ቅዳሜ ነሐሴ 6 ቀን 2015 ዓ.ም በሀገር ፍቅር ቴአትር ትንሹ አዳራሽ፣ የደራሲና ሐያሲ አስፋው ዳምጤ ‹‹የአማርኛ ጥበበ ቃላት ቅኝት›› መጽሐፍ በተመረቀበት ዕለት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ደረጀ ገብሬ፤ በመጽሐፉ ላይ ባቀረቡት የዳሰሳ ጽሑፍ፤ ‹‹ጥበበ ቃላት በመጽሐፍ መልክ ተጠርዞ የምናገኘው መች ይሆን? የሚለው የብዙዎቻችን ጥበቃና ጉጉት ነበር›› በሚል የመነሻ ንግግር፣ የመጽሐፉን ይዘትና ቅርጽ ለዕለቱ ታዳሚያን አቅርበዋል፡፡
የመጽሐፉን መታተም ከጠበቁት አንዱ ነኝ ያሉት ደራሲ ሳህለሥላሴ ብርሃነማርያም በበኩላቸው፤ ‹‹ሁላችንንም እንኳን ደስ ያለን !›› የሚል አጭር መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ደራሲ አበረ አዳሙ፤ ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ ‹በአባቶች ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ› እንዲል፤ ሁሴን ከድርና መሰል ወጣቶች ጋሽ አስፋው ዳምጤን አግዛችሁ፣ በዚህ መጽሐፍ ምረቃ እንድንሰባሰብ ስላደረጋችሁ ምስጋና ይገባችኋል›› በማለት አድናቆትና ምስጋና አቅርበው፤ ጋሽ አስፋው ለስነ ጽሑፍ ዘርፍ አርማ፤ በተፈጥሯቸውም ትሑት፣ ግልጽ፣ ፊት ለፊትና ጠንካራ ሰው መሆናቸውን ገለጹ፡፡
ለጋሽ አስፋው ዳምጤ፤ ‹‹የኤሊ ዕድሜ እመኝሎታለሁ››፣ ‹‹የአህያ ፈስ ያርግዎት››፣ ‹‹የማቱሳላን ዕድሜ ይስጥዎ›› የሚሉ መልካም ምኞቶች በተዥጎደጎዱበት መድረክ፤ ስለ ጋሽ አስፋው ንግግር ያደረጉ የሙያ አጋሮቻቸው ምስክርነታቸውን በሚከተለው መልኩ ነበር ያቀረቡት፡፡
"አስፋው ስፖንጅም አለትም ናቸው”
እሸቱ ጥሩነህ (ሰዓሊ)
አርቲስት ተስፋዬ ገሠሠ፣ የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ስራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት፣ ተስፋዬን ፈልገው ወደ ሀገር ፍቅር ሲመጡ ነበር ጋሽ አስፋውን ለመጀመሪያ ጊዜ የማየት ዕድል ያገኘሁት፡፡ በኋላ የሰዓሊያን ማኅበር አባል ሆኜ በሙያ ማህበራት የጋራ ስብሰባ መካፈል ስጀምር፣ በአንድ መድረክ የምንገናኝበት ዕድል ተፈጠረ፡፡ ሰንበትበት ብሎ ሰዓሊ ስዩም ወልዴ ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ባዘጋጀው የራት ግብዣ፣ ከጋሽ አስፋው ጋር በአንድ የራት መድረክ የመታደም ዕድል አገኘሁ፡፡ በባህል ሚኒስቴር ተመድቤ ስሰራ፣ ጋሽ አስፋው ለንባብ ወመዘክር ይመጡ ስለነበር ትውውቃችን እየጠነከረ ሄደ፡፡
ጋሽ አስፋው በየመድረኩ ሳገኛቸው ቁጥብ ቢሆኑም፤ ስፖንጅና አለት መሆናቸውንም አስተዋልኩ፡፡ ለቀረባቸው እንደ ስፖንጅ ወደ ውስጣቸው የመሳብ ልዩ ተፈጥሮ አላቸው። ራሳቸውን በፈጠሩበት መንገድ ሌላውን ይቀርጻሉ፡፡ አስፋው ለወጣቶች ሱቅ በደረቴ ናቸው፤ ዕውቀት ያቀብላሉ፡፡ በአስፋው የታገዙ ወጣቶች አሁን ውለታቸውን መመለስ ስለቻሉ ነው፣ በዛሬው የምረቃ መድረክ ልንገናኝ የቻልነው፡፡
ጋሽ አስፋው ከአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን እስከ ዛሬ ብዙ ችግሮች ገጥመዋቸዋል። ሁሉንም ተቋቁመው ለዛሬ ደርሰዋል፡፡ አስፋው፤ የአፈወርቅ ተክሌ፣ የመንግስቱ ለማ፣ የሳህለሥላሴ ብርሃነማርያም … ጓደኛ ናቸው፡፡ ዛሬም በዚህ ዕድሜያቸው እየሰሩ በመሆናቸው ነው፣ የመጽሐፍ ምረቃቸውን ለማድመቅ የተገኘነው፡፡
”በርና መስኮት ሆነውናል“
እንዳለጌታ ከበደ (ደራሲ)
ስንመኘው የነበረ መጽሐፍ ነው ያገኘነው፡፡ ጋሽ አስፋው በማተሚያ ቤት ግቢ ተወልደው በአብዛኛው ከመጽሐፍና ሕትመት ጋር በተያያዘ ስራ ውስጥ መኖራቸው ያስገርመኛል፡፡ ጸጋዬ ገብረመድህን፣ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፣ እስክንድር በጎሲያን … ሁሉም ስለ ማንነታቸው ሲጠየቁ፤ ‹‹ስለ እኔ የሚያውቀው አስፋው ነው›› ማለታቸውም ያስደንቃል፡፡ በተለያየ ምክንያት በቤታቸው ተወስነው ያሉ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ‹‹ከማን ጋር ትገናኛላችሁ›› ሲባሉ፣ የአብዛኛው ምላሽ፣ ‹‹ከአስፋው ዳምጤ ጋር›› ማለታቸውም ሌላው አስደማሚ ጉዳይ ነው፡፡
እስከዛሬ እያነበቡ፣ እየጻፉም ነው፤ ያውም ያለመነጽር፡፡ ስዕል ይሞክራሉ፤ ወዳጃቸው ገብረክርስቶስ ደስታ የሰጣቸውን አንድ ስዕል አስመስለው ስለው በቤታቸው አይቻለሁ። በ“አንድ ለአምስት” ረጅም ልቦለድ መጽሐፋቸው፣ ወንድራይድን የመሰለ የማይረሳ ገጸ ባሕሪ ሰጥተውናል፡፡ ያልታተሙ በርካታ ስራዎች አሏቸው፡፡
በስነ ጽሑፍ ላይ በሰሯቸው የሒስ ጽሑፎች፣ ዘርፉ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ የሚያሳይ ትልቅ ሐውልት ነው ያኖሩት፡፡ የመጽሐፉ ርዕስ፣ ”ከጦቢያ እስከ አጥቢያ“ ቢባል ጥሩ ነው የሚል ሀሳብ አቅርቤ ነበር፡፡
በወረቀት ዋጋ ውድነት ምክንያት በቁም ጽሕፈት መጽሐፍ አዘጋጅቶ በማሳተም ጀማሪው ዳኛቸው ወርቁ ይመስለን ለነበርነው፤ ከዚያ በፊት መንግስቱ ለማም ተመሳሳይ ጥረት ማድረጋቸውን ያሳዩን፤ በአማርኛ ቋንቋ አጭር ልቦለድ በመጻፍ ጀማሪው ታደሰ ሊበን ሳይሆን ቀዳሚው ተመስገን ገብሬ ስለመሆኑ ለተመራማሪዎች ጥቆማ የሰጡት ጋሽ አስፋው ናቸው፡፡
ወጣቶች በየመድረኩ ሲጋብዟቸው ይገኛሉ፤ ያዘጋጁትን መጽሐፍ ከሕትመት በፊት እንዲያዩላቸው ሲጠይቋቸውም እምቢ አይሉም። ለብዙዎቻችንም በር ሆነው ወደ ጥበቡ ዓለም አስገብተውናል፣ መስኮት ሆነው ብዙ ነገር አሳይተውናል፡፡ ለተቸገርንበት ጉዳይ (በርና መስኮት መሆን ባይችሉ) ቢያንስ አንድ ቀዳዳ በማበጀት ከፍለጋችን ጋር እንድንገናኝ በብዙ ረድተውናል፡፡
“ፈረስ ገዝተን ሸልመናቸዋል”
የዝና ወርቁ (ደራሲ)
ስለ ዕውቀት፣ ችሎታና መልካም ሰብዕናቸው ከተነገረውም በተጨማሪ የአዕምሮና የአካል ጥንካሬያቸው ልዩ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር በሚያዘጋጃቸው የጥበብ ጉዞዎች ከሚሳተፉት መሐል ጋሽ አስፋው ዳምጤ አንዱ ናቸው፡፡ የዛሬ አስር ዓመት ወደ ትግራይ ጉዞ ባደረግንበት ወቅት፣ የአክሱም ሐውልቶች የተፈለፈሉበት አለቶች ወደሚገኙበትና ከአክሱም 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ተራራማ ስፍራ ስንሄድ ቀድመውን በቦታው የተገኙት ጋሽ አስፋው ነበሩ፡፡ ከጉዞ ስንመለስ ለብርታትና የጥንካሬ አርአያነታቸው የፈረስ ሐውልት ገዝተን ሸልመናቸዋል፡፡
“የማስታወስ ችሎታቸው ልዩ ነው”
ዘነበ ወላ (ደራሲ)
የባሕር ኃይል ዐባል ሆኜ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ ያደረግነውን ጦርነት አይቻለሁ፡፡ በጦር ሜዳ የሚካሄድን ጦርነት ማንም ጎበዝ ፀሐፊ በመጽሐፍ ሊገልጸው አይችልም፡፡ የጦርነት ሜዳ ሕሊናን የሚያቆስል ብዙ ነገር ይታይበታል....
ከዚያ ቀውስ ወጥቼ በ1982 ዓ.ም ወደ መሐል ሀገር ስመጣ፤ ደራሲ አስፋው ዳምጤ፣ ሳህለሥላሴ ብርሃነማርያምንና ስብሐት ገብረእግዚአብሔርን እኩል ነው ያወቅኋቸው፤ ያገኘኋቸውም፡፡ እነ ጋሽ አስፋው ‹‹ኢትዮጵያ ጦርነት አያስፈልጋትም›› የሚል አቋም እንዲኖረኝ አድርገውኛል፡፡ ራሴንም ሌላውንም እንዳከብር ረድተውኛል፡፡
አስፋው ዳምጤ የማስታወስ ችሎታቸው ልዩ ነው፤ አድማጭ ካገኙ ብዙ ዕውቀት ያቀብላሉ፡፡ ለሰዓሊያን፣ ለደራስያን፣ ለቀራጺያን … ዕውቀትና ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡ ስለ አሜሪካ ሕዝብ፣ ሀገርና ዕውቀት … ካጫወቱን፣ እዚህ ቁጭ ብለን ስለዚያች ሀገር ሙሉ ዕውቀት እንዲኖረን ያደርጋሉ። የእንግሊዝ ተማሪ ሆነው አማርኛን ካከበሩ ታላላቅ ሰዎቻችን መሐል አንዱ ናቸው፡፡ ጋሽ አስፋው ያለፈውን ዘመን፣ ሀገርን፣ የሀገር መሪዎችን … ያከብራሉ፡፡ ስለ ጋሽ አስፋው ታላቅነት ስመሰክር እኔም ኩራት ይሰማኛል፡፡
‹‹ውጭ ሀገር መቅረትን እንዳትመኚ›› ብለውኛል
አጋረደች ጀማነህ (መምህር)
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በጋዜጠኝነት ስሰራ ከተዋወቅኋቸው ብዙ ሰዎች አንዱ ጋሽ አስፋው ዳምጤ ናቸው፡፡ ዘመኑ እነ አሸናፊ ዘደቡብ መሰል ሐያሲያን በጋዜጦች ላይ ሒሳዊ ንባብ በብዛት የሚያቀርቡበት ወቅት ነበር፡፡ ጋሽ አስፋው በእኔ ሙያና ሕይወት ላይ ሁለት መሠረታዊ ነገር አኑረዋል፡፡ አንደኛው፣ ደራስያንንና አዲስ የሚወጡ መጻሕፍትን ማስተዋወቅ የሚያስችል አጭር የመጽሐፍ ቅኝት አጻጻፍን አሳይተው ዓምድ ከፍቼ እንድሰራበት አድርገዋል፡፡
ሁለተኛው፣ ሀገሬን ኢትዮጵያ በመውደድ ከወላጆቼ በመቀጠል የማይናወጥ አቋም ያስያዙኝ ጋሽ አስፋው ዳምጡ ናቸው፡፡ ለትምህርት ወደ ጀርመን በሄድኩበት ወቅት ብዙ ወዳጆቼ በዚያው እንድቀር ሲወተውቱኝ፤ ትምህርቴን አጠናቅቄ እንድመለስ ካደረገኝ ምክንያቶች አንዱ፣ ጋሽ አስፋው ዳምጤ ስለ ሀገር ፍቅር በ12 ቁጥር ምስማር በልቤ አጣብቀው ያኖሩት እውነት ሲሆን፤ ‹‹ውጭ ሀገር መቅረትን እንዳትመኚ›› ነበር ያሉኝ፡፡ በጀርመን ሀገር ለተከታተልኩት ትምህርት መጽሐፍ በመስጠት ጭምር ያደረጉልኝ ውለታ ታላቅ ነበር፡፡
“የስዕል ስራዎችም አሏቸው”
ዳንኤል ታዬ (ሰዓሊ)
ጋሽ አስፋውን ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ አውቃቸዋለሁ። በወቅቱ ያዘጋጀሁትን የስዕል ኤግዚቢሽን ሊጎበኙ በመጡበት አጋጣሚ ተዋውቀን፣ ይኸው እስከ ዛሬ በየሳምንቱ ሁለት ቀን ቡና እየጠጣን፣ በወዳጅነት ዘልቀናል፡፡ ወዳጆቻቸው እንዳሉት፣ ጋሽ አስፋው ሰዓሊ ናቸው። ጥቂት የማይባሉ የስዕል ስራ ስብስብ አላቸው። ስዕሎቻቸውን አንድ ቀን እናየዋለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
የጋሽ አስፋውን የራስ ምስል (ፖርትሬት) በ6 የተለያዩ ጊዜያት ሰርቻለሁ፡፡ አሁን በተመረቀው መጽሐፍ የፊት ገጽ ላይ የወጣው ስዕል ለ83ኛ ዓመት ልደታቸው የሰራሁት ነው፡፡ ልዩ የማስታወስ ችሎታ አላቸው፡፡ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን አይተው፣ በማግስቱ ጨዋታውን ካዩ ሰዎች ጋር የሚያደርጉት ውይይት፣ ነገሮችን በጥልቀትና በትኩረት የመመልከት ልዩ ተሰጥኦ እንዳላቸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡
“ደራሲውንና ስራውን ለያይተው ያያሉ”
ኤርሚያስ ሁሴን (ደራሲ)
በ1985 ዓ.ም ነው ትውውቃችን የጀመረው፡፡ ጋሽ አስፋው፤ ስዩም ወልዴ ራምሴ፣ አብደላ እዝራ ከመሳሰሉ በሐያሲነት ከሚታወቁ ጥቂት የዘርፉ ባለሙያዎች አንዱ ናቸው፡፡ ሐያሲያን በተለይ ሒስ በሚቀርብባቸው የስራው ባለቤቶች (ሰዎች) በጥሩ ሁኔታ አይታዩም፡፡ የጋሽ አስፋው ዳምጤ ለየት የሚለው ከሐያሲነታቸው አንጻር በጥላቻ የሚያያቸው የለም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደራሲውንና ስራውን ለያይተው መመልከታቸው ነው፡፡ ሁሉንም ደራሲ በአንቱታ ክብርና እውቅና ይሰጣሉ፡፡ የድርሰት ስራውን ከመተቸት ይልቅ ሰፋና ዘርዘር አድርገው ያሳያሉ፡፡ ክርክርና ሙግት ውስጥ አይገቡም፡፡ ሙያዊ በሆነ መልኩ ትንታኔ ያቀርባሉ፡፡
ዛሬ የተመረቀውን መጽሐፍ ተከታይ ክፍል፣ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ የመለሱት የትርጉም ስራ፣ የግለ ሕይወት ታሪክ እና መሰል ስራዎቻቸው ለአንባቢያን እንዲደርሱ ለማገዝ ጥረት እያደረግን ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡-
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ማግኘት ይቻላል፡፡
Sunday, 20 August 2023 00:00
የጋሽ አስፋው ወዳጆች ምን አሉ?
Written by ብርሃኑ ሰሙ
Published in
ህብረተሰብ