Sunday, 27 August 2023 19:31

ባነገሡት ላይ ተመልሶ ይነሣባቸዋል፤ ያፈቀሩትን ያስጨንቃቸዋል።

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ሦስቱ የተባረኩና የተረገሙ ኃይሎች
እውቅና ጉልበት (ጥበብና ሥልጣን)
የሥራ ፍሬና ገንዘብ (ምርትና ሀብት)
ፍቅርና አልጋ (ሩጫና ሜዳልያ)
የማንገሥ ፍላጎት ወይም መንግሥትን የማዋቀር ሐሳብ ተገቢ የኑሮ ጉዳይ ቢሆንም፣ አደጋዎቹን ማገናዘብና መላ ማዘጋጀትም የሕልውና ጉዳይ ነው። አስቀድመው መጠንቀቅ እንደሚኖርባቸው ሙሴ ለተከታዮቹ ያስተማራቸውም በዚህ ምክንያት ነው። ለሕዝብና ለንጉሥ የሚበጁ ምክሮችን ሰጥቷቸዋል።
ንግሥና ወደ ሦስት ጠማማ መንገዶች እንዳያመራ በንጉሡ ላይ ሦስት የሥልጣን ገደቦች እንደሚያስፈልጉ ነግሯቸዋል።
ለእርሱ ፈረሶችን አያብዛ፤
ልቡም እንዳይስት ሚስቶችን ለእርሱ አያብዛ፤
ወርቅና ብር ለእርሱ እጅግ አያብዛ (ዘዳ 17፡ 16-17)።
ንጉሡ፣ ተወዳጅነትን ለማግኘት በውሸት ይሸነግላል። ከተጠያቂነት ለማምለጥ ሌሎች ሰዎችን በውሸት እየወነጀለ ያሳድዳቸዋል። አቤቱታ የሚያቀርቡ ተበዳዮችን እንደ ከሃዲ ይቆጥራቸዋል። ከተቀናቃኞቹ ጋር ሆነው ያሤሩበት ይመስለዋል።
የሕዝብ ፍቅር እንዳያጣና ሥልጣኑን የሚነጥቅ ሌላ ጉልበተኛ እንዳይመጣበት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ሐሰትን መናገር፣ ተበዳዮች ቅሬታ እንዳያቀርቡ ማሳደድ፣ የራሱን ጥፋት በሌሎች ላይ ማላካክ፣ ቀላል አቋራጭ መንገዶችን ሁሉ ይሞክራል። በዐላዋቂነትና በስንፍና ወይም በክፋትና በምቀኝነት ስሜት እየታወረ ከእውነት ጋር ይጣላል። እምነት ያጣል። ዓላማ ይደበዝዝበታል። የሥነ ምግባር መስመሮች፣ የፍትሕና የፍቅር መርሖች እንቅፋትና ጠላት ሆነው ይታዩታል።
‘እውነተኛ ሐሳብ፣ ትክክለኛ ዓላማ፣ መልካም ሥነ ምግባር’ እያለ ያነበንባል። ግን ለይስሙላ ነው። እንደ አድማጮቹ ሁኔታ ቃሉን ይለዋውጣል። ባለ ብዙ ምላስ ይሆናል።
ዳኝነት ለማግኘት ከሳሽና ተከሳሽ ለሙግት ሲመጡ ለየብቻ እየነጠለ “አንተ ትክክለኛ ነህ” እያለ ሁለቱንም እያስደሰተ ሁለቱንም ለማታለል ይሞክራል። ብልጥ መሆኑ ነው። የተቀናቃኞችን የኃይል ሚዛን እያየ ፍርዱንና አቋሙን፣ ዓላማና ተግባሩን ይገለባብጣል።
የተመልካቾችን ስሜት እያየ መልኩን ይቀያይራል። ባለ ብዙ ጭንብል አስመሳይ ሰው ይሆናል።
እውነትና ውሸት፣ ጥሩና መጥፎ መለየት እስኪያቅተው ድረስ በራስ የመተማመን ዐቅሙ ይመነምናል። የማንነት መንፈሱ በየዕለቱና በየሰዓቱ እየተበጣጠሰ ይወናበድበታል። ስሜቱ ይዘበራረቅበታል።
እንዲህ እንዲህ እያለ፣ ንጉሡ ቀስ በቀስ የእኔነት ክብር እየጎደለው ሲመጣ፣ ውስጣዊ ባዶነት በተሰማው ጊዜ፣ የሕይወት ጣዕም ሲጠፋበትና የመንፈስ እርካታ ሲያጣ… ይህን ለማካካስ ወደ ሦስት ጠማማ መንገዶች ይገባል። ሥነ ምግባርን እንደ ጠላት ማየት ከጀመረ በኋላ…
ሕግ የማይገዛው ሥርዓት አልበኛ ይሆናል (አምባገነን፣ ወሮበላና ነውረኛ)።
አምባገነን (በሽንገላ ይጨክናል)፡
በዕውቀትና በጥበብ መንገድ የተራመደ ሰው፣ ተሰሚነትንና ክብርን ቢያገኝ ተገቢ ነው። ዕውቀት ‘ኃይል’ ነው። ጥቂት የፊዚክስ ቀመሮች ለእልፍ አእላፍ ቴክኖሎጂዎች መነሻ ይሆናል። ከአንድ ሜትር በላይ መዝለል የማይችል ሰው፣ አየር ባየር ውቅያኖሶችን እየዘለለ የመሻገር ብቃት ያገኛል።
ሰዎችን እየረገጠ አይፈነጭም። በጥበበኛ መንገድ ጨረቃን ረግጦ ይመለሳል።
ወደ ማርስ ለመምጠቅ ሌሎች ሰዎችን ወደ መቀመቅ አያወርድም።
ኃያልነቱ ሕይወትንና ንብረትን የሚያጠፋ ሳይሆን የሚያለመልምና መልካም ፍሬዎችን የሚያበዛ ነው።
የተባረከ ኃይል እንጂ የተረገመ ኃይል አይደለም - የዕውቀትና የጥበብ መንገድ።
እግረ መንገዱን ለሰው ልጆች ሁሉ መልካም ጸጋዎችን ያበረክታል። አርአያነቱን በማየት ገሚሶቹ ወደ ጠፈር የመብረር ዐቅም ያገኛሉ። ለዓለም ሰዎች ሁሉ በሳተላይት የመጠቀም አዲስ ዕድል ይፈጥራሉ።
የዕውቀትና የጥበብ መንገድ በሌሎች ሰዎች ላይ  ጉልበቱን ለማሳየትና ገዢ ኃይል ለመሆን አይሻም። ሰዎች ፈልገውት ይመጣሉ። ዕውቀቱንና ሐሳቡን ያከብራሉ።
እርስ በርስ ተፈቃቅደው ይማማራሉ፣ ተከባብረው ይደጋገፋሉ እንጂ ባሪያና ገዢ አይሆኑም።
ጥቂት የፍልስፍና ሐሳቦችና የፖለቲካ መርሖች የእልፍ ሰዎችን ቀልብ ይገዛሉ፤ ሚሊዮን ሰዎችን ሊያነቃንቅ የሚችል ኃይል ያመነጫሉ። ከዚያም ወደ ሕገ መንግሥት አንቀጾች እየተተረጎሙ ለመላው ዓለም የነጻነት ፋና ይሆናሉ። ቢሊዮኖች በየፊናቸው ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ ሰፊ የነጻነት ዕድል ያገኛሉ። የዕውቀትና የጥበብ መንገድ እጅግ የተባረከ ተአምረኛ ኃይል ነው።
በአቋራጭ እሄዳለሁ ብሎ ራሱን ያጣመመ ሰውስ? ሕይወትን የሚያጠፋ የተረገመ ኃይል እንጂ ሕይወትን አክብሮ የሚያለመልም የተባረከ ኃይል አይኖረውም።
“የሥልጣን ጥመኛ፣ ጸብ ፈላጊ ወራሪ ጦረኛ ይሆናል። ሕዝብን አሰልፎ ያዘምታል። በሰበብ አስባቡ ይማግዳቸዋል። (“ዐዋቂ ስለሆንኩ ሕዝብ ይሰማኛል፤ ይከተለኛል። አቻ ያልተገኘልኝ ጥበበኛና ወደር የለሽ ጀግና ነኝ” ለማለት ነው ፍላጎቱ)።
የራሱን ሕይወት ጠብቆ የሌላውንም ሰው ሕይወት አክብሮ በሰላም መኖር አያረካውም። የሰፈር ዱርዬ ወይም የአገር መሪ ሊሆን ይችላል። የሥልጣን ጥመኛ ከሆነ፣ መከባበር አይጥመውም። በመንደርም ሆነ በአገር፣ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በሰዎች ላይ አዛዥና አናዛዥ ለመሆን ይመኛል።
በሰዎች ሕይወትና ሰብዕና ላይ፣ በሰዎች ኑሮና ንብረት ላይ፣ በሰዎች ሐሳብና ዓላማ ላይ ዘው ብሎ እየገባ እንዳሰኘው የማዘዝ ሥልጣን ለማግኘት ይጎመጃል።
ኃያልነት ማለት ሰዎችን የማታለል ብልጠትና የመርገጥ ጉልበት ነው ብሎ ያስባል።
ትንሽ ሥልጣን አግኝቶ እልፍ ሰዎችን መኮርኮም ይጀምራል። ግን አያረካውም። ከእግሩ ስር ተደፍተው በላያቸው ላይ ካልተረማመደ የሥልጣን ትርጉም ይጠፋበታል። ይሄም አያጠግበውም። ሚሊዮኖችን መርገጥ ያምረዋል። ዐሳራቸውን ያበላቸዋል። ከአፈር ጋር ይቀላቅላቸዋል።
ገደብ በሌለው ሥልጣንና በጦር መሳሪያ ብዛት አገሬውን ከዳር እስከ ዳር ስለጨፈለቀና ስላስጨነቀ፣ ሚሊዮን ሰዎች ስለፈሩትና ስለታዘዙለት፣ እንደ ዐዋቂ ተሰሚነትን ያገኘ፣ በጥበብ የመጠቀና ታላቅ  ክብር የተቀዳጀ ይመስለዋል።
ተወዳጅ ለመሆን እንቅልፍ አጥቶ ያድራል። በሕዝብ ከተወደደ በኋላም ግን ይጨንቀዋል። የሚያደርገውን ያሳጣዋል።
በአንድ በኩል የሕዝብ ፍቅር ለማግኘት ይሟሟታል። ሕዝብን ዘወትር ይሸነግላል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝብ ላይ እንዳሻው ሥልጣኑን ለማሳየት ይጨክናል።
ተወዳጅነቱን በየዕለቱ ለማረጋገጥ ሕዝብን ይፈታተናል። የሚያስቆጡ በደሎችን ይሰራል። የሕዝቡ ታማኝነት እንደማያወላውል ማየት አለብኝ ብሎ በየዕለቱ የባሰ ግፍ ይፈጽምባቸዋል። እንዲያጨበጭቡ፣ በጽናት እንዲደግፉት፣ ያለማመንታት እንዲታዘዙለት ያስጨንቃቸዋል።
በሁሉም ነገር ላይ ዐዋቂ ነኝ ብሎ እንደመጣለት ይናገራል። ውሸት ያወራል። እውነትን ለመናገር በነጻነት ለመተንፈስ የሚደፍር ሰው እንዳይኖር ይፈልጋል። ሁሉም ሰዎች አፋቸውን ይዘው እንዲሰሙት ብቻ ሳይሆን፣ አሜን ብለው ንግግሩን እንዲያጸድቁለት ንጉሡ ይጠብቃል።
‘የሥልጣን ጥም’ በንጉሦች ወይም በፖለቲከኞች ላይ ብቻ የሰፈረ ልክፍት አይደለም።
አገር ምድሩ ላይ የገነነ ገዢ ንጉሠ ነገሥት ወይም አንዲት ጉብታ ላይ የመሸገ ሽፍታ ሊሆን ይችላል።
ከአባቱ ዘውድ ለመቀማት የጎመጀ የንጉሥ ልጅ አልጋ ወራሽ ሊሆን ይችላል።
የዓመፅ ጊዜ ጠብቆ በግርግር ሥልጣን ለመያዝ የሚያሤር የቤተ መንግሥት ቤተኛ፣ አልያም በሽምቅ ውጊያ ሥልጣን ላይ ለመውጣት አገርን የሚያሸብር ‘ተስፈኛ’ ሊሆን ይችላል።
የትርፍ ሰዓት አጫፋሪዎችም አሉ። ፖለቲካ እንደ ቁማርና እንደ ድራማ ሆኖ የሚታያቸው ሰዎችም በሥልጣን ሽሚያው ውስጥ ይራኮቱበታል። አንዳንዶቹ እስከ ፒኤችዲ የተማሩ ናቸው። ነገር ግን የተማሩትን አይመረምሩም። ስህተትንና ትክክልን እየለዩ አያገናዝቡም። እንደ ቁም ነገርና እንደ ዕውቀት አይቆጥሩትም። ‘መማር ለዕውቀት ሳይሆን ለብልጠት’ ይመስላቸዋል። በሌላ ወገን ደግሞ፣ ለትምህርት ቅንጣት ጊዜና ክብር የማይሰጡ ይሉኝታ ቢስ ጋጠወጦች አሉ።
አመቺ ዘመን መጣልን ብለው የሚያስቡ ብልጦችና ጋጠወጦች፣ ከመኖሪያ ቤት ሳይወጡ፣ ከተጋደሙበት ፍራሽ መነሣት ሳያስፈልጋቸው፣ ከባርሕ ማዶም ጭምር በትርፍ ሰዓታቸው የፖለቲካ ቁማር አዳማቂ ይሆናሉ። አንጋሽና አውራጅ፣ ሿሚና ሻሪ ለመሆን የሚቋምጡ ‘የኢንተርኔት አስጨፋሪዎችና አስለቃሾች’ ሞልቷል።
የሥልጣን ጥም የተጠናወታቸው ሰዎች የኑሮ ደረጃቸውና ዐቅማቸው ቢለያይም፣ በአንድ ነገር ይመሳሰላሉ።
ከንጉሥ እስከ አሰስና ገሠሥ ድረስ ነው - ልዩነታቸው።
ነገር ግን በሰዎች ሕይወትና ንብረት ላይ የማዘዝ ረሀብ አለባቸው።
በሰው ንብረት ላይ ማዘዝ ማለት፣ በምቀኝነት የሰዎችን ቤትና ንብረት ማውደም፣ በስግብግብነት መዝረፍ ወይም ከአንዱ ነጥቆ ለሌላ መስጠት ሊሆን ይችላል።
በሰው ሕይወት ላይ ማዘዝ ማለት፣ ሰዎችን በውሸት መወንጀልና ስም ማጉደፍ፣ ማሰርና ማገት፣ መጥለፍና በባርነት ማዋረድ፣ መደብደብና መግደልን ሁሉ ይጨምራል።
ጥቃቱ  የሚመጣው በቀጥታ ከፈጻሚው በአካልና በቅርበት ሊሆን ይችላል። ከሩቅ ሆኖ ሌሎች ሰዎችን በመቀስቀስ ወይም በማሰማራት ሊሆን ይችላል።
በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ በሰዎች ሕይወትና ንብረት ላይ ‘ሰጪና ከልካይ’ ቢሆን ይመኛል። እሱ እንዳሻው የሚዘውራቸው መጫወቻ እንዲሆኑለት ይፈልጋል።
ረሀቡ…
ሰዎች በገዛ ሕይወታቸውና ንብረታቸው ላይ ሥልጣን እንዳይኖራቸው ማድረግ ነው። ሰው የመሆን ብቃታቸውን ለማምከንና ለማኮላሸት ነው ጉጉቱ። በሌላ አነጋገር…
የሥልጣን ጥም ማለት የማጥፋት ጥም ማለት ነው።
በስብከትም ይሁን በዐዋጅ፣ በስድብም ይሁን በሚሳዬል፣ በንግሥናም ይሁን በሽፍትነት፣ በጦር ሜዳም ይሁን በኢንተርኔት… የስልጣን ጥመኛ ሁሉ እንደየዐቅሙ ሰዎችን እያቧደነ ተከታይ ሕዝብ እንዲበዛለት ይስገበገባል። አይጦችን ለማጥመድ እንደቋመጠ ቀበሮ የሕዝብን ስሜት ለማሾር ይቅለበለባል።
ንጉሥም ይሁን ሽፍታ፣ አወዳሽ አስጨፋሪም ሆነ ሙሾ አውራጅ፣… አድማጮቹና ተከታዮቹ… በስሜት እስኪጦዙ ድረስ፣ ሌሎች ዜጎችም እስኪደነዝዙ ድረስ በፕሮፓጋንዳ ወይም በአልቧልታ ዘወትር ይነዘንዛቸዋል። በአፈናና በእስር ወይም በስድብና በማስፈራሪያ ዝም ያሰኛቸዋል። ከቻለም ያዘምራቸዋል።
ወሮበላ (በመደለያ ይዘርፋል)፡
በጥበብና በትጋት ኑሮን ማሻሻል፣ ሀብት ማፍራትና ባለጸጋ መሆን ተገቢ ነው። ገበያ ይደራለታል። በብዙዎች ዘንድ ተፈላጊ ይሆናል። ሰዎችን መርዳትና መለገስም ይችላል።
በአቋራጭ ልሂድ ብሎ ከተጣመመ ግን…
በአንድ በኩል፣ በአቋራጭ አየር ባየር የሚመጣ ሀብት ለማግኘት ይመኛል። ገንዘብ ብቻ እየታየው ከአምራች ዜጎች እየዘረፈ ያግበሰብሳል። (ስኬታማና ፍሬያማ ነኝ ለማለት ነው ምኞቱ)። የሰዎችን ምርት ነጥቆ ሲወስድ፣ የምርታማነት ክብራቸውንም እንደወረሰ ይቆጥረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ “ገንዘብ የኃጢአት ሥር ናት” ብሎ የሰብካል። በትጋት የተገኘ ሀብትን በጭፍን እያወገዘ ያወድማል። የግል ንብረትንና ገንዘብን ሁሉ እያንቋሸሸ ይዘርፋል። ገንዘብ እያተመ ይከምራል።
ለጋስነት ማለት ከአምራቾች ቀምቶ ለሌሎች መስጠት ይመስለዋል። ‘ድሆችን ለማብላት አገርን ለማልማት’ እያለ ይናገራል። ተመሳሳይ የመደለያ ሰበቦችን እየፈጠረ ሁሉንም ያራቁታል፤ አገርን ያደኸያል።
ነውረኛ (በማስመሰያ ያዋርዳል)፡
ብቃቱን ያስመሰከረና በትጋት ለውጤት የደረሰ ሰው፣ መንገዱ ቀና ነው። በስራው ከብሯልና ሰዎች ቢያደንቁትና ቢያከብሩት፣ ቢያፈቅሩትና በአርአያነት ቢከተሉት ተገቢ ነው።
ጠማማ ጉራንጉር ውስጥ ልግባ ካለስ?
ያለ አጨብጫቢ በሰላም ማደር የማይችል አስመሳይ ጉረኛ ይሆናል። ወይም ደግሞ…
“ሰው ከንቱ መናኛ ፍጡር መሆኑን እመኑ” የሚል ፈሊጥ ያመጣል። ሁሉም ሰው ዐንገቱን እንዲደፋ የሚሰብክና የሚኮረኩም ምቀኛ ይሆናል።
ሁሉንም ለወሲብ የሚጎትት ክብረ ቢስ እንስሳ ወይም…
ወሲብን በጭፍን የሚያወግዝ ፍቅር አልባ ብኩን ወገኛ ሰው ይሆናል።
የፍቅርና የወሲብ በረከቶች እንደ ውጤትና እንደ ሽልማት ናቸው። ከማዕርግና ከሽልማት በፊት ‘ብቃት’ ይቀድማል። ከሜዳሊያ በፊት፣ ‘በብልኀት የተገነባ የሩጫ ብቃት’ መኖር አለበት። ብቃትም በጥረት ወደ ውጤት ይገሰግሳል፤ ማዕርግና ሜዳሊያም ይህን ተከትለው ይመጣሉ።
ለሰው ተፈጥሮ የሚመጥኑ የፍቅርና የወሲብ በረከቶችስ? የእኔነት መንፈስንና የማንነት ክብርን በመገንባት የሚገኙ አስደሳች ውጤቶችና ሽልማቶች ናቸው።
ብቃት-አልባው ክብረ-ቢሱ ሰውዬ ግን፣ የሜዳሊያ ዐይነቶችን በባዶና በአቋራጭ እየሰበሰበ ቢያንጠለጥል፣ የብቃት ባለቤት የሚሆን ይመስለዋል። በጉልበትና በብልጠት ብዙዎችን ጎትቶ ዐልጋ ላይ ሲዘርር፣ የእኔነት መንፈስና የማንነት ክብር የሚያገኝ፣ የሕይወት ጣዕም የሚሆንለት ይመስለዋል።
እንዲያ የሚቅበዘበዘው ለምን ይሆን? ነፍስ አለኝ፤ አፍቃሪ ነኝ ብሎ ራሱን ለማሳመን ነው ፍላጎቱ። የተከበርኩ አስደናቂና ተፈቃሪ ሰው ነኝ ለማለትም ነው ልፋቱ። መቅበዝበዙ ግን ይመሰክርበታል እንጂ አይመሰክርለትም።
ሌሎችን እያዋረደ ራሱን ከፍ አድርጎ ለማሳየት ይደክማል። ሌሎችን በመስደብ ራሱን የሚያሞግስ፣ የሌሎችን ማዕርግ በመሻር ራሱን የሚክብ፣ የሌሎችን ሜዳሊያ ስለወሰደና ሽልማታቸውን ስለነፈገ ልዕልናን የሚቀዳጅና የሚያምርበት ይመስለዋል።
በእርግጥ ሦስቱ ጠማማ መንገዶች፣ ንጉሦችን ለይተው የሚያጠቁ የሥነ ምግባር ብልሽቶች አይደሉም። በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሠቱ የሚችሉ የስህተትና የስንፍና፣ የጥፋትና የክፋት መንገዶች ናቸው።
በንጉሥ ላይ ከተከሠቱ ወይም በመንግሥት ባለሥልጣናትና በፖለቲካ መሪዎች ዘንድ ከተለመዱ ግን፣ ጉዳታቸው እጅግ ይበዛል። ከሥነ ምግባር ብልሽት ባሻገር፣ የፍትሕ ፀር የባርነት ቀንበር ይሆናሉ። አደጋቸው ቀላል አይደለም። እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ሙሴ ለተከታዮቹ መናገሩም፣ ዐዋቂነቱንና ጥበበኛነቱን ያመለክታል።

Read 1050 times