት መሞከር ፈጣሪን በግማሹም ብቻ ሳይሆን በሙሉው ማንነቱን ከሰው ጭንቅላት ውስጥ ለመሰወር ወይንም አሳሳች ማንነቶችን ለመስበክ የሚደረግ ጥረት መኆኑን ማሰብ ከጀመርኩ ቆየሁ፡፡ የሰማያት አዛዥ የሆንከው…የምሬን ነው ግራ ግብት ብሎኛል፡፡ ምን እየተከናወነ ንዳለም ለመረዳት ውስብስብ የሆነ የሀሳብ መሰበጣጠር ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ ይህም እምነቴን ንዶብኝ አዲስ እውቀትን እንድመኝ ይገፋፋኛል፡፡
ባንተ ቃላት መሰበክ ናፍቆኛል፡፡ ያንተን እውነቶች ማድመጥ እፈልጋለሁ፡፡ ፀሎታቸው የተሰማላቸውን እያደመጥኩ አንድ ቀን ከኔ ጋር ይደርስ ይሆን እያሉ መጠበቁ ሰልችቶኛል፡፡ ባንተ ለመኘት ራሴን ማግኘት እንዳለብኝ እንጂ የሚገባኝ…በማንም የግል መረዳት ውስጥ ባለ ሰበካ ክብርህን ላስሳት አልወድም፡፡
ያንተን ቃላት የሚሰብኩትማ…ያንተን ክብር ለመግለፅ የሀይማኖት መቅደሳቸውን ገንብተው የጨረሱትማ…እነሱ…የሀገሬና የወንዜ የምላቸው ሰባኪዎች…የእውነትም እኔ ካየኋቸው በላይ እንዳየሀቸው አልጠራጠርም። ስምህን ቀምተው በራሳቸው እውቀት ሸፍነውት ለምዕመኖቻቸው አምላክ መስሎ ለመታየት ቀን ከሌሊት ይለፋሉ… ተዓምራቶችን እየሰሩ ያንተን ሳይሆን የራሳቸውን መቅደስ ይገነባሉ…በመጀመሪያ ላይ ይጠሩትና ይፈሩት የነበረውን የተከበረ ስምህን አሁን ላይ በስጋ የደከመው የሀጥያት ገድላቸውን የሚፈፅሙበት መሳሪያቸው አድርገውታል፡፡ ሌሎቹ ዋሻ ፈልፈለው በአርምሞ ያስሱሀል…ሌሎቹ በገዛ ፍልስፍናቸው ውስጥ ሆነው ላንተ ክብር ሲሉ ራሳቸውን ይገድላሉ ያስገድላሉ። ሌሎቹ ያገኙትን ሚስጥር ላለመናገር እውቀታቸውን ከራሳቸው ጋር ብቻ አድርገው አለምን ይሰናበታሉ…ስጠይቃቸውም የማይነግሩኝ ለኔ ብለው እንደሆነ ያስረዱኛል… ለይተህ እንደእውቀታችን መርጠህ የምትገልፀው የተለየ መለኮታዊ እውቀት ካለ ንገረኝ፤ የኔና የአለማት ጌታ የሆንከው አንተ? ማናቸው ውስጥ ልፈልግህ፡፡ ሰዎቹ በዙብኝ፡፡ የሚያምኑት ነገር በዛ፡፡ የትኛቸው ጋር ነህ? ከሀይማኖት በፊትና ከስነ ፍጥረታት በላይ አድርገህ የሰራኸኝ የምድር አለቃ….የቱ ውስጥ ልፈልግህ?
ራሴው ውስጥ እንዳልፈልግህ እኔ ራሱ ማነኝ? የምሬን ነው የሁሉ ባለቤትና የሚስጥራት ሁሉ ገላጭ የሆንከው ፈጣሪዬ…እኔ ማነኝ? እኔ ማን ነኝ ብዬ መልስ ፍለጋ ጉዞዬን ብጀምር፣ ከየት ነው ልጀምር የሚገባኝ?
ራሴን ስመለከተው በጣም እጅግ ውስብስብ በሆኑ የደም ማጓጓዣ ገመዶች፣ አጥንቶችና ስጋ የተሰራሁ ነኝ፡፡ አሁን ራሴን ሳየው የሚታየኝ ይሄ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ነኝ? ከዚህ በላይ ማለት ራሱ ምን ማለት ነው? አሁን ካለሁበት ማንነት የሚያድግና የሚለወጥ ነገር ካለ፣ እንዴት ሆኖ ነው ሽግግሩ ሊከሰት የሚችለው? ምን ያህል ነው በራሴ ላይ ማዘዝ የምችለው? እኔን ሰው ተብዬ እንድጠራ የሚያደርገኝ የሰውነቴ ክፍል ላይ ዝም ብዬ ሳፈጥ ብውልበት የምረዳው አንድ ነገር ብቻ ነው…እሱም የማየውን ማንነት እኔ አልፈጠርኩትም የሚል። ታዲያ ያልፈጠርኩትና አንድም የባለቤትነት ስልጣን በሌለኝ ሰውነቴ ላይ ግዘፍ አድሬ በእንዴት አይነት መልኩ ነው፣ ራሴን “እኔ ነኝ” የምለው? ራሴን “የኔ” ለማለት የራሴ ሀሳብና የእጅ ስራ አብሮት መካተት አለበት… ሆኖም የኔ የምለው ነገር የለኝም…ታዲያ እያሰብኩት ያለሁት ሀሳብ፣ የኔ ስለመሆኑ እንዴት እርግጠኛ ልሆን እችላለሁ?
እነዚህን ሚስጥራት አንተው ንገረኝ… የሁሉም ፈጣሪ የሆንከው አንተ? የምር እኔ ነኝ እያሰብኩ ያለሁት…አሁን??
አንተ የራስህ አይደለህም ይሉኛል፡፡ ይህች ምድርና የሰው ልጅ አዕምሮ የፈጣሪና የሰይጣን መመላለሻና ግዛት ማስፋፊያ ስፍራዎች ናቸው ይሉኛል፡፡ ፈጣሪውን እስካሁን እየታገለውና ሽንፈትን እስካሁን ያልቀመሰው ሰይጣን የተባለው ፍጥረት፤ የአመፃና የእውነት አባት ነው ይሉኛል፡፡ ጭንቅላቴም ከነዚህ ሁለት መንፈሶች ውጭ የሆነ የራሱ ሀሳብ የለውም ይሉኛል፡፡ ትንሽ ደግሞ ቆይተው ራስህን ፈልገህ አግኘው…ያኔ የፈጣሪህን መልክ ታየዋለህም ይላሉ፡፡
በውስጤ የተለያየ አቋምና እምነት ይዘው የሚከራከሩትን ብዙ አይነት የድምፅና የማንነት አይነቶች አሉኝ… አንዱ አንዱን እየገሰፀውና እየመከረው፣ ከከፋም እያሳተው ነው የሚጓዙት። ነገር ግን አንዱን ከአንዱ ነጥዬ ለማየት ብሞክር አሁንም እነዚሁ ብትንታኝ ማንነቶች መንበራቸው ላይ ሆነው እየተፈራረቁ እኔን ካልሰማህ እኔን ካለመንክ ይሉኛል፡፡ እኔ ውስጥ ያሉት እኔነቶች እነማን ናቸው? እኔ ካልሆንኩስ እኔ ውስጥ ማን የራሳቸው ሀሳብ ያላቸው ፍጥረታት እስኪመስሉ ድረስ ቦታና ጊዜ ሰጥቶ ገነባቸው? እኔ ማነኝ የኔ አምላክ…? ምንስ አሰኝቶህ ጊዜ ሰጥተህና አስበህ ፈጠርከኝ?
አይኖቼ በሚያዩት ነገር እያዘኑ ነው፣ ጆሮዎቼ ምንም ላለመስማት ሙከራ ላይ ናቸው፤ የምበላው ነገር ተፈጥሮን እየራቃት እየሄደ ነው፣ ሙሉ ተፈጥሮና ሙሉ መለኮት ምድራችንን ከጎበኘ የቆየ እየመሰለኝ ነው፣ ረግጫት እየኖርኳትና ከማህፀኗ የሚወጣውን ሰብል እየበላሁ ያደኩባት ሀገሬ አሁን የት ናት ያለችው? የኢትዮጵያ ሀገሬ እረፍት እየናፈቀኝ ስለምን ከምድር እሸኛለሁ?
የብዙ ሺህ አመታት ሀብትና እውቀት ያላት ሀገር ላይ እንዳለሁ ተነግሮኛል፡፡ ምድር ላይ ያለው እውቀት ከዚህችው ሀገሬ የወጣ የጥበብ ንፋስ እንደሆነ ተተርኮልኛል፡፡ ከየትኛውም አለማት መካከል ተለይታ ፈጣሪ የመረጣት ሀገር እንደሆነች ነበር የሀይማኖት ሰባኪዎቼ ሲሰብኩኝ የከረሙት። መሬት ረግጦ የማገኘው እውነት ግን ከሰማሁት ከግማሽ በላይ ይፃረራል፡፡
የቱ ጋር ነው እኛ ኢትዮጵያዊያን በፍቅር ተዋደን፣ ያለምንም ጦርነት የኖርንበት ዘመን? የሰው ልጅ እንዴት መሰሉንና ያንተን እጅ ስራ እየገደለ፣ ከፈጣሪ የተሰጠኝ ጥበብና ጥበቃ ነው እዚህ ያደረሰኝ ይላል? እንዴት እያሰቡ ነው በጦርነት ያሸነፉ ሀገራት፣ ያንተን እርዳታ እየመሰከሩ የሚያመሰግኑህ? በእንዴት አይነት ጥበብና የአስተሳሰብ ስልት ውስጥ ሆነህ ነው፣ አንዱ ልጅህን ሌላኛው እንዲገለው ልትረዳው የምትችለው? ወይስ እኔ ነኝ ማንነትህን ስቼ እየተረዳሁህ ያለሁት? አሁንም የሀገሬ ልጆች እየተዋጉ፣ እየተገዳደሉ፣ ዘር የሚባል ቅዠት ፈጥረው እየተራረዱ ነው፡፡ ከትዕግስትህ ዘመም ብለህ አንድ ጊዜ አይኖችህን ወደኛ ላክ? የሰው ልጅን ሰው እንዲያስተዳድረውና በምድር ህግጋት አስሮ እንዲያኖረው ከመጀመሪያውም አልፈቀድክ ይሆን? በኛ እጣ ፈንታ ላይ ያንተ ፍቃድ ምን ያህል አቅም አለው? ወይስ አንዳችንም የምናስብ ፍጥረቶች አይደለንም?
ለምን የተቀደሰች ምድር የተባለችው ሀገሬ ጤነኛ የሚባል፣ ክፋትን የራቀ፣ በሀሜት ያልጨቀየ፣ በመግደል የማይደሰት፣ በሴት ህፃናት ነፍስና አካል ላይ የማይሰለጥን፣ በድግምት እውቀት ያልሰከረ፣ በሰው ስቃይ ደስታውን የማያመርት፣ የሌላው ጓዱ ፈገግታ ውስጥ ደስታውን የሚያገኝ፣ በዳንኪራና በወሲብ ስልት ማንነቱን ከሰውነት ፀጋ ያላወረደና ድሀን የማይጠላ -- ትውልድ መፍጠር ስትችል፤ ነገን ማየት እዳ የሆነበት፣ በሱስ አካሉንና በህይወቱ ላይ የመፍቀድ አቅሙን አዳክሞ ለራሱም ለቤተሰቡም ሸክም የሆነ፣ ከማስተዋልና ከእውቀት ይልቅ ደረቅ እምነትን ለመሃይምነቱ መሸፈኛ ጭንብል የሚያደርግ፣ ገንዘብ ፍለጋ ሰይጣናትን ከማባረር ይልቅ ትውልድ የሚሰራው መገለጥህን መስበክ ያቃተውና በራሱ Ego ውስጥ ከትሞ ምዕመንን የሚያወናብድና ምህይምና ውስጥ ያለ ርህራሄ የሚከት…ጨካኝ ግን አዋቂ ሰባኪ …የበዛባት፡፡ ለምን የሚፀልየውና ከልቡ የሚፈልግህ፣ ህግህን ከሚያፈርሰው አንሶ ተገኘ?
ነፍሴ ሁሌ ትጠይቅሀለች፡፡ በጠነከረ እምነት ውስጥ ሆና በተፈጥሮ ሚስጥራት ውስጥ ታስሳሀለች። እረፍት ይሆናት ዘንድ ያንተን መልስ ፍለጋ የምድርን እውቀት ትበረብራለች። መኖርህን በማይክደው ጭንቅላቴ እውቀትህንና ምንነትህን መተርጎም እፈልጋለሁ፡፡ ይህንም ለማድረግ ጥበብህን ስጠኝ፤አውቄህ እንድወድህ…ተረድቼህ እንድፈራህ…ገብቶኝ እንድሰብክህ…ራሴን አውቄ አለምን ከራቃት እውቀቷ እንድመልሳት ማን መሆንህን ማወቅ አለብኝና፣ በተፈጥሮ ውስጥ የሚመላለሰው ሚስጥራዊ ድምፅህን ለጆሮዬና ለህሊናዬ አቅርብልኝ። ሰናፍጭ በምታክለው እውቀቴ ላይ ተንጠልጥዬ የምናፍቅህና የምፈልግህ ፈጣሪዬ ሆይ…አንተም ከማንም በላይ በሆነው ጥበብህ ነፍሴን ጎብኛት፤ የክብርህን ስፋት ተረድቶ መግለፅ ለሚጓጓው አንደበቴ መንፈስህ አይዘገይ?
ለኔ…የጥበብ መጀመሪያ ፈጣሪን ማወቅ ነውና….
Saturday, 19 August 2023 20:20
የጥበብ መጀመሪያው ፈጣሪን ማወቅ ነው!
Written by ኪሩቤል ሳሙኤል
Published in
ህብረተሰብ