• “ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር፣ አገሪቱ በዓመት 1.2 ቢ. ዶላር የውጭ ምንዛሪ ታገኝበታለች
• “ቀንጢቻ ማይኒንግ”፣ከፍተኛ አስተዋጽኦና ድጋፍ አድርጓል ላለው ለሰባቦሩ ወረዳ የ2 ሚ. ብር ድጋፍ አበርክቷል
* ሳኡዲ አረቢያ፣ የ200 ሚሊዮን ዶላር የሊትየም ቅድመ ግዢ ስምምነት፣ ከቀንጢቻ ማይኒንግ ጋር ተፈራርማለች
ሪፖርታዥ
በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን፣ ደርሚ ወረዳ፣ ቀንጢቻ አካባቢ የሚገኘውና የሊትየም ማዕድን ለማምረት የተቋቋመው ቀንጢቻ ማይኒንግ ኃ.የተ.የግ.ማህበር፤ በመጪው መስከረም ወር ሥራ እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው በዛሬው ዕለት የድርጅቱ አመራሮችና ባለአክሲዮኖች፣ የፕሮጀክቱን ሂደትና የደረሰበትን ደረጃ እንዲሁም 150 ሚሊዮን ብር የወጣበት የሊትየም ማዕድን ማውጫ ወደ ኢትዮጵያ እያስገባ መሆኑን በተመለከተ በሸራተን አዲስ ሆቴል፣ ለባለድርሻ አካላትና ለጋዜጠኞች ማብራሪያ በሰጡበት መርሃግብር ላይ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት፣ በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው ነው የተባለ የሊትየም ማዕድን ማውጫ ማሽነሪ፣ በቀጣይ ሳምንታት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገባ፣ የቀንጢቻ ማይኒንግ ኃ.የተ.የግ.ማህበር መሥራችና ከፍተኛው የአክሲዮን ባለድርሻ የሆኑት ሀጂ አሊ ሁሴን፣ ከሳኡዲ አረቢያ በስካይፒ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ማስታወቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የቀንጢቻ ማይኒንግ መሥራችና በኢትዮጵያ የአፍሪካ ማይኒንግና ኢንጂነሪንግ ተወካይ የሆኑት ሀጂ አሊ ሁሴን በዛሬው የሸራተን አዲስ መርሃ ግብር ላይ በሰጡት ማብራሪያ፣ ከፍተኛ መዋዕለንዋይ የፈሰሰበት ይኸው የሊትየም ማሽን፣ ከደቡብ አፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመርከብ የተጫነ ሲሆን፤ በመጪው መስከረም ወር ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባና ድርጅቱም ሥራ እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡
ሁለት ተጨማሪ አቅም ያላቸው የሊትየም ማውጫ ማሽነሪዎች ከ2023 የፈረንጆች ዓመት ማገባደጃ በፊት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያስገቡ የገለጹት ሀጂ አሊ ሁሴን፤ይህም በጠቅላላው በሰዓት 270 ቶን ሊትየም የማምረት አቅም እንደሚሰጣቸውና በዓለም ላይ በጣት ከሚቆጠሩ ጥቂት የሊትየም አምራች አገራት ጎራ እንደሚያሰልፋቸው ጠቁመዋል።
ቀንጢቻ ማይኒንግ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባና የሊትየም ማዕድን ከሀገራችን ከርሰ ምድር ወጥቶ ለዓለም ገበያ ሲቀርብ፣ ኢትዮጵያ በዓመት 1.2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ታገኝበታለች ያሉት የድርጅቱ መሥራች፤ ከዚህም ባሻገር ለ500 ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርላቸውና መንግሥትም ከፍተኛ የታክስ ገቢ እንደሚያገኝበት አክለው ገልጸዋል፡፡
ኩባንያው በወር እስከ 20 ሺህ ቶን የሚደርስ የሊትየም ማዕድን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ማቀዱን ያስታወቀ ሲሆን፤ ገና ምርት ሳይጀመር ሳኡዲን ጀምሮ ከ12 በላይ አገራት የግዢ ስምምነት መፈጸማቸውን ሀጂ አሊ ሁሴን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሰረት፣ቀንጢቻ ማይኒንግ፣ ከሳኡዲ አረቢያ ጋር የ200 ሚሊዮን ዶላር የሊትየም ቅድመ ግዢ ስምምነት፣ መፈጸሙ ተጠቁሟል፡፡
ቀንጢቻ ማይኒንግ ኃ.የተ.የግ.ማህበር፣ በአጠቃላይ በ80 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ወደ ሥራ መግባቱን ያስታወቁት የድርጅቱ መሥራች፤ በዓለም ላይ አሉ የተባሉ የማዕድን ፍለጋ ባለሙያዎችን አሰማርተው ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት እየተዘጋጁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
“በቀጣይነትም ሊትየም፣ የባትሪ ምርት ዋነኛ ግብአት በመሆኑ፣ ማዕድናችንን እየላክን የበዪ ተመልካች እንዳንሆን፣ የሊትየም ባትሪ ፋብሪካ ለመክፈትም፣ ጥናቱን አጠናቅቀን በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡” ብለዋል፤ሀጂ አሊ ሁሴን፡፡
በዛሬው መርሃግብር ላይ የቀንጢቻ ማይኒንግ ፕሮጀክቶችን አጠቃላይ ሂደት የሚያሣይ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን ለዕይታ የቀረበ ሲሆን፤ ኤግዚቢሽኑ በባለድርሻ አካላትና በክብር እንግዶች ተጎብኝቷል፡፡
በሌላ በኩል፣ ቀንጢቻ ማይኒንግ ፈቃድ ወስዶ ፕሮጀክቱን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦና ድጋፍ ያደረጉ አካላት የዕውቅና ሽልማት በድርጅቱ የተበረከተላቸው ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ የፌደራል ማዕድን ሚኒስቴር፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት፣ የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የቆንጢቻ ቀበሌ ይገኙበታል፡፡
ከዕውቅና ሽልማቱ በተጨማሪ፣ ቀንጢቻ ማይኒንግ ኃ.የተ.የግ.ማህበር፣ባለፉት ወራት ለፕሮጀክቱ ስኬታማ ሂደት ከፍተኛ አስተዋጽኦና ድጋፍ አድርጓል ላለው ለሰባቦሩ ወረዳ፣ የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አበርክቷል፡፡
ቀንጢቻ ማይኒንግ ኃ.የተ.የግ.ማህበር ባዘጋጀው በማክሰኞው የፕሮጀክት ሂደት ማብራሪያ መርሃግብር ላይ አምባሳደሮች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ባለድርሻ አካላት፣ የባንክ ተወካዮች፣ አባ ገዳዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ም ተገኝተዋል፡፡
Saturday, 19 August 2023 21:17
በ80 ቢ ብር ኢንቨስትመንት የተቋቋመው፣ “ቀንጢቻ ማይኒንግ“፣ በመጪው ወር ሥራ ይጀምራል
Written by Administrator
Published in
ንግድና ኢኮኖሚ