Sunday, 27 August 2023 19:47

ከ85 ዓመታት አገልግሎት የቅርቡን ዘመናት የሚያሳዩ 12 ታሪኮች

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

“‹‹ሸንጎ›› በሚል ርዕስ ለግቢው ማኅበረሰብ እንዲቀርብ ታስቦ የተዘጋጀው የመድረክ ቴአትር ጠቀሜታው የጎላ ሆኖ በመገኘቱ፣ ከአማኑኤል ሆስፒታል ውጪ ለሚገኘው የሕብረተሰብ ክፍልም ማድረስ ስለሚቻልበት ሁኔታ ምክክር ተደርጎ እቅድ ተነደፈ፡፡ እቅዱም ከሆስፒታሉ ግቢ ወጥቶ ጤና ሚኒስቴር ደረሰ፡፡--”


ወ/ሮ ጆዘሊን የኮንጎ ብራዛቪል ነዋሪ ነበሩ። በሀገራቸው በተከሰተ የእርስ በእርስ ግጭት ባለቤትና ሴት ልጃቸውን በሞት ካጡ፣ ንብረታቸው ከወደመ፣ ብዙ ሰቅጣጭ ነገሮችን ካዩ በኋላ፣ ከወንድ ልጃቸው ጋር በመጀመሪያ ወደ ኬኒያ፣ በመቀጠል ወደ ኢትዮጵያ በስደት መጡ፡፡ በተፈጥሯቸው ‹‹ሳቂታና ተጫዋች›› የነበሩት ወይዘሮ፤ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ቢሆኑም፤ በሀገራቸው የተከሰተው ግጭት ባሳደረባቸው ድንጋጤና በሞት ለተለዩዋቸው ወገኖቻቸው ሀዘናቸውን የሚገልጹበት መድረክ ስላጡ፣ በየዕለቱ ከዓይኖቻቸው ከሚወርደው ዕንባ በስተቀር ‹‹ምንም መናገር›› አለመፈለጋቸውን ያዩ የስደተኞች ጣቢያ ክሊኒክ ባለሙያዎች ሪፈር ጽፈው፣ ወደ አማኑኤል ሆስፒታል ላኳቸው፡፡
ይህ ታሪክ ዶ/ር ዮናስ ላቀው ‹‹የአማኑኤል ሆስፒታል ታሪኮች›› በሚል ርዕስ ካሳተሙት መጽሐፍ የተወሰደ ነው፡፡ በ177 ገጾች የቀረበው መጽሐፉ፤ ይህንንና መሰል 12 አጫጭር ታሪኮችን ይዟል፡፡ ደራሲው ስለ ታሪክና ባለታሪኮቹ በምስጋና ገጻቸው፤ ‹‹በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረቱ ይሁኑ እንጂ የተጠቀሱት የታካሚ ገጸ ባሕሪያት ልብ ወለዳዊ ናቸው›› ብለዋል፡፡
‹‹ስለ አማኑኤል ሆስፒታል የሚነገሩ ታሪኮች አንዳንዶቹ የተሳሳቱ ብዙዎቹ ደግሞ የተጋነኑ ናቸው›› የሚሉት ዶ/ር ዮናስ ላቀው፤ ልቦለዳዊ የሆኑ ባለታሪኮችን በማሳያነት አቅርበው ማስተላለፍ የፈለጉት አንኳር መልዕክት፤ ተገቢ ሕክምናና ክትትል ካገኘ የአእምሮ ሕመም  ሊድን የሚችል የጤና ችግር ነው የሚል ነው፡፡ ከላይ በማሳያነት የቀረቡት ወ/ሮ ጆዘሊን፤ የሕክምና አገልግሎት ካገኙ በኋላ ከሌላው ጋር መግባባት ብቻ ሳይሆን፣ ስሜትና ፍላጎታቸውን በሚገባ የሚገልጹ ሆነው፣ ‹‹ሳቅና ተጫዋችነታቸው›› ተመልሶላቸው ከሆስፒታል ስለመውጣታቸው እናነባለን፡፡
እንደማንኛውም የጤና ችግር የአእምሮ ሕመምም፣ በሕክምና የመዳን ተስፋ እንዳለው ማሳየትን ዓላማ አድርገው መጽሐፉን ያሰናዱ የሚመስሉት ዶ/ር ዮናስ ላቀው፤ በዘርፉ ያለውንም ችግር ከተለያዩ ባለታሪኮች ጋር እያያያዙ ለማመልከት ጥረት አድርገዋል። የአእምሮ ሕመም የገጠመውን ሰው ወደ ሆስፒታል መውሰዱ ከባድ፣ አስቸጋሪና ጥንቃቄ የሚፈልግ ተግባር ስለመሆኑ በ‹‹ሰርጉ›› ታሪክ ቀርቧል፡፡
ከአእምሮ ሕመም ጋር በተያያዘ ቤት ውስጥ ታስረው እንዲቀመጡ የሚደረጉ ታማሚዎች ለተጨማሪ የአካል ጉዳት (ሽባ መሆን) እንደሚዳረጉ በ‹‹መምጣት አይችልም›› ተተርኳል፡፡
የትራንስፖርት ችግርና ድንገተኛ የመኪና አደጋ ታማሚን፣ አስታማሚንና የሕክምና ባለሙያዎችን እንዴት ባለ ሁኔታ ለጉዳት እንደሚዳርግ፤ ከገጠር ወደ አዲስ አበባ ለሕክምና የሚመጡ ሰዎች ‹‹የቁጭ በሉዎች›› ሰለባ ስለመሆናቸው በ‹‹ሳሚ››፣ በ‹‹አማኑኤል ሆስፒታል ምን ያህል ይርቃል?›› እና በ‹‹ሱስ›› ታሪኮች በሚገባ ማሳየት ተችሏል፡፡ በመድሐኒት ‹‹ሱስ›› ምክንያት ለሕልፈተ ሕይወት የተዳገረው ባለታሪክ (ዶክተር)፤ ‹‹ውሃ እያሳሳቀ ይወስዳል›› ብሂልን የሚያስታውስ ነው፡፡
ዳያስፖራዎች በሀገር ቤት የሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው በሞት ሲለዩዋቸው በቅርብ ሆነው ሀዘናቸውን ባለመግለጻቸው ምክንያት በውስጣቸው ያልወጣ የተዳፈነ ስሜት ያለባቸው፤ የ‹‹ሶሻል ፎቢያ ወይም ማህበራዊ ፍርሐት›› ተጠቂዎች ከፍተኛ በሆነ የስነ ልቦና ጉዳት ላይ እንደሚወድቁ በ‹‹የሁለት ሀዘን ወግ››፣ በ‹‹የአይናፋርነት እዳ››፣ በ‹‹ጤንነቴን ያያችሁ አላየንም ባካችሁ›› እና በ‹‹እሾህን በጦር›› ባለታሪኮች በማሳያነት ቀርበዋል፡፡
ለሕክምና ሆስፒታል ገብቶ በዚያ አጋጣሚ የጀመረው ስውር የሲጋራ ንግድ ትርፍ ጥሞት ከሆስፒታል ‹‹አልወጣም›› ብሎ ያስቸገረው ባለታሪክ፤ የአእምሮ ሕክምና ችግር ዘርፈ ብዙ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ‹‹የተጨናገፈ ጽንስ›› በሚል ርዕስ በመጽሐፉ የተካተተው 12ኛ ታሪክ፣ የአእምሮ ሕክምናን ያሻሽላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ትልቅ እቅድ እንዴት እንደከሸፈ ያስቃኛል፡፡
በ15 ገጾች በቀረበው በዚህ ታሪክ፤‹‹በንባብ፣ በስፖርት፣ በቴአትር፣ በሙዚቃ፣ በስዕል … ስለሚሰጥ ሕክምና ነው›› የሚገለጸው፡፡ ታካሚዎችና ሐኪሞችን ጨምሮ በአማኑኤል ሆስታል ውስጥ የሚገኙና የጥበብ ፍቅርና ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ተሰባስበው በፈጠሩት የኪነ ጥበብ መድረክ፣ የግጥም ንባብና መሰል አዝናኝና አስተማሪ ዝግጅት በተከታታይ በመካሄድ ላይ እያለ፤ ለሕክምናና መሰል የተለያየ ጉዳይ ወደ አማኑኤል ሆስፒታል የመጡ አርቲስቶች ጅምሩን ለማሳደግ ቃል ገብተው አብረው መስራት ይጀምራሉ፡፡
‹‹ሸንጎ›› በሚል ርዕስ ለግቢው ማኅበረሰብ እንዲቀርብ ታስቦ የተዘጋጀው የመድረክ ቴአትር ጠቀሜታው የጎላ ሆኖ በመገኘቱ፣ ከአማኑኤል ሆስፒታል ውጪ ለሚገኘው የሕብረተሰብ ክፍልም ማድረስ ስለሚቻልበት ሁኔታ ምክክር ተደርጎ እቅድ ተነደፈ፡፡ እቅዱም ከሆስፒታሉ ግቢ ወጥቶ ጤና ሚኒስቴር ደረሰ፡፡
ፕሮጀክቱ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ተቀባይነትና ድጋፍ ስላገኘ፣ የቴአትር ቡድኑ በክልሎች ተንቀሳቅሶ ለሕዝብ እንዲቀርብ ተወስኖ ተግባራዊ ሆነ፡፡ ከዚያ ጎን ለጎንም በየጎዳናው የሚገኙ የአእምሮ ሕመምተኞችን ለመርዳት ታስቦ ተስፋ የሚሰጥ ነገር ተሰራ፡፡ ‹‹በደብረ ብርሃን፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ መቀሌ፣ ሽሬ፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ›› ድረስ ተንቀሳቅሰው፣ ሕብረተሰቡ ስለአእምሮ ሕመም ጤናማ ግንዛቤ እንዲኖረው አደረጉ፡፡
(ዶ/ር ያናስ ላቀው የመጽሐፋቸው አካል ባያደርጉትም፤ ይህ ታሪካዊ ስራ በተጀመረበት ወቅት፤ ‹‹አርት ቴራፒ›› በስዕል ዘርፍም በአማኑኤል ሆስፒታል በስፋት መስጠት ተጀምሮ ነበር፡፡ በሆስፒታሉ አልጋ ይዘው የአእምሮ ሕክምና ይከታተሉ የነበሩ ታማሚዎች የሰሯቸው ስዕሎች፣ በሒልተን ሆቴል ለሕዝብ እይታ የቀረበበት ጊዜ እንደነበር አስታውሳለሁ።)  
‹‹ሸንጎ›› ቴአትር  ከቦታ ወደ ቦታ ተንቀሳቅሶ ለሕዝብ በማቅረብ የተገኘውን ለውጥና ተስፋ ለማሳደግ ሰፊ ውይይትና ምክክር ከተደረገ በኋላ ቀጣይ እቅድና መርሐ ግብር ተነድፎ፣ ‹‹የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ በማጥናት በሀገራችን የአእምሮ ጤና ኢንስቲትዩት ስለማቋቋም››ም  ታሰበ፡፡ ለዚህም ተግባራዊነት በአዲስ አበባ ኮተቤ አካባቢ፣ ‹‹ለአእምሮ ሕክምና እንዲሁም ለአእምሮ ጤና ኢንስቲትዩት የሚሆን ባለ ሰባት ፎቅ ሕንፃ›› ግንባታ ተጀመረ፡፡ ሕንፃው ሲጠናቀቅ ግን ባልታወቀ ምክንያት አጠቃላይ ሆስፒታል ሆኖ አገልግሎት መስጫ እንዲሆን ተደረገ፡፡
በመጽሐፉ ከተጠረዙ 12 ታሪኮች በተለየ መልኩ የአንድ ታሪካዊ ሂደት ‹‹ክሽፈት›› የቀረበበት ‹‹የተጨናገፈው ጽንስ›› ታሪክ፣ በማጠቃለያው የአእምሮ ሕክምና ትኩረት እንዲሰጠው ጩኸታችንን ማሰማት እንቀጥላለን ብሎ ሲያጠቃልል፤ ‹‹ከሀገራችን ሕዝብ ሀያ ሰባት ከመቶ የአእምሮ ሕመም ያጋጥመዋል ሲባል፣ የሆነ ቦታ ያሉ ሀያ ሰባት ሰዎች ማለት አይደለም፡፡ ሁላችንም ቤት አለ ማለት ነው፡፡ የመርሳት ህመም ያለባት እናት፣ ኦቲዝም ያለበት ልጅ፣ ሱስ ውስጥ ያለ ወንድም፣ በጭንቀት የምትቸገር እህት … ማለት ነው፡፡ ቅንነት ካለ እናታችን፣ ልጃችን፣ ወንድማችንና እህታችን የተሻለ የአእምሮ ህክምና የሚያገኙበት ተቋም መፍጠር ይቻላል፡፡››
የዶ/ር ዮናስ ላቀው መልዕክትና ጥሪ ቸል የሚባል አለመሆኑ ከላይ የቀረበው የወ/ሮ ጆዘሊን ታሪክ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ከእርስ በእርስ ግጭት ጋር በተያያዘ፣ የኮንጎ ብራዛቪሏ ወይዘሮ የገጠማቸውን የሚመስል ችግር በሀገራችን ኢትዮጵያም በተደጋጋሚ ተከስቷል፡፡ ከእርስ በእርስ ጦርነትና መገዳደል ጋር በተያያዘ፤ 1970 ዓ.ምን መነሻ ብናደርግ እንኳን፤ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ጥለው መሰደድ ከጀመሩ ግማሽ ክፍለ ዘመን ሊያስቆጥር ጥቂት ዓመታት ናቸው የቀሩት፡፡
በአዲስ አበባ መሳለሚያ አካባቢ የሚገኘው አማኑኤል የእእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አመሠራረት ታሪክም፣ ከጦርነት ጋር በተያያዘ፣ ለአእምሮ ሕመም የተዳረጉ ሰዎች ማቆያ እንዲሆን ታስቦ ነበር፡፡ በፋሽስት ጣሊያን ወረር ዘመን፣ በአዲስ አበባ ከተማ በተፈጠረ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያው መመሰቃቀል ምክንያት፣ የአእምሮ ሕመምተኞች ቁጥር ተበራክቶ በየአደባባዩ ስለታየ፣ የፋሽስት ጣሊያን ባለስልጣናት በ1929 ዓ.ም አማኑኤል ሆስፒታልን አቋቋሙ፡፡ ያ ዘመን በሦስት ቀናት 30 ሺህ ኢትዮጵያውያን የተጨፈጨፉበት የየካቲት 12 አሳዛኝ ክስተት የተፈጠረበት እንደነበር ይታወቃል፡፡
85 ዓመታት ያስቆጠረው አማኑኤል የእእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ በጳውሎስና መሰል የመንግስትና የግል ተቋማት በዘርፉ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ በየፀበሉ፣ በየጸሎት ቤቶችና ባህላዊ የሃይማኖት ስርዓት በሚፈጸምባቸው ስፍራዎችም ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ የአእምሮ ህመምተኞች ‹‹መዳንን›› ፈልገው ለዓመታት ሲንከራተቱ ማየት፣ ለብዙዎቻችን አዲስ መረጃ አይደለም፡፡
በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ለአእምሮ ጤና ችግር መስፋፋት የእርስ በእርስ ጦርነቶችና መገዳደል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስለማድረጋቸው የሕክምና ባለሙያዎች፣ በየመገናኛ ብዙኃኑ እየቀረቡ በተደጋጋሚ ገለጻና ማብራሪያ ሲሰጡበት ሰምተናል፡፡ ዶ/ር ዮናስ ላቀው በመጽሐፋቸው፣ ሃያ ሰባት ከመቶ (27%) ደርሷል ያሉትን ቁጥር እስከ አርባ አምስት (45%) ከመቶ የሚያደርሱትም አሉ፡፡ እንዲህ በፍጥነት እያደገ ለመጣ ችግር፣ ምንጩን ማድረቂያው ዘዴ መቀየስ የተሻለ ነው የሚሆነው፡፡ የአእምሮ ጤና ኢንስቲትዩት የማቋቋሙ እቅድ ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ፣ ለዚህ አስተዋጽኦ ያደርግ ነበር፡፡ ለቆዳ፣ ለእንጨት፣ ለሆቴል … ኢንዱስትሪዎች ማደግና መስፋፋት በርካታ ተቋማት ባሉት ሀገር፣ የአእምሮ ጤና ኢንስቲትዩት የማቋቋም እቅድ እውን እንዳይሆን የተደረገበት ምክንያት አነጋጋሪ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡-   This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 356 times