Monday, 28 August 2023 17:33

መንግሥት ወደድነውም ጠላነውም፣ ስራውን እንዳያጎድል፣ እላፊ ሥልጣን እንዳያገኝ ማሰብ እንጀምር።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

(ለአገራዊ ምክክር የማይቀርብ ሐሳብ እነሆ።)


የምንወደው መንግሥት ሁልጊዜ ሥልጣን ይዞ በጎ ነገሮች እንደሚሰራ እናስባለን።
ስራውን ብቻ እንዲያከናውን፣ አለስራው እንዳይገባ፣ የሥልጣን ገደቡን እንዳያልፍ… ብለን አንጨነቅም።
መቆጣጠሪያ ትክክለኛ ሕግና ስርዓት ለማበጀት ለመገንባት አናስብበትም።
 የምንወደው በጎ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ ሁሉም ነገር አማን ይሆናል የሚል ነው ሐሳባችን።
እውነታው ግን ከዚህ ይለያል።
ገሚሶቹ የወደዱት መንግሥት ገሚሶቹ ላይወዱት እንደሚችሉ በእውን አላየንም ወይ?
የፓርቲዎች ፉክክርና የፖለቲካ ምርጫ ጥሩ እንደሆነ እናወራለን። ገሚሶቹ የመረጡት ፓርቲ ገሚሶቹ እንደሚቃወሙት ያጠራጥራል?
የሕዝብ ፍቅርና ስሜት ተለዋዋጭ ነው ይባላል። ምን ማለት እንደሆነ አስቡት። የደጋፊዎች ወይም የተቃዋሚዎች ቁጥር ይዋዥቃል። የድምጻቸው  ጩኸት ይቀንሳል፤ ይጨምራል ማለት ነው።
በአጭሩ ገሚሱ ሕዝብ የማይወደውና የማይመርጠው መንግስት ሁሌም ይኖራል።
“ባንወደውም ባንመርጠውም ግን፣ ከሕግና ከሥርዓት ውጭ ያሻውን ነገር መስራት፣ እንዳሰኘው በደል መፈጸም አይችልም” ብለን የምንተማመንበት፣ የሁሉንም ሰው መብት የሚያስከብር ትክክለኛ ሕግና ሥርዓት (ሥልጡን ፖለቲካ) የመገንባት ሐሳብ ላይ ተመካክረን እናውቃለን ወይ?
የመንግሥትን ሥልጣን የሚገድብና በግለሰብ ነጻነት ላይ የተመሰረተ ሥልጡን ፖለቲካ ላይ ለመነጋገር፣ ከትላንት ትረካዎች መነሻ ሐሳብ መያዝ እንችላለን። ሙሴ በዘመኑ እንደ ዋና አስተዳዳሪና እንደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ፣ እንደ ጦር አዛዥና እንደ ሃይማኖት መሪ ሁሉንም የሚጠቀልል ሥልጣን ነበረው።
ወዶ አይደለም። ገና ሕግና ሥርዓት በወጉ መሬት አልያዘም። አገርና ድንበር ገና አልተመሠረተም ነበር። ወደ ፊት ግን፣ የመንግሥት ሥልጣንና የሃይማኖት ተቋም ቀስ በቀስ በሂደት ድርሻቸው እየተለየ ለየብቻ እንደሚዋቀሩ ታይቶታል። መሆንም አለበት።
ሕዝብ ውሎ አድሮ “የሆነ ዐይነት ንጉሥ” መፈለጉ እንደማይቀር ሙሴ ገብቶታል። ለተከታዮቹም አስቀድሞ ነግሯቸዋል። ከብዙ ዓመታት በኋላ የሙሴ ሐሳብ በእውን ደርሷል።
በሳሙኤል ዘመን ላይ ሕዝብ ንጉሥ አማረው።
የእስራኤል ልጆች ከግብፅ በሙሴ መሪነት ከወጡ በኋላ ለብዙ ዓመታት ንጉሥ አልነበራቸውም። መልክና ቅርጽ የያዘ መንግሥት ገና አልተዋቀረም።
በየአጋጣሚው ጎልተውና ገንነው የሚመጡ ሰዎች የዳኝነት ሥልጣን ይይዛሉ። ወረራ ሲመጣም የውጊያ መሪ ይሆናሉ። ወይም የጦር አዛዥ መርጠው ይሾማሉ፤ የዘመቻ ትዕዛዝ ይሰጣሉ። እንደ ሳሙኤል የመሳሰሉ የሃይማኖት መሪዎች የበላይ ባለሥልጣንና ዋና ዳኛ የሚሆኑበት ጊዜም አለ።
በዕብራይስጥ “ሶፈት” በሚል ስያሜ ነው ትረካቸው የተጻፈው። ዳኞች ወይም አውራ ባለሥልጣናት የሚሉ ሁለት ትርጉሞች አሉት። በግዕዝ ‘ሰፋኒያት’ ወይም ‘መሳፍንት’ ይላቸዋል። ሁለቱንም ትርጉሞች ያካትታል። አዝማች ገዢዎች ወይም ዳኞች፣ አዝማቾች ማለት እንደሆነ የኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ይገልጻል። ንጉሦች ግን አይደሉም። ቋሚ የመንግሥት መዋቅር ወይም ቤተ መንግሥት አልነበረም።
የዛሬ 3000 ዓመት ገደማ፣ በሳሙኤል የሽምግልና ዘመን ላይ ግን የንግሥና ሐሳብ በሕዝብ ዘንድ አደረ።
ሳሙኤል እንዴት እንደሚከፋው አስቡት። በጣም ከፋው። የሳሙኤል ሥልጣን በአብዛኛው ተቀንሶ ለንጉሥ ይሆናል። ሳሙኤል የተበሳጨው ግን ‘ሥልጣን አጣለሁ’ በሚል ምክንያት ላይሆን ይችላል። ለምዕተ ዓመታት የዘለቀ ልማድና ወግ፣ እንዲህ በአንዴ ሲለወጥ ምን እንደሚመጣ ማን ያውቃል?
አንዳንዴ እጅግ አጥፊ የለውጥ ዓላማዎች እንደ መልካም ሐሳብ ተቆጥረው ሕዝብ ይዘምርላቸዋል። ክፉ የመዘዝ መዓት ያስከትላሉ።
ሌላ ጊዜ ደግሞ፣ ጠቃሚ የለውጥ ዓላማዎች ይመጣሉ። ግን ምን ዋጋ አለው? ወደ ትርምስ ያመራሉ። ለምን?
ያልተፍታታና ተከፍቶ ያልታየ ድፍን ሐሳብ ለመፈክር ይመቻል። አደባባዮችን በጩኸት ለማናጋት ይጠቅማል። ከብዙ ሐሳብ ያድናል። የሐሳብ ልዩነቶችን ያዳፍናል። ሁሉም የለውጥ ኃይሎች በሙሉ በአንድ ስሜት እንዲሰባሰቡ፣ በአንድ ጊዜ እንዲጮኹ እንፈልጋለን። እናም በመሐላቸው ክፍፍልና ልዩነት ጎልቶ እንዳታይ፣ “ዝርዝር ሐሳብ አይነሳ” እንላለን።
 ‘ለውጥ ፈላጊዎች’ በድፍን ሐሳብና በምኞት ብቻ እየተነዱ መትመም ይጀምራሉ። እየተቻኮሉ፣ ያለ ዝግጅትና ያለ ጥንቃቄ ነባሩን ለማፍረስ ይጣደፋሉ። በዘፈቀደ በጭፍን ምኞት ሲንደረደሩ ባዶ እጃቸውን ይቀራሉ፤ ወይም ገደል ይገባሉ። ምን ተሻለ?
ለድፍን ሐሳብ መፍትሔው ብጥስጣሽ ሐሳብ አይደለም።
መልካም የለውጥ ዓላማ ለፍሬ የሚበቃው፣ በጥቅልና በዝርዝር በቅጡ ከታሰበበት፣ ከዚያም ዝግጅትና ጥንቃቄ፣ ጥበብና ትጋት ካልተለየው ብቻ ነው። አድካሚና አስቸጋሪ ስራ ነው።
ሳሙኤል ደግሞ ዕድሜ ተጫጭኖታል። የለውጥ ጉዞ … መልካም ዓላማ የያዘ ቢሆንም እንኳ እጅግ ከፍተኛ ዐቅምን፣ ጥበብንና ብርታትን ይጠይቃል።
 አብዛኛው ሰው (ሕዝቡ) የለውጥ ሐሳብ ሲያድርበት፣ መልካም ተስፋ እንጂ ክፉ አደጋ አይታየውም። አያሳስበውም። የምኞትና የፈቃደኝነት ጉዳይ ብቻ ይመስለዋል። “የሥርዓት ለውጥ የሕዝብ ጥያቄ ነው” የሚል መፈክር ይፈጥራል።
ምን ዓይነት ለውጥ? የሚያጠፋ ወይስ የሚያለማ?
የትኛው የለውጥ መንገድ? በትክክለኛ መርሖች እየተናበቡ እየተከባበሩ መተባበር የሚችሉበት መንገድ?
ወይስ እንደተመቸ እንደ ሁኔታው አንዱ ሌላውን እየማገደ እሞቃለሁ ሲል አብሮ የመንደድ ሲዖል?
በሽሚያና በወከባ አንዱ ሌላውን ለማጥፋት ሲሮጥ ተያይዘው ገደል የሚገቡበት መንገድ?
እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች በለውጥ ጊዜ ሰሚ ጆሮ አያገኙም። የለውጥ ፍላጎትን ለመበረዝ፣ የለውጥ ኃይሎችን ለመከፈፋል፣ የለውጥ ግስጋሴን ለማደናቀፍ የመጡ ጥያቄዎች ናቸው ተብለው ይዳፈናሉ። ይወገዛሉ።
ደግሞም አብዛኛው ሰው (ሕዝቡ) በየተሰማራበት ሙያ በየራሱ ዕውቀት ኑሮውን ይመራል እንጂ፣ ፈላስፋ ወይም ፖለቲከኛ አይደለም።
ሕመም ከተሰማው “ለውጥ እፈልጋለሁ” ይላል።
ሕዝብ የሕክምና ባለሙያ አይደለም። ጤንነትን ይመኛል በደፈናው።
ዝርዝሩን እና መንገዱን ሐኪሞች ያውቁታል ብሎ ይጠብቃል።
እናም  ብዙ ሰው (ሕዝብ ተሰብስቦ) ምኞቱን ተናገረ።
የሥርዓት ለውጥ የሕዝብ ጥያቄ ሆነ።
ንጉሥ እንፈልጋለን አለ። ቀላል ስራ መስሏቸዋል። ምን ጨነቃቸው! እንዲያውም ከችግርና ከጭንቀት የሚያድን ቀላል መፍትሔ እንደሚሆንላቸው ያምናሉ።
ንጉሥ መፈለጋቸው ጭንቀታቸውን እንዲሸከምላቸው፣ ከሐሳብ እንዲገላግላቸው ነው። የሚወዱት በጎ ንጉሥ ስልጣን ከያዘ… ሁሉም ነገር ይሳካል ብለው ያስባሉ።
የሚያነግሡት ሰው፣ ውሎ ሲያድር ሥልጣኑን ከጣሪያ በላይ ተራራ አሳክሎ አናታቸው ላይ ቢጭንባቸውስ? በጭካኔ ቢጨፈልቃቸውስ?
ለጊዜው አላሳሰባቸውም። ንጉሥ ፈልገዋል።
ንጉሥ ፈላጊ ሕዝብ በሕብረት በአንድ ልሳን ድምፁን ማስጮህ ይችላል። ማንን ማንገሥ እንደሚፈልጉ በቅድሚያ አይነጋገሩም። የሐሳብ ልዩነት ተገልጦ እንዳይመጣ ይሰጋሉ። ንጉሡ ምንና በምን መንገድ እንደሚሰራ… አንድ ሁለት ሐሳብ ሊናገሩ ይችላሉ። ወደ ዝርዝር ሐሳቦች አይገቡም።
የሥልጣን ገደቦች ላይ አይነጋገሩም። የሚወዱት በጎ ንጉሥ ሥልጣን ይይዛል፤ የሥልጣን ገደብ ለምን ያስፈልጋል? በቃ! ንጉሥ እንፈልጋለን ብለዋል።
ሳሙኤል በጣም እንደተናደደባቸው ከንግግሮቹ ያስታውቃል። በእግዚሄር ላይ ክህደት የፈጸሙ ያህል ያወግዛቸዋል። ኀጢአታቸውን አክብዶ እየደጋገመ ይወቅሳቸዋል። ግን ደግሞ፣ ሌላ የመፍትሔ ሐሳብ አልነበረውም።
አገርንና ድንበርን ከወረራ መከላከል፣ ሰላምን መጠበቅ፣ ሕግና ሥርዓትን መገንባት… የዘልማድ ወይም የትርፍ ሰዓት ስራ ሆኖ መቀጠል አይችልም። ቅርጽና ሥርዓት የያዘ መንግሥት የግድ ያስፈልጋል።  ጎደሎ ሐሳብ መሆኑ እንጂ የማንገስ ፍላጎት ቁም ነገር የያዘ ነው።
በእርግጥ ከቁም ነገረኛ ‘የሕዝብ ጥያቄ’ ጎን ለጎን፣ “የማንገሥ አምሮት” መኖሩ አይካድም። ሕዝብ እንደሌሎች ሕዝቦች ‘የማንገሥ ረሀብ’ ቢሞረሙረው አይገርምም።
መንግሥት ላልወደዱትም እንኳ አደጋ እንዳይሆን ምን አዘጋጅታችኋል?
ሃይማኖትና መንግሥት ሙሉ ለሙሉ ባይነጣጠሉም እንኳ በአወቃቀር ተለይተው የየራሳቸውን ድርሻ መያዝ የሚችሉበት ጊዜ መጥቷል። የሳሙኤል ትረካ እንዲህ ይላል።
የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ተሰብስበው ወደ ሳሙኤል ወደ አርማቴም መጡና፣ “እነሆ አንተ ሽምግለሃል።… እንደ ሕዝቦች ሁሉ የሚፈርድልን ንጉሥ አድርግልን” አሉት።
ሳሙኤልም፣ የሚፈርድልን ንጉሥ ስጠን ባሉት ጊዜ ነገሩ አስከፋው (1 ሳሙ 8፡ 5-6)።
እንግዲህ ሳሙኤል ማለት በእስራኤላውያን ዘንድ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ ዳኝነት ሲሰጥ የነበረ እጅግ የተከበረ የሃይማኖት መሪ ነው። ‘በሕዝብ ጥያቄ’ ሳቢያ በጣም ስለከፋው እግዚሄር ሳሙኤልን ያጽናናዋል። አንተ ላይ ሳይሆን እኔ ላይ ሲያምፁ አታይም ወይ ብሎ ያረጋጋዋል። የሚፈልጉትን እንዲሰጣቸውና እንዲያስጠነቅቃቸው እግዚሄር ለሳሙኤል እንዲህ ይለዋል።
“ቃላቸውን ስማ። ነገር ግን፣ አጥብቀህ አስጠንቅቃቸው። የሚገዛቸው ንጉሥ ወግና ልማዱን ንገራቸው” አለው (1 ሳሙ 8፡9)።
ሳሙኤልም የእግዚሄርን ቃል ለሕዝብ ተናገረ። ከንግሥና ጋር አብረው የሚመጡ አደጋዎችን ዘረዘረላቸው። እንዲህም አለ።
“በእናንተ ላይ ገዢ የሚሆነው የንጉሡ ወግ እንዲህ ነው።
ወንዶች ልጆቻችሁን ይወስዳል፤ ለራሱ ሰረገላ ነጂና ፈረሰኛ ያደርጋቸዋል። በሰረገሎቹም ፊት ይሮጣሉ።…
እርሻውንም የሚያርሱ እህሉንም የሚያጭዱ፣ የጦር መሣሪያውንና የሰረገሎቹንም ዕቃ የሚሰሩ ያደርጋቸዋል።
ሴት ልጆቻችሁንም ይወስዳል፤ ቅመም ሰሪዎች፣ ወጥ ቤቶችና ጋጋሪዎች ያደርጋቸዋል።
ከእርሻችሁና ከወይናችሁም መልካም መልካሙን ይወስዳል፤ ለአገልጋዮቹ ይሰጣቸዋል።
ከበጎቻችሁና ከፍየሎቻችሁ ዐሥራት ይወስዳል።
እናንተም ባሪያዎቹ ትሆናላችሁ።
በዚያም ቀን ለእናንተ በመረጣችሁት በንጉሣችሁ የተነሣ ትጮኻላችሁ።
በዚያም ቀን እግዚሄር አይሰማችሁም” አላቸው ሳሙኤል (1 ሳሙ 8፡ 11-18)።
የሳሙኤል ማስጠንቀቂያ ያስበረግጋል። ‘ንጉሥ ስጠን’ ሲሉ የነበሩ ሰዎች፣ ‘ንጉሥ ይቅርብን’ እንዲሉ ነበር የፈለገው። እንዴት ይሆናል?
መንግሥት ያስፈልጋል። ንጉሥ ይኑረን ሲሉ እውነት አላቸው።
በእርግጥ፣ ሳሙኤልም እውነት አለው። ማስጠንቀቂያዎቹ ባዶ ማስፈራሪያዎች አይደሉም።
ደግሞስ ከመንግሥት ውጭ ያን ሁሉ ግፍ ማን ሊፈጽም ይችላል? የመንገድ ሽፍቶችና የከተማ ወንጀለኞች የዚህን ያህል ዐቅም አይኖራቸውም። መንግሥት ግን አንዳች ገደብ ካልተበጀለትና መቆጣጠሪያ ዘዴ ካልተፈጠለት በቀር፣ አገር ምድሩን የመርገጥ ዐቅም ሊኖረው ይችላል።
ይዋጋልናል ብለው የሚሾሙት ንጉሥ ውጋት ቢሆነባቸውስ?
በቅንነት እየዳኘ ይፈርድናል ብለው ያሰቡት መንግሥት ፍርጃ ቢያመጣባቸውስ?
ሳሙኤው እውነት ብሏል። ነገር ግን የመፍትሔ ሐሳብ አልጨመረበትም። ሕዝቡም የሳሙኤልን ማስጠንቀቂያ ከሰማ በኋላ “ንጉሥ ይቅርብን” አላለም። ንጉሥ እንፈልጋለን አሉት።
“ንጉሥ ይሁንልን። እኛም ደግሞ እንደ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ እንሆናለን። ንጉሣችን ይፈርድልናል። በፊታችንም ወጥቶ ስለ እኛ ይዋጋል” አሉት(1 ሳሙ 8፡ 20)።
የትረካው ሐሳብ፣ ንግሥናን ለማስቀረት ሳይሆን፣ አደጋውን አውቀው እንዲገቡበት የሚያስጠነቅቅ የምክር ሐሳብ ነው። የንጉሣችሁን ሥልጣን ለመገደብና ለመቆጣጠር ከወዲሁ ዘዴ ብትፈጥሩ ይሻላችኋል የሚል ነው የትረካው ምክር።
የሳሙኤል ሐሳብ ደግሞ ንግሥናን ለማስቀረት ነው። ብስጭቱም ገና አልበረደም። እግዚሄር ግን እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ በአጽንኦት ጭምር ይነግረዋል።
እግዚሄርም ሳሙኤልን “ቃላቸውን ስማ፣ ንጉሥም አንግሥላቸው” አለው (1 ሳሙ 8፡ 22)።
የሳሙኤል ሐሳብ አልተለወጠም። የንግሥና ጥያቄዎችን እንደ ከባድ ኀጢአት ቆጥሮ እየደጋገመ ይወቅሳቸዋል። የትረካው አጠቃላይ መልእክት ግን ለየት ይላል። አንግሥላቸው ተብሏል። ደግሞም ከሳሙኤል በፊት፣ በጥንት በጥዋቱ በኦሪት ዘዳግም ትረካ ላይ ሙሴ ንግሥናን አላወገዘም። መንግሥት ከሃይማኖት ተለይቶ የሚዋቀርበት ጊዜ እንደሚመጣ ሙሴ አስተምሯል። እንደ ኀጢያት አልቆጠረውም።
ይልቅስ፣ በንጉሡ ሥልጣን ላይ ገደቦች ሊኖሩት ይገባል በማለት ነበር ምክር ያቀረበው። ንጉሥ አንግሡ። ነገር ግን ጦረኛ፣ ዘራፊና ነውረኛ እንዳይሆንባችሁ ተጠነቀቁ። አለበለዚያ አደጋ ላይ ትወድቃላችሁ የሚል ነበር የሙሴ መልእክት። “ንጉሥ ለራሱ… ጦር፣ ገንዘብና ሚስት አያብዛ” ብሎ መክሯቸዋል።
የሳሙኤል ትረካም በጥቅሉ ከሙሴ ትምህርት ጋር ተመሳሳይ መልእክት የያዘ ነው። እግዚሄር ለሳሙኤል የተናገረውን ተመልከቱ። “ቃላቸውን ስማ፤ ግን አስጠንቅቃቸው” አለው። ከዚያም “ቃላቸውን ስማ፤ ንጉሥ አንግሥላቸው” ብሎ ደገመለት።
ሳሙኤል እየከነከነውም ቢሆን ለንግሥና ሐሳብ እጅ ሰጠ። ሳኦል የተባለውን ወጣት ሲያነግሥላቸውስ? ገሚሱ ሕዝብ በእልልታ ንግስናውን አጸደቀ። ገሚሱ ሕዝብ ደግሞ ሳኦል አይንገሥብን ብለው ተቃወሙ።
ቢሰጉና ቢቃወሙ አይገርምም።
ያልወደዱት ንጉሥ አደጋ እንዳይሆንባቸው አስተማማኝ የሆነ ሕግና ስርዓት አላበጁም።

Read 592 times