Saturday, 26 August 2023 00:00

“መንግስት በፌደሬሽኑ የቴክኒክ ጉዳይ ጣልቃ አይገባም”

Written by  ግሩም ሠይፉ (ከቡዳፔስት፤ ሃንጋሪ)
Rate this item
(0 votes)

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር መስፍን ቸርነት  በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ቡዳፔስት ገብተዋል። አምባሳደሩ ቡዳፔስት የገቡት 19ኛውን የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመታደም  ሲሆን፤ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ግሩም ሰይፉ አምባሳደሩን የኢትዮጵያ ቡድን ባረፈበት ፓርክ ኢን ራዲሰን ሆቴል አግኝቶ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡


አትሌት ጥላሁን ሃይሌ ከወንዶች 5ሺ ሜትር ውድድር ተቀንሶ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ላይ ያሰማው ቅሬታ አነጋጋሪ ሆኗል።  የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ  ከሰጠው ምላሽ በኋላ ነው ለዚህ ቃለምምልስ የተገናኘነው፡፡ ቅሬታው በአትሌቶችና በፌደሬሽኑ መካከል አለመተማመን መፈጠሩን  ያሳያል፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?  
ሲጀምር ይሄ ተግባር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሃላፊነት ነው። ከዚያ በመቀጠልም በዝርዝር ካየኸው የዓለም ሻምፒዮናውን በአጠቃላይ የሚመራው የልዑካን ቡድኑና የፌደሬሽኑ ቴክኒክ ኮሚቴ ነው። ከዚህ አንፃር ነው የምመለከተው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአትሌቶችና በአሰልጣኞች መካከል የተለየ አለመግባባት አለ የሚለውን  ነገር በዚያ ደረጃ አላየውም፡፡ እንደምታውቀው እንኳን በአትሌቲክስና በእግር ኳስም ብትሄድ  ምርጥ 11 ተጨዋቾችና ተቀያሪዎቹን ለይቶ የመምረጥ ሃላፊነት ያለው አሰልጣኙ ላይ ነው፡፡ ምን መሰራት እንዳለበት፣ ቡድኑ መቼ እንደሚያጠቃ፣ መቼ እንደሚከላከል ... ምን ውጤት አስጠብቆ መሄድ እንዳለበት  ውሳኔ የመስጠቱ ሃላፊነት በከፍተኛ ደረጃ የአሰልጣኙ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ተመልካቹም መንግስትም ራሱ  ተወዳዳሪው  ተጨዋቹም ቢሆን ለአሰልጣኙ ህግ መገዛት ይኖርበታል፡፡ ስለዚህም በአትሌቲክስ ውስጥም ይህ ነው የሚሆነው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን እስካሁን ያለውን ውጤት በማየት ማን ከማን ይሻላል፤  ማን የኢትዮጵያን ውጤት ያስጠብቃል ብሎ የሚሄድበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ አሁን ሁላችንም እንደምናውቀው የዓለም ህዝብም ሆነ የኢትዮጵያ ትኩረትም፣ የዓለም ሻምፒዮናው ነው፡፡ ስለዚህም ከዓለም ሻምፒዮናው ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ምን ያህል ሜዳልያዎችን ታገኛለች፣ የአምናውን ውጤት ታስጠብቃለች ወይ፣ አምና ያገኘችውን ክብር መድገም ትችላለች ወይ አትሌቶችስ በዚያ ብቃት የሚገኙ ናቸው… የሚሉት ጥያቄዎች የሚታዩ ናቸው። የተወዳደርንባቸውን የውድድር አይነቶች፣ የተወዳደርንበትን   አገር የአየር ፀባይ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህንን ውጤት ማስጠበቅ እንችላለን ወይ ነው ጥያቄው፡፡ በአጠቃላይ ጉዳዩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስስ ፌደሬሽን የስራ አስፈፃሚ አባልና የዚህ የዓለም ሻምፒዮናን ልዑካን፤ የሚመራውና የቴክኒክ ኮሚቴው ሃላፊነት ነው፡፡ እናም ከዚህ አንፃር አይተው በ5ሺ ሜትር ወንዶች ያለውን አሰላለፋችን በዚህ በዚህ መልክ ይሻላል ብለው አቅርበዋል፡፡ ይሄ ትክክለኛ አሰራር ነው፡፡ ማንም ሰው በአትሌቲክስ ፌደሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሃላፊነት በቴክኒክ ስራ ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ እኔ በሚኒስቴር መስርያ ቤቱ በተሰጠኝ ሃላፊነት እንደዚያ አላደረግኩም፡፡ ምክንያቱም አሰራሩን ጠብቆ መሄድ ያለበት ጉዳይ ስለሆነ ነው። እንደ ሚኒስቴር መስርያ ቤት የምንጠይቅ ከሆነ የምንጠይቀው፣ የነደፋችሁት ስትራቴጂ ውጤታማ ነበር? አሳካታችኋል ወይ? አልተሳሳታችሁም ብለን ወደኋላ ላይ የምናነሳው እንጅ ሌላ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ከዚያም አልፎ ቡዳፔስት ከመጣሁ በኋላ አትሌት ጥላሁንን በግንባር አግኝቼው ሃሳብ ሲሰጠኝ በተለይ ከቴክኒክ ኮሚቴውና ከአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባላት ጋር ውይይቶች አድርገናል፡፡ ስለዚህም በትክክለኛው ሁኔታ በ5ሺ ሜትር ወንዶች ለማሸነፍ የሚያስችላቸውን ታክቲካዊ እቅድ እንዳዩ ነው የተረዳሁት፡፡ ለታክቲኩ ማነው የሚመጥነው? በዚህ ከፍተኛ ሙቀት ላይ ጫናውን ተቋቁሞ ለምዶ ከተወዳዳሪ አገሮች እንደ ኬንያ ኖርዌይና አሜሪካን ጨምሮ ሌሎችም ያቀረቧቸውን አትሌቶች ተወዳድሮ ማጣርያውን በማለፍ ወደ ፍፃሜው በመግባት ውጤት ሊያስመዘግብ የሚችለው ማነው?  የሚለው ነገር የማበላለጥና የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ አጠቃላይ ውሳኔው አትሌት ጥላሁንን ከመጥላትና ከግል ጉዳይ ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ ማንም የቡድን መሪ ለማሸነፍ የሚፈልገውን ታክቲክ ይከተላል፡፡ የፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚም ይህንን ነው ያደረገው። ችግሮች እንኳን ቢኖሩም እንደ ሚኒስቴር መስርያ ቤት ያለውን የቡድን መንፈስ አጠናክረን፤ ተረባርበን ውጤት  አስጠብቀን መሄድ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ችግሮች ካሉ በቅርበት መነጋገር ነው መፍትሄው፡፡
አትሌት ጥላሁን  በመጀመርያ ቅሬታውን የገለፀለት ባለስልጣን እርስዎ እንደሆኑ ነው የገለጸው። መፍትሄ ብለው ያቀረቡትን ሃሳብ ሲገልጹለት ምን አለ?
መታወቅ ያለበት ጥላሁንም ሆነ ማንም አትሌት በዓለም ሻምፒዮና አገሩን ወክሎ የመሳተፍ ፍላጎት አለው፡፡ ጥላሁንም ካምፕ ገብቶ ከቡድኑ ጋር በተሟላ ዲስፕሊን ሲዘጋጅ ነው የቆየው፡፡ ከዚህ የተነሳ ቅሬታ ተሰምቶታል፡፡ ለምን ቅሬታውን ገለፀ ሊባልም አይችልም። ማናቸውም አትሌቶች የልፋታቸው ውጤት አድርገው የሚያዩት የዓለም ሻምፒዮናውን ተሳትፎና ልዩ ስኬት ማስመዝገብ ነው። ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን መሳተፍም ይፈልጋሉ ።ከዚህ የተነሳ ነው የጥላሁን ቅሬታ የተነሳው እኔም ቡዳፔስት እንደገባሁኝ ይህን ገልፆልኛል፡፡ መንግስት በፌደሬሽኑ የቴክኒክ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አይገባም። ይህን ካደረግን ብዙ ነገር ይበላሻል፡፡ የቴክኒክ ጉዳዩን ለቴክኒክ ሰዎች መተው አለብን፡፡ምንድነው የተፈጠረው ብለን ግን የቡድኑ መንፈስ እንዳይጎዳና ቀሪዎቹ አትሌቶች ላይ ጫና እንዳይፈጠር አንዳንድ ሃሳቦችን ከአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጋር አውርተናል፡፡ ጠይቄ እንደተረዳሁት ውሳኔው የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር የአሸናፊነት ደረጃውን  ለማስቀጠል የተፈጠረ ታክቲክ እንህዘጅ ከጥላቻና ከተለየ የሴራ ፖለቲካ ጋር እንደማይገናኝ ነው፡ ለጥላሁን ያልኩትም ይህንን ነው፡፡ ጥላሁን ኢትዮጵያዊ ነው፤ እንደሌሎች ውጤታማ አትሌት ነው። አሁን ላለው ስትራቴጂ ግን አልሆነም። “ስለዚህም አሰልጣኞች ያቀረቡትን ነገር መረዳትና መቀበል አለብህ፤ በአንተ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ውጤት ከተመዘገበ እንደ ራስህ ውጤት መውሰድ አለብህ፡ የኢትዮጵያን ክብርና ከፍታ ማስቀደም አለብህ” ብዬ እንደ ታላቅም እንደ አመራርም ያለውን ነገር  አስረድቸዋለሁ። በርግጥ መጀመርያ ላይ መበሳጨት ማልቀስና ስሜት ውስጥ የመግባት ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ እያደረ እየቆየ ነገሩን ሊረዳ ይችላል ብዬ ስለማምን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም መረዳት ያለበት ይሄን ነው፡፡ የልዑካን ቡድኑም ማወቅ ያለበት ይሄን ነው፡፡ እዚህ ጋ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ለማስጠበቅ የሚያስችል ስትራቴጂ እስከሆነ ድረስ ሃላፊነት ወስዶ መፈፀም ያለበት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ነው፡፡
በአጠቃላይ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው የኢትዮጵያን ተሳትፎ አስመልክቶ የሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ያደረገውን አስተዋፅኦ እንዴት ይገለፁታል?
ወደ ቡዳፔሰት የመጣነው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ሲጋመስ ነው፡፡ ሚኒስቴር መስርያ ቤታችን  በአትሌቶች ዝግጅት ላይ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጋር በቅርበት ሲሰራ ነበር፡፡ ያው እንደሚታወቀው የመንግስት ሃላፊነት አትሌቶችን ማበረታታት፤ የፌደሬሽኑን የስራ እንቅስቃሴና እቅድ አፈፃፀም መከታተልና ግብረመልስ መስጠት ነው። ከዚያም አልፎ ደግሞ ለስራው የሚያስፈልጉ ድጋፎችን ማድረግ ነው፡፡  በቅድሚያ ለዓለም ሻምፒዮናው የሚደረገውን ዝግጅት ለመደገፍ ከአትሌቲክስ ፌደሬሽን  በጋራ ስንሰራ ዝግጅቱን በቅርበት እየተገኘን ታዝበናል። በየደረጃው በሪፖርት ላይ የምናየውን ስራ በሜዳ ላይ በተግባር እየተፈፀመ መሆኑን በመከታተል ሰርተናል፡፡ አጠቃላይ የዓለም ሻምፒዮናውን ቡድን ዝግጅት ሁለቴም ሶስቴም በአካል ተገኝተን አይተናል፡፡  አትሌቶቹ ዝግጅቶቻቸውን ሲያጠናቅቁ ከቀድሞ አትሌቶች ጋር ልምድ የሚለዋወጡበትን መድረክ አዘጋጅተናል። ኢትዮጵያ በጣም ታዋቂ ስማቸው ጣራ የነኩ፣ የዓለም ሻምፒዮናና ኦሎምፒክን የተቆጣጠሩ አትሌቶች አገር ናት፡፡ በእኛ እምነት  በነባሩና በአዲሱ ትውልድ መካከል የነበረውን ግንኙነት በማጠናከር ልምድ መካፈል እንዲኖርና መስተጋብር እንዲፈጠር የሚያደርጉ የምክክር መድረኮችን ፈጥረናል። በመጨረሻም ከፌደሬሽኑ ጋር በመሆን እንደ መንግስት የክብር አሸኛኘት አድርገናል፡፡ በአጠቃላይ በዓለም ሻምፒዮናው ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲከስ በውጤታማነት እንዲቀጥል ነው የሰራነው፡፡  የበጀት ድጋፍን በተመለከተ የመንግስት አቅም ውስን ቢሆን  ፌደሬሽኑ የጠየቀውን የስራ ማስኬጃ ገንዘብ ለሚፈልጉት ስራ እንዲያውሉ ድጋፍ አድርጓል። አትሌቶቹ በድል ወደ አገራቸው ሲመለሱ ደግሞ  መንግስታዊ የክብር አቀባበል  ስራዎች ይከናወናሉ። እስካሁን የተመዘገቡ ውጤቶች ጥሩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በታላላቅ ውድድሮች  የምትታወቅበት ውጤትን አጠናቅቀን ስንመለስ ምን አይነት አቀባበል ሊኖር ይገባል በሚል እየተነጋገርን ነው፡፡ በአጠቃላይ እነዚህን ተግባራት በሃላፊነት ስናከናውን ቆይተናል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶች የብሄራዊ ኩራት ምሳሌ ናቸው። የአገር ገፅታ በመገንባት ረገድ ወሳኝ አካል ሆነው ይታያሉ፡፡ የአገሪቱን የገፅታ ግንባታ በአትሌቶቻችን አማካኝነት እንዲከናወን የስፖርት ዲፕሎማሲ በጠነከረ ሁኔታ እንዲካሄድ ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው፡፡ ከአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ጋርም በቅርበት እየሰራን ነው፡፡
ከቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮና ጋር በተያያዘ ከተነሱ አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ዋንኛው ከአትሌቲክስ የስፖርት መሰረተልማቶች አለመመሟላት ጋር የተያያዘ ነው። አትሌቶች ለስልጠና የሚያመቻቸው በቂ ትራኮች የሏቸውም፤ ለዓለም አቀፍ ውድድር የሚሆኑ የልምምድ ካምፖችና ማዕከሎችም የሉም። ለዚህ ሻምፒዮና የመሰረተልማት ችግሩ የተቀረፈ ባይሆንም በቀጣይ  ምን ታስቧል?
የኢትዮጵያ ስፖርት ልማቶችን ማነቆ አድርገው ከያዙት ሁኔታዎች አንዱ የስፖርት ማዘውተሪያ ነው፡፡ ለአትሌቲክስ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የስፖርት መሰረተልማቶች ማለት  ይቻላል። በተለይ ደግሞ ውጤታማ የሆንበት የስፖርት የስፖርት ዘርፋችን አትሌቲክስ በቂ የሆነ  ደረጃውን  የመጠነ የስፖርት ስፍራ እንደሌለው እንደ መንግስት እናምናለን። ችግሩን ለመፍታት በመንግስት በኩል ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ በመጀመርያ መነሳት ያለበት አሁን ያለው ችግሩ ሚኒስትር መስርያ ቤት የፈጠረው አይደለም፣ ለዘመናት የቆየ ችግር ነው፡፡ በስፖርት  ልማታችን ውስጥ የስፖርት ማዘወተሪያ ወሳኝ ነው ተብሎ የተሰራበት አይደለም። ሜዳ ስንሰራ በስታንዳርድ አስበን የሰራነው ነገር የለም። አለም ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር ራሳችንን አቀራርበን እየሰራን አልነበረም፡፡  አትሌቲክሳችን የሚፈልገውን ትራክና ሌሎች የሜዳ ላይ ስፖርቶችን የምናከነውንባቸውን ልማቶች ከመስራት አንፃር ችግር ነበር፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ ሜዳ ሙሉ ለሙሉ የለም በሚለው ሃሳብ እኔ አልስማማም፡፡ ለምሳሌ የዓለም ሻምፒዮናው ዝግጅት የመንግስት ልማት በሆነው የኢትዮጵያ የስፖርት አካዳሚ ነው የተገነባው፡፡ በመንግስት በጀት  የተገነባ ነው፡፡ ወጣት አትሌቶችን የምናፈራበት  ማዕከል ነው፡፡ ከወጣቶች ስልጠና ጎን ለጎን፣ አትሌቶቻችን እንዲሰለጥኑበት ተደርጓል።  ከፊታችን ካለው የኦሎምፒክ ዝግጅት አንፃር ደግሞ የአዲስ አበባ ስታድዬምን ጨምሮ በሌሎች ትራኮች ላይ የኦሎምፒክ ቡድኑ በሚሰራበት ሁኔታ ላይ  እያቀድን ነው፡፡   አዲስ አበባ ስታድዬም በቅርቡ በአዲስ መልክ ጨረታ ወጥቶ ትራኩን የማስተካከል ስራዎች እያከናወንን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአትሌቲክስ አገርና ወጣቶች የበዙባት እንደመሆኗ የስፖርት ማዘወተሪያ ችግር በጣም ሰፊና ጥልቅ ነው፡፡ በክልልም በፌደራልም  የተጀመሩ የስፖርት  ማዘወተሪያዎች በስታድዬም ብቻ ሳይሆን በሌሎች የስፖርት መሰረተልማቶች መጠናከር አለባቸው። የአትሌቲክስ መንደሮችና ሌሎች ማሰልጠኛ ተቋማት ብዙ መስፋፋትና  መልማት ስላለባቸው በልዩ ትኩረት የምናከናውናቸው ተግባራት ይኖራሉ፡፡
በዓለም አቀፍ ውድድር በምናደርገው ተሳትፎ ዙርያ የሚነሱ ጉዳዮች አሉ፡፡ በተለይ በአሰልጣኞችና በአትሌቶች መካከል የሚፈጠረውን ውዝግብ ለማስቀረት፤ የአትሌቲክስ ቡድኖችን በመምረጥ የሚኖረውን አሰራር ለማሻሻልና ውጤታማ ዝግጅት ለማድረግ የአሰልጣኞችን የእውቀትና የትምህርት ደረጃ ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ከዓለም አቀፍ  የአትሌቲክስ እድገትና ለውጥ ጋር አገራችንን ማራመድ ወሳኝ ነው፡፡ አትሌቶች የበዙ ቢሆንም በስልጠናው፤ በዝግጅትና በውድድር ታክቲክ ክፍተቶች አሉ። ውጤቶች እየተመዘገቡ ያሉት በአትሌቶች ጥረት ይመስላል...
ድሮ የነበረውን የብሄራዊ ቡድን አሰራር ለመመለስ በሚኒስቴሩ በኩል ምን ያህል እየተሰራ ነው
በሚኒስቴር መስርያ ቤቱ በኩል የስፖርቱን ዘርፍ የአቅም ግንባታ ስራ በትኩረት እናካሂዳለን። ስለዚህም የሚያስፈልጉ አቅጣጫዎችና እቅዶች አሉ፡፡ በዚህ መሰረት በየትኛው ስፖርት ዘርፍ ላይ ነው ቁልፍ ችግሮች ያሉብን በሚል  ያሉትንም ክፍተቶች እንዴት በእውቀትና በክህሎት እንሞላለን ብለን ለውጥ ለማድረግ የራሳችንንን ጥረት እያሳየን ነው፡፡ በሌላ በኩል የአትሌቲክስ ፌደሬሽንም ለምሳሌ በዓለም  ሻምፒዮና በኦሎምፒክ ዙርያ፣ በዝግጅት ወቅት መሰራት ያለባቸው ስራዎች አሉ። ለምሳሌ  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች ተመርጠው ለብቻቸው መሆን አለባቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ  በእያንዳንዱ ርቀት የተመረጡ አትሌቶቻቸውን ይዘው የመጡት በርካታ ማናጀሮችና አሰልጣኞች ናቸው፡፡ አትሌቶችን አንድ አድርጎ በአንድ ሰንደቅ አለማ ስር ለማሰራት ነው የምንፈልገው፡፡ ስለዚህ ይህን ችግር  ለመፍታት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን መዘጋጀት አለበት። በእግር ኳስ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ እንዳለው ሁሉ  በአትሌቲክስም በየዓመቱና በየሁለት ዓመቱ ሃላፊነት የሚሰጠው የብሄራዊ ቡድን  አሰልጣኝ፣ በእያንዳንዱ ርቀቶች የተለያየ የሰው ሃይል ተቀጥሮ መስራት ይኖርበታል። ይሄን በማድረግ በአሰልጣኞች መካከል የሚኖረውን ክፍተት ለመሙላት የልምድ ልውውጥ ለማድረግና የክህሎት ሽግግር ለመፍጠር እየሰራን ነው፡፡ በስፖርት አቅም ግንባታና በስፖርት ዲፕሎማሲ መሰራት ካለባቸው ትልቅ ተግባራት ዋንኛው የአትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን የመመስረት ጉዳይ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ እንደ መፍትሄ መወሰድ ያለበት ነገር ነው፡፡ አቅም የማሳደግና አብሮ የመስራት ባህል ለመፍጠር የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ መሰየም ወሳኝ ነው፡፡ እንደ ሚኒስቴር መስርያ ቤት በዚህ ላይ በቂ ምክክር አድርገን ለመስራት ነው የምናስበው፡፡ ወደ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን ምስረታ ከቀጣዩ ኦሎምፒክ በፊት እንደምንመጣ ነው የምናስበው፡፡ በቀድሞው ፌደሬሽን  አመራርና አሁን ባለው ፌደሬሽን መካከል በቂ የስራ ርክክብ ባለመኖሩ፣  ብሄራዊ ቡድኑን በመያዝ መቀጠል የነበረበት አሰራር አልተካሄደም፡፡ የልምድ ሽግግር አልተደረገም፡፡ አዲሱ የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ሊከተለው የፈለገው ስትራቴጂም የተለየ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ይህ ስትራቴጂ አዋጭ አልሆነም። የአትሌቶችን አንድነት በመፍጠር፤ ልምድ በማሸጋገር ውጤታማ አልተሆነበትም፡፡ አሰልጣኞች በአህጕርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ባስመዘገቧቸው ውጤቶች ለብሄራዊ ቡድን ተመርጦ ከዚያ በኋላ  አትሌቶችን በዓለም አቀፍ መሰረት መልምሎ እንደ ብሄራዊ ቡድን የሚያሰለጥንብት እድል መፈጠር ይኖርበታል። ይህን ለማድረግ  ደግሞ በአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ በኩል ፍላጎትና ሃሳብ መኖሩን ተረድቻለሁ፡፡ ሊሳካ የሚችል ነው፡፡ ብሔራዊ ቡድን ይዘን አትሌቶችን የአየር ንብረት ለማላመድ ስልጠና  ለመስጠት ነው የምናስበው፡፡ አሁን ለምሳሌ የቡዳፔስት ሙቀት እስከ 34 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ነው። እኛም አገር በተመሳሳይ የሙቀት መጠን ባለበት የአየር ንብረት  ላይ ለመስራት ነበረባቸው፡፡ ይህን በሎጀስቲክ በእቅድና በበጀት አጠናክሮ ለመስራት በአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ በኩል ጥረት ያስፈልግ ነበር፡፡ በቀጣይ ለኦሎምፒክ የምንሰራበት ይሆናል፡፡ አትሌቶቻችን ጥሩ ብቃት ላይ ቢሆኑም የሙቀቱ ጉዳይ ችግር ፈጥሮባቸዋል፡፡ ችግሩ የወጭ ብቻ አይደለም፡፡ አለም አቀፍ ውድድር ሲመጣ በዶላር ወጭ አድርገን ነው የምንሰራው። በአገር ውስጥ ለዓለም አቀፍ ውድድር ዝግጅት ስናደርግ የሆቴልና ሌሎች  ወጭዎችን ለመሸፈን የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ነው መስራት ያለበት፡፡ የአቅም ችግር ካለ ለሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ጥያቄ በማቅረብ አብሮ መስራት ይቻላል፡፡ ደረጃውን የሚመጥን ዝግጅት ለማድረግ ያስፈልግናል የሚል ጥያቄ ወደ እኛ ቢሮ አልመጣም፡፡ ስራ አስፈፃሚው በአንድነት ሰርቷል፤ በአትሌቶች ምልመላና ቅድመ ዝግጅት በቂ ትኩረት በማድረግ ተንቀሳቅሷል፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከተመዘገበው ውጤት አንፃር ከሽልማት ገንዘብ ባሻገር እንደ ቅርስ ለማቆየት፤ በከፍተኛ ደረጃ ለመዘከርና የሚገባውን ክብር ለመስጠት በአትሌቶች የተሰየሙ ፓርኮች፤  ትራክ ያላቸው ስታድዬሞችና ሙዚዬሞች የሉንም፡፡ ይህን በተመለከተ ምን ያስባሉ?
ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህን ሁሉ ችግሮች  በአንድ ጊዜ መፍታት አትችልም፡፡ እንደሚታወቀው ከ1948 ጀምሮ የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም አቀፍ የውድድር በኦሎምፒክ መሳተፍ ጀምረዋል።  አትሌቶቻችን ያስመዘገቡት ውጤት በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ  ስኬት ነው፡፡ እነ አበበ ቢቂላ ማሞ ወልዴ ምሩፅ ይፍጠር እነ ኃይሌ ቀነኒሳ ታላላቅና  ዘመን የማይሽራቸው ጀግኖች ናቸው። በትውልድ ውስጥ እንደ አብሪ ኮከብ የሚታዩ አትሌቶች ያሉባት አገር ነው ያለችን፡፡ ለእነዚህ ጀግኖቻችን በቂ ስራዎች ተከናውነዋል የሚል ግምት የለኝም። የአቅምና የአስተሳሰብ ጉዳይ ነው፡፡ የመንግስት የስፖርት አደረጃጀትና የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ተጣጥመን ባለመስራታችን ነው፡፡ አገራችን ትልልቅ የስፖርት ሙዚዬሞች ሊኖሯት ይገባል፡፡ የስፖርት  ፓርኮች፤ የስፖርት ቤተመፅሃፍት ሊኖሯት ይገባል፡፡ ለአገሪቱ ትልቅ የኢኮኖሚ ምንጭ የሚሆን ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻዎች የምንፍጥርበት ነው፡፡

Read 815 times