Saturday, 19 August 2023 21:15

የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር፣ በኤዲተሮች የሦስተኛ ወገን ጣልቃገብነትና ጫና ዙሪያ ምክክር አደረገ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

*ዜጠኝነት መጀመሪያ እንደ ሙያ መከበር አለበት - የኢቲቪ ዜና አቅራቢ


የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር (ኤዲተርስ ጊልድ ኦቭ ኢትዮጵያ)፣ ሳምንታዊ የምክክርና ውይይት መርሃግብሩን፣ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በሒልተን አዲስ  ያካሄደ ሲሆን፤ የውይይቱ ርዕስም፤“Media Independence- Editorial Decision Making in Newsrooms and Society”  የሚል ነበር፡፡
ውይይቱ በዋናነት በኢትዮጵያ በመንግሥትም ሆነ በግል ሚዲያው ተቀጥረው የሚሰሩ አዘጋጆች (ኤዲተሮች)፣የቱን ያህል ከተጽዕኖና ጣልቃ-ገብነት ነጻ ሆነው ሙያቸውን ይተገብራሉ የሚለውን የሚዳስስ ነው፡፡
መንግሥት የፖለቲካ ፍላጎቱን ለማሳካት፣ የግል ሚዲያ ባለቤቶች ደግሞ ለገንዘብና ለትርፍ ሲሉ ምን ያህል በኤዲቶሪያል ውሳኔዎች ላይ ጣልቃ ሊገቡ እንደሚችሉም በውይይቱ  የተነሳ ሲሆን፤ ለመፍትሄውም የተለያዩ  ምክረሃሳቦች ቀርበዋል፡፡
በአገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳቱ በጋለ ቁጥር፣በሚዲያና በጋዜጠኝነት  ላይ ጫናና ወከባ እንደሚበዛ የሚገልጹ  የዘርፉ ባለሙያዎች ፤ዘርፉን ከህገወጥ ክልከላና አፈና ለመታደግ የማህበሩ አባላት በጋራ መቆምና አቅማቸውንም ማጎልበት እንደሚገባቸው ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር በመላው አገሪቱ በህትመት፣ በብሮድካስትና በዲጅታል ሚዲያ መድረኮች ላይ የሚሰሩ ኤዲተሮችን (አዘጋጆችን) በማቀፍ፣ በ2019፣የዛሬ አራት ዓመት የተመሰረተ የሙያ ማኅበር ሲሆን፤ ከተልዕኮዎቹ አንዱም በአገሪቱ የተሻለ የሚዲያ ነጻነትን መፍጠር ነው።
የጋዜጠኞችን ደህንነት ማስጠበቅ፣እንዲሁም የማህበሩን አባላትና የተቋሞቻቸውን አቅም ማሳደግም ማህበሩ የተቋቋመበት ሌላው ዓላማው ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ጥራት ያለው ጋዜጠኝነት እንዲያብብም በየሳምንቱ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ከአባላቱ ጋር ይመክራል ተብሏል፡፡
በዕለቱ የማህበሩ አባላት በርዕሰጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶች የሰጡ ሲሆን፤የኢቢሲ አንጋፋው ዜና አንባቢ መለሰ “ከሁሉም በፊት ጋዜጠኝነት እንደ ሙያ መከበር አለበት፤በሙያው ተቀጥሮ ለመሥራት የወደደም በቅድሚያ በዘርፉ መሰረታዊ ትምህርትና ክህሎት ማግኘት ይገባዋል፤ ያኔ ጋዜጠኝነት እንደ ሙያ ይከበር ይሆናል“ ብሏል፡፡  
.የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር አባላት (Editors Guild of Ethiopia)፤ በየሳምንቱ እየተገናኙ የቁርስ ላይ ውይይት ‘ (Breakfast Meeting) የሚያካሂዱ ሲሆን፤  የኤዲተሮችን ሙያዊ ነጻነትና ደህንነት በሚያስጠብቁበት፣ ጋዜጠኞችና አዘጋጆች ያለስጋት በነፃነት ሙያቸውን በሚተገብሩበት፣ በአጠቃላይ ያለ ውጭያዊ ተፅዕኖና ጣልቃገብነት በራሳቸው እየወሰኑ መሥራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እየመከረ፣ የተሻለ የሥራ ድባብ ለመፍጠር እየተጋ እንደሚገኝ አባላቱ ለአዲስ አድማስ አረጋግጠዋል፡፡

Read 514 times