Sunday, 27 August 2023 19:35

የፕሬስ ነጻነት ጠበቃ - ጆሴፍ ፑልቲዘር

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ጆሴፍ ፑልቲዘር፤ ጋዜጠኛ፣ መርማሪ  ሪፖርተር፣ አሳታሚ፣ የፕሬስ ነጻነት ጠበቃ ነበር፡፡
በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያውን የጋዜጠኝነት ት/ቤት ከፍቷል - በተጨማሪም
ለጋዜጠኝነትና ሥነጽሁፍ ዘርፎች፣ ዝነኛውን የፑልቲዘር ሽልማትም ፈጥሯል፡፡
ጆሴፍ ፑልቲዘር፤ የተሻለ የዕይታ ብቃት ይዞ ቢወለድ ወይም ቼዝ መጫወት ባይችል ኖሮ፣ ጋዜጦቻችን ዛሬ ከምናውቃቸው የተለዩ ይሆኑ ነበር፡፡ ጆሴፍ በ1860ዎቹ በሃንጋሪ በታዳጊነት ዕድሜው ሳለ፣ ወታደር የመሆን ብርቱ ፍላጎት ነበረው፡፡ ነገር ግን ዓይኑ (ዕይታው) ደካማ በመሆኑ የተነሳ የትኛውም ሠራዊት ሊቀበለው አልቻለም፡፡ በመጨረሻ ግን የአሜሪካ ቀጣሪዎች፣ በአሜሪካው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እንዲዋጋ መለመሉት፡፡  
በወታደርነት ለአንድ ዓመት ያገለገለው ጆሴፍ፤ ከእርስ በርስ ጦርነት ህይወቱ ተርፎ እዚያ አሜሪካ ተቀመጠ - ያገኘውን  ሥራ እየሰራና እንግሊዝኛ ቋንቋ እየተማረ፡፡ ከዚያም በአጋጣሚ የተከሰተ ድንገተኛ ትውውቅ፣ የራሱንም ህይወት ሆነ የዓለም ጋዜጠኝነትን ታሪክ ለዝንተ-ዓለም ለወጠው፡፡
እንዲህ ነው የሆነው፡፡
ጆሴፍ በቅዱስ ሉዊስ ቤተመጻህፍት ውስጥ እያጠና ሳለ፣ ሁለት ወንዶች ቼዝ ሲጫወቱ ይመለከታል፡፡ ጠጋ ብሎም የአንደኛውን የቼዝ አጨዋወት በማድነቅ ተናገረ፡፡ ከዚያም ሦስቱ ሰዎች መጨዋወት ይጀምራሉ፡፡ ሁለቱ ሰዎች የጋዜጣ አሳታሚዎች ነበሩ፡፡ እናም የሥራ ዕድል ሰጡት - ለጆሴፍ፡፡  
ጆሴፍ ፑልቲዘር ብሩህና ትጉህ ሪፖርተር መሆኑን አስመሰከረ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላም የጋዜጣ አሳታሚ ሆነ፡፡ ከዚያም  አዋጭ  ድርድሮችን ተራ በተራ  ሲያካሂድ ቆይቶ፣ የከተማው ትልቁን ጋዜጣ በእጁ አስገባ - ”St. Louis Post- Dispach” የተሰኘውን ጋዜጣ ገዛው፡፡
ይሄኔ ነው የፑልቲዘር እውነተኛ የላቀ አዕምሮ  የታየው፡፡ ጋዜጣውን የሰፊው ህዝብ ድምጽ አደረገው፡፡ ህገወጥ የቁማር ተግባራትን፣ የፖለቲካ ሙስናንና ዳጎስ ያሉ የግብር ስወራዎችን መመርመርና  ሃቁን አደባባይ ላይ ማስጣት ያዘ፡፡ ሰዎች ይህን አዲስ የምርመራ ጋዜጠኝነት ስታይል ወደዱለት፤የጋዜጣው ሥርጭትም በእጅጉ አሻቀበ፡፡
ጆሴፍ ፑልቲዘር ከታመመም በኋላ እንኳን ተግቶ መሥራቱን አላቋረጠም፤ እናም የዓይኑን ብርሃን ሊያጣም ደርሶ ነበር፡፡ ፑልቲዘር፤ጋዜጦች የማህበረሰቡን ዓላማ ማገዛቸው እንዲሁም ህዝቡን ከሸፍጥና ሙስና መታደጋቸው አስፈላጊ ነው ብሎ ያምን ነበር፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሌላ ጋዜጣ መግዛት ቻለ፡፡ የኒውዮርክን ጋዜጣ፡፡ የህዝበኝነት አቀራረቡንም ለብዙ ተደራሲያን ተገበረ፡፡
እ.ኤ.አ በ1909 ዓ.ም የኒውዮርክ ጋዜጣው፣ በአሜሪካ ታሪክ ታላቁ የፖለቲካ ቅሌት የተባለውን ታሪክ ሰበር ዜና አድርጎ አወጣው - የፓናማ ካናል ስምምነት፣ 40 ሚሊዮን ዶላር ህገወጥ ክፍያን  አጋለጠ፡፡ ይሄን ጊዜ የአሜሪካ መንግሥት ፍ/ቤት ሊያቆመው ሞክሮ ነበር፤ ነገር ግን ፑልቲዘር ”ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ” አለ፡፡ በጽናት በመቆም፣ ለፕሬስ ነጻነት ትልቅ  ድል አስመዘገበ፡፡
ጆሴፍ ፑልቲዘር፤በዓለም የመጀመሪያው  የጋዜጠኝነት ት/ቤት፣ በኒውዮርክ፣ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ እንዲቋቋም ከሃብቱ ከፊሉን መድቧል፡፡ ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ ለጋዜጠኞችና ጸሃፍት ዓ መታዊ የሽልማት መርሃግብር የሚሆን ገንዘብም ለግሷል፤ ዛሬ ከዝነኞቹ የፑልቲዘር ሽልማቶች አንዱን ማሸነፍ፣ በጸሃፍት ዘንድ እንደ ልዕለ ኮከብ የሚያስቆጥር መሆኑ ይታወቃል፡፡   
ጆሴፍ ፑልቲዘር፤ ምንም እንኳ ወደ  ጋዜጠኝነት  የገባው በአጋጣሚ ቢሆንም ቅሉ፣ ጋዜጦች ዛሬም ድረስ ሊያሳኩት የሚተጉበትን ስታንዳርድ አስቀምጦ ነው ያለፈው፡፡

Read 939 times