Sunday, 27 August 2023 19:35

ፊስቱላን ችግሩን መከተል ሳይሆን መቅደም ያስፈልጋል፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

እኔ በስራው ላይ በቆየሁበት ዘመን ሶስት እህትማማቾች በአንድ ጊዜ በፊስቱላ ሕመም ወደ አዲስ አበባ መጥተው የታከሙ አውቃለሁ፡፡
እናትና ልጅ በአንድ ጊዜ በፊስቱላ ሕመም ወደ አዲስ አበባ መጥተው የታከሙ አስታውሳለሁ።
አባት የአስራ አራት አመት የፊስቱላ ታማሚ ልጁን ሊያሳክም መጥቶ ወደ አገሩ ተመልሶ የአስራ ሁለት አመት ልጁን ለመዳር የነበረውን ችኮላ አልረሳውም፡፡
ምንጭ ዶ/ር አምባዬ ወ/ሚካኤል  
ባለፈው ሳምንት እትማችን የአንጋፋዋን የጽንስና ማህጸን ሐኪም እና የፊስቱላ ቀዶ ጥገና ሐኪም የዶ/ር አምባዬን የፊስቱላ የስራ ድርሻ አስነብበናችሁ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን ከሳቸው ጋር ውይይት ያደረግንባቸው ፊስቱላን የተመለከቱ አሰራሮች አልተቋጩም ነበር፡፡ እናም ዛሬም እነሆ ለንባብ ብለናል፡፡
የፊስቱላ ሕክምና ሲጀመር በበጎ አድራጊዎቹ ባልና ሚስት በአዲስ አበባ ሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ብቻ ነበር ፡፡ ፌስቱላ ህመም የሚከሰትበት ምክንያት ካለእድሜ ጋብቻ ነው ይባላል፡፡ በእርግጥ ሰውነት ሳይጠና ማግባታቸውና ለእርግዝና መብቃታቸው ውጤቱን አስከፊ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ነገር ግን በጊዜአቸው ያገቡም ቀደም ሲል ልጅ ወልደው የሚያውቁም በፊስቱላ ይጎዳሉ፡፡ ለሁሉም ምክንያቱ የተራዘመ ምጥ ነው፡፡ ሴቶች በምጥ በሚያዙበት ወቅት በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋም መሄድ ሲገባቸው በተለያዩ ምክንያቶች ከቤታቸው እንዲቆዩ እና እንዲያምጡ ሲደረጉ የማህጸንና በአካባቢው ባሉ የሽንትና የመሳ ሰሉት አካላት መቀደድ ይገጥማቸዋል። ይህ እንግዲህ በየትኛውም እድሜ ላይ ያሉ ሴቶችን የሚያገጥም ችግር ነው፡፡  
ዶ/ር አምባዬ ወደ ስራው ከተቀላቀሉ በሁዋላ ግን ይህ ነገር ውስን በሆነ ሆስፒታል በዋና ከተማዋ ብቻ መሆኑ ብዙዎችን አያዳርስም ወይንም በየክልሉ በችግሩ ለሚሰቃዩ ሴቶች መልስ አይሰጥም የሚል ሀሳብ አነሱ፡፡ ስለዚህም ታማሚዎቹ ወደሆስፒታሉ መጥተው መታከም ካልቻሉ እኛ ለምን ወዳሉበት ቦታ በዘመቻ መልክ ሄደን በዚያው ሊታከሙ የሚችሉትን ባሉበት አካባቢ ሆስፒታሎች በመውሰድ ህክምናውን መስጠት ፤አለዚያም በከፍተኛ ሁኔታ የታመሙትን ወደአዲስ አበባ መጥተው እንዲታከሙ የማድረግ ስራ እንዲጀመር ሀሳብ አቅርቤ ከስምምነት ተደረሰ ብለዋል፡፡
ዶ/ር አምባዬ እንዳሉት የፌስቱላን ችግር ለመመልከት በተለይም ሕመምተኞቹ ወደ አዲስ አበባ ለህክምና ከሚመ ጡበት ሰሜናዊ ክፍል በቅድሚያ ለመገኘት የህክምና ተንቀሳቃሽ ቡድን በማደራጀት በተወሰነ ጊዜ መጉዋዝ ጀመረ። ከአማራና ትግራይ ክልሎች በመገኘት ስራው ሲጀምር በጣም ብዙ ተጎጂዎች የመምጫ መንገዱ ስላልነበራቸው እጅግ ተጎድተው ማግኘታቸውን ዶክተር ያስታውሳሉ፡፡ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ለመታከም ገንዘብ፤ መጉዋ ጉዋዣ፤ በፈቃደኝነት ወደ ህክምናው የሚያደርሳቸው ሰው ያስፈልጋቸዋል። ይህንን ባለማ ግኘታችው በየቤታቸው ጉዋዳና ጉዋሮ ተደብቀው የነበሩ ሴቶች በቅስቀሳ እና በጤና ኤክስ ቴንሽን ባለሙያዎች አማካኝነት ወደ ተንቀሳቃሹ የህክምና ቡድን ሲመጡ ግን በጣም ያሳዝኑ እንደነበር ነው የመሰከሩት፡፡
ዶ/ር አምባዬ አሁንም ሀሳባቸው አልተቋጨም። በየቤታቸው በፊስቱላ ህመም ተጎድተው ተደብቀው ያሉ ሴቶች ብዙ ናቸው፡፡ ህመማቸውም የከፋ ነው። ታድያ ሁልጊዜ ችግሩን ተከትሎ መሄድ ሳይሆን ተገቢው አካሄድ ችግሩን መቅደም ነው የሚሉት ዶ/ር አምባዬ በህክምናው ዘርፍ አገልግሎቱን በአለመስጠት ምክንያት በሚከሰት ውድቀት ችግሩ እንደ ሚከሰት አስባለሁ ብለዋል። ስለዚህ በጉዞ ፕሮግራማችን ወደገጠር ሄዶ ህክምናውን ሰጥቶ መመለስ ብቻውን በቂ አልሆነም፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡን ማስተማር እና ንቃተ ህሊናውን ማዳበር ሌላው ያልታየ ነገር ነበር፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ የጤና ባለሙያዎችም እንዲሳተፉ በማድረግ በሂደት የተጀመረ አሰራር ነበር፡፡ ስልጠናው ማንን ይመለከታል፤ እንዴትስ ነው ልናስተምር የምንችለው የሚለው ደረጃ በደረጃ ወደክልሎች ሄዶ ህክምናውን በሚሰጠው ቡድን ስራ ላይ ተጨማሪ በማድረግ ተነደፈ፡፡ ስለዚህም ስለፊስቱላ ህመም አመጣጥና መወሰድ ስለሚገባው እርምጃ የህብረተሰብ መሪዎችን፤ ቤተሰቦችን፤ የሀይማኖት መሪዎችን፤ ባለሙያዎችን፤ ተማሪዎችን፤ ዳይሬክተርና መምህራንን ባጠቃላይም ህብረተሰቡን ባካተተ መልኩ ስልጠናው ተነድፎ በጥሩ ሁኔታ ስራ ላይ ዋለ፡፡
ትክክለኛ የጤና ባለሙያ በአቅራቢያቸው አለመገኘት፤
የጤና ተቋሙ በተገቢው ሁኔታ አገልግሎት መስጫው ሳይኖረው ሲቀር፤
የህክምና ተቋሙ በአቅራቢያቸው እያለም ሄደው አገልግሎቱን ለማግኘት አስፈላጊ መሆኑን አለማወቃቸው፤
በመሳሰሉት ምክንያቶች ለፊስቱላ ይጋለጣሉ፡፡ ለምንድነው ወደ ህክምና አገልግሎቱ የማ ትሄዱት ሲባሉ እዚያም እዚህም ያው መውለድ መውለድ ነው የሚል መልስ ይሰጣሉ፡፡ በእርግጥ መውለድ ተፈጥሮአዊ መራባት ነው፡፡ ልክ እንደመተንፈስ ያለ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ነው፡፡ አንዳንዶች ካለችግር ሊገላገሉ ይችላሉ፡፡ ሁልጊዜ ከመቶ ሴቶች አስራ አምስት የሚሆኑት ግን ለፊስቱላ ይጋለጣሉ፡፡
የልጁ አቀማመጥ በትክክል ላይሆን ይችላል፡፡
ወይ የልጁ አመጣጥ መጥፎ ሊሆን ይችላል፡፡
ወይንም እርጉዝዋ ሴት የማህጸን ጥበት ሊኖራት ይችላል፡፡
ወይም የልጁ ክብደት ከልክ በላይ ሊሆን ይችላል፡፡… ወዘተ
ስለዚህ ፊስቱላ የሚመጣው በልጅነት በመዳር ነው የሚለውን ድምዳሜ የሚያስቀሩ ሌሎች ብዙ ችግሮች መኖራቸውን የምናይበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ስለዚህ እንደዚህ ያለ ችግር የገጠማቸውን ሴቶች አስፈላጊውን ሕክምና ለመስጠት የተሟላ የጤና ተቋም እና በሙያው ብቁ የሆነ የህክምና ባለሙያ ሊያገኛቸው ይገባል፡፡ ይህም በተናጠል ሳይሆን የሚመለከታቸው ተቋማት በጋራ ተቀናጅተው ሊሰሩት የሚገባ ነው፡፡
በገጠር ያሉ ሴት ልጆች ብዙውን ጊዜ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ይስተዋልባቸዋል። በዚህም የተነሳ ሰውነታቸው በተለይም ማህጸናቸው ጠባብና ቀጭን ይሆናሉ፡፡
በገጠር ያሉ ሴት ልጆች የትምህርት እድሉን በተገቢው ሁኔታ አያገኙም፡፡ ቢያገኙም እንኩዋን ከቤት ውስጥ በሚኖርባቸው ተጽእኖ የተነሳ በተገቢው ሁኔታ እውቀቱን ይገበያሉ ማለት አይቻልም፡፡
ሴት ልጅ ተሰሚነት የላትም፡፡ እኔ መውለድ የምፈልገው በሆስፒታል ሄጄ ነው ብትልም የሚሰማት የለም፡፡
ስለዚህ ማህበረሰቡን የማሰልጠን የማንቃት ነገር እነዚህን ነጥቦችን በግልጽ እንዲረዱና ለተግባራዊነቱ እራሳቸውን አሳምነው ሴት ልጆቻቸውን እንዲጠብቁ የሚያስችሉ ስራዎች በስፋት ተሰርቶአል፡፡ ሴት ልጆች በሚያረግዙበት ወቅት የእርግዝና ክትትል እንዲያደርጉ፤ ቤታቸው እሩቅ ከሆነ መውለጃቸው ሲደርስ ወደ ሆስፒታሎች ወይንም ጤና ተቋማት ጠጋ ብለው እንዲቀመጡ እና ምጥ ሲመጣ ቶሎ እንዲሄዱ የማድረግ፤በገንዘብም ይሁን በማጉ ዋጉዋዙ ድጋፍ የሚያደርጉ ሰዎችን አስቀድሞ ማዘጋጀት፤ክትባት ማግኘት እንዳለባቸው… ወዘተ የመሳሰሉትን  እርምጃዎች እንዲወስዱ ህብረተሰቡን የማሰልጠን ስራ ተሰርቶአል፡፡ ወደሆስፒታል ሄዳችሁ ውለዱ የሚለውን አስተያየት ብዙ ጊዜ ሲቃወሙ ይስተዋላሉ፡፡ ይሄንን ለምን እንደሆነ ስንጠይቃቸው እኛ በበቤታችን ብንወልድ ይሻለናል፡፡ ከዚያ ወልደን ምን ልንበላ ነው የሚለው ደግሞ ሌላው ጉዳይ ነበር ዶ/ር አምባዬ እንደሚሉት፡፡ ይሄንን ነገር ለመፍታት መነጋገር ግድ ነበር፡፡ በመውለድ ጊዜ የሚመገቡትን ምግብ ፤ማብሰያ እቃዎችንና ማገዶውን ጭምር ይዘው ወደ ሆስፒታሉ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ በወሊድ ጊዜ የሚበሉትን የገንፎ እህል፤አጥሚት ዱቄቱን ከየቤታቸው ዘይቱን ቅቤውን በርበሬውን የመሳሰለውን ሁሉ አዋጥተው በሚወልዱበት ጊዜ አንዱዋ ለአንዱዋ እየሰራች እንዲረዳዱ ማድረግ በስፋት የተሰራበት ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ፊስቱላ ሕክምናው የሚሰጠው በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በጅማ፤በጎንደር፤ በአሰላ ሆስፒሎች ጋር (ሆፕ ኦፍ ላይት ያቋቋማቸው) ሲሆን በሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ስር ደግሞ መቀሌ፤ ሐረር፤ ይርጋለም፤ ባህርዳር እና መቱ ሆስፒታች ጋር እየተሰራ ነው፡፡
ፊስቱላ በሰብ ሰሃራን አፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ የታወቀ በሽታ በመሆኑ ዶ/ር አምባዬም ከኢትየጵያ ውጭ ስልጠናና ሕክምናውን በኬንያ፤ ታንዛንያ፤ ኡጋንዳ፤ ማሊ፤ ጊኒ፤ ቻድ፤ ዚምባቡዌ እና ሌሎችም ሀገራት መስጠታቸውን ለአብነት አስታውሰዋል፡፡   
ፊስቱላ በእርግጥ እንደቀድሞው ነው ባይባልም ነገር ግን አሁንም ስራ ይፈልጋል እንደ ዶክ ተር አምባዬ እምነት፡፡ ዶ/ር አምባዬ ወ/ሚካኤል የጽንስና ማህጸን ህክምና እስፔሻሊስትና የፊስቱል ቀዶ ሕክምና ባለሙያ በስተመጨረሻው ሴቶቹ ከቤተሰብም ይሁን ከአገልግሎት ሰጪዎቹ ባጠቃላይ ከሁሉም አቅጣጫ የሚደርስባቸ ውን ችግር በቃን ማለት አለባቸው… ብለዋል፡፡ እሳቸውም የሴቶቹን ሕይወት እንዲቀጥል በማስቻላቸው እድለኛ ነኝ ብለዋል፡፡ 

Read 612 times